Artcles

ኢህአዴግ ሆይ ቃል ገባህ፤ ቀጥሎስ??

By Admin

January 05, 2018

ኢህአዴግ ሆይ ቃል ገባህ፤ ቀጥሎስ??

                                                              ይልቃል ፍርዱ

ኢሕአዴግ በተለያዩ አመታትና ወቅቶች ከባድና ውስብስብ ችግሮች ገጥመውት ፈተናውን በብቃት ማለፍ የቻለ ድርጅት ነው፡፡ ችግሮችን ለመፍታት፣ ወቅቱንና ሁኔታዎችን፣ አካባቢውን፣ በመሬት ላይ ያለውን ሀገራዊ እውነታ፣ የኃይል አሰላለፉን በአግባቡ ለማንበብም ሆነ ለመተንትን፤ ከዚህም በመነሳትም ሀገራዊ መፍትሔዎች ማስገኘትን በበርካታ አመታት ተሞክሮው ያዳበረ ልምድ ነው፡፡

የአሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባለፉት 18 ቀናት ሲያደርግ የነበረውን ሰብሰባ አጠናቆ መግለጫ አውጥቶአል፡፡ መግለጫው ሀገራዊ ጉዳዮችን በስፋት ያካተተና ለተፈጠሩት ሰፊና ወቅታዊ ሀገራዊ ትርምሶችና ቀውሶች በዋነኛነት የከፍተኛው አመራር ድክመት መሆኑን አስምሮበታል፡፡ ይህንኑ መሰረት በማድረግ ችግሮቹን ፈጥኖ ለማረም እንደሚንቀሳቀስ ቃል ገብቶአል፡፡

ይህ የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ አጣዳፊና አንገብጋቢ ከሆኑት ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች አንጻር የሚያስተላልፈው ውሳኔ በሕዝቡ ዘንድ በስፋት ሲጠበቅ የነበረ ነው፡፡ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በዚህ ስብሳባ ቀደም ሲል የተጀመረው የመታደስ ሂደትና የደረሰበትን ደረጃ በአገራችን የሚታዩ ወቅታዊና የቆዩ ችግሮችን ከነዝርዝር መገለጫቸው በመለየት በመንስኤና መፍትሄዎቻቸው ላይ መክሮ የሀሳብ አንድነትና መተማመን ፈጥሮአል፡፡ ችግሮቹን በመቅረፍ በእስከአሁኑ ትግል የተመዘገቡ መልካም ውጤቶችን አስጠብቆ ለማስቀጠል የሚያስችል ቁርጠኝነትና መግባባት አረጋግጦ መውጣቱን በአጽንኦት ገልጾአል፡፡

ኢሕአዴግ አገራችንን በለውጥ ጎዳና መምራት ከጀመረበት ከ1983 አ/ም ጀምሮ በሁሉም የሕይወት መስኮች መሰረታዊና ተስፋ ሰጪ ለውጥ ሲመዘገብ የቆየ ቢሆንም ከቅርብ አመታት ወዲህ ለውጡን በተጀመረው ስፋትና ግለት ለማስቀጠል የሚደረገውን ጥረት የሚፈታተኑ ችግሮች እየታዩ መምጣታቸውን ይገነዘባል፡፡ አገራችን በአንድ በኩል በተከተልነው መሰረታዊና ትክክለኛ አቅጣጫ በተገኙ ውጤቶች እጅግ የሚያስጎመዥ ሁኔታ ላይ ትገኛለች ያለው መግለጫው በሌላ በኩል ደግሞ በፈጸምናቸው ስሕተቶችና ከእድገታችን ጋር ተያይዘው በተከሰቱ አዳዲስ ለውጦችና ፍላጎቶች ምክንያት ለግዜውም ቢሆን በአሳሳቢ ወቅታዊ ችግሮች ሀገራችን ተወጥራ የቆየችበት ሁኔታ መፈጠሩን የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው መገምገሙን ገልጾአል፡፡

ለሁሉም የሀገራችን ሕዝቦች ግልጽ እንደሚሆነው ለበርካታ ዘመናት በማሽቆልቆል ሂደት ውስጥ ለማለፍ የተገደደችው አገራችን ለ25 አመታት ቀና ብላ ስትጓዝ ቆይታለች፡፡ ይህም በሁሉም ሀገር ወዳድ ዜጎች የሚታመንበትና አለምም የመሰከረለት ጉዳይ ነው፡፡ የኢኮኖሚ ማሽቆልቆል ተገትቶ ለሩብ ምእተ አመት የዘለቀው አገራዊ እድገት ኢትዮጵያችን በትንሳኤ ጎዳና መገኘቷን አብስሮአል፤ እኩልነትን አረጋግጧል፡፡ የግልና የቡድን መብቶችን አስከብሮአል፡፡ የሰላምና የእድገት መሰረት እንደሆኑ በእነዚሁ አመታት ተረጋግጦአል፡፡ ብዝሀነት የኢትዮጵያችን መሰረትና መገለጫ እንደሆነ በመቀበል ይህንኑ በአግባቡ ለማስተዳደር ያደረግነው ጥረት የአገራችን ዜጎች ለረጅም አመታት በፍቅርና በሰላም የሚኖሩባት የሰላም ሀገር እንደሆነች አስመስክሮአል ሲል ኢሕአዴግ ገልጾአል፡፡

ይሁንና ይህ የሚያስጎመዥ እውነታ ከቅርብ አመታት ወዲህ በመታየት ላይ ባሉ ግዜያዊ ችግሮች የተነሳ ለአደጋ እየተጋለጠና ለሁሉም ማሕበረሰቦቻችን የስጋት ምንጭ መሆን በጀመረ አዲስ ክስተት መልክ የሚገለጽበት አዝማሚያ ሰፋ ብሎ ታይቶአል፡፡ ከዚህ የተነሳም መላ የሀገራችን ሕዝቦች ኢትዮጵያችንን ከገጠሟት ግዜያዊ ችግሮች በማውጣት በትግላችን የተመዘገቡ ስኬቶችን ለመጠበቅና ለማስፋት ድክመቶችንና አደጋዎችን ደግሞ በቁርጠኝት ለማስተካከል የሚሹበት ሁኔታ መፈጠሩን  ድርጅቱ አስምሮበታል፡፡

መንግስት የለውጡን ሂደት የሚመራው ድርጅታችንም ለዚህ የሕዝብ ጥያቄ አስተማማኝ ምላሽ የሚሰጡበት ሁኔታ እንዲፈጠር አጥብቀው ሲጠይቁ ቆይተዋል፡፡ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከሁለት ሳምንት ግዜ በላይ ያካሄደው ግምገማ በዚህ የሕዝባችን ልባዊ ፍላጎትና ቅን ሀገራዊ አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተና ለዚሁም መላውን ድርጅታዊ አቅሙን ተገዥ ለማድረግ በሚያስችል ቁርጠኝነት የተካሄደ መሆኑን አመልክቶአል፡፡

በመሆኑም ስብሰባው ከምንም ነገር በላይ በአመራር ድክመት የተፈጠሩትን አደጋዎችና ስጋቶች ለመቅረፍ በሚያስችል ስምምነትና መግባባት ተጠናቆአል፡፡ በግምገማው በየደረጃው ባሉ የአመራር እርከኖች በተለይ ደግሞ በከፍተኛው አመራር ደረጃ የውስጠ ድርጅት ዲሞክራሲ እጦት ስር እየሰደደ መምጣቱን አረጋግጦአል፡፡ ይህም ሀሳብ በነጻነት የሚንሸራሸርባቸውን የመታገያ መድረኮች የሚገድብና የሚያጠብ ስለዚህም ደግሞ በአመራሩ ውስጥ የአመለካከትና የተግባር  አንድነትና ጥራት እንዳይፈጠር መሰናክል ሆኖ እንደቆየ መመልከቱን ገልጾአል፡፡

ይህ ችግር በዋነኛነት በድርጅታችን ከፍተኛ አመራር ደረጃ ከታየው የተዛባ የስልጣን አተያይና አጠቃቀም ጋር ተያይዞ የተከሰተ ሲሆን ችግሩ የድርጅታችን አይነተኛ መለያ የሆነውን ዲሞክራሲያዊነትን በማዳከም ሳይወሰን ስልጣን የሕዝብ መገልገያ እንዲሆን የጀመርነውን መልካም ጉዞ ለአደጋ ያጋለጠ ሆኖ ቆይቶአል ብሎአል በመግለጫው፡፡

ኢሕአዴግ ዲሞክራሲ እየጠበበ አድርባይነት በመስፋፋቱ ምክንያት በግልጽነትና በመርሕ ላይ ተመስርቶ ከመተጋገል ይልቅ መርህ አልባ ግንኙነት ማስፈን የተለመደ ስልት ወደ መሆን ተሸጋግሮአል ሲል ገልጾአል፡፡ ይህን የመሰለው ጠባብ ቡድናዊ ጥቅሞች ላይ የተመሰረተ መርሕ አልባ ግንኙነት ኢሕአዴግና አባል ድርጅቶቹን የማዳከም ውጤት አስከትሎአል ብሎአል የድርጅቱ መግለጫ፡፡

የስራ አስፈጻሚው መግለጫ ከውስጠ ድርጅት ዲሞክራሲ መጥበብ እስከ ተፈጠሩት ሁከቶችና ግጭቶች በነዚህም ምክንያቶች ሰላም መደፍረሱ የንጹሀን ዜጎች ሕይወት  መጥፋት ንብረት መውደም የሀገር ሰላም መደፍረስ ዜጎች ከቤትና ንብረታቸው የመፈናቀል ከባድ ችግርና አደጋ ውስጥ መውደቃቸውን የኢኮኖሚው እንቅስቃሴ መጎዳቱን ገልጾ የሀገሪቱን ሰላምና መረጋጋት ወደነበረበት ሁኔታ ለመመለስ እንደሚሰራ በአጽንኦት ገልጾአል፡፡

ሚዲያና ፕሬሱ በሚገባው ደረጃ ነጻነታቸው ተጠብቆ የሕዝብ አይንና ጆሮ ሁነው ያገለግሉ ዘንድ የተደረገው እንቅስቃሴ የሚፈለገውን ውጤት እንዳላመጣ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በግምገማው ተመልክቶአል፡፡ በዚህ ረገድ የታየው ዘገምተኛ እድገት እንደተጠበቀ ሁኖ ከቅርብ ግዜያት ወዲህ በክልልም ሆነ በፌደራል ያሉ የሕዝብ የሚዲያ አውታሮች ሕግና ስርአትን ጠብቀው የማይሰሩበት ሁኔታ እያመዘነ የሕዝቡን ሰላምና አብሮ የመኖር ገንቢ ባሕል የሚሸረሽሩ ሰበካዎች የሚሰጥባቸው ብሎም ሕዝብ ከሕዝብ ጋር የሚያጋጩ አጥፊ ቅስቀሳዎች የሚካሄዱባቸው እየሆኑ ለመምጣታቸው የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚም ሆነ የሚመራው መነግስት አስተዋጽኦ እንዳደረገ ይቀበላል ብሎአል፡፡

ስራ አስፈጻሚው የሲቪል ማሕበረሰቡ ተሳትፎ መሆን በሚገባው ደረጃ ከፍ ለማድረግ ያስቻለ እንዳልሆነ ተመልክቶአል፡፡ መልካም አስተዳደር የማስፈን እንቅስቃሴያችን በአመራር ድክመት ምክንያት ለበርካታ ችግሮች እንደተጋለጠ አረጋግጦአል፡፡ በሙስናም ሆነ በሌሎች ጥፋቶች ውስጥ የተዘፈቁ ግለሰቦችን በወቅቱ ሕጋዊና አስተማሪ በሆነ መንገድ መጠየቅ ሳይቻል መቅረቱንም አምኖአል፡፡

ዜጎች በሕገመንግስቱ ዋስትና ያገኙ መብቶቻቸውን የሚጥሱ ሰዎችን በሕግ ተጠያቂ ማድረግ መሆን በሚገባው ደረጃ ሳይፈጸም ቆይቶአል፡፡ መንግስት የሕዝብና የሀገር ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በነደፋቸው ፕሮጀክቶች ዙሪያ የሚታዩ የአፈጻጸምና የስነምግባር ችግሮችን አስተማማኝና ውጤታማ በሆነ መንገድ የማረምና የማስተካከል ጉድለት መታየቱን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው  ይፋ አድርጎአል፡፡

ስራ አስፈጻሚው እነዚህ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ሕዝብና ሀገርን ያልተገባ ዋጋ የሚያስከፍሉ እንደሆኑ በመገንዘብ በአፋጣኝ እንዲስተካከሉ ማድረግ እንደሚገባ አምኖበታል፡፡ በዚህ ረገድ ይህንን የመልካም አስተዳደር ችግር በተግባር ማቃለል ሲገባ በአጉል ተስፋና በባዶ ቃልኪዳን የመሸንገል ሕዝበኛ አዝማሚያዎች በጥብቅ መመከት እንዳለባቸው ወስኖአል፡፡

በአጭሩ በሕብረተሰባችን ዘንድ ሕገመንግስታዊ ስርአቱን ልማታዊ አስተሳሰብና በብዝሀነት ላይ የተመሰረተ ኢትዮጵያዊ አንድነትን በማጠናከር ረገድ የተሰራው ስራ መሆን የሚችለውን ያህል ውጤት ሳያመጣ እንደቀረ ስራ አስፈጻሚው ባደረገው ግምገማ ማረጋገጥ ችሎአል፡፡ በዚህ የተነሳ ብሔረሰባዊና ሀገራዊ ማንነትን አስተሳስሮ በመገንባት በኩል የታየውን ጉድለት በአፋጣኝና በአስተማማኝ መንገድ መፍታት እንደሚኖርብን ታምኖበታል ብሎአል ኢህአዴግ በመግለጫው፡፡

ከላይ የተገለጹት ችግሮች በተራዘመ ትግል የተገነባችውን ሀገር ለአደጋ ማጋለጥ የጀመሩት ጉድለቶች በዋነኛነት የኢሕአዴግ ከፍተኛ አመራር በተለይም የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ድክመቶች ናቸው፡፡ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አባላቱ የድርጅትና የመንግስት ከፍተኛ ኃላፊዎች በተናጠልና በጋራ ስትራቴጂያዊና ታክቲካዊ አመራር የመስጠት ኃላፊነታቸውን ባለመወጣታቸው የተፈጠረ ችግር መሆኑን አስምሮበታል፡፡

በዚህ ግምገማ የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴና የመንግስት የበላይ አመራሮች ወቅቱ የሚጠይቀውን ስትራቴጂያዊ አመራር የመስጠት ጉድለታቸው ሰፊ እንደሆነ ታይቶአል፡፡ ከፍተኛ አመራሩ ችግር አስቀድሞ የመለየት፤ ተንትኖ የማወቅ፤ የመፍቻ መንገዶች የመተለምና በዚሁ መሰረት የመፍታት ብቃቱ ወቅቱና መድረኩ ከሚጠይቀው ደረጃ ጋር አብሮ ባለማደጉ የተወሳሰበውን ሀገራዊ መድረክ በብቃት የመምራት ጉድለት እንደነበረበት የጋራ አቋም ተይዞአል በሚል ዝርዝር መግለጫ የሰጠ ሲሆን ለአደጋ የሚያጋልጥ ሁኔታ እንዲፈጠር በማድረጉም የተሰማውን ከልብ የመነጨ ጸጸት ገልጾአል፡፡ ይህ ሁኔታ እንዳይደገም እንዳለፉት አመታት ሁሉ በቁርጠኝነትና በጽናት እንደሚንቀሳቀስ ቃልኪዳኑን ያድሳል ካለ በኃላ መሰረታዊ የሆኑ ስምንት ነጥቦችን የያዘ የአቋም መግለጫዎችን አውጥቶአል፡፡ በተግባርም ወደ ፈጣን የማስተካከያ እርምጃዎች እንሚገባ አስታውቋል፡፡ እኛም “ኢህአዴግ ሆይ ይህን በማለትህ እሰየው፤ ተግባራዊነቱስ?” ብለን መጠየቃችን የግድ ነውና ከወዲሁ አስብበት እንላለን።