Artcles

አቅጣጫው ፍጥነትን ይሻል

By Admin

January 25, 2018

አቅጣጫው ፍጥነትን ይሻል

                                                       ደስታ ኃይሉ

የአገራችን ወጣቶች ሲያነሱዋቸው የነበሩ ኢኮኖሚያዊና ዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ የመሪው ድርጅቶች ከፍተኛ አመራሮች አቅጣጫዎች አስቀምጠዋል። አቅጣጫዎቹ ለአገራችን ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው ናቸው። በተለይም ከወጣቶች ተጠቃሚነት ጋር ተያይዞ የወጣቶችን ሁለንተናዊ ችግሮች በመፍታት ስለሚወሰደው እርምጃ የተቀመጠው አቅጣጫ ተገቢ ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ወጣት ቁጥር ከፍተኛ ነው። ይህ ወጣት አገርን ለመገንባትና እድገትን ለማሳለጥ ጉልህ ሚና ያለው በመሆኑ ገዥው ፓርቲም ይሁን መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥተው አቅም በፈቀደ መጠን በፍጥነት ችግሮቹን መቅረፍ ይኖርቸዋል። የወጣቶችን ጥያቄዎች መመለስ የአገርን ችግሮች የመመለስ አስኳል ጉዳይ በመሆኑ የመሪው ድርጅት ከፍተኛ አመራሮች ያስቀመጡት አቅጣጫ በፍጥነት ሊተገበር የሚገባ ይመስለኛል።

መንግስት ወጣቱ ኃይል አፍላ ጉልበት ያለው በመሆኑ፤ ሀገራችን ይህን ለስራ ዝግጁ የሆነ ጉልበት በሚገባ መንገድ መጠቀም ይኖርባታል። ይህን ጉልበት አጣጥሞ በተገቢው መንገድ መጠቀምም ለአገራዊ ዕድገት ያለው ፋይዳ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው። ወጣቶች በተፈጥሯቸው ሁሉንም ነገር የመስራት ስሜት የታደሉ ናቸው። እነርሱን በማናቸውም ሀገራዊ የልማት ትልሞች ውስጥ በማስገባት ማሳተፍ ስራዎችን በአፍላ ጉልበት እንዲሁም በፈቃደኝነትና በፍላጎት ስሜት ሊተገብሩት ይችላሉ።

ይህ ደግሞ የተያዙ ዕቅዶችን ለመፈፀምና የሚፈለገውን ሀገራዊ ዕድገት ለማምጣት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል። ስለሆነም በወጣቶች ላይ መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስ ውጤቱ መልሶ የሚከፍለው አገርን መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።

ወጣቶች አገራችንን ከድህነት ለማውጣት በሚደረገው ትግል ፋና ወጊዎች ሆነው መንቀሳቀስ ይገባቸዋል። በወጣቶች ላይ ኢንቨስት ማድረግ ሀገርን ማበልፀግ መሆኑን ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል። በእኔ እምነት እንደ ኢትዮጵያ ያለ በርካታ ቁጥር ወጣት ያለው ሀገር በወጣቱ ላይ ኢንቨስት አድርጎ ከወጣቱ አፍላ ጉልበት የሚያገኘውን ልማታዊ ፋይዳ ማረጋገጥ ካልቻለ ሁለት ችግሮች ሊያጋጥሙት ይችላሉ።

አንደኛው በርካታ ቁጥር ያለው ስራ አጥ ወጣት ይፈጠርና ይህ ስራ አጥ ኃይልም የራሳቸው አጀንዳ ያላቸው የውስጥና የውጭ ሃይሎች መጠቀሚያ ሆኖ ለሁከትና ብጥብጥ በር የሚከፍት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ሀገራት ከወጣቱ ማግኘት የሚገባቸውን የልማት ተጠቃሚነት ዕውን ማድረግ አይችሉም።

እርግጥ ስራ የሌለው ወጣት ማናቸውንም ጉዳዮች እንደ ስራ ሊመለከት ይችላል—የሁከት ተግባርንም ቢሆን። ይህ ደግሞ የተረጋጋ ሰላምና የልማት ስራ የሚከናወንበትን ሀገር ሊረብሽና ወደአልተፈለገ አቅጣጫ ሊወስድ ይችላል።

ለዚህም በቅርቡ በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው የሁከት ተግባር ሁነኛ አስረጅ ይመስለኛል። ወጣቶች በየአካባቢያቸው ካለው የመልካም አስተዳደር ችግር በተጨማሪ በሚፈለገው መጠን ስራ ሳይፈጠርላቸው በመቆየቱ፤ ለሀገራችን የውጭ ጠላቶች ለሚላላኩ የጥፋት ሃይሎች ፀረ-ኢትዮጵያ አጀንዳ ሰለባ ሆነው ነበር።

ይህ ሁኔታም በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማስከተሉ የሚዘነጋ አይደለም። እናም አስቀድሞ ወጣቱን በሚፈለገው መጠን በስራ እንዲታቀፍ ማድረግ ቢቻል ኖሮ፤ የተከሰተው ጥፋት ዕውን አይሆንም ነበር። ከአገራዊ ልማት ተጠቃሚ የሆነ ወጣት በምንም መልኩ የሀገሩን ጥቅም በመፃረር የሌሎች ባዕዳን ሃይሎች መጠቀሚያ ሊሆን ስለማይችል ነው።

እናም የኢፌዴሪ መንግስት ወጣቱን አቅም በፈቀደ መልኩ አደራጅቶ ከልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ፕሮግራም ቀርፆ ወደ ስራ መግባቱ ይበል የሚያሰኝ ተግባር ይመስለኛል። አሁንም የኢህአዴግ አመራሮች ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት ለወጣቶች የተገባው ቃል በሚፈለገው ፍጥነት መተግበር የሚገባው ነው።

አመራረሮቹ ድርጅታቸው ኢህአዴግ ለ17 ቀናት ባደረገው ግምገማ ማጠቃለያ ላይ “…በአገራችን የተመዘገቡት ስኬቶች ዋነኛ ምስጢር የሕዝብን ተሣትፎ ማረጋገጥ መቻሉ ነው፡፡ በዚህም መሰረት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የህዝብን አመኔታ መልሶ ለማግኘትና ለህዝብ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ተከታታይ ርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባ ወስኗል፡፡ ሕዝብ የሚደመጥበትና ወሳኝነቱ በሚገባ የሚረጋገጥበት እድል እንዲሰፋ አፅንኦት ሰጥቶታል፡፡ በተለይ ደግሞ ወጣቶቻችን የሚያነሱዋቸውን ጥያቄዎች በሚገባ ለመመለስና በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና በልማት ሊኖራቸው የሚገባውን ተሣትፎ በተሟላ መልኩ ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተከታታይ ሥራዎች እንዲሰሩ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል” በማለት የተገለፀው አቅጣጫ ፍጥነትን የሚሻ ይመስለኛል።

አቅጣጫው በፍጥነት ከተተገበረ የወጣቶችን አፍላ አቅም በሚገባ ለአገራዊ እድገት ይበልጥ ማዋል ይቻላል። ወጣቶች በተፈጥሯቸው ሁሉንም ነገር የመስራት ስሜት የታደሉ ናቸው። እነርሱን በማናቸውም ሀገራዊ የልማት ትልሞች ውስጥ በማስገባት ማሳተፍ ስራዎችን በአፍላ ጉልበት እንዲሁም በፈቃደኝነትና በፍላጎት ስሜት ሊተገብሩት ይችላሉ። ይህም የተያዙ ዕቅዶችን ለመፈፀምና የሚፈለገውን ሀገራዊ ዕድገት ለማምጣት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል።

ይህ ማለት ግን ሁሉም ነገር ለመንግስት ይተዋል ማለት አለመሆኑን ወጣቶቻችን የሚገነዘቡት ይመስለኛል። እርግጥ ለልማት ዝግጁ የሆነውን ወጣት በአግባቡ ይዞ መጠቀሙ ከመንግስት የሚጠበቅ ነው። ሆኖም ወጣቱም የራሱን ስራ መስራት አለበት። መንግስት ለወጣቱ ቢሊዩኖችን መድቦ ጣቶችም ተጠቃሚ የሆኑ ነው። ለነገሩ ገንዘቡን በተገቢው ቦታ ማዋልና ስራን ሳይንቁ በማናቸውም ስራዎች ውስጥ ሊያንቀሳቅሱት ይገባል። አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር በአንድ እርምጃ ይጀመራል እንደሚባለው፤ ወጣቶች ማንኛውንም ስራ ከታች መጀመር ይኖርባቸዋል። የስራ ክቡርነት መታወቅ አለበት። በማንኛውም ስራ ላይ እጃቸውን ማስገባት አለባቸው።

ወጣቱ የመንግስትን ትኩረትና የተመደበለትን ተንቀሳቃሽ ፈንድ በአግባቡ ሲጠቀም ራሱን ለስራ ዝግጁ ማድረግ ይኖርበታል። ራስን ለስራ ማዘጋጀት አንድን ችግር ለመፍታት ግማሽ መንገድ እንደመሄድ ያህል የሚቆጠር ነው። እናም ወጣቱ አስቀድሞ ራሱን ለማንኛውም ስራ ማዘጋጀት አለበት። ማንኛውም ስራ ከችግር መውጫ ቀዳዳ መሆኑን ማመን ይኖርበታል።

ይህ ሃይል ስራን ሳይንቅና ምናልባትም በስደት ቢሄድ ለባዕድ ሀገራት ሊያበረክተው የሚችለውን የጉልበት ስራ ዓይነት ጭምር ስራዎችን አክብሮ በመስራት የመንግስትን ትኩረት አሟጦ ሊጠቀምበት ይገባል። “ስራ ክቡር ነው” የሚለውን አርማ ከፍ አድርጎ ማውለብለብ ይጠበቅበታል። ያኔ ራሱን፣ ቤተሰቡንና ከምንም በላይ እያሰበችለት ያለችውን ሀገሩን መጥቀሙ አጠያያቂ አይሆንም።

እንዲሁም ወጣቱ የስራ ፈጣራ ባለቤት መሆን አለበት። የፌዴራል መንግስትና ክልሎች ወጣቱ በስራ ውስጥ እንዲያልፍ ተንቀሳቃሽ ፈንድ አዘጋጅተው እያከፋፈሉ ነው። ወጣቱ በዚህ ፈንድ እንደምን ራሱን ለስራ ዝግጁ ማድረግ እንደሚችል ማሰብ ይኖርበታል። በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ውስጥ የተመቻቸ የስራ ምህዳር አለ።

ለወጣቶቹ ዋናው ነገር ይህን ምቹ የስራ ድባብ በፈጠራ ክህሎት አጅቦ እንዴት ውጤታማ ማድረግ እንደሚቻል ማወቁ ላይ ነው። ወጣቱ የራሱን ተግባሮች እየተወጣ ባለበት ሰዓት የኢህአዴግ አመራሮች ያስቀመጡት ተደማሪ አቅጣጫም በፍጥነት መተግበርን የሚሻ መሆኑ መዘንጋት የለበትም።