Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አስተሳሰብ ላይ ትርጉም ያለው ስራ እንስራ

0 522

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አስተሳሰብ ላይ ትርጉም ያለው ስራ እንስራ

ኢዛና ዘ መንፈስ

 መቼስ ሀገራችን የምትገኝበት ወቅታዊ እውነታ እኛ ኢትዮጵያውያን በጋራ ችግሮቻችን ዙሪያ ይበጃል የምንለውን የመፍትሔ ሀሳብ እንለዋወጥ ዘንድ የሚያስገድድ ነው አይደል? እንግዲያውስ እኔም እንደ አንድ ዜጋ የጋራ ህልውናችን ለተመሰረተባት ሀገር ምልዓተ ህዝቦች ዘለቄታዊ የጋራ ዕጣ ፈንታ መቃናት የሚበጅ መስሎ የሚሰማኝን ሀሳብ ከመሰንዘር የማልቦዝነው ያለ ምክንያት እንዳይመስላችሁ፡፡ ይልቁንስ ከላይ በመግቢያየ እንዳልኩት ይሄ የምንገኝበት ወቅት እኛ ኢትዮጵያውያን ህዝቦች እንደህብረተሰብ የየራሳችን የመፍትሔ ሀሳብ እያቀረብን መነጋገር፤ መደማመጥና ብሎም መተማመን እንደሚጠበቅብን የሚያመላክት ስለሆነ እንጂ፡፡ ስለዚህም የዛሬው መጣጥፌ ዋነኛ ዓላማም ገዢው ፓርቲ ኢ.ህ.አ.ዲ.ግ. እንዲሁም ደግሞ በእርሱ የሚመራው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. መንግስት እያካሄዱት ያለው የጥልቅ ተሀድሶ መርሀ ግብር አሁን ላይ የደረሱበትን ደረጃ እንደ በጎ ጅምር በመውሰድ ንቅናቄውን ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚረዱ ተጨማሪ ግብዓቶችን ለመጠቆም መሞከር ይሆናል፡፡

እናም አሁን በቀጥታ የማልፈውም ሀገራችን ኢትዮጵያ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ለአሳሳቢ የሠላምና መረጋጋት መጓደል ችግር የተዳረገችበት መሰረታዊ ምክንያት ምንድን ነው ሊባል ይችላል?ሰ ሞነኛው የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ. ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ጥልቅ ግምገማስ ይህን ቁልፍ ጥያቄ በተሟላ መልኩ የሚመልስ ውይይት አካሂዷል ወይ? ከሆነስ ለምን የሚያጠግብ ማብራሪያ ሲሰጥበት አልሰማንም? ወዘተ.. በሚሉ ነጥቦች ዙሪያ አንዳንድ ተጨማሪ ጉዳዮችን ወደ ማነሳበት የግል አስተያየቴ ነው፡፡ ስለሆነም ከዚህ አኳያ እኔ ለወቅታዊው የሀገራችን አጠቃላይ ችግሮች መሰረታዊ መንስኤ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ዋነኛ ምክንያት ነው የምለው ቁልፍ ነጥብ፤ አስተሳሰብ ላይ መስራት የነበሩብንን ያህል ሳንሰራ መቅረታችን ያስከተለው ቀውስ ነው፡፡ እንዴት? አሊያም ደግሞ ለምን? ለሚለው ጥያቄም እነሆ ከዚህ እንደሚከተለው ምላሽ እሰጣለሁና አብረን እንመልከት፡፡

እውነቱን ተነጋግረን ከስህተቶቻችን መማር ካለብን የዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰፍኖ ስለሚስተዋለው የውጥረትና የስጋት ደባብ ትክክለኛ ምንጭ ለመረዳት የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ሊቅ መሆን የሚጠበቅብን አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ደግሞ እስከ 2008 ዓ.ም. የመጀመሪያ ወራት ድረስ በየትኛውም የሀገራችን ክፍል ነዋሪውን ህብረተሰብ የደህንነት ስጋት ላይ የሚጥል ምንም ዓይነት አሳሳቢ የፀጥታ መደፍረስ ችግር ስለመከሰቱ የሰማንበት አጋጣሚ እንብዛም እንዳልነበር ማስታወስ አያዳግትምና ነው፡፡ ስለዚህ ከዚያን ጊዜ ወዲህ በየስበብ አስባቡ እየተቀሰቀሰ ለበርካታ ዜጎቻችን ህልፈተ ህይወት መንስኤ ከመሆኑም ባሻገር የዚህችን ደሀ ሀገር ውስን ሀብት ላልተገባ ኪሳራ ሲዳርግ የተስተዋለው ተደጋጋሚ የሁከትና ብጥብጥ ተግባር ሊከሰት መቻሉ ለምን እንደሆነ ስናስብ መልሱ የዘመኑ ዓለም አቀፋዊ ተፅዕኖ ድምር ውጤትም ጭምር ተደርጎ የሚወሰድ የአመለካከት ቀውስ ያስከተለው አደጋ እያጋጠመን ነው የሚል እንደሚሆን ይሰማኛል፡፡

ከዚህ አኳያ እየተስተዋለ ያለው ኢትዮጵያውያን ህዝቦችን በየጥቃቅኑ ሰበብ አስባብ እርስ በእርስ ለማቃቃርና ስለ ዘለቄታዊ የጋራ እጣ ፈንታችን መቃናት ያለመቃናት ጉዳይ እንዳናስብ ለማድረግ ያለመ ጽንፈኛ አስተሳሰብን እንደወረርሽኝ በማዛመት ረገድ እንደ ሀገር የተከፈተብን ጦርነት ተደርጎ የሚወሰድበት አግባብ እንዳለ ሆኖ የሚሰማኝም ደግሞ ሰሞኑ የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ. አባል ድርጅቶች ከፍተኛ የአመራር አካላት ለመገናኛ ብዙኋን በሰጡት የጋራ ቃለ ምልልስ ላይ የተነሱ አንዳንድ ወቅታዊ ችግሮቻችን መገለጫ ነጥቦች ሳስታውስ ነው፡፡ ለአብነት ያህልም ይህቺን ሀገር የመምራት እጅጉን የከበደ ታሪካዊ ኃላፊነት በተሸከመው የግንባሩ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ደረጃ እርስ በእርስ መናበብም ሆነ መተማመን እስኪጠፋ ድረስ ጎልቶ የሚገለፅ የመርህ የለሽነት ችግር ይስተዋላል ሲባል መስማት ምንኛ ሊያስደነግጥ እንደሚችል አስቡት፡፡ ይህን አደገኛ አዝማሚያ እያስከተለብን ያለው ተጨባጭ ምክንያትስ ምንድ ነው? ሲባልም ደግሞ እኛ እንደ ሀገር አስተሳሰብ ላይ መስራት በነበረብን ልክ ያለመስራታችንና በአንፃሩም ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ. መራሹ የኢትዮጵያ ህዝቦች የትግል መስመር የሚያራምደውን ዓላማ አምርረው በማጥላላት የሚታወቁ አክራሪ ተቀቃዋሚ የፖለቲካ ቡድኖች  የየራሳቸውን ወደ አንድ ፅንፍ ጭልጥ ብሎ የመንጎድ አባዜ የተጠናወተው እሳቤ ጠቃሚ አስመስለው በማቅረብ ተግባር ላይ ስለሚጠመዱ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ይልቁንም ደግሞ በምዕራባዊያኑ ባለፀጋ ሀገራት ውስጥ እየኖሩ የህዳሴው ዘመን ኢትዮጵያ ህዝቦች እጅ ለእጅ ተያይዘን የምናካሂደውን ፈርጀ ብዙ የፀረ ድህነትና ኋላ ቀርነት ትግል ለማምከን ሲሉ የሚያውጠነጥኑት የጥፋት ሴራ የሌላቸው ዲያስፖራ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች መርዘኛ ፕሮፖጋንዳቸውን ሲያዛምቱ የሚስተዋሉበት አግባብ እንደ ህብረተሰብ ላልተለመደ የአስተሳሰብ ቀውስ የምንጋለጥበትን የተጠና ውዥንብር እያቀነባበሩ ማሰራጨት እንደመሆኑ መጠን ለአመለካከት ብዥታ መጋለጣችን ላያስገርም ይችላል፡፡

እንዲያውም እንደ አንዳንድ የፌደራል ስርዓቱን ሲፈታተኑት ከሚስተዋሉት መንገራገጮች     በስተተጀርባ ስላሉ አሉታዊ ተፅዕኖዎች ጉዳይ የየራሳቸውን  ማብራሪያ ሲሰጡ እንደሚደመጡ አንዳንድ የፓለቲካ ተንታኞች ከሆነማ “በስልጣን ላይ ያለው ገዢ ፓርቲ መሰረታዊ ድክመት ተደርጎ ሊወሰድ የሚችለው ህገ-መንግስታዊ አስተሳሰብ የበላይነት እንዲይዝ የማድረግ ስራ ላይ የሚያሳየው ጥረት አጥጋቢ ያለመሆኑ ነው” ሲሉ ይሰማሉ፡፡ እነዚህ የፌዴራል ስርዓቱ ለመላው የሀገራችን ህዝቦች ዘለቄታዊ የጋራ ዕጣ ፈንታ መቃናት የሚበጅ መሆኑን ከመረዳት የመነጨ ቅን ምክር ሲለግሱ የሚደመጡ ወገኖች አክለው እንደሚሉትም “በህገ መንግስቱ ላይ የተቀመጡትን የሠብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተጨባጭ ጠቀሜታ ተረድቶ ያለመሸራረፍ እንዲረጋገጡ የሚጠይቅ ህብረተሰብ የመፍጠር ስራ ባለመሰራቱ ምክንያት እኮ ነው እንደ እነ ጁሀር መሀመድ አይነቶቹ ፅንፈኛ ዲያስፖራ ግለሰቦች በሚጽፉት ብጣቂ ማስታወሻ ሀገር አውዳሚ የሁከትና ብጥብጥ ተግባር የሚቀሰቅሰው። ትርጉም ያለው ጥረት ባለማድረጋችን ምክንያት እንጂ ሌላ ተዓምር ስለተፈጠረ አልነበረም፡፡ ስለሆነም በኢትዮጵያ ታሪክ እምብዛም ያልተለመደ ነው የሚባልለትን ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ለሚያካሂዱት ኃይሎች ሁሉ ቁልፉ የማስፈፀምያ መሳሪያ በአስተሳሰብ ልዕልና ላይ የተመሰረተ ህዝባዊ ድጋፍ ማግኘት እንደመሆኑ መጠን፤ ከዚህ አኳያ መስራት የሚጠበቅባቸውን አስተማማኝ የቤት ስራ ያልሰሩ የሀገራችን የፖለቲካ ድርጅቶች፤ ፓርቲዎችና ግንባሮች አሁን እንኳን የምር መንቃት ይኖርባቸዋል” ነው የሚሉት፡፡

  በእርግጥም ደግሞ ይህንን አስተያየት የሚሰጡት ወገኖች እውነት አላቸው፡፡ ምክንያቱም ሀገራችን የምትመራበትን ፌደራላዊ ህገ መንግስት አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ዜጋ በቅጡ ተገንዝቦት እዚያ ላይ የተደነገጉት ሠብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶቹ ያለ አንዳች መሸራረፍ ተግባራዊ እንዲደረጉለት ሊታገል እንዲችል ትርጉም ያለው አወንታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድር የአስተሳሰብ ብዝሃነትን ስለማክበርና ስለማስተናገድ አስፈላጊነት ጉዳይ የጋራ መግባባት የመፍጠር ስራ እንደ ሀገር በእኩል መጠን ሰርተን ቢሆን ኖሮ ይሄው ዛሬም ድረስ ጥቂት ከአትላንቲክ ውቅያኖስ ወዲያ ማዶ የሚኖሩ ስልጣን ናፋቂ ዲያስፖራ ግለሰቦች ሆን ብለው እኛን በሁከትና ብጥብጥ ተግባር ለማተራመስ ሲሉ የሚያቀነባብሩትን ውዥንብር ከቁም ነገር ቆጥሮ ለእነርሱ የጥፋት ተልዕኮ ማስፈፀሚያ መሆንን የሚመርጥ ወጣት ዜጋ ባልተበራከተ ነበር፡፡ ስለዚህም እንደ እኔ እንደ እኔ ወቅቱ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ የፖለቲካ ኃይሎች ለየራሳቸው የአስተሳሰብ ልዕልና መረጋገጥ ያለመ ፈርጀ ብዙ ትግል ሲያካሂዱ የሚስተዋሉበትና በዚያው ልክም ትርጉም ያለው ተጽዕኖ የሚያሳድር ዓለም አቀፋዊ የእንቅስቃሴ አድማሳቸውን የማስፋት አቅም የመፍጠር ስራ በመስራት ተግባር ላይ ተጠምደው የሚገኙበት ሆኖ ሳለ ለጉዳዩ ተገቢ ትኩረት አለመስጠት ያስገርማል ባይ ነኝ፡፡ እንኳንስ ዛሬ ላይ እየተስተዋለ ካለው ዓለም አቀፋዊ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ተጨባጭ እውነታ አኳያ ትግሉ ከደርግ ኢሰፓው ወታደራዊ አምባገነን አገዛዝ ጋር በሚደረግ ደም አፋሳሽ የእርስ በእርስ ጦርነት ላይ የተመሰረተ በነበረበት ዘመን ኢ.ህ.አ.ዲ.ግ. መራሹ የኢትዮጵያ ህዝቦች ፀረ ጭቆና የትግል ሂደት ከምንም ተነስቶ ጨፍጫፊውን የአፈና መዋቅር ለማፈራረስ የበቃው የአስተሳሰብ ልዕልና ያቀዳጀውን ቅድመ ሁኔታ በማሟላት ረገድ የተሻለ ስራ መስራት ስለቻለ እንደነበር አይዘነጋም፡፡

 አለበለዚያ ግን ሰላማዊ የፖለቲካ ኃይሎች ትግል እየተካሄደ ነው ስንል ድንገት ባለፈው ታሪካችን እንታወቅበት ወደ ነበረው ደም አፋሳሽ የእርስ በእርስ ጦርነት አዙሪት የመመለስን አደጋ ሊያስከትልብን ወደሚችል ግጭትና ብጥብጥ የምናመራበት ሁኔታ የሚስተዋለው ያለምክንያት እንዳልሆነ መገመት አይከብድም፡፡ ስለዚህ እኔም ይህቺን ኢትዮጵያውያን ህዝቦች እንደ ህብረተሰብ ትርጉም ያለው የአስተሳሰብ ለውጥን የማምጣት ስራ ላይ እናተኩር ዘንድ የምታስገነዝብ ሐተታዬን የምቋጨው ሰሞኑን የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ. አባል ድርጅቶች ሊቀመናብርት ለመገናኛ ብዙኋን ስለወቅታዊው የሀገራችን ፖለቲካ ማብራሪያቸውን ከሰጡበት የጋራ ቃለ ምልልስ ላይ በተለይም አቶ ለማ መገርሳ የተናገሩትን አንድ ጠቃሚ ነጥብ አስታውሼ ይሆናል፡፡

  “እንግዲህ እንደ እኔ አረዳድ ከሆነ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ለረጅም ዘመናት አብረው ሲኖሩ በመካከላቸው ፈርጀ ብዙ ትስስርን እንደፈጠሩ የሚካድ ጉዳይ አይደለም፡፡ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያዊ አንድነታችን የሚገለጽበት የህዝቦች ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ትስስር የጠበቀ ነው ብዬ ስለማምን በአንድ ሰሞን ግርግር እንበታተናለን የሚል ስጋት የለኝም፡፡ ግን ደግሞ በመካከላችን መሰረታዊ ችግር ኖሮ መለያየት እንኳን ካለብን ተነጋግረንና ተወያይተን በመተማመን ብቻ ነው እንጂ ሊሆን የሚገባው ሌላ የመፍትሄ መንገድ ለማንኛውም ወገን የሚጠቅም አማራጭ አይደለም፡፡ ልዩነቶቻችንን ሁሉ ከሀሳብ ፍጭት በሚመነጭ ሰላማዊ ትግል ለህዝብ እያቀረብን ህዝቡ ራሱ እንዲዳኘን ማድረጊያ መንገድ ተጠርጎልን ሳለ  ወደ ሌላ አላስፈላጊ አቅጣጫ አምርተን እንዲቀሰቀስ ምክንያት ሲሆን የሚስተዋልበት አጋጣሚ ጥቂት አይደለም፡፡ ስለዚህ እርስ በእርሳችን የምንጠፋፋበትን አደጋ ለሚያስከተል ማንኛውም ዓይነት አደጋ በር መክፈት አይኖርብንም” ሲሉ ወቅታዊውን የሀገራችን ጉዳይ አስመልክተው የበኩላቸውን ምላሽ የሰጡት የኦ.ህ.ዴ.ድ. ሊቀ መንበር አቶ ለማ መገርሳ እግረ መንገዳቸውን የዘመነ ኢህአፓው ፖለቲካዊ የእርስ በእርስ መጠላለፍ ይህቺን ሀገር ስላስከፈላት ዋጋ አስታውሰዋል፡፡ እኔም የእርሳቸውን ሐሳብ እንደምጋራ እነሆ በዚህ አጋጣሚ ጠቁሜ ለማለፍ እወዳለሁ፡፡ በተረፈ ግን ለዛሬ እዚህ ላይ ይብቃኝ፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy