Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አቀበቱ ተጋምሷል፤ብርሃንም ፈንጥቋል

0 325

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አቀበቱ ተጋምሷል፤ብርሃንም ፈንጥቋል

                                                          ደስታ ኃይሉ

ኢትዮጵያ የጀመረቻቸው ስኬቶች ሳይስተጓጎሉ ተጠናክረው የመቀጠላቸው ምስጢር ትናንት ያስመዘገበቻቸው መልካም ነገሮች ተዓማኒነት በማትረፋቸው ነው። በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች ነውጥ ቢከሰትም የአገራችን ፈጣን የዕድገት ባቡር ግን አልተቋረጠም።

መንግስት አገራችን በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንድትገኝ ያስቻለው ችግሮችን ከህዝብ ጋር እየተመካከረ በሰከነ መንገድ መፍታት በመቻሉ ነው። ዛሬ ስለ አገራችን ሁለንተናዊ ለውጥና እድገት የማይዘግም የሚዲያ አውታር፣ የማይመሰክር ዓለም አቀፍ ተቋም የለም። ትናንት የነበርንበት አቀበት በአሁኑ ሰዓት ከመጋመሱም በላይ፤ የብርሃን አውድም በመላው አገሪቱ መፈንጠቅ ችሏል።

የፈነጠቀውን ብርሃን የሚያጎላው “የኢትዮጵያ ከፍታ ነው” ብለን የተቀበልነው መጪው ዘመን ነው። መንገድ ላይ የምናልፋቸው አባጣ ጎርባጣዎች ልማታችን በማሳካት የመታደሳችንን ሂደት የሚያፋጥኑልን መሆናቸው አይቀርም። ከቅርቡ ለመነሳትም በአገራችን ህዝቦች ርብርብ እየተተገበረ ያለውን ሁለተኛው የልማት እቅድ በተገቢው መጠን መፈፀም ለዚህ ሃቅ የሚያበቃን መሆኑ ጥርጥር የለውም።

እንደሚታወቀው ሁሉ ከግብርና አኳያ የዕድገቱ ምንጭ በአነስተኛ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ቤተሰቦች በሚካሄድ ልማት ላይ የተመሠረተ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ባለን አቅም የምንጠቀምባቸውን ቴክኖሎጂዎች በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋልና የኤክስቴሽን ስርዓቱን በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ተግባራዊ ቢደረግ እንኳን እጅግ የላቀ የምርታማነትና የምርት መጠን ልንደርስ እንችላለን፡፡

ስለሆነም ከግብርና አኳያ በሰብል ልማትም ሆነ በእንስሳት ሃብት ልማት እንዲሁም የተፈጥሮ ሃብት ልማትና የመስኖ ሥራን ጨምሮ የማምረት አቅማቸው ከፍተኛ እንዳይሆኑ ያሉትን ችግሮች መፍታት ይገባል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን አሁን ባለው ቴክኖሎጂ የማምረት አቅማቸው ደረጃ ለተቃረቡ ሞዴሎች ተጨማሪ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የማዘጋጀት የማባዛትና የማሰራጨት ሥራ በተጨማሪነት ለመስራት ታቅዷል፡፡ ከስትራቴጂክ የምግብ ሰብሎች ምርታማነት መጨመር በተጓዳኝ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ የማምረት አቅምን ለማሻሻል በሆርቲካልቸርና በእንስሳት ሃብት ልማት እንዲሁም ሌሎች የኢንዱስትሪ ግብዓቶችና የኤክስፖርት ምርቶች ላይ ለማተኮር ዕቅድ ተይዟል፡፡

የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪን መሰረት ለማስፋት የግብርና ምርቶችን በግብዓትነት የሚጠቀሙ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪያችን ማስፋት አማራጭ የሌለው ተነፃፃሪ መወዳደሪያችን ነው፡፡ የአገራዊ ባለ ሃብቶች በስፋት እንዲሰማሩ ለማድረግም ታቅዷል።

ይህ በመሆኑ የፋብሪካ አካላቶችንና መለዋወጫዎችን በሀገር ውስጥ ለማምረት የሚያስችል ገና ያልተሟጠጠ የማምረት አቅም በመኖሩ በዘርፉ በችግርነት የሚታወቁ የቴክኖሎጂ የመቅዳት ዲዛይን የማድረግ፣ ፍብረካና የማላመድ ስራዎችን በፍጥነት ለመሻገር እንዲሁም የተመረቱትን ፍብረካዎች የማሠራጨትና የማስተግበር ሥራ ዋነኛው አቅጣጫ በመሆኑ መስራት ይገባል፡፡ ይህ የአሰራር ዓይነት አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን ለማስፋፋት የሚያስችል ነው፡፡

ከዚህ በተጓዳኝ በሀገር ውስጥ ሊፈበረኩ አቅማችን ያልደረሰባቸውን የካፒታል ዕቃዎችን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት የዘርፉን ዕድገት ማፋጠን ይገባል፡፡ ስለሆነም የኢንጂነሪንግና የፋብሪካ አሰራሮች አቅምን ማጐልበትና በዚህም ሳቢያ የማምረት አቅማችን መድረስ የምንችልበት ደረጃ በማድረስ የዘርፉን ትራንስፎርሜሽን ማረጋገጥ በዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ መሆን የሚገባው ይመስለኛል፡፡

እርግጥ በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ወቅት የኢኮኖሚ መሠረተ ልማቱን ለማሰፋፋት ከፍተኛ ጥረት በመደረጉ አመርቂ ውጤት ተገኝቷል። ይሁንና አሁንም ከመሰረተ ልማት አገልግሎት አኳያ ዕጥረቱ ሙሉ ለሙሉ ተፈትቷል ማለት አይቻልም፡፡

ታዲያ ዘርፉ የሚጠይቀው ኢንቨሰትመንት ከፍተኛ በመሆኑና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚፈልግ ስለሆነ የውስጥ አቅምን ማጎልበት ያስፈልጋል፡፡ እንደሚታወቀው ሁሉ የማስፈፀም አቅምን ከመገንባት በተጠናቀቀው የልማት ዕቅድ በርካታ ሥራዎች የተከናወኑ ቢሆንም የዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይልና የማስፈፀም አቅም አሁንም ውስን ነው። ይህ በመሆኑም የትላልቅ ፕሮጀክቶችን ዲዛይንና ግንባታ በሚመለከት በተያዘስው የልማት ዕቅድ በራስ አቅም እየተከናወነ ነው፡፡

የኢኮኖሚ መሠረተ ልማት በሚፈለገው ደረጃ ለማሳደግ ባለፉት የዕቅድ ዓመታት በዘርፉ የታዩ ፈታኝ ሁኔታዎች የማቃለልና መልካም ተሞክሮዎችን አጠናክሮ መቀጠል ትኩረት እየተሰጠ ነው፡፡

በዘርፉ ከፍተኛ ኢንቨሰትመንት እንዲካሄድ ማድረግ፣ ከውጭ የሚገቡ ቁሳቁሶችን በአገር ውስጥ እንዲመረቱ ማስቻልና በዚህም የውጭ ምንዛሪ ፍላጎቱ ላይ የሚፈጠረውን ጫና ለመቀነሰ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ሆኗል፡፡ በዚህም በሁሉም የመሠረተ ልማት መስኮች የሰለጠነ የሰው ኃይልና የፋይናንስ ዕጥረትን ማቃለል፣ የፕሮጀክት ፋይናንስ የማፈላለግና የማስተዳደር አቅምን የማጎልበት እንዲሁም የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ማምጣት…ወዘተ. የሚያስችሉ ጉዳዩች እየተከናወኑ ነው፡፡

የኢኮኖሚ መሠረተ ልማት ሀገራችንን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ ለማሳለፍ የተቀመጠውን ራዕይ ለማሳካት የሚያስፈልገውን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት በሚደግፍ ደረጃ፣ ጥራትና ፍጥነት እንዲያድግና ኢኮኖሚው ተወዳዳሪ እንዲሆን ብሎም ሁሉን አቀፍ ዕድገት እንዲመጣ ለማድረግ የላቀ ትኩረት ተሰጥቶት ስራው እየተከናወነ ነው፡፡

ከዚህ አኳያ የግሉ ዘርፍ በመሠረተ ልማት ዘርፍ የሚጠበቅበት ተሳትፎ ከፍተኛ በመሆኑ እንዳግባቡ ለግሉ ዘርፍ በተፈቀዱ ንዑስ ዘርፎች ውስጥ ያለው ተሳትፎ እንዲያድግ አስፈላጊውን ማበረታቻና ድጋፍ በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡ በግሉ ዘርፍ ከሚጠበቁ ተሳትፎዎች ውስጥ ጥራት ያለው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እንዲበረታታ በማድረግ ከገንዘብ በተጨማሪ የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲያመጣ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

እርግጥ በርካታ መሠረተ ልማቶች በሁለተኛው የልማት ዕቅድ በመንግስት መቅረባቸው ይቀጥላል። ሆኖም በተመረጡት መረተ ልማቶች ላይ በመንግስትና በግል አጋርነት ሊለሙና ሊቀርቡ የሚችሉበት መንገድ በጥናት ተለይቶ ተግባራዊ እንደሚደረግ ዕቅድ ተይዟል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከመሠረተ ልማት ዘርፍ ዕድገት ጋር የተገናኙ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ የልማት ግቦች ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ሀገራዊ የልማት አጀንዳዎች ጋር ተጣጥመው ሥራ ላይ እንዲውሉ ለማድረግም ቁርጠኛ አቋም ተይዟል፡፡

የኢኮኖሚ መሠረተ ልማት ዕድገት ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፣ አዳዲስ የገበያ ዕድሎችን ለመፍጠር፣ የሸቀጦች ዋጋን ለመቀነስ፣ የተወዳዳሪነት አቅም ለመፍጠር፣ የቀጣና የኢኮኖሚ ትስስርን ለመፍጠር ካለው ፋይዳ አኳያ ገቢራዊ እየተደረገ ነው። በዚህም የመንገድ፣ የባቡር፣ የደረቅ ወደብ፣ የአየር ትራንስፖርት፣ የኢነርጂ፣ የቴሌኮም፣ የውሃና የመስኖ ሥራዎች የተለየ ትኩረት ተሰጥቷቸው እንዲስፋፉ እየተረደጉ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት የመንግስትና የግል ኢንቨስትመንት እየተስፋፉ መጥተዋል። ይህም የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው እንዲጎለብት ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ዘርፉን በማሳደግ ላይ ይገኛል፡፡ እንደሚታወቀው ሁሉ በአሁኑ ወቅት የአገራችን ኢኮኖሚ ፈጣንና ቀጣይነት ባለው የዕድገት ምዕራፍ ላይ ይገኛል። ይህም ተወዳዳሪ የኮንስትራክሽን አቅምን ጠይቋል፡፡ በዚህም ሳቢያ መንግስት ኢንዱስትሪውን የሚመራበትን የኮንትራክሽን ፖሊሲን በመንደፍ ለተግባራዊነቱ ጉልህ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው፡፡

ፈጣን የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዕድገትን ለማረጋገጥ የተደረገው ጥረት ከወዲሁ ፍሬ እያፈራ ነው፡፡ ይህን የዕቅዱን ትልም ዕውን ለማድረግም በሀገር ውሰጥ ባለሃብቶችና በተመረጡ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስተሮች አማካይነት ሰፋፊ የኢንቨስትመንት ተግባራት እንዲተገበሩ እየተደረገ ነው፡፡

ይህን ዕውን እንዲሆንም ነባር ኢንዱስትሪዎችም ሆነ አዳዲሳቹ ይህንን ተልዕኮ ማሳካት የሚችሉት የቴክኖሎጂ አጠቃቀማቸውን፣ ምርታማነታቸውን፣ የጥራት አመራር አቅማቸውንና ተወዳዳሪነታቸውን እንዲገነቡ ድጋፍ በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡ እነዚህ መንግስታዊ ትልሞች ቀስፎ የያዘንን የድህነት አቀበትን እንዳጋመስን ማሳያዎች ብቻ አይደሉም፤ የመጪው ጊዜ ውጋጋናዊ ብርሃን ፍንተው ብሎ እየታየ መሆኑንም የሚመሰክሩ ጭምር እንጂ፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy