Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ተስፋ ሰጪው ግንኙነት

0 331

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ተስፋ ሰጪው ግንኙነት

ዳዊት ምትኩ

በቅርቡ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በፅህፈት ቤታቸው የበርካታ አገራትን አምባሳደሮች የሹመት ደብዳቤዎችን በተቀበሉበት ወቅት “ኢትዮጵያ ከቻይና እና ከሌሎች አራት የአፍሪካ እና አውሮፓ አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ልታጠናክር ይገባል” ማለታቸው ይታወሳል። ይህ የፕሬዚዳንቱ ንግግር የአገራችንን የውጭ ግንኙት ሁኔታ የተመለከተ ነው ማለት ይቻላል።

በተለይም አገራችን ከቻይና ጋር በጋራ ተጠቃሚነት ረገድ እያደረገች የሁለትዮሽ ግንኙነት አገራቱ በሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ ብቻ አራት ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ግንኙነት እንዲመሰርቱ እንዳስቻላቸው መረጃዎች ያስረዳሉ። ይህ በሁለቱ አገራት መካከል የተፈጠረው ተስፋ ሰጪ ግንኙነት የአገራቱን በጋራ የማደግ ተስፋ ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑ ግልፅ ነው።

ይህ ከምስራቁም ይሁን ከምዕራቡ እንዲሁም ከአፍሪካዊያን ወንድሞቻችን ጋር ያለን ግንኙነት መነሻውም ይሁን መድረሻው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲያችን ነው። እንደሚታወቀው ሁሉ የኢፌዴሪ መንግሥት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲሁም የአካባቢውንና ጎረቤት ሀገሮችን ለጋራ ጥቅምና ሰላም እንዲሰሩ የሚጋብዝ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲን መከተሉ የሚያጠያይቅ አይመስለኝም፡፡

ይህም እንደ ቀድሞዎቹ የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲዎች የሀገር ውስጥ ጉዳዮችን ቸል በማለትና ወደ ውጭ ያነጣጠረ ሳይሆን በቅድሚያ በሀገር ውስጥ ሰላም በማስፈን በማረጋጋት ላይ ትኩረት በማድረግ በከባቢያችን ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም እንዲፈጠርና የጋራ ልማትና ትብብር እንዲጠናከር ማድረግ ነው፡፡  

የሀገራችን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ብሔራዊ ጥቅማችንን የማስጠበቅና ሀገራዊ ህልውናችንን የማረጋገጥ እንዲሁም ሌሎችን በጠላትነት ሳይሆን በአጋርነት መንፈስ በመመልከት ሀገራት ከእኛ፣ እኛም ከእነርሱ ተጠቃሚ የምንሆንበትን መንገድ ቀይሷል። እርግጥም ፖሊሲው ከማንኛውም ሀገር ጋር የሚኖረን ግንኙነት በመሰረታዊ ሀገራዊ ጥቅማችን ደህንነት ላይ የተመሰረተ፣ እንዲሁም የልማትና የዴሞክራሲ ሂደቱ ስር እየሰደደና የሀገራችን ዕድገት እየተፋጠነ በሄደ ቁጥር ለአደጋ ተጋላጭነታችን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚቀንስ ያየሚያረጋግጥ ነው።

የኢፌዴሪ መንግስት ደህንነታችንን ለማስጠበቅ ዋናው መሣሪያ ልማትና ዴሞክራሲን በሀገር ደረጃ ማረጋገጥ እንደሆነ በፅኑ ያምናል፡፡ በዚህ ረገድ ተመስርቶም ዲፕሎማሲያችን በቂ ጥናት በማካሄድ አደጋዎችን ለመቀነስ፣ ግጭቶች ሲፈጠሩ በድርድር እንዲፈቱ ለማድረግ፣ በዚህ ሂደት ሊፈቱ ያልቻሉትን ለመከላከል አቅም መገንባት ወሳሽ መሆኑንም ያስረዳል።

ሀገራችን የምትከተለው የፖለቲካ ዲፕሎማሲ ለተፈላጊነቷ መጨመር ምክንያት የሆነ ይመስለኛል። ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራትና ተቋማት ጋር የምታደርጋቸው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገና እየጎለበተ መጥቷል፡፡

በሰጥቶ መቀበል መርህ ከልዩ ልዩ ሀገሮች ጋር ግንኙነቷን በማጠናከር የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲጨምር እየሰራች ነው፡፡ በዚህም ውጤታማም በመሆን ላይ ትገኛለች፡፡ ቀደም ሲል በመግቢያዬ ላይ የጠቀስኩት ከቻይና ጋር ያላት ግንኙነት በአዚህ ረገድ ተጠቃሽ ነው፡፡

የሀገሪቱን የውጭ ግንኙነትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ስፍራ ለማጎልበትም ባለፉት 26 ዓመታት ያህል ሰፊ ጥረት ተደርጓል፡፡ ለሀገሪቱም ሆነ ለአካባቢው የተረጋጋ የፖለቲካ ሂደት እንዲኖር ግጭቶችና ውዝግቦች በሰላማዊ ጥረት እንዲፈቱ ብቻ ሳይሆን የሠላምና የትብብር አድማሱ እንዲሰፋ እያደረገች ትገኛለች፡፡

ኢትዮጵያ በምትከተለው በዚህ የትብብርና የሰላም ዲፕሎማሲ መርህ መሰረት በዓለም ዙሪያ ካሉት ሀገሮች ጋር ያላት ግንኙነት በጋራ ጥቅም ላይ እንዲመሰረት ሆኗል፡፡ በዚህም ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ትስስሯ ከኤርትራ በስተቀር ከሌሎች ሀገሮች ጋር ትልቅ ስፍራ ደርሷል፡፡

እርግጥ የኢፌዴሪ መንግስት ቀደም ሲል ሀገሪቷን ያስተዳድሩ የነበሩ መሪዎች ይከተሉት በነበረው የተሳሳተና ጎረቤት ሀገሮችንም ሆነ ሌሎችን በጠላትነት የመፈረጅ አካሄድ ላይ በፅንሰ ሃሳብም ሆነ በተግባር መሰረታዊ ለውጥ እንዲኖረው መደረጉ ሀገራችን አሁን ለምትገኝበት የተፈላጊነት ቁመና አብቅቷታል ማለት ይቻላል፡፡

እንዲሁም በሀገር ውስጥም የሀገሪቷ ዋነኛ ጠላት ድህነት ነው የሚል ፅኑና ቁርጠኛ እምነት ስለተያዘ ጭምር ነው፡፡ እናም ሀገሪቱ ከውርደት፣ ከኋላ ቀርነትና ከተለያዩ የስጋት ምንጮች ነፃ ልትሆን የምትችለው፣ ፈጣን የኢኮኖሚ ልማት እንዲሁም የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና መልካም አስተዳደር በተሳካ መንገድ እንዲካሄዱ ስለተደረገም ነው፡፡ የእነዚህ ድምር ውጤቶችም ሀገራችንን የተፈላጊነት ማማ ላይ እንድትወጣ አድርጓታል፡፡

ሀገራችን የምስራቅ አፍሪካን ሰላም ለማስጠበቅ ብሎም የዓለማችን ጠንቅ የሆነውን አሸባሪነትን በመዋጋት እያከናወነቻቸው ያለችው ተግባራትም ለተፈላጊነቷ መሰረት የሆኗት ይመስለኛል። በዓለምና አህጉር አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያ ሰላም የማስከበር ተልዕኮ ረዥም ዓመታትን ያስቆጠረ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከደርግ ውድቀት በኋላ የሰላም ግንባታ ዲፕሎማሲን በመከተሏ የአፍሪካ ቀንድን ጨምሮ የአህጉሪቱን ሠላምና መረጋጋት ለማጠናከር የሰላም አስከባሪ ኃይሏን በብሩንዲ፣ በሩዋንዳ፣ በላይቤሪያ፣ በሱዳን ዳርፉርና አብዬ ግዛቶች በሙሉ ፈቃደኝነትና በብቃት አሰማርታለች፤ አኩሪ ተግባርም በመፈፀም ላይም ትገኛለች፡፡ በሶማሊያም በአሚሶም ጥላ ስር ሆና አልሸባብን ለመደምሰስ በሚደረገው ጥረት ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተች ነው፡፡

እነዚህ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ስኬታማ መሆናቸውና በአሁኑ ወቅት ወደ ላቀ ደረጃ እየተሸጋገሩ መምጣታቸው እንዲሁም ሀገራችን ለሰላም መስፈንና አሸባሪነትን ለመዋጋት እያደረገችው ያለችው ጥረት ብሎም ሰላም የተናጠል ሳይሆን የጋራ አጀንዳ መሆኑን በማረጋገጧ ይበልጥ ተፈላጊነቷ እንዲጨምር አድርጓል፡፡

ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያ የምትከተለው ሰጥቶ የመቀበል ፖሊሲ በሁሉም የዓለማችን ሀገራት በሚባል መልኩ ተፈላጊ እንድትሆንና ግንኙነቷም እንዲጠናከር አድርጓታል፡፡

እርግጥ አሁን በምንገኝበት ዓለም ውስጥ ለብቻ ሮጦ ማሸነፍ አሊያም ተጠቃሚ መሆን አይቻልም፡፡ ያለው አማራጭ ተያይዞ ማደግ ብቻ ነው። ተያይዞ ለማደግ ደግሞ በመርህ ላይ የተመሰረተ ፖሊሲ የግድ ይላል፡፡

እንዲህ ዓይነቱ ሁሉንም ወገን ተጠቃሚና አሸናፊ የሚያደርግ ፖሊሲ ደግሞ ተፈላጊ ያደርጋል፡፡ ሀገራችንም ያደረገችው ይህንኑ ተስፋ ሰጪና የህዝቦችን ተጠቃሚነት የሚያሰፋ ግንኙነትን ነው፡፡ ይህን መሰሉ ተስፋ ሰጪ ግንኙነት የሀገራችንንና የህዝቦቿን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ይበልጥ ስለሚያበዛ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy