Artcles

ተስፋ ሰጪው ጅምር

By Admin

January 25, 2018

ተስፋ ሰጪው ጅምር

                                                         ደስታ ኃይሉ

መንግሥት ግጭቶችን በፍጥነት ለማስወገድ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት እየሰራ ነው። ሁሉም ክልሎችና ሁለቱ የከተማ መስተዳድሮች የሚገኙበት የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት ከክልሎች ጋር በመናበብ ስራቸውን በማከናወን ላይ ይገኛሉ።

በዚህም በአሁኑ ሰዓት በሁሉም አካባቢዎች ሰላም መስፈን ችሏል። የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥም በርካታ ስራዎች በመከናወን ላይ ናቸው። ፌዴራላዊ ስርዓቱ ወሰንን ማካለል ጨምሮ ማናቸውንም ተግዳሮቶች በሚያጋጥሙበት ወቅት የራሱን የአፈታት መንገድ የሚከተል በመሆኑ፤ ይህን መሳይ ችግሮችን ለመፍታት የሚመለከታቸው አካላት በጥምረት እየሰሩ ነው።

የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት ባለፈው አንድ ወር በሃገሪቱ ተከስቶ የነበረውን ግጭት ለማረጋጋት ለአንድ ወር የሰራውን እቅድ ክንውን መገምገሙ ይታወሳል። ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በወቅቱ እንዳሉት ምክር ቤቱ ግጭቶችን በማስወገድ መፈናቀልን ለማስቀረትና የዜጎችን በነጻነት የመንቀሳቀስ መብት የማረጋገጥ ስራ ሲሰራ ቆይቷል። በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች የተፈናቀሉ ዜጎችም ወደ ቀድሞ ስፍራቸው እንዲመለሱ እየተሰራም ነው።

በተለይ ዋና ዋና መንገዶችን የመቆጣጠርና የዜጎችን በነጻነት የመንቀሳቀስ መብት የማረጋገጥ ስራ ተከናውኗል። ከዚህ አንጻር የተሰሩ ስራዎችም በአብዛኛው ውጤታማ ነበሩ። እንደሚታወቀው ሁሉ በተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ግጭቶች ተቀስቅሰው ነበር። ችግሩን ከመፍታትና ሁኔታውን ከማረጋጋት አኳያ የፌደራልና የክልል የፀጥታ ሃይሎች የማረጋጋት ስራ አከናውነዋል።

በዚህ ሳቢያ ግንኙነት የነበራቸው ተማሪዎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል። አሁን ላይም በተቋማቱ የመማር ማስተማር ሂደቱ ወደ ነበረበት ተመልሷል። ከሀገሪቱ የፀጥታ ሁኔታ አንጻርም የፖለቲካ አመራሩ የሚጫወተው ሚና፣ ከህብረተሰቡ ጋር የሚደረገው ሰላምን የማረጋገጥ ተግባር የፀጥታ ሃይሉ መሰረታዊ መፍትሄ የሚያመጣ ነው።

ከዚህ ጋር ተያይዞም የዜጎችን በነጻነት የመንቀሳቀስ መብት ይገድቡ የነበሩ ድርጊቶችን፥ የፌደራልና የክልል የፀጥታ ሃይሎች ከተለያዩ የክልል አመራሮች ጋር በቅንጅት በሰሩት ስራ ውጤት ተገኝቶባቸዋል። በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ተከስቶ የነበረው ችግርም የፀጥታ አካላት በሰሩት ስራ በአሁኑ ሰዓት አንጻራዊ መረጋጋት አሳይቷል።

ከግጭቱ ጋር ተያይዞ በሂደቱ ተሳታፊ የነበሩ አካላትን በተገቢው መልኩ ለህግ ከማቅረብ አንጻር ክፍተት ቢኖርም፤ በቀጣይ እነዚህን አካላት ለህግ የማቅረቡ ስራ ተጠናክሮ መሰራት አለበት። በአጠቃላይ በአሁኑ ሰዓት ግጭት ተከስቶ የነበረባቸው አካባቢዎች የመረጋጋት ሂደት በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል።

ይህ የምክር ቤቱ ስራ ጅምር በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። በተለይ የህግ የበላይነትን በማስከበር ረገድ የዜጎችን ህገ መንግስታዊ መብት ይበልጥ ማረጋገጥ ይገባል። ለዚህም ፌዴራላዊ ስርዓቱ የህግ የበላይነትን ከማስከበር አኳያ የሚከተላቸውን ንገዶች በማስፋት ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።

እንደሚታወቀው ሁሉ በፌዴራላዊ ስርዓቱ ውስጥ የህግ የበላይትን ማረጋገጥ ለነገ የሚተው ተግባር አይደለም። ፌዴራላዊ ስርዓቱ የህግ የበላይነትን በሚገባ የሚያስከብር ነው። የህግ የበላይነትን ተላልፎ የሚገኝ ማንኛውም ዜጋ ተጠያቂ ይሆናል። ሁሉም ሰው በህግ ፊት እኩል እንደመሆኑ መጠን፤ በመረጃና በማስረጃ በተረጋገጠበት ጥፋት ልክ ተጠያቂ መሆኑ አይቀርም። ይህ አሰራር በማንኛውም ዜጋ ወይም አካል ላይ ገቢራዊ የሚሆን ነው።

አንዱን ዜጋ ከሌላው በማበላለጥ የሚከናወን የህግ አሰራር በፌዴራላዊ ስርዓቱ ውስጥ ፈፅሞ ሊኖር አይችልም፤ መቼም ቢሆን። እናም የህግ የበላይነትን ኢትዮጵያ ውስጥ ማስከበር ማለት የህገ መንግስቱን መንፈስ በሁሉም መስኮች ማስፈፀም ማለት መሆኑን የትኛውም ዜጋ ግንዛቤ መያዝ ይኖርበታል።

እንኳንስ ዛሬ ያኔም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ በነበርንበት ወቅት እንኳን የህግ የበላይነትን ለማስከበር ሲባል የዜጎች ሰብዓዊ መብት እንዳይነካ ከፍተኛ ጥንቃቄ ተደርጓል። ይህ ጥንቃቄ የተደረገው ህገ መንግስታዊው ፌዴራላዊ ስርዓት ለሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ጥንቃቄ ስለሚያደርግ ነው። የቱንም ወገን ለማስደሰት አሊያም ለማስከፋት ሲባል የሚከናወን የሰብዓዊ መብት ጥበቃ የለም።

ለሰላምም ልዩ ትኩረት መስጠት ይገባል። የህግ የበላይነት ከሌለ ሰላም የሚባልን ነገር ማሰብ አይቻልም። ሰላም ከጠፋ ደግሞ ስለ ልማትና ዴሞክራሲ ማሰብ አይቻልም። ፀረ-ልማትዊነትና ፀረ-ዴሞክራሲያዊነት ቦታውን ይረከባሉ። ይህ ሁኔታ ደግሞ እንደ እኛ ሰላምን፣ ልማትንና ዴሞክራሲን የህልውናው ጉዳይ ላደረገ ሀገር አሜኬላ እሾህ መሆኑ አያጠያይቅም።

አገራችን የጀመረችው የዕድገትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ባህል ግንባታ ሂደት ስኬታማ ሆኖ እንዲቀጥል፤ አስተማማኝ ሰላም የሰፈነበት ምህዳርን መፍጠር የግድ ነው። ምክንያቱም ሀገራችን ፈጣን ልማትን ማምጣትና ከተመፅዋችነት መላቀቅ ብሎም ዴሞክራሲን መገንባት ወሳኝ ጉዳይ ስለሚሆንባት ነው። ሰላምን በማረጋገጥ ሂደት ውስጥ ለብሔራዊ ደህንነቷ ስጋት የሆኑ እንቅስቃሴዎችን መከላከልና መቆጣጠር ያስችላት ዘንድ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ይኖርባታል።

ተማሪዎች ያለ ሰላም ትምህርታቸውን ሊከታተሉ አይችሉም። በሰላም ውስጥ ሆነው ነው ነገ ተምረውና ተመራምረው ሀገርን ሊጠቅሙ የሚችሉት። ያለ ሰላም በብጥብጥ ውስጥ የሚዳክር የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪ ምንም ዓይነት አገራዊ ትሩፋት ሊያስገኝ አይችልም።

የህግ የበላይነት ልዕልና ካልተጠበቀ በሀገሪቱ የሚረቀቁ ማናቸውም ህጎች በሚፈለገው መጠን ገቢራዊ ሊሆኑ አይችሉም። ህጎች በሚፈለገው መጠን ገቢራዊ ካልሆኑና በቸልታ የሚታለፉ ከሆኑ የዜጎች መብቶች ሊሸራረፉ ይችላሉ። የመብት መሸራረፎች ደግሞ አንዱ እንዳሻው እንዲፈነጭ፤ ሌላው ደግሞ ህግና ስርዓትን አክብሮ እንዲንቀሳቀስ በማድረግ ሚዛኑን ያዛባዋል።

በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍሎች ውስጥ የህግ የበላይነትን አለማረጋገጥ ህገ መንግስቱን መፃረር ነው። “ለምን?” ከተባለ፤ ህገ መንግስቱ የህጎች ሁሉ የበላይ እንደመሆኑ መጠን፤ እርሱን ተከትለው የሚወጡ አዋጆችን ተፈፃሚ አለማድረግ መልሶ ህገ መንግስቱን መቃወም ስለሆነ ነው። የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲሁ ለይስሙላ የተደነገጉ አይደሉም። ዜጎች ሰዎች በመሆናቸው ሳቢያ የተጎናፀፏቸው መብቶች ናቸው።

በመሆኑም ማንኛውም አካል የህግ የበላይነት እንዳይሸረሸር መፍቀድ ያለበት አይኖርበትም። እንዲህ ዓይነት ዝንባሌ በሌላኛው እሳቤ የህግ የበላይነት ዕውን እንዳይሆን መፍቀድ በመሆኑ ነው። የህግ የበላይነትን መፃረር ስርዓት አልበኝነትን የሚፈጥር ከመሆኑም ባሻገር፤ ህጎች ለሁሉም ዜጎች እኩል እንዳይሰሩ ያደርጋል።

ይህም ሁሉም ሰው በህግ ፊት እኩል ነው’ የሚለውን ህገ መንግስታዊ መርህ ይጥሳል። በመሆኑም የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤቱ የጀመራቸው ሰላምን የማስጠበቅና የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ጅምር ስራዎች ተስፋ ሰጪዎች በመሆናቸው ጅምሮቹ ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል።