Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኢትዮጵያ በስራ ላይ

0 279

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ኢትዮጵያ በስራ ላይ

                                                              ዋኘው መዝገቡ

ሀገራችን ለኢንቨስትመንት ካላት አመቺ ሁኔታ አንጻር ዛሬም ለውጭ ኢንቨስተሮች  ተመራጭ ሀገር ሆናለች፡፡ ሀገር ውስጥ ገብተው ኢንቨስት ካደረጉት ባለሀብቶች ሌላ በርካቶች በመግባት ላይ ይገኛሉ፡፡ አገራችን ከውጪው አለም፤ በተለይም ከበለጸጉ ሀገራትና አለም አቀፍ ተቋማት ጋር በፈጠረችው ግንኙነትና ትስስር አሁንም ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ ማግኘቷን ቀጥላለች፡፡ የተጀመረውን የኢኮኖሚ አብዮት በማስፋት ረገድም ረዥም ርቀት ተጉዛለች፡፡

በአሁኑ ሰአት ያለው ሁለንተናዊ እድገት ታላቅ ተስፋ ሰጪ የልማትና የኢኮኖሚ  ጉዞን አመላካች ነው፡፡ በሁሉም መስክ ከድሕነት ጋር በሚደረገው ወሳኝ ትግል ኢትዮጵያና ዜጎችዋ ወሳኝ በሆነ ሀገር የማልማትና የማሳደግ ስራ ላይ ይገኛሉ፡፡ ለሁከት፣ ለብጥብጥም ሆነ ለረብሻ የሚውል ምንም አይነት ግዜ የላቸውም፡፡ የሀገሪቱን ልማትና እድገት ለመግታት በውጭ ኃይሎችና በሀገር ውስጥ አጋፋሪዎቻቸው የተቀናበረው ሀገር የማመስና የእድገት ጉዞውን የማሰናከል ሙከራ ብዙም የሚራመድ  አይሆንም፡፡

ከአለም አቀፍ ተቋማት እያገኘች ያለችውን እርዳታና ብድር ሀገራችንን በማልማትና በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል፤ የራሳችንን አቅም በማሳደግ ረገድ የበኩላቸውን አስተዋጽአ ያበረክታሉ፡፡ ከትላልቅ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ከበለፀገው አለም እርዳታና ብድር ማግኘቷ አሁንም ተጠናክሮ እየቀጠለ ነው፡፡ ሀገራችን ተጨባጭ የልማትና የእድገት ውጤት ለማስመዝገብ በመብቃቷ፤ ይህም በእነሱ መመዘኛ በተግባር ላይ የዋለ መሆኑን ደግመው ደጋግመው አረጋግጠዋል፡፡

ለሀገር ልማት የሚገኘውን ብድር በአግባቡ በስራ ላይ ማዋል ከሙስና መከላከል ሰርቶና ውጤትም አስመዝግቦ መመለስ የሚጠበቀው ከእኛ ነው፡፡ ለዚህም መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራበት ይታመናል፡፡ ብድርን በአግባቡ ለመመለስ ገንዘቡ በዋለበት የልማት ዘርፍ ላይ ተግቶ መስራት ውጤታማና ትርፋማ እንዲሆን ማድረግ ተገቢ አመራርና ቁጥጥርን ይጠይቃል፡፡ በብዙ ታላላቅ መስኮች የተቀዳጀናቸው ታላላቅ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ስኬት ድሎች በበለጠ ጎልብተው እንዲቀጥሉ ኢንቨስትመንቱን ከማሳደግ ጎን ለጎን ሀገራዊ ሰላማችንን መጠበቅ የበለጠ ውጤታማ እንድንሆን ያደርገናል፡፡ ኢትዮጵያ በስራ ላይ ናት የምንለውም ለዚህ ነው፡፡

ሀገራችን ገንዘቡን በታቀደለት ልማት ላይ በማዋል ረገድ ከረጂዎች አመኔታ ለማትረፍ የበቃች ሀገር ነች፡፡ ድሕነትን በማስወገድ ላይ ያነጣጠረ ፖሊሲ ተግባራዊ ለማድረግ በመቻሏ ሰፊ ተቀባይነትን አግኝታለች፡፡ ይሄንን ጠብቆ መዝለቅ የኢትዮጵያውያን ሁሉ የጋራ ኃላፊነትና ግዴታ ነው፡፡ በብዙ መስክ ወደ ታላቅ ሀገርነት የጀመርነው ጉዞ አኩሪ ነው፡፡ እንደጥንታዊና ታላቅ ሕዝብ የውስጥ ችግሮቻችንን በመደማመጥ በመቻቻል እየፈታን ልማትና እድገታችንን  ጠብቀን መዝለቅ ግድ  ይለናል፡፡

በአበባ ኤክስፖርት ረገድም አለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን እያዳበርን በመምጣት የዓለምን ገበያ እየሰበርን መግባት ችለናል፡፡ ይህም አንድ ትልቅ ሊቀጥል የሚገባው ኢኮኖሚያዊ ድል ነው፡፡ በአለፈው አመት ወደስራ የገቡት ኢንዱስትሪ ፓርኮቻችን ሀገራችንን የተለያዩ ቀላልና ከባድ ዘመናዊ አንዱስትሪ ባለቤት ከማድረጋቸውም በላይ ለዜጎቻችን ሰፊ የስራ እድል ከፍተዋል፡፡ በተለያየ መስክ የሚደረጉት ኢንቨስትመንቶች የእውቀትና የቴክኒዮሎጂ ሽግግር ወደ ሀገራችን በማስገባት ረገድ ሰፊ ሚና ይጫወታሉ፡፡ ይህም በበኩሉ የነገን ሀገራዊ ተስፋ ይበልጥ ያሳድጋል፡፡ ሀገራችን ከዚህ በፊት ባልነበረና ባልታየ በኢንዱስትሪ ዘመን አብዮት ውስጥ መሆኗ በገሀድ እየታየ ነው፡፡

በቂሊንጦ ግንባታው እየተፋጠነ ያለው ግዙፍ የመድኃኒት ማምረቻ ኢንዱስትሪ የአገራችንን የመድኃኒት ኤክስፖርት በማሳደግ በአጠቃላይ ያስቀመጠችውን ራዕይ ከማሳካት አንጻር ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ ከዚህ በፊት ከውጭ የምናስመጣቸውን መድሀኒቶች ዛሬ በራሳችን ሀገርና ባለሙያዎች ማምረት ለሕብረተሰቡ ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ ማድረስ መቻል ትልቅ እድገት ነው፡፡

በመስኩ የተሰማሩ ባለሙያዎቻችን የበለጠ እውቀትና ልምድ እያገኙ ለሌሎች ዜጎች እውቀታቸውን የሚያካፍሉበት ሁኔታ እየሰፋ ስለሚሄድ በባለሙያ ረገድ የሚኖረውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ያስችላል፡፡ የቂሊንጦ መድኃኒት ማምረቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ኢትዮጵያ ከሚያስፈልጋት መድኃኒት 80 በመቶ ያህሉን ከውጭ አገራት በውጭ ምንዛሬ የምታስገባውን ከመሸፈን ባለፈ እንደገናም የውጭ ምንዛሬ ገቢ እንደሚያስገኝ ይጠበቃል፡፡

በ2009 መስከረም ወር መጨረሻ ላይ የተመረቀው የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት እስከ አሁን ድረስ በሙከራ ሥራ ላይ ቆይቶ የሙከራ ጊዜውን በማጠናቀቁ የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት አግኝቶ ወደስራ ገብቶአል፡፡ የሚሰጠው ሀገራዊ አገልግሎት ኢኮኖሚያችንን ከማሳደጉም በተጨማሪ ከጎረቤት አገራት ጋር በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለመፍጠር  ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡

በአፍሪካ የመጀመሪያው የሆነውና ቆሻሻን ወደ ኃይል ማመንጫነት እየተጠቀመ ያለው የረጲ የደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ኢንዱስትሪ ከመዲናዋ ነዋሪዎች ቤት የሚወጣውን ደረቅ ቆሻሻ ወደ ኃይል ምንጭነት በመቀየር ቆሻሻን በአግባቡ ከማስወገድ ባለፈ ለነዋሪዎች በአነስተኛ ዋጋ ኃይል ለማቅረብ የሚያስችል ነው፡፡ ይህ የቴክኒዮሎጂ ግብአት በሀገራችን ባሉ ክልሎችም እየተስፋፋ በመሄድ ሕብረተሰቡን በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ይታመናል፡፡

የባቡር አገልግሎቶቻችንም ይሁኑ የረጲ የደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያ ለታዳሽ ኃይል የሰጠችውን ትኩረት ማሳያዎች ናቸው፡፡ በዚህም አገራችን በአፍሪካም ሆነ በሌሎች አለማት ከፍተኛ አድናቆትን ማትረፍ ችላለች፡፡ ሀገራችን በተለያዩ ክልሎች የተፈጥሮ እንፋሎት እምቅ ሀብት አላት፡፡ ይህንን እስከዛሬ ሳንጠቀምበት የኖርነውን ሀብት በስራ ላይ ለማዋል ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ሲሆን  የእንፋሎት ኃይል ማመንጫ ለመገንባት ልዩ ልዩ ድጋፍ ከውጭ በመገኘት ላይ ይገኛል፡፡

በኃይል አቅርቦት ዘርፍ የተለያዩ የግል ኩባንያዎች መሰማራት ጀምረዋል፡፡ ይህም አገራችንን ከብድር በማላቀቅ በተፈለገው ፍጥነትና መጠን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ለማግኘት የሚያግዘን ሲሆን ለምስራቅ አፍሪካ አገሮች የኤሌክትሪክ ሃይል በሽያጭ ለማቅረብ በዚህም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ለሀገራችን ለማስገኘት የሚያስችል ነው፡፡

በየመስኩ የተከፈቱት የሀገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስትመንቶች ከቴክኒዮሎጂ ሽግግር እስከ እወቀትና ልምድ ድረስ ለዜጎቻችን በማካፈል ረገድ ትልቅ እገዛና አስተዋጽኦ አድርገዋል፤ ሰፊ የስራ መስክም ከፍተዋል፡፡ በተገኘው ሰፊ የስራ እድልም ዜጎቻችን ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡ በግብርናው መስክ በተሰሩት ሰፋፊ ስራዎች ኋላቀር የነበረውን ግብርና ዘመናዊና ምርታማ በማድረግ አርሶአደሮቻችን ዘመናዊ አስተራረስና ምርታማነትን እንዲያጎለብቱ የመሬት አጠቃቀማቸውን በዘመናዊ መልክ እንዲደርጉ በርካታ ስራዎች በመሰራታቸው ከፍተኛ ለውጥ ተመዝግቦአል፡፡

በአሁኑ ሰአት ሀገራዊ ምርታችን ከነበረው በተሻለ ደረጃ ማደግ ችሎአል፡፡ ከግብርናው ጋር በተያያዘ የተጋለጡ ቀድሞ በዝናብ ውሀ የተሸረሸሩ ቦታዎች ሕክምና ተደርጎላቸው ምርት የሚሰጡበትን እውቀት አርሶአደሮቻችን አግኝተዋል፡፡ የተጋለጡ ባዶ ተራራዎች በደን የተሸፈኑበት፤ በከባድ ዝናብ ወቅት ውሀን የማቆር እውቀት በስፋት የተገበየት በዚህም ውኃውን ወደመሬት የማስረግ ሰፊ ጉድጓዶችን መቆፈርና ተጠቃሚ ማድረግ የተቻለበት ሁኔታ በሰፊው ተፈጥሮአል፡፡ ሌላው ግብርናችንን በማሳደግ በኩል የተሰራው ሰፊ ስራ የመስኖ ውሀ ተጠቃሚነትን ያሳደገ ነው፡፡ በዚህም በተለያዩ ክልሎች ሰፊ የመስኖ ግድቦች ተሰርተው በስራ ላይ ውለዋል፤ ውጤታማም ሆነዋል፡፡ ሀገራችን በብዙ መስኮች ሰፊ የልማትና የእድገት ስራዎችን ሰርታለች፡፡ ኢትዮጵያ በስራ ላይ ነች የምንለውም ለዚህ ነው፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy