አስመስጋኙ ተግባር
ዳዊት ምትኩ
በቅርቡ መንግስት በፈፀሙት ወንጀል ምክንያት ለእስር የተዳረጉ ግለሰቦችን በይቅርታና በምህረት መልቀቁን አስመልክቶ፣ አንዳንድ ወገኖች ተግባሩ በጫና የተደረገ በማስመሰል የሚሰጧቸው አስተያየቶች ፈፅሞ ትክክል አይመስሉኝም። መንግስት የህዝብን ጥያቄ ሰምቶ ወንጀል የፈፀሙ እስረኞችን መልቀቁ ሊያስመግነው የሚገባ ተግባር ነው። በአንፃሩ ይህ ተግባር መንግስት ህዝብን የሚያዳምጥና ለህዝብ ወገናዊነት ያለው መሆኑን የሚያሳይ እንጂ ከጫና ጋር የመያገኛነው ጉዳይ የለም።
በሌላ በኩልም ሁሉም እስረኞች መፈታት አለባቸው በማለት አስተያየት የሚሰጡ አንዳንድ ወገኖች እሳቤያቸው የህግ የበላይነትን የሚሸረሽርና ፍፁም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን መገንዘብ የሚኖርባቸው ይመስለኛል። አንድ ወንጀል የፈፀመ ግለሰብ በወንጀሉ ልክ መጠየቅ ካልቻለና ዝም ተብሎ የሚታለፍ ከሆነ እንዲህ ዓይነቱ ተግባር ነገና ከነገ ወዲያ ወንጀልን የሚያበረታታ ከመሆን ባለፈ ስርዓት አልበኝነትንም የሚፈጥር ነው።
እንደሚታወቀው ሁሉ በየትኛውም አገር ውስጥ የህግ የበላይነት መጠበቅ አለበት። የህግ የበላይነት ካልተጠበቀ መዘዙ የከፋ ይሆናል። ሁሉም ሰው በህግ ፊት እኩል በመሆኑ በሰራው ወንጀል ልክ ይጠየቃል። እርግጥ በፃፈው ፅሑፍ ወይም ሃሳቡን በነፃነት በመግለፁ ብቻ ለእስር የተዳረገ ሰው ያለ የለም። በህግ ጥላ ስር የዋሉት ጋዜጠኝነትን በሽፋንነት በመጠቀም ከሀገሪቱ ህግ ውጪ ወንጀል የፈፀሙ ግለሰቦች ናቸው። ወንጀለኛ ደግሞ ጋዜጠኛም ሆነ ፖለቲከኛ፣ ቀዳሽም ሆነ ተኳሽ…በየትኛውም ሀገር በህግ አግባብ መጠየቁ አይቀርም።
እርግጥ የሀገሪቱን የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅንና ሌሎች ህጎችን አክብረው ሃሳባቸውን በነጻነት የሚያንጸባርቁ በርካታ የመገናኛ ብዙሃን የመፈጠራቸውን ያህል፤ ሀገሪቱን ለመበታተንና አንዱን ብሔር ከሌላው ጋር ለማጋጨት ይሰሩ የነበሩ መገናኛ ብዙሃን እንደነበሩ የሚካድ አይመስለኝም። ይህ ሁኔታ ዛሬም ቢሆን በማህበራዊ ድረ ገፆች ላይ የሚታይ ነው።
ይህም ሚዲያው ራሱ የሚከተለውን ሙያዊ ስነ-ምግባር ከመጣሱም በላይ፤ በተለያዩ ውስጣዊ ፍላጎቶቹ ሳቢያ የሀገሪቱን ህጎች አክብሮ ካለመስራት የመነጨ መሆኑ ከማንም የሚሰወር አይመስለኝም። እናም ሚዲያው ነጻና ጤናማ ሆኖ መስራት ሲገባው፤ በአንድ ሀገር ውስጥ የወጡ ህጎችን የሚፃረሩ ተግባራትን ከፈፀመ እንደማንኛውም ተቋም ከተጠያቂነት ሊያመልጥ የሚችል አይመስለኝም።
እንደ እውነቱ ከሆነ የኢፌዴሪ መንግስት በህገ-መንግስቱ ላይ በግልፅ የተደነገጉት ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብቶች እውን እንዲሆኑ ከመታገሉም በላይ፣ እንዳይሸራረፉም በፅናት ታግሎላቸዋል፤ እየታገለላቸውም ነው።
በተለይም ሚዲያ በሀገሪቱ የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ እመርታዎች ላይ የራሱን እሴት የሚጨምር መሳሪያ አድርጎ ነው የሚመለከተው፡፡ ይሁንና ሚዲያ ህግና ስርዓትን አክብሮ ካልተንቀሳቀሰ ከጠቀሜታው ባሻገር፤ በሁለንተናዊ የዕድገትና የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዓላማዎች ላይ ጉዳት ሊያደረስ እንደሚችልም እስካሁን ከታዩት ዝንባሌዎች የተረዳ ይመስለኛል።
እርግጥ በእኔ ዕይታ መንግስት የሚዲያን ጉዳት ለማስቀረት ሲል ጥቅሙን የመገደብ አካሄድ የሚከተል አይመስለኝም፡፡ እንደ ሌሎቹ የዴሞክራሲ ግንባታ ስራዎች ሁሉ፤ ሚዲያው ነፃና ጤነኛ ሆኖ እንዲያድግ ፈርጀ ብዙ ተግባራትን ማከናወኑንም ማጤን ያስፈልጋል። ይህም መንግስት ሚዲያውን ለማሳደግ የሚሰራ እንጂ ጋዜጠኞችን ያለ ወንጀላቸው ለማሰር ፍላጎት ያለው መሆኑን አያሳይም።
ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፖርቲ አመራሮችና አባላት ጋር በተያያዘም የሚነሳው ጉዳይ ተመሳሳይ ነው። ፖለቲከኛ ወንጀል ቢሰራም መታሰር የለበትም የሚል ህግ የለም። በእኛ አገርም ፖለቲከኛ (ተቃዋሚም ይሁን የገዥው ፓርቲ አባል ቢሆን) ባጠፋው ልክ ተጠያቂ ይሆናል። ፖለቲከኛውን ለማሰር ተብሎ የሚደረግ ምንም ዓይነት ነገር የለም። እንዲያውም በተለይ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ተሳታፊ በማድረግ የፖለቲካ ምህዳሩን ይበልጥ ለማስፋት እየተሰራ ነው።
እርግጥ እነዚህ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ዓላማቸውን ለማሳካት በሚያካሄዱት ማናቸውም እንቅስቃሴ ጣልቃ የሚገባ አንድም የመንግስት አካል ያለ የለም። በተለያዩ ጊዜያት ከመገናኛ ብዙሃን እንደምታተለው ፓርቲዎቹ በአገራዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ ይሰጣሉ፤ አቋማቸውንም ያንጸባርቃሉ። ተደራሽነታቸውን ለማስፋትም መገናኛ ብዙሃንን ተጠቅመው ዓላማቸውን ለህዝቡ ሲያደርሱ ማየት የተለመደ ነገር ነው።
እኔ እስማውቀው ድረስ ለምን ይህን አቋም አንጸባረቅክ ተብሎ የታገደ ፓርቲም ይሁን የታሰረ ግለሰብ የለም። ከዚህ ባሻገር ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚ ድርጅቶችን የሚያቀራርብና በወቅታዊ ጉዳዮች ያላቸውን አቋም የሚያንጸባርቁበት የክርክር መድረኮች መኖራቸው ብሎም የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ተፈጥሮ ተቃዋሚዎችም ሆኑ ገዥው ፓርቲ ቅሬታቸውን እንዲያቀርቡ ሁኔታዎች እንዲመቻቹ ተደርጓል።
ሀገራችን በ1987 ዓ.ም በመሰረተችው ፌዴራላዊ ሥርዓት አማካኝነት ሁሉም ብሔሮች በቋንቋቸው የመጠቀምን መብት ተጎናጽፈዋል፣ በሁለት ሚሌኒየም ዓመታት ታሪካችን ለአምስት ጊዜያት የመድብለ ፓርቲ ምርጫዎችን ለማካሄድ በቅተናል። በዚህም ላለፉት 26 ዓመታት የዴሞክራሲ ስርዓት ባህል ግንባታ ሂደት ስር እንዲሰድ ጥረት ተደርጓል።
እንደሚታወቀው ሁሉ ሠላም ባልሰፈነበት ሁኔታ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን መገንባት አይቻልም። ልማትንም ማምጣት እንዲሁ። በሌላ በኩልም የሀገራችን መንግሰት ምንም እንኳን ሀገራዊ ሠላምን ማረጋገጥ ተቀዳሚ ተግባሩ ቢሆንም፤ የጎረቤት ሃገሮች ሰላም ማጣት አገራዊው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ላይ የሚያስከትለውን ችግር ጠንቅቆ ስለሚገነዘብ፤ በዚህ ዙሪያ ጠንካራ አቋም ይዞ ተንቀሳቅሷል።
በአገራችን ዕውን እየሆነ የመጣው ፈጣንና ተከታታይ ዕድገትም አስተማማኝ ሠላምና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባህል ግንባታ ሂደት ስኬታማነትን ብሎም የሂደቱን ውጤታማነት የሚያመላክት ነው። ምክንያቱም ሠላም በሌለበት ፈጽሞ ስለ ልማትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባህል ግንባታ ማሰብ ስለማይቻል ነው።
እናም ዓለም የመሰከረው ዕድገት ባለቤት የሆነው የሀገራችን ህዝብ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቱ ሳይከበር ተምሳሌታዊ ልማት ሊያስመዘግብ አይችልም። ይህ ተግባራዊ ክንዋኔም በ26 ዓመታት ውስጥ በአብዛኛው የተከናወኑ ዴሞክራሲያዊ ሁነቶችን የሚያመላክት እንጂ፤ አንዳንድ ወገኖች እንደሚሉት ተገላቢጦሹን የሚያሳይ ሁኔታ አይመስለኝም። እናም በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ወንጀልን ለመከላከልና የህግ የበላይነትን ለማስፈፀም ሙያቸው ፖለቲካ የሆኑ የተቃዋሚውም ይሁን የገዥው ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮችና በሰሩት ወንጀል ምክንያት በቁጥጥር ስር ሊውሉ ይችላሉ። ይህ በየትኛውም አገር ውስጥ የሚሰራበት ነው።
ያም ሆኖ ሰሞኑን መንግስት በቁጥጥር ስር ያዋላቸውንና በጥፋታቸው ምክንያት የተፈደረባቸው ወይም ጉዳያቸው በመታየት ላይ ያሉ ግለሰቦችን ሁሉ ሊፈታ አይችልም። በዚህ ዓይነት አሰራር የህግ የበላይነትን ማስከበር አይቻልም። በወንጀል የተከሰሱ ሰዎችን ሁሉ እንፍታ ቢባል፤ አገሪቱ ነገና ከነገ ወዲያ ህግና ስርዓትን ልታስከብር አትችልም። እስካሁን ድረስ በፌዴራል መንግስትና በክልሎች ውስጥ መንግስት ለታሳሪዎች የሰጠው ይቅርታና ምህረት የሚያስመሰግነው እንጂ የሚያስወቅሰው አለመሆኑን ማወቅ የሚያስፈልግ ይመስለኛል።