Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አህጉራዊ ሚናችን

0 362

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አህጉራዊ ሚናችን

ስሜነህ

የአፍሪካ አንድነትና ህብረት ሁለት መሰረታዊ አላማዎች ይዞ በየተራ የተጠነሰሰ ድርጅት እና ህብረት ነው። አንደኛውና ግንባር ቀደሙ ከቅኝ ግዛት ነፃ ያልወጡ የአፍሪካ ሀገራት ነፃነታቸውን እንዲቀዳጁ ሀገራቱ በጋራ ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና ወታደራዊ ድጋፍ ማድረግ  ያለባቸው መሆኑን የተመለከተ የቀደመው የድርጅት አላማ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ አፍሪካ በአለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እንዲኖራት ተባብሮ የመስራት መርህን ያነገበ የህብረቱ አላማ ነው።  

የአፍሪካ አንድነት ድርጅ (OAU)  እ.ኤ.አ በወርሃ ግንቦት1963 ዓ.ም ነፃ የአፍሪካ ሀገሮች የመሰረቱት በይነ-መንግስታዊ ድርጅት (Inter Governmental Organization) በመሆን አዲስ አበባ ላይ ነው የተመሰረተው። ድርጅቱ ከላይ የተመለከቱ ሁለት ዓላማዎችን ይዞ የተጣለበትን ኃላፊነት ለ39 ዓመታት ያህል መወጣቱ ስለታመነበት፤ በደቡብ አፍሪካ ደርባን በተካሄደ የድርጅቱ ጉባኤ በይፋ ወደ አፍሪካ ህብረትነት (AU) እንዲሸጋገር ተደርጓል።   

ሃገራችን ይህን አህጉራዊ ድርጅት ከማዋለድ ጀምሮ በማሳደግና ወደ ኅብረትነት እንዲቀየር በማድረግ ታሪካዊ ድርሻዋን ተወጥታለች። እንደ መስራችና እንደ ዋና መቀመጫነቷም የትኛውም የፖለቲካ ሥርዓት ይሁን የቱም በአፍሪካዊ ወንድማማችነትና መንፈስ ተቀብሎ በማስተናገድ፣ ጭቆናና በደልን፣ ግፍና ብዝበዛን በመቃወም አቅሟ የፈቀደውን ሁሉ አድርጋለች። አለመግባባትና ግጭቶች ሲከሰቱም በማብረድ ረገድም ከሁሉም የላቀ ሚናዋን ተወጥታለች። በአህጉሪቱ የሚፈጠር አለመረጋጋትን በመረጋጋት በመተካት፣ የተጎዱትን በማቋቋምና የተቸገሩትን በመርዳት የማይናወጥ አቋሟን ስታንጸባርቅ ኖራለች። ኢትዮጵያ አህጉሪቱን ከቅኝ አገዛዝ ሙሉ በሙሉ ነጻ በማውጣትና አፍሪካውያን ነጻነታቸውንና ክብራቸውን ለመመለስ እንዲሁም አፍሪካን ወደ ኢኮኖሚ ዕድገት ለመምራት በተደረገው ትግል የማይነጥፍ አስተዋጽኦ ስታደርግም ቆይታለች።

ከድርጅቱ ምስረታ በፊት አፍሪካን ለሁለት ከፍሏት በነበረው በክዋሜ ንኩርማና በብዙሀኑ ቡድኖች መካከል የነበረው የአካሄድና የአስተሳሰብ ልዩነት እንዲፈታ በማድረግ ታላቅ አስተዋጽኦ አበርክታለች። ሃገራችን ወራሪውን የጣሊያን ኃይል ታግላ ነጻነቷን በማስመለስ ያስመዘገበችው ድል በአህጉሪቱ ለነጻነት ሲደረግ የነበረውን ትግል በማቀጣጠል በርካታ ሃገሮች ነጻነታቸውን እንዲጎናጸፉ አድርጓል። እ.ኤ.አ በ1960ዎቹ አፍሪካውያን በቅኝ አገዛዝ ሲሰቃዩ በዓለም-አቀፍ ፍርድ ቤት እየቀረበች በሕግ ትሟገትላቸውና ትከራከርላቸው የነበረችውም ሃገራችን ናት። በቅኝ አገዛዝና በአፓርታይድ ሥርዓት ሲሰቃዩ ለነበሩ አፍሪካውያን የሞራል፣ የዲፕሎማሲና የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ ረገድም ሚናዋን በሚገባ ተወጥታለች።

በንጉሱ ዘመን ሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጥሪ በመቀበል የሰላም አስከባሪ ሃይሏን ለሁለት ዓመታት በኮሪያ ልሳነ ምድር አዝምታለች። በአሁኗ ኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ የነበረውን ችግር ለመፍታትም የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል እ.ኤ.አ. ከ1960 እስከ 1964 በነበረው ጊዜ ውስጥ ግዳጁን ሥነ-ምግባር በተሞላበትና ሁኔታ ተወጥቷል። ለደቡብ አፍሪካ፣ ለናሚቢያና ለዚምባቡዌ የነጻነት ትግል ወታደራዊ ስልጠና በመስጠት ያደረገችው አስተዋጽኦም በታሪክ ሲወሳ የሚኖር ነው።

በዚህ ዘመን በሩዋንዳ እ.ኤ.አ በ1990ዎቹ በተከሰተውና የዓለምን ሕዝብ ባስደነገጠው የዘር ማጥፋት እንቅስቃሴ ሰላም እንዲያስከብሩ ከተደረጉት ሃገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ነች። በሩዋንዳ ሁቱና ቱትሲ የተባሉ ጎሳዎቿ ግጭት ውስጥ ነበሩ። ዘር ለይቶ የተፈጠረውን ዘግናኝ ድርጊት ለማስቆም በአፋጣኝ ሰላም አስከባሪ ኃይላቸውን እንዲልኩ ከተደረጉት ሀገሮች መካከል ኢትዮጵያ ቀዳሚዋ ናት። በዚህም ታሪካዊ አስተዋጽኦዋን አበርክታለች፤ በላይቤሪያም እንዲሁ። ላይቤሪያ ባለፈው የአውሮፓውያን አስርት መጨረሻ ዓመታት ላይ በከፍተኛ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ነበረች። ሀገሪቱን ወደ ሰላምና መረጋጋት ጎዳና ለመመለስ በተደረገው ሂደት የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል ተሳትፎ ወደር አልነበረውም። በሀገሪቱ ሰላምና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን በማድረግም ሚናውን ተጫውቷል።

በሱዳን ዳርፉር ግዛት ከሌሎች ሀገሮች ጋር በመሆን ባሰማራችው ሰላም አስከባሪ ሃይልም የእርስ በርስ ግጭት እንዳይከሰት ማድረጓም ይታወሳል። ሱዳንና ደቡብ ሱዳን በይገባኛል በሚከራከሩበት የአብዬ ግዛት በሰላም አስከባሪ ኃይልነት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥላ ሥር ከአለም በብቸኝነት በመሰማራት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነቷን ያሳደገ ተግባር አከናውናለች። ሃገራችን በሁለቱም ሃገሮች መንግሥታትና ሕዝቦች ያላት አክብሮትም ከፍተኛ ነው። በምሥራቅ አፍሪካ ሃገሮች ሰላም፣ ጸጥታና መረጋጋት እንዲሰፍን ከፍተኛ የሚባለውን ሚና ተጫውታለች።  

ሃገራችን በኢኮኖሚው መስክ ያላት አህጉራዊ ትብብር ኮሜሳ በሚሰኘው በምሥራቅና ማዕከላዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ የተጠናከረ ውህደት ለመፍጠር አስችሏል። በመሠረተ ልማት ግንባታ መስክ ንግድና ኢንቨስትመንትን ለመሳብም እያደረገች ያለው ጥረት በውጤት እየታጀበ ነው። የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግም በመሥራት ላይ ነች። ከጅቡቲ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ጋር የመንገድ ግንኙነት በመፍጠር ለጋራ ጥቅም ሰርታለች። ከጅቡቲ ጋር የሚያገናኘው የባቡር መሥመር አንዱ የዚህ ማሳያ ነው።   ለዚህች ሃገር የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ተጠቃሚ እንድትሆን ከማድረጓም በላይ፤ ኬንያንም በተመሳሳይ ሁኔታ እንድትጠቀም እንቅስቃሴ እያደረገች መሆኗን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በአህጉሪቱ መልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲን ለማስፈን የተያዘውን ጥረትም በአፍሪካ እርስ በርስ መገማገሚያ ስልትም እየተገበረችው ነው። ኢትዮጵያ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት ሕንጻ የተገነባበትን 2ሺህ ስኩዬር ሜትር መሬት መስጠቷም የአህጉራዊ ሚናችን  አንዱ ማሳያ ነው። የአፍሪካ ህብረት ጽህፈት ቤትን በአዲስ አበባ ከተማ እንዲሆን በማድረጓም ከሁሉም በፊት በኢትዮጵያና በሌሎች የአፍሪካ አገሮች መካከል ያለው ግንኙነት እንዲሻሻል አድርጋለች። ከዚህ በተጨማሪም ከተማዋ የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ መናኸሪያ እንድትሆን አድርጋለች። በዚህ ረገድ የሚወዳደሯት ኒውዮርክ፣ ጄኔቫና ብራስልስን የመሳሰሉ ከተሞች ብቻ ናቸው። በከተማዋ የሚደረጉት ጉባዔዎች፣ ስብሰባዎችና ዐውደ ጥናቶች ሌሎችም ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎችን በማስገኘት  አዲስ አበባችን ከፍ ብላ እንድትታይ አስችሏል። የከተማዋን አውራ ጎዳናዎች በአፍሪካ አገራት ስም መሰየሟ፤ እንዲሁም ለሁሉም አፍሪካ አገራት ለኢምባሲያቸው ህንፃ መስሪያ የሚውል መሬት በነፃ መስጠቷ ሌላውና ተጠቃሽ አፍሪካዊ ውለታዋ ነው።

የአፍሪካ ህብረት ምሥረታ የመሪዎች ጉባዔ ውይይት በቶጎ ርዕሰ ከተማ ሎሜ ላይ በተካሄደበት ወቅት፤ የሴኔጋል ፕሬዚዳንት የነበሩት አብዱላሂ ዋዴ “የህብረቱ መቀመጫ አዲስ አበባ ይሆናል” የሚለውን አንቀጽ እንደማይቀበሉት አስታውቀው ነበር፡፡ ታዲያ በወቅቱ ታላቁ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ ባቀረቡት የማሳመኛ ሃሳብ፤ “…ኧረ ለመሆኑ ማነው ማንዴላን ያሰለጠነው?- ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ናቸው፡፡ አድሃሪው ኃይለ ሥላሴ ናቸው አብዮታዊውን ማንዴላን ያሰለጠኑት፡፡ …ማነው ሮበርት ሙጋቤ ከሮዴሽያ አገዛዝ ነፃ ለመውጣት በሚፋለምበት ወቅት የረዳው? -መንግሥቱ ነው፡፡ መንግሥቱ ኃይለማርያም በሀገር ውስጥ አምባገነንና ጨፍጫፊ ነው፡፡ ነገር ግን በአፍሪካ ጉዳይ ልክ እንደ ኃይለ ሥላሴ አቋሙ ጠንካራ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ መሪዎች ቢለዋወጡም፤ በአፍሪካ ጉዳይ ላይ ግን አቋማቸው አንድ ነው፡፡ የአዲሱ አፍሪካ ህብረት መቀመጫ አዲስ አበባ መሆን የለበትም፣ ለእኔ ይገባኛል የሚል ካለ እውነቱን ፍርጥርጥ አድርገን ልንነጋገርበት እንችላለን…” በሚል ያቀረቡት ሃሳብ ገዢ ሆኖ ዛሬም የአፍሪካ ህብረት መቀመጫነታችንን አረጋግጠን ለዚህ እንድንበቃ አስችሎናል። ከሁሉም በላይ ከውስጥ ወደውጭ የሚመለከተው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያችን፤ ሰላማችን እንዲጠበቅ በማስቻሉ መቀመጫ መሆናችን እንዲጸና አስችሏል። ዛሬም እየተካሄደ የሚገኘው ጉባዔ የዚህ ማሳያና የአህጉራዊ ሚናችን ነጸብራቅ ነው። በመሆኑም በእስከዛሬው ተግባራችን ልንደሰት፤ በሚናችን ልንቀጥል ይገባል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy