Artcles

አሁን አብሮ የመዳን ተስፋችን ለምልሟል!

By Admin

January 11, 2018

አሁን አብሮ የመዳን ተስፋችን ለምልሟል!

ኢዛና ዘ መንፈስ

ወቅታዊው የሀገራችን ፖለቲካ በየቀኑ አዳዲስ ክስተቶችን እያስከተለ ነው፡፡ ከዚሁ ውጥረት ካልተለየው የሀገራችን ፖለቲካዊ ትኩሳት የተነሳም፤ ትናንት ስለሆነው ነገር የተሰማንን አስተያየት ለመሰንዘር የፃፍነው ሐተታ ሳይነበብ፤ ሌላ አዲስ ክስተት ያስከተለው የመወያያ ርዕሰ ጉዳይ እየተነሳ ትንፋሽ እንዲያጥረን ማድረጉ አልቀረም፡፡ ምክንያቱም ደግሞ፤ ቀልድ በሚመስል መልኩ ከጥቂት ዓመታት በፊት የተስተዋለው የሁከትና ብጥብጥ ተግባር፤ ቆሟል ሲባል የሚያገረሽ ሀገር አውዳሚ አድማሱን እያሰፋ ቀጥሎ፤ የጋራ ህልውናችን የተመሰተበትን ሀገራዊ ደህንነታችን አሳሳቢ አደጋ ላይ ወደጣለ ቀውስ እንዳስገባን ይታመናልና ነው፡፡ ከዚህ አኳያም ሀገር የመምራት መንግስታዊ ስልጣን የያዘው ገዢ የፖለቲካ ፓርቲ፤ በተለይም ከ2008 ዓ.ም መጀመሪያ አንስቶ የሚስተዋለውን የሰላምና መረጋጋት መጓደል ችግር ስላስከተለው ትክክለኛ መንስኤ ማጣራትን ጨምሮ፤ ክስተቱን ከምንጩ ለማድረቅ የሚያስችል ዘላቂ መፍትሔ በማፈላለግ ብርቱ ጥረት ላይ ተጠምዶ መሰንበቱ የሚካድ ጉዳይ አይደለም፡፡

በዚህ መሰረትም የኢህአዴግ መራሹ መንግስት ከፍተኛው ውሳኔ ሰጪ አካል ተደርጎ የሚወሰደው የግንባሩ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ፤ ከመቸውም ጊዜ በተለየ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ላይ ተመስርቶ ለ16 ቀናት ያህል ያካሄደውን ጥልቅ ግምገማ፤ ታህሳስ 21 ቀን 2010 ዓ.ም እንዳጠናቀቀ ባወጣው የአቋም መግለጫ፤ አማካኝነት ለምልዓተ ህዝቡ ማሳወቁ አይዘነጋም፡፡ ገዢው ፓርቲ ከላይ በተመለከተው ቀን ያወጣውን የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መግለጫ ተከትሎም፤ አራቱ የኢህአዴግ ብሔራዊ አባል ድርጅቶች፤ በየሊቃነ መናብርቶቻቸው የተወከሉበትን ሰፋ ያለ የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ሰጥተዋል፡፡ እንግዲያውስ እኔ በዛሬው መጣጥፌ ለማንሳት የምፈልገው ዋነኛ ነጥብም ወቅታዊው የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መግለጫ ገዢው ፓርቲ ሀገራችን አሁን ላይ የምትገኝበትን አጠቃላይ እውነታ በቅጡ ካገናዘበ የኃላፊነት ስሜት በመነጨ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ላይ የተመሰረት እውነተኛ ግምገማ ስለማካሄዱ አጉልቶ የሚያሳይ ሆኖ ማግኘቴን የሚያትት ነው፡፡ ታህሳስ 21 ቀን የወጣው የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ድርጅታዊ የአቋም መግለጫ በዝርዝር የተብራሩትን የግምገማው ማጠቃለያ ላይ ስለተደረሰበት የጋራ መግባባት (ስምምነት) የሚያመለክቱ ስምንት ነጥቦችን ጨምሮ፤ ሰኞ ታህሳስ 23 ቀን 2010 ዓ.ም አራቱ የግንባሩ ብሔራዊ አባል ድርጅቶች በአንድነት ግምገማውን አስመልክተው የሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የጥልቅ ተሃድሶው መርሐ ግብር የሚጠይቀውን ጥልቀት በሚመጥን መልኩ የተቃኘ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ጎልቶ የተንፀባረቀበት እውነተኛ እርስ በርስ የመተጋገል ስሜት ተላብሷል ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

ይሄን ስልም ደግሞ፤ እኔ እንደ አንድ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ የገዛ ራሱን ውስጣዊ ድክመቶች ትርጉም ባለው መልኩ ቀርፎ፤ ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን አክብሮ ለማስከበር የሚያስችል አስተማማኝ ፖለቲካዊ ቁመና እንዲኖረው ከመሻት በሚመነጭ ስሜት የጥልቅ ተሃድሶውን መርሐ ግብር፤ የሚደግፍ ዜጋ፤ አሁን ላይ ለምልዓተ ህዝቡ ይፋ የሆነውን የግንባሩ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አጠቃላይ ሃሳብ፤ የኢትዮጵያን የህዳሴ ጉዞ የመምራት ታሪካዊ ኃላፊነት እንደተሸከመ ከሚታመንበት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ እስከዛሬ ድረስ እንጠብቅ የነበረውን ጥልቅ ተሃድሶ የሚመጥን ጥልቀት ባለው መልኩ የተቃኘ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚገባ ነው የሚሰማኝ፡፡ ይልቁንም ደግሞ ኢህአዴግን ኢህአዴግ ስለሚያሰኙት የፖለቲካዊ ባህል እና ዕሴቶች፤ የግንባሩ አባል ድርጅቶች ከፍተኛ አመራር አንድ ዓይነት የጋራ መግባባት ላይ መድረሱንና መርህ የለሽነትን አምርሮ ስለመታገል አስፈላጊነት አቋም መያዙን እንደገዢ ነጥብ ልንወስደው እንችላለን፡፡ ይህን ስል ግን፤ ሌሎቹ በኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሰሞነኛ መግለጫ ላይ የተዘረዘሩት ነጥቦች ገዢ አይደሉም ለማለት እየቃጣኝ እንዳይመስልብኝ፡፡

እኔ ለማለት የፈለግኩት በተለይም ዛሬ ዛሬ የፌደራል ስርዓቱ ለቀለም አብዮት ናፋቂዎቹ ጽንፈኛ ተቃዋሚ የፖለቲካ ቡድኖች ፈርጀ ብዙ ጥቃት ሲጋለጥ የሚስተዋልበት ዋነኛው ምክንያት ተደርጎ የሚወሰደው፤ በተለይም ለኢህአዴጋዊ የአስተሳሰብ ወገንተኝነት ታምኖ ያለመገኘት ችግር የተጠናወታቸው የግንባሩ ብልጣብልጥ አባላት የመበራከታቸው ጉዳይ እንደመሆኑ መጠን፤ ይህን መሰረታዊ ድክመት መቅረፍ ሳይቻል ገዢው ፓርቲ ሀገር የመምራት ታሪካዊ ኃላፊነቱን በአግባቡ ለመወጣት የሚያስችለውን አስተማማኝ ድርጅታዊ ቁመና እንዲኖረው መጠበቅ ይከብዳልና የመርህ የለሽነት ወረርሽ መገታት አለበት ነው፡፡ እንጂ እያንዳንዱ በአሁኑ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መግለጫ ላይ የሰፈረ ነጥብ ወደ ተግባር እስከ ተለወጠ፤ የጋራ ህልውናችን የተመሰረተባትን ሀገራችንን፤ ክፉኛ ሲፈታተኗት ለሚስተዋሉበት የወቅቱ አሳሳቢና አንገብጋቢ መፍትሔ የሚያሻቸው ፈርጀ ብዙ ችግሮች መቃለል የየራሱን አዎንታዊ ድርሻ ሊወጣ እንደሚችል ይገባኛል፡፡ ያ ይሆን ዘንድ መሟላት ከሚኖርባቸው ቁልፍ ቅድመ ሁኔታዎች መካከል፤ እንደ ወሳኝ ነጥብ ሊወሰድ የሚችለው፤ ኢህአዴግ እንደ አንድ ተራማጅ የፖለቲካ ፓርቲ የሚታወቅበት የትግል መስመር በተግባር ለሚገለፅበት የጋራ መርሆ የመገዛትን (ታምኖ የመገኘትን) ጠቃሚ ድርጅታዊ ባህል እና ዕሴቶች አክብሮ የማስከበር ጉዳይ ነው ባይ ነኝ እኔ፡፡

ስለዚህ ኢህአዴግን ኢህአዴግ በሚያሰኙት አራቱ ብሔራዊ አባል ድርጅቶቹ የአመራር አካላት መካከል የሚስተዋለውን ጤናማ ያልሆነ ግንኙነት፤ ወይም ደግሞ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት የማጣት ችግር ለማስቀረት ሲባል፤ የምር ጥልቀት ባለው መልኩ መገማገም ተገቢ የመሆኑን ያህል፤ መንግስትን ህዝባዊ አመኔታ የሚያሳጣ መሰረታዊ ችግር ተደርጎ የሚወሰደውን የመልካም አስተዳደር ዕጦት በማባባስ ረገድ የአንበሳውን ድርሻ እንደሚይዝ ተደጋግሞ የተነገረለትን የሲቪል ሰርቪስ መዋቅር እንዳሻቸው እንዲፈነጩበት ሕጋዊ ስልጣን የተሰጣቸው እስኪመስል ተገልጋዩን ህብረተሰብ ሲቀልዱበት የሚታዩ የሥራ ኃላፊዎች ተጠያቂነትን እንዲፈሩ የሚያደርግ የእርምት እርምጃ መውሰድ እጅግ አንገብጋቢ መፍትሔ ከሚጠይቁን ሀገራዊ ተግዳሮቶች ተርታ እንደሚመደብ አለመዘንጋት ይጠቅማል፡፡ ደግነቱ ግን ክቡር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስቴርን ጨምሮ ሁሉንም የኢህአዴግ ብሔራዊ አባል ድርጅቶች ሊቃነ መናብርት ከስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው መግለጫ በኋላ ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን የሰጡት የጋራ ቃለ ምልልስ ላይ ከመግለጫው በተሻለ መልኩ እያንዳንዱ ነጥብ ተብጠርጥሮ የቀረበበት ነው፡፡ አሁን በከፍተኛው የግንባሩ አመራር አካል መካከል እንዲፈጠር የተደረገው የአስተሳሰብ አንድነት፤ ደረጃ በደረጃ ወደታች ወርዶ ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው የአራቱም አባል ድርጅቶች ሊቃነ መናብርት በሰሞነኛ ቃለ ምልልሳቸው ለመላው የሀገራችን ህዝቦች አስረግጠው የገለፁት፡፡

ለዚህም፤ እንደኔ እንደኔ፤ አሁን ላይ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ በእርግጥም የጥልቅ ተሃድሶውን መርሐ ግብር እያሳካ ነው ብለን እንድናምን የሚያደርግ ከውስጣዊ ድክመቶቹ ጋር የመበጣጠስ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ያሳየበትን እውነተኛ ግምገማ ስለማካሄዱ የሚያመለክት አስተማማኝ የከፍተኛ አመራር አካላት የአስተሳሰብ አንድነት መፍጠር እንደቻለ ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡ ስለሆነም ይህን የአስተሳሰብ አንድነት ወደ መላው የግንባሩ አባል ድርጅቶች መዋቅር ደረጃ በደረጃ ወርዶ ተግባራዊ እንዲሆን ማድረግ የማይቻልበት ምንም ምክንያት አይኖርም ብለን ከወዲሁ ብንገምት ስህተት አይመስለኝም፡፡ በግልጽ አነጋገር፤ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ በረጅሙ የትግል ታሪኩ ሂደት ውስጥ የሚታወቅባቸውን የአስተሳሰብ ልዕልናው መገለጫ የፖለቲካዊ ባህል ጠቃሚ ዕሴቶቹን የመዘንጋት አደጋ እንደተጋረጠበት በቅጡ ተገንዝቦ አደጋውን ለመቀልበስና ወደ ትክክለኛ ህዝባዊ ወገንተኝነቱ ለመመለስ የሚያስችለውን ኢህአዴጋዊ ዕርስ በርስ የመግባባት (የመናበብ) ሀገር አቀፍ የኃላፊነት ስሜት እንደፈጠረ ለመረዳት አራቱ የብሔራዊ አባል ድርጅቶቹ ሊቃነ መናብርት በአንድነት፤ ለመገናኛ ብዙኃን ከሰጡት ወቅታዊ ቃለ ምልልስ የተሻለ ማረጋገጫ የሚያሻ አይሆንም ብሎ ማጠቃለል ገቢነት ይኖረዋል፡፡ ከዚህ የተነሳም ነው፤ በሰሞነኛው የግንባሩ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የጥልቅ ግምገማ መድረክ ላይ የተሳተፉትን ባለድርሻ አካላት ሁሉ ከልብ እንድናደንቅ ግድ የሚል የእውነተኛ ታጋይነት ታራማጅ አቋም የታየበት ኢህአዴጋዊ የፖለቲካ ባህል አጉልቶ የሚያንፀባርቅ ዕርስ በርስ የመተጋገል ጓዳዊ መንፈስ መስፈን ስለመጀመሩ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል የምለውም፡፡

እናም ጉዳዩን ከዚህ አጠቃላይ እውነታ ጋር እያገናዘብን እንመልከተው ከተባለ፤ ሀገር የመምራት ታሪካዊ ኃላፊነት የተጣለበት ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ፤ ከመቸውም ጊዜ ይልቅ ህዝባዊ ወገንተኝነቱን ማሳየት እንደሚጠበቅበት ከመረዳቱ የመነጨ ቁርጠኛ አቋም ላይ ለመድረስ የመረጠበት አግባብ ስለ መፈጠሩ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ በእርግጥም ደግሞ ኢህአዴግ መራሹ የኢትዮጵያ ህዝቦች የትግል መስመር እንደ አንድ የፖለቲካ ድርጅት ከትናንት እስከዛሬ በተጓዘበት ረጅም ታሪኩ ከሚታወቅበት የተወሳሰቡ ፈርጀ ብዙ ፈተናዎች ባጋጠሙት ቁጥር፤ እንደየወቅታዊው ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ተጨባጭ እውነታ ሊወሰን በሚችል ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ላይ ተመስርቶ አንዳች ከራሱ ውስጣዊ ጥንካሬ የሚመነጭ የመፍትሔ እርምጃ የመውሰድ ባህል አኳያ አሁን የግንባሩ ከፍተኛ የአመራር አካላት የደረሱበት የጋራ ውሳኔ የሚጠበቅ እንጂ እንብዛም ሊያስገርመን የሚገባ አይደለም፡፡ ስለዚህም፤ ከታህሳስ ወር የመጀመሪያ ሳምንት አንስቶ ለአስራ አምስት ተከታታ ቀናት የተካሄደው የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የጥልቅ ግምገማ መድረክ መጠናቀቁን ተከትሎ የወጣው የአቋም መግለጫና እንዲሁም ደግሞ በአራቱ የግንባሩ አባል ድርጅቶች ሊቃነ መናብርት አማካኝነት ለመገናኛ ብዙኃን የተሰጠው ቃለ ምልልስ፤ የጋራ ህልውናችን የተመሰረተባት ሀገራችን ውስጥ በሚስተዋለው ተደጋጋሚ የሁከትና ብጥብጥ ተግባር ምክንያት፤ እንደ ህብረተሰብ እንቅልፍ እየነሳን ያለውን የደህንነት ስጋት አስወግዶ የህዳሴው ዘመን ኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋዎቻችንን የሚያለመልም ድምር ውጤት ማምጣት ስለሚቻልበት ዘለቄታዊ የመፍትሔ አቅጣጫ በማያሻማ መልኩ እንድንገነዘብ የሚያደርግ ሆኖ እንደተሰማኝ ነው እኔ አሁንም በድጋሜ ለመግለፅ የምወደው፡፡

ስለሆነም፤ ይህች የጋራ ህልውናችን የተመሰረተባት ሀገራችን ኢትዮጵያ፤ በመላው ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድም ሳይቀር ተገቢ ክብር እንዲሰጣት እያደረገ ያለውን ፈርጀ ብዙ በጎ ገጽታችንን፤ ይበልጥ አጠናክረን በመቀጠል፤ አሳፋሪውን የድህነትና የኋላ ቀርነት ታሪካችንን ከመቀየር የሚቀድም አንገብጋቢ የጋራ አጀንዳ ሊኖረን እንደማይችል እየታወቀ፤ ግን ደግሞ ይህ የህዳሴው ዘመን ኢትዮጵየ መልዓተ ህዝቦች ፍላጎት እንዳይሳካ የሚሹ ታሪካዊ ባላንጣዎቻችን ያጠመዱልን የዕርስ በርስ ግጭትና ትርምስ ወጥመድ ውስጥ የመግባት አዝማሚያ ስናሳይ የምንሰተዋልበትን እጅግ አደገኛ ክስተት የማይደግፍ ዜጋ ሁሉ፤ ለገዢው ፓርቲ የጥልቅ ተሀድሶ መርሐ ግብር ውጤታማነት የየራሱን በጎ አስተዋጽኦ ሊያክልበት ይገባል እላለሁ፡፡ ሌላው ቀርቶ ኢህአዴግን በምርጫ ሂደት አሸንፈን ሀገር የመምራት መንግስታዊ ስልጣኑን እንረከባለን የሚል ዓላማ ይዘው የሰላማዊ ትግል እንቅስቃሴ በማድረግ ረገድ የሚታወቁት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ደጋፊዎቻቸውም ጭምር እንደዚህ ዓይነቱን ለፌደራላዊው ስርዓታችን ዴሞክራሲያዊ ገጽታዎች መጎልበት የማይናቅ በጎ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል የሚታመንበት ውሳኔ ሊያበረታቱ ይገባል የሚል ፅኑ እምነት ነው ያለኝ፡፡ ይህን የተለየ ህዝባዊ ወገንተኝነትን ከሚጠይቅ የሀገራዊ ኃላፊነት ስሜት በሚመነጭ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ወደ ራስ ውስጣዊ ድክመቶች የመመልከት ድፍረት ጎልቶ የተንፀባረቀበትን ኢህአዴጋዊ የጥልቅ ተሃድሶ መድረክ አለማድነቅና እንደጠቃሚ የትግል ባህል ወስዶ ትምህርት ለመቅሰም አለመፈለግ ለትዝብት መዳረጉ ስለማይቀር፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ዛሬ እንኳን ግንባሩን “ጎሽ አበጀህ!” ይሉት ዘንድ ተገቢነቱ አጠያያቂ አይሆንም፡፡ አለበለዚያ ግን ከዚህ በላይ ለፖለቲካዊ የጋራ ችግሮቻችን ፖለቲካዊ መፍትሔ ለመስጠት ያለመ ምቹ ቅድመ ሁኔታ የመፍጠርና ለመድበለ ፓርቲያዊ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት መጠናከር እንደ ቁልፍ ጉዳይ የሚወሰደውን ግልጽነት የማሳየት ጥረት እንዲኖር መጠበቅ ብቻውን እንደ የሰላማዊ ትግል መገለጫ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ሊቆጠር የሚችል አይሆንም፡፡ መቸስ የገዛ ራሱን ድርጅታዊ ቁመና ጤናማነት በቅጡ የመፈተሽ ድፍረት ከሚያንሰው የፖለቲካ ፓርቲ የአንድን ሀገር ህዝቦች ወደ ተሻለ ዴሞክራሲያዊ የመንግስት አስተዳደር የሚያሸጋግር ትግልና ድል መጠበቅ ያዳግታል አይደል ወገኖቼ!? ስለዚህ ሁሉም የራሱን ጥልቅ ተሃድሶ ተግባራዊ ያደርግ ዘንድ ነው የኔ ቅን ምክር፡፡