Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

‘አልተገናኝቶም!’

0 278

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

‘አልተገናኝቶም!’

                                                    ቶሎሳ ኡርጌሳ

በቅርቡ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አመራሮች ድርጅታቸው ያካሄደውን ግምገማ አስመልክተው የሰጡትን ማብራሪያ ተከትሎ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዋና ዐቃቤ ህግ አቶ ጌታቸው አምባዬ መግለጫ ሰጥተው ነበር። በመግለጫቸው ላይም ታራሚዎች በምህረትና በይቅርታ መለቀቃቸውን በዝርዝር አስረድተዋል። እኔ በበኩሌ ከእርሳቸው አባባል ለመረዳት የቻልኩት የታራሚዎቹ መፈታት ዋነኛ ፋይዳ የፖለቲካ ምህዳርን ማስፋት ሳይሆን የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የተሻለ ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር ይመስለኛል።

የፖለቲካ ምህዳር መስፋት ማለት ማንኛውም ዜጋ በህገ መንግስቱ መሰረት ተደራጅቶ የፈለገውን ሃሳብ በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ አግባብ ማንሸራሸር መቻሉ ነው። የፖለቲካ ምህዳር መስፋት ከመደራጀት ህገ መንግስታዊ መብት ጋር የተያያዘ ነው ማለት ይቻላል። ታዲያ ይህ ተግባር ላለፉት 26 ዓመታት እየተሰራበት የመጣና በአሁኑ ወቅትም ምህዳሩን ይበልጥ ለማስፋት ዘርፈ ብዙ ተግባሮች እየተከናወኑ በመሆናቸው የፖለቲካ እስረኞቹ መፈታት ከዚህ እውነታ ጋር የሚያያይዘው ነገር አይኖርም።

የፖለቲካ ምህዳር መስፋት ተደራጅቶ ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት ሃሳብን በነፃነት፣ በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ከሆነ፣ በሌላ ዘውጉ ደግሞ ፀረ ዴሞክራሲያዊ አሰራሮችንና አዝማሚያዎችን ማውገዝ ማለት መሆኑን ለመገንዘብ አይከብድም። ይህም የፖለቲካውን ምህዳር ለማስፋት ሲባል በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ በፈፀሙት ወንጀል የህግ የበላይነትን ተፃርረው በህግ ጥላ ስር የዋሉትን ታራሚዎች ከመፍታት ጋር የሚያገናኘው ነገር የሚኖር አይመስለኝም።

በመሆኑም እኔ እስከሚገባኝ ድረስ እሰረኞችን የመፍታት ተግባር የተፈፀመው ቀደም ሲል የተከናወነንና እየተከናወነ ያለን የፖለቲካ ምህዳርን ለማስፋት ሳይሆን የተሻለ ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር ነው። ምንም እንኳን በአሁኑ ወቅት ሀገራዊ መግባባር በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዩች ዙሪያ አለ ተብሎ የሚታሰብ ቢሆንም፤ ይህን መግባባት ይበልጥ ማስፋትና ማጥለቅ ያስፈልጋል። ይህ አንዲሆን ደግሞ መንግስት እስከ ዛሬ ድረስ ሲያደርገው እንደነበረው ታጋሽና ሆደ ሰፊ መሆን አለበት። መንግስት ያደረገውም ይህን ይመስለኛል።

ስለሆነም መንግስትን የሚመራው ኢህአዴግ አመራሮች የድርጅታቸውን ግምገማ አስመልክተው የሰጡት ማብራሪያ መሰረት የተፈፀመው እስረኞችን የመፍታት ጉዳይን አንዳንድ ወገኖች የፖለቲካውን ምህዳር ለማስፋት ታስቦ የተከናወነ ነው በማለት የሚገልፁበት አግባብ ከዚህ አኳያ መታረም ያለበት ይመስለኛል። ምክንያቱም ቀደም ሲል እንደገለፅኩት የፖለቲካ ምህዳር መስፋት ትርጓሜና የእነዚህ ወገኖች እሳቤ የሰሜኑ የሀገራችን አርሶ አደሮች እንደሚሉት ‘አልተገናኝቶም!’ ስለሆነ ነው። እናም የእስረኞቹ መለቀቅ ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር ሲባል በኢህአዴግ ግምገማ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የተከናወነ እንጂ ከፖለቲካ ምህዳር መስፋና መጥበብ ጋር ግንኙነት የሌለው መሆኑን መገንዘብ አስፈላጊ ይመስለኛል።

ርግጥ የእስረኞቹ መፈታት በየትኛውም መስፈርት ቢሆን በበጎ ጎኑ የሚታይ ነው። በተለይም በአሁኑ ወቅት የሚታየውን የአንድ ወገን የተሳሰተ እይታን የሚያርቅ ያርቃል ብዬ አስባለሁ። ይህን የተገነዘበው መንግስትም የፍትህ ዘርፉንና ሌሎች የተቀመጡ አቅጣጫዎችን ለመፈፀም ግብረ ኃይል እንዲቋቋም አድርጓል።

ይህ ግብረ ኃይል የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ዕቅድ አፈፃፀም ተግባራትን ለይቶ ስራ ጀምሯል። ይህ ግብረ ሃይል  በሚቀጥሉት ሁለት ወራት የህግ የበላይነትን ባከበረ መንገድ ክሳቸው በመታየት ላይ ያሉ ተጠርጣሪዎችን ክስ የማቋረጥ፣ በተመሠረተባቸው ክስ ጥፋተኝነታቸው ተረጋግጦባቸው የተፈረደባቸውን ፍርደኞች ምህረት የመስጠት ስራን ጀምሯል። በዚህም እስካሁን ድረስ በፌዴራልና በደቡብ ክልል በመጀመርያው ዙር 528 ተጠርጣሪዎች ክስ እንዲቋረጥ ተደርጓል።

ተፈርዶባቸውም ይሁን ተጠርጥረው በህግ ጥላ ስር የሚገኙትን ግለሰቦች ክስ ለማቋረጥና ምህረት ለማድረግ ተከሳሹ ወይም ተከሳሿ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በተደረጉ ሁከቶች፣ ብጥብጦችና ሌሎች ጉዳዮች ላይ የሰው ህይወት ያላጠፋና ከባድ የአካል ጉዳት ያላደረሰ፣ ትልልቅ የኢኮኖሚ አውታሮችን በማውደም ተግባር ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ያልነበረው፣ ህገ መንግስቱንና ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በሃይል ለመቀልበስ በተደጋጋሚ አመፆችን ያልመራ መሆኑን ግብረ ኃይሉ በመስፈርትነት አስቀምጦ ሌሎች እስረኞችን ለመፍታት እየሰራ ነው።

ቀደም ሲል ክሳቸው የተቋረጠላቸውም ይሁን በሂደት የሚቋረጥላቸው ሌሎች ግለሰቦች ከዚህ በፊት በስርዓቱ ተጠቃሚ ሆነው ሳለ፣ ነገር ግን መንግስት መስራት የሚገባውን ስራ ባለማከናወኑ ሳቢያ በሌሎች ኃይሎች ፍላጎትና ዓላማ ተነሳስተው በጥፋትና በውድመት ተግባር ላይ የተሳተፉ ናቸው። እነዚህ ወገኖች በመንግስት ጥፋት ምክንያት ወደ ስህተት የገቡ በመሆናቸው፣ ክሳቸው እንደሚቋረጥና የምህረቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል፤ ወደፊትም ይደረጋል።

ግብረ ኃይሉ በሚቀጥሉት ሁለት ወራትም ተገቢውን ማጣራት በማድረግ ምህረት የሚደረግላቸውን ፍርደኞችና ተጨማሪ ክሳቸው የሚቋረጥላቸውን ተጠርጣሪዎች እያቀረበ፣ ምህረት እንደሚደረግላቸውና ክሳቸው እንደዲቋረጥ ይደረጋል። ታዲያ ይህ ሲከናወን የሀገሪቱ አዋጆች እንዲሁም ህጋዊ አሰራሮች ከግምት ውስጥ ይገባሉ።

ለምሳሌ ምህረትን በተመለከተ ቀደም ሲል የተቋቋመው ግብረ ሃይል ዝርዝር ጥናት አድርጎ ለፌዴራል ይቅርታ ቦርድ በማቅረብ ቦርዱም የግብረ ሃይሉን ጥናት መዝኖና መርምሮ ለርዕሰ ብሔሩ ያቀርባል። የሀገሪቱ ርዕሰ ብሔር ሲያፀድቁትም ለታራሚዎቹ ምህረት ይደረጋል። በክልልም በተቀመጠው አሰራር መሰረት በፈቃደ ስልጣኑ ልክ የክልሉ ይቅርታ ቦርድ አይቶ ለሚያፀድቀው አካል በመስጠት ምህረቱ ይደረጋል። ይቅርታም ቢሆን የሀገሪቱን የፍትህ ስርዓት አሰራሮች ተከትሎ የሚከናወን መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው።

ያም ሆኖ እነዚህ ተግባሮች የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ታስቦ የሚከናወኑ አይደሉም። የገዥው ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ባስቀመጡትና እስረኞችን ለመፍታት በገቡት ቃል መሰረት የሚከናወንና በዚህ ተግባርም ሀገራዊ መግባባትን ይበልጥ ለማስፋት ነው። እናም ክንዋነኔውን ከፖለቲካ ምህዳር መስፋት ጋር ማያያዝ ‘አልተገናኝቶም’ መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል።

ርግጥ እዚህ ላይ የሚነሱ በርካታ ጉዳዩች ሊኖሩ ይችላሉ። በተለይም የፀጥታ ሃይሎች አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የሚወስዱት ተመጣጣኝ የሃይል ርምጃ አንዱ ነው። ታዲያ ‘ተመጣጣኝ የሃይል ርምጃ ምን ማለት ነው?’ የሚጉዳይ በሚገባ መመለስ ይኖርበታል። አሊያ ግን አሁንም ቢሆን ለፅንፈኞችና ለፀረ ሰላም ሃይሎች ምቹ መደላድል መሆኑ አይቀርም። ይህን ቀዳዳ ለመድፈን አንድ አዋጅ መኖር አለበት። እንደሚታወቀው የፌዴራል ፖሊስ ማቋቋሚያ አዋጅ፤ ህግን ለማስከበር ተመጣጣኝ የሃይል ርምጃ መውሰድ ቢገልፅም ‘የተመጣጣኝ ሃይሉ ደረጃ እስከየት ድረስ መሆን አለበት?’ የሚለው ጉዳይ አልተመለሰም። መንግስት ይህን ለመወሰን የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ ለማዘጋጀት ረቂቁን አሰናድቷል።  ይህ ረቂቅ በቅርቡ ለህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት ለውይይት ቀርቦ አዋጅ ሆኖ የሚወጣ ይሆናል።

እነዚህ ሁሉ ተግባራት የሚፈፀሙት የፍትህ አካላትን አሰራርና አፈፃፀም በማሻሻል በመግባባት ላይ የተመሰረተ አንድነትን ለመፍጠር እንጂ ከፖለቲካ ምህዳር መስፋትና መጥበብ ጋር አንዳችም ዓይነት ግንኙነት ሊኖረው እንደማይችልና እንዲህ ዓይነቱ እሳቤም ‘አልተገናኝቶም’ መሆኑን መገንዘብ ከተሳሳተ ትርጓሜ የሚያድን ይመስለኛል።

   

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy