Artcles

ተማሪዎቻችን ተስፋ እንጂ የአደጋ ሥጋት መሆን የለባቸውም

By Admin

January 05, 2018

ተማሪዎቻችን ተስፋ እንጂ የአደጋ ሥጋት መሆን የለባቸውም

ኢብሳ ነመራ

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት አንድ ክፍለ ዘመን ያህል እድሜ አስቆጥሯል። ይህ ማለት ግን በኢትዮጵያ ትምህርት ከተጀመረ አንድ ክፍለ ዘመን ያህል እድሜ ብቻ ነው ያስቆጠረው ማለት አይደለም። በኢትዮጵያ ትምህርት የሃገሪቱን የሥልጣኔ ታሪክ ያህል እድሜ አስቆጥሯል። ጥንታዊ ሃይማኖታዊ፣ የፍልስፍና፣ የስነፈለክ ይዘት ያላቸው በተለይ በግዕዝና በአረቢኛ ቋንቋዎች የተዛጁ መጻህፍትን እንዲሁም የኪነጥበብብ ስራዎችን ለዚህ አስረጂነት መጥቀስ ይቻላል። በኢትዮጵያ አንድ ክፍለ ዘመን እድሜ ያስቆጠረው ሃገር በቀሉን ትምህርት ወደጎን በመተው እንደ አዲስ እንዲጀመር የተደረገው አውሮፓዊ ትምህርት ነው። ዘመናዊ የሚባለው ይህ አውሮፓዊ ትምህርት ነው።

የነገስታቱ መቀመጫና የሃገሪቱ ርዕሰ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ በ20ኛው ክፍለ ዘመን መግቢያ ላይ የተጀመረው ዘመናዊ ትምህርት ጊዜው በሚጠይቀው፣ ስርአቱ ትምህርትን በፈለገበት ዓላማና በሰጠው ትኩረት ልክ እየሰፋ ወደጠቅላይ ግዛት ዋና ከተሞች ዘለቀ። እያደረ ደግሞ ወደአውራጃ ከተሞች ዘለቀ። ከ1966 ዓ/ም በፊት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ስርጭት ከአውራጃ ከተሞች ወርዷል ለማለት የሚያስደፍር እውነታ የለም። እርግጥ አንዳንድ የወረዳ ከተሞች 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንደነበራቸው አይካድም። አውሮፓውያን ሚሺነሪዎች የገቡባቸው አካባቢዎች በመጠኑ ሻል ያለ የትምህርት እድል እንደነበረም ይታወቃል።

ወደከፍተኛ የትምህት ስንመጣ፣ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ከ1940ዎቹ በኋላ የተጀመረ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፤ በቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በኋላም ዩኒቨርቲ። እርግጥ የአዲስ አበባ ንግድ ስራ ኮሌጅ በ1930ዎቹ አጋማሽ፣ የአዲሰ አበባ ተግባረ ዕድ በ1943 ዓ/ም ተቋቁመዋል። እነዚህ የሞያና የቴክኒክ ማሰልጠኛ ተቋማት በአዲስ አበባ የተገደቡ ነበሩ። ከዚህ በኋላ በባህርዳር፣ በሃረርጌ ሃሮ ማያ (ዓለም ማያ)፣ በጎንደር ጥቂት ተማሪዎችን የመቀበል አቅም ያላቸው ኮሌጆች ተከፍተዋል። በመቀጠል በአምቦ፣ ሃዋሳ፣ ጅማ ወዘተ መለስተኛ የግብርና ኮሌጆች ተከፍተዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ በቁጥር አነስተኛ ከመሆናቸው ባሻገር የመቀበል አቅማቸውም እጅግ ውስን ነበረ። አነሰም በዛም እነዚህ ተቋማት ለለተለያዩ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦቸና ህዝቦች ተወላጅ ወጣቶች የትምህርት እድል አስገኝተዋል። የአሁኗ ኢትዮጵያ እንድትፈጠር በማደረግ ረገድ እነዚህ ተቋማት ውስጥ ተማሪ የነበሩ ወጣቶችና ተምረው የወጡ ልሂቃን ትልቅ ድርሻ ነበራቸው።

በእነዚህ ተቋማት ውስጥ ይማሩ የነበሩ ተማሪዎችና ተምረው የወጡ ልሂቃን የዘውዳዊው ስርአት ህዝቡን ለብሄራዊና ለኢኮኖሚያዊ ጭቆና የዳረገ ቢሆንም፣ አንዱ የሌላውን ብሄር አባል በጠላትነት አልፈረጁም። አንዱን  የሌላውን ብሄር በበታችነት አይመለከቱም ነበር። የሁሉም የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች አባላት የሆኑ ተማሪዎችና ልሂቃን በኢትዮጵያዊነት ስሜት በህዝቡ ላይ የተጫነውን ብሄራዊና ኢኮኖሚያዊ ጭቆና መቃወም ላይ ነበር ያተኮሩት። የመሬት ለአራሹ፣ የብሄርና የኃይማኖት እኩልነት፣ የህዝባዊ መንግስት ምሥረታ ወዘተ መፈክሮችን አንግበው ለተቃውሞ ተነስተዋል። ለተቃውሞ የተነሱት በስሜት እየተነዱ ሳይሆን የፍልስፍና መርህ ላይ ተመስርተው ነበር።

አንዱ የሌላውን ብሄር አባል ጨቋኝ በሚል ተነስቶበት እየተጋጩ ሳይሆን በአንድነት ለጋራ ህዝብ ነበር የቆሙት። በዚህ የእኩልነትና የመብት ጥያቄ ያነገበ ትግል ውስጥ የመሳፍንቱና የመኳንቱ ልጆችም ተሳታፊ የነበሩበት ሁኔታ ነበር። በብሄራዊ መንነታቸው አልተወገዙም፣ በድንጋይ አልተወገሩም፤ አነርሱም ሌሎችን ለጭቆና የተፈጠራችሁ መብት አልቦዎች ናችሁ ብለው አላንቋሸሹም። ሁሉንም ኢትዮጵያዊነት አንድ ያደርጋቸው ነበር። እንዲፈጠር የሚፈልጉትን አንድነትና እኩልነት በራሳቸው ውስጥ በተግባር አሳይተውት ነበር።

ከ1950ዎቹ አጋማሽ በኋላ የተጀመረው የተማሪዎች እንቅስቃሴ በመባል የሚታወቀው ትግል ያልተደራጀና በአመዛኙ በአደባባይ ተቃውሞ የሚገለጽ ነበር። ትግሉ በተደራጀ መልክ እንዳይካሄድ በማደረግ ረገድ ስርአቱ የአመለካከትና የመደራጀት መብትና ነጻነትን የማያካበር መሆኑ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ይገመታል። ቢያንስ በአመለካከት ተደራጅቶ የመታገል ልምድና ባህል እንዳይዳብር አድርጓል። ማንኛውንም የመብት ጥያቄዎች ከአደባባይ ተቃውሞ በተለየ ሰላማዊ መንገድ ማቅረብና ማሰማት የሚያስችል እድልም አልነበረም። በዘውዳዊው ስርአት የመደራጀት፣ ሃሳብን በማንኛውም መንገድ በነጻነት የመግለጽ፣ የፕሬስ፣ የመሰብሰብ፣ ከስርአቱ የተለየ አመለካካት ይዞ ለሥልጣን የመፎካከር ወዘተ መብቶች በህግ የተገደቡ ነበሩ። በመሆኑም ጥያቄዎችን ማቅረብና መደመጥ፣ ምላሽ እንዲያገኙና ምላሾች ተፈጻሚ እንዲሆኑ ተጽእኖ ማሳደር የሚያስችሉ ሰላማዊ መድረኮችና እድሎች ፈጽሞ እልነበሩም። ጥያቄዎች በአደባባይ ተቃውሞ መልክ ብቻ እንዲገለጹ የሚያስገድድ ሁኔታ የፈጠረው ይህ እውነታ ነበር።

ይህ የያኔዎቹ ተማሪዎችና ልሂቃን ትግል ዘወዳዊውን ስርአት ከነአካቴው እንዲወገድ በማደረግ ረገድ ትልቅ ድርሻ ነበረው። ይሁን እንጂ ይህ በዋናነት በተማሪዎች ሲካሄድ የነበረው ትግል ያልተደራጀ መሆን የመንግስት ስልጣን ያንኑ ስርአት ሲያገለግል የነበረው ወታደራዊ ሃይል እጅ እንዲወድቅ አድርጓል። በህዝቦች ትግል የተገኘውን አብዮት የመነተፈው ወታደራዊ ምክር ቤት (ደርግ) የራሱን ወታደራዊ የመንግስት ስርአት መሰረተ። ይህ ስርአት በተወሰነ ደረጃ የመሬት ለአራሹን ጥያቄ የመሰለ ቢመስልም፣ አርሶ አደሩን በምርቱ ላይ የተሟላ የባለቤትነት መብት እንዳይኖረው ማድረግ አልቻለም። እንዲሁም ለብሄር እኩልነት፣ ለዴሞክራሲያዊ መበቶችና ነጻነቶች ጥያቄዎች ምላሽ አልሰጠም። እንዲያውም እነዚህን መብቶችና ነጻነቶች በአዋጅ አገደ።

በዚህ ስርአትም የዜጎች የፈቀዱትን አመለካከት የመያዝ፣ በአመለካከት የመደራጀት፣ ሃሳብን የመግለጽ፣ ለፖለቲካ ስልጣን የመፎካከር መብቶችና ነጻነቶች በህግ የተገደቡ ነበሩ። ዘውዳዊውን ስርአት በማስወገዱ ሂደት ከፍተኛ ድርሻ የነበራቸው ተማሪዎችና ልሂቃን የመብትና ነጻነት ጥያቄዎች የተረጋገጡበትን ስርአት ለመመስረት የነበራቸው አንድ የትግል ስልት አማራጭ የትጥቅ ትግል ብቻ ነበር። ከዚህ ውጭ መብቶችና ነጻነቶችን መጠየቅና ማስከበር የሚያስችሉ እድሎችና መድረኮች አልነበሩም።

እናም የሁሉም የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች አባላት አንዱ ሌላውን በጠላትነት ሳይፈርጅ፣ አንዱ ሌላው ላይ የጥላቻ ቅስቀሳ ሳያካሄድ፣ ለጋራ መብትና ነጻነት፣ ለጋራ ሃገር ግንባታ፤ እየተናበቡ፣ በሃሳብ እየተደጋገፉ እንዲሁም በአንድ ግንባር ተሰልፈው መታገል ጀመሩ። በዚህ መስዋዕትነትን በጠየቀ ትግል አዲሲቷ ኢትዮጵያ ተመስርታለች። በአዲቱ ኢትዮጵያ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እኩልነት በህገ መንግሥት ተረጋግጧል። የኢትዮጵያ ብሄሮችና ብሄረሰቦች ራሳቸውን ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ የልዩነት አንድነት ያላት ፌደራላዊ ስርአት ገንብተዋል። ሁሉም ራሳቸውን በራሳቸው ስለሚያስተዳድሩ የበላይና የበታች፤ ጨቋኝና ተጨቋኝ ብሄር የለም። ስርዓቱ ለዚህ እድል አይሰጥም።

የዜጎች፣ የፈቀዱትን አመለካከት የመያዝ፣ አመለካከታቸውን በግልም ሆነ ከሌሎች ጋር በመደራጀት የማራመድ፣ ሃሳብን የመግለጽ፣ ለፖለቲካ ሥልጣን የመወዳደር፣ በህዝብ ውክልና ስልጣን የመረከብ ዴሞክራሲያዊ መብቶች በህገ መንግሥት ተረጋግጠዋል። አሁን በሃገሪቱ በብሄርና በአመለካካት የተደራጁ ከ70 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ። ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በተጨባጭ የህዝቡ ኑሮ ላይ መሻሻል ያሳየ የማህበራዊና የኢኮኖሚያዊ እድገትና ልማት ተመዝግቧል። እርግጥ በልማት በኩል አሁንም ብዙ ይቀራል።

በአሁኗ ኢትዮጵያ አንዱ ብሄር ሌላውን በጥርጣሬ እንዲመለከት፣ ጥላቻ እንዲያድርበት፣ ለጥቃት እንዲነሳ የሚያደርግ አንዳችም ምድራዊ ምክንያት የለም፤ ሰይጣናዊ ምክንያት ካልሆነ በስተቀር። የኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ የፍትህ፣ የአስተዳደራዊና የፖለቲካ ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ የሚያስችሉ መብቶች ተረጋግጠዋል። አመለካከትና አማራጭ ፖሊሲን ተግባራዊ ለማድረግ በህዝብ ይሁንታ የክልላዊ መንግስትንም ሆነ የፌደራል መንግስትን ስልጠን መረከብ የሚያስችሉ መብቶችና ነጻነቶች ተረጋግጠዋል። እርግጥ በዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነጻነቶች ዙሪያ ባህል እየሆነ መዳበር የሚኖርበት ብዙ የሚቀር ነገር መኖሩ አይካድም። መሰረቱ ግን ተጥሏል።

ይሁን እንጂ፣ በዚህ አሁን ባለንበት የእኩልነት ዘመን በተለይ በዩኒቨርሲቲዎቻችን ውስጥ የአገሪቱ ተስፋ የሆኑ ወጣት ተማሪዎች እርስ በርስ በጥርጣሬ የሚተያዩበት፣ ከዚህም አልፈው የሚጋጩበት ሁኔታ የተለመደ እየሆነ መጥቷል። ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት አዲሲቷን ኢትዮጵያ በመፍጠር ሂደት ጉልህ ድርሻ የነበራቸው የቀድሞዎቹ ተማሪዎች የብሄር ጭቆና በነበረበት ወቅት እንኳን እርስ በርስ አልተጋጩም። አሁን ተማሪዎችን ለግጭት ያበቃቸው ምንድነው? የሚለው ለብዙዎች እንቆቅልሽ ሆኗል።

ተማሪዎቻችን ከነባራዊው እውነታ ይልቅ ሃገሪቱን ለማፈራረስ የሚንቀሳቀሱ ቡድኖችና መንግስታት ፕሮፓጋንዳ ያሸነፋቸው፣ ከመርህና እውነታ ይልቅ ስሜት የሚነዳቸው መሆናቸውን እያስተዋልን ነው። ይህ የነገ ሃገር ተረካቢ ትውልድ ላይ የሚስተዋል ግራ አጋቢ ሁኔታ አሁን ከሚፈጥረው ችግር ባሻገር የነገ የሃገሪቱን እጣ ፈንታ ብስጋት እንድንመለከት ያደረገ ሁኔታን ፈጥሯል። ስለዚህ ተማሪዎቻችን ቆም ብለው ራሳቸውን እንዲፈትሹ እንመኛለን።

ከዚህ በተጨማሪ ተማሪዎቻችን ጥያቄዎቻቸውን በሰላማዊ መንገድ ከማቅረብ ይልቅ ወደአውዳሚ ሁከት የመግባት ዝንባሌ ይታይባቸዋል። የሃይል አካሄድ ዴሞክራሲያዊ መብቶች በታገዱበት ሁኔታ እንጂ ሁሌም የሚመረጥ አካሄድ አይደለም። የቀድሞዎቹ ተማሪዎች ወደሃይል ትግል የገቡት የተሻለ ስለሆነ ሳይሆን፣ ከላይ እንደገለጽኩት ሁሉም የመሰሚያና ተጽእኖ መፍጠሪያ መንገዶች በህግ ስለተዘጉ ነው። እናም ተማሪዎቻችን ይህን አስተውለው ለሰላማዊ መንገዶች ቅድሚያ እንዲሰጡ እንመክራለን። ወደየሃይለ አካሄድ የሚመሯቸውና የመጠላላት አመለካካት የሚመግቧቸው የሃገሪቱ ጠላቶች መሆናቸውን ሊያስተውሉ ይገባል። ተማሪዎቻችን የሃገሪቱ የሰላምና የብልጽግና ተስፋ እንጂ የግጭትና የመፈራረስ አደጋ ስጋት ምንጭ ላለመሆን መጠንቀቅ አለባቸው፤ አሁን ከሚታየው፣ በታሪክም ተወቃሽ ከሚያደርገው ጸያፍ ድርጊትና አካሄድ ራሳቸውን መጠበቅ አለባቸው።