Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አገራዊ ተጠቃሚነትን ይመርኮዝ

0 296

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አገራዊ ተጠቃሚነትን ይመርኮዝ

                                                     ደስታ ኃይሉ

በኢትዮጵያ ውስጥ በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፖርቲዎች የድርድር ሂደትን “የሚያጠግብ እንጀራ…” እንዲሉት ዓይነት እየሆነ ነው። የድርድሩ ሂደት ያኮራል። ከመጀመሪያው የድርድር ወቅት ጀምሮ ፓርቲዎች በአስተሳሰብ ደረጃ እየተቀራረቡ መጥተዋል።

ፓርቲዎቹ በየጊዜው በሚያካሂዷቸው ድርድሮች የሚያቀርቧቸው ሃሳቦች ሁሉንም ወገኖች እየወከሉ መምጣታቸውንና ይህም በሰጥቶ መቀበል መርህ አገራዊ  ተጠቃሚነትን ተመርኩዘው እንዲካሄዱ ያደረገ ነው። አሁንም ግን ድርድሩ ይበልጥ አገራዊ ተጠቃሚነትን መመርኮዝ ያለበት ይመስለኛል።

እርግጥ ዴሞክራሲ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ የሚመጣ የሂደት ውጤት መሆኑን አልዘነጋም። የመራጩ ህዝብ አስተሳሰብ፣ በጊዜ ሂደት ለምርጫ የሚሰጠው ትርጉም የሚያድግና የሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር እንዲሁም እየሰፋ የሚመጣ ብሎም ተወዳዳሪ ፓርቲዎች በምርጫ የሚኖራቸው ተሳትፎ እየጎለበተ የሚሄድበት አውድ ነው።

ይህ ተጨባጭ ሁኔታም በጅምር ላይ ያለ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እና ረዥም ዕድሜን ያስቆጠረ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በምንም መልኩ አንድ ሊሆን እንደማይችሉ የሚያመላክት ነው። ዴሞክራሲ በአንዴ የሚገነባ ሳይሆን በጊዜ ዑደት ውስጥ ከህዝቡ አስተሳሰብ ደረጃ ጋር እያደር አብሮ የሚራመድ ሂደት ነው የሚባለው ለዚሁ ይመስለኛል።

ከዚህ አኳያ የአገራችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ስንመለከተው ሂደቱ 26 ዓመታትን የተሻገረ ነው። በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ የተሟላ ነው ለባል አይችልም። በመሆኑም ምንም ዓይነት ተግዳሮቶች የሉበትም ለማለት አይቻልም። አሁን በምንገኝበት ደረጃ የህዝብ አስተሳሰብ አድጓል፣ የአገሪቱ የፖለቲካ ምህዳርም በሚፈለገው መጠን ሰፍቷል ለማለት አይቻልም። ይሁን እንጂ ረጅም ርቀት መጓዛችን ከማንም የሚሰወር አይደለም።

በገዥው ፓርቲ ኢህአዴግና በሀገር ውስጥ በሰላማዊ መንገድ በሚንቀሳቀሱ 15 ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ክርክርና ድርድር አካሂደው በበርካታ ጉዳዩች ላይ እየተስማሙና ሰጥቶ በመቀበል መርህ ድርድራቸውን እያካሄዱ መሆኑ ተዘግቧል። ዴሞክራሲን ከማስፋትና ጥልቀት እንዲኖረው ከማድረግ አኳያ ይህ በገዥው ፓርቲ አማካኝነት ተጠርቶ እየተደረገ ያለው የድርድር መድረክ ሊመሰገን የሚገባው ተግባር ነው።

እንዲህ ዓይነት መድረኮች በበዙና በተበራከቱ ቁጥር የአገራችን ዴሞክራሲ ይበልጥ አሳታፊ፣ ግልፅነት የተሞላበትና ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች በበቂ ሁኔታ ሊያሳትፍ የሚችል ይሆናል። ታዲያ በገዥው ፓርቲና በተቃዋሚዎች መካከል የሚካሄደው ክርክርና ድርድር የሥርዓቱ ውጤት መሆኑን መዘንጋት አይገባም።

እርግጥ የሀገራችን የህዳሴ ጉዞ ሊረጋገጥ የሚችለው በመጎልበት ላይ የሚገኘው የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታችን ያለ አንዳች እንቅፋት ሳይሸራረፍ ሲቀጥል ነው፡፡ እናም ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታችን መጠናከርና ማበብ ጤናማ እና ገንቢ ሚና የሚጫወቱ የፖለቲካ ፖርቲዎች መኖር አለባቸው፡፡

መንግስት በአገሪቱ ዴሞክራሲን የሚያጠናክሩ ፖርቲዎች መኖር እንዳለባቸው ያምናል፡፡ ተደጋግሞ እንደሚነገረውም የመንግስት ፍላጐት የሀገራችን የመድብለ ፖርቲ ስርዓት ዳብሮ እና ጐልብቶ ማየት የዘወትር ፍላጐቱ መሆኑ ነው፡፡ ሁሉንም የሀገራችንን ህዝቦች የሚወክሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምፃቸው እንዲሰማ ጥረት እያደረገ ነው፡፡

የኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታ ጤናማነቱ ተጠብቆ ሊጓዝ የሚችለው ጤናማ እና ገንቢ ሚና የሚጫወቱ የፖለቲካ ፖርቲዎች ተሳትፎ እየጐለበተ ሲመጣ ነው፡፡ በመሆኑም በተለይም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ራሳቸውን በማብቃትና ከጅምላዊ አካሄድ በመታቀብ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ማበብ ሀገራዊ ግዴታ ያለባቸው ይመስለኛል፡፡

እንደሚታወቀው ሁሉ በየትኛውም ዴሞክራሲያዊ ሀገር ውስጥ አንድ በህዝብ የተመረጠ ፓርቲ የሚያከናውናቸው ማናቸውም ተግባር የህዝብን ውክልና መሰረት ባደረገ መልኩ ነው። ህዝቡ የሚፈልገውን ለማስፈፀም እንጂ እርሱ የሚፈልገውን ነገር በህዝቡ ላይ ለመጫን አይደለም። እናም የድርድሩ ሂደት አኩሪ ቢሆንም፤ አሁንም በተጠናከረ መልኩ አገራዊ ተጠቃሚነት ማመዘን ይኖርበታል።

የአገራችንን ዴሞክራሲ ለማጎልበትና ለማጠለቅ ገዥው ፓርቲ፣ ህጋዊና ሰላማዊ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ ውጤት ሊያሙ አይችሉም። የሀገራችንን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ለፓርቲዎች ተሳትፎ የሚሰጠውን ትኩረት ባልተናነሰ ሁኔታ፤ በከፍተኛ ትምህርትና በልዩ ልዩ የስራ ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ምሁራን፣ የተለያዩ የሲቪክ ማህበረሰብ አደረጃጀቶችና በእነርሱ ውስጥ የታቀፉ ዜጎችን በቀጥታ በማሳተፍ ጠቃሚ ሃሳቦቻቸውንም ማካተት ይገባል።

በመሆኑም በክርክሩና በድርድሩ ወቅት እነዚህ ጉዳዩችም ታሳቢ መሆን ይኖርባቸዋል። ክርክርና ድርድር ሲባል በውጤቱ የሚገኘውን ግብዓት ለሀገር ግንባታና ዕድገት ለማዋል እንጂ፣ የሀገራችን ውድቀት ለሚመኙ ኃይሎች ፍላጎት ማሳኪያ አለመሆኑን ተደራዳሪዎቹ አጥብቀው ሊያስቡበት ይገባል። አገራዊ ጠቀሜታ ሁሌም ቀዳሚውን ቦታ መያዝ ይኖርበታል።

እርግጥ ያለፉት ስርዓቶች በሀገራችን ህዝቦች መካከል ፈጥረውት ያለፉት ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰቦች በቀላሉ የሚሽሩ አይደሉም። ፀረ-ዴሞክራሲያዊ እሳቤዎችን በዴሞክራሲያዊነት ለመቀየርም አስተሳሰብንና ስለ ዴሞክራሲ ያለንን አመለካከት መለወጥ ይገባል። በህዝቦች ውስጥ ለዘመናት ሲፈጠሩ የነበሩትን የተዛቡ ግንኙነቶች በጥቂት ዓመታት ውስጥ መቀየርም ባይቻልም ሩቅ መንገድ ሄደናል።

ይህ ሁኔታም ምናምባትም ችግሮችን በዴሞክራሲያዊ ማዕቀፍ ውስጥ ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶችን ሊያሰናክል ይችላል። እናም ዴሞክራሲው እንዲሰፋ እነዚህን ሁለት ተግዳሮቶች መፍታት ይገባል። ይህን ዕውን ለማድረግም የህዝቡ ወኪሎች የሆኑት ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ ይገባል።

ስለሆነም ፓርቲዎቹ በክርክሩና በድርድሩ ሂደት ውስጥ ‘እነዚህን የዴሞክራሲ ተግዳሮቶች ለመፍታት ከእኔ ምን ይጠበቃል?’ ብለው ራሳቸውን በመጠየቅ አገራዊ ተጠቃሚነትን ማደርጀት ይኖርባቸዋል።

ተደራዳሪ ፓርቲዎች ድርድሩ ሰላምን ከማረጋገጥ አኳያ ሊኖረው የሚገባውን ፋይዳንም  መመልከት አለባቸው። እንደሚታወቀው የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች ሁከት ተፈጥሮ ነበር። የሁከቱ አነሳሽ ምክንያት ምንም ይሁን ምን፤ ፓርቲዎች እንዲያ ያለው ሁከት ዳግም እንዳይፈጠር መስራት ይጠበቅባቸዋል። ይህም ድርድሩ አገራዊ ተጠቃሚነትን እንዲመረኮዝ ያስችለዋል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy