Artcles

ኢንቨስትመንትና የግሉ ባለሃብት

By Admin

January 02, 2018

ኢንቨስትመንትና የግሉ ባለሃብት

                                                       ዘአማን በላይ

ሰሞኑን አንድ ዘገባ ወጥቷል— በኢትዮጵያ የቻይና የግል ኢንቨስትመንት በ11 ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ 269 ሚሊዮን ዶላር ማስመዝገቡን የሚገልፅ። ይህ በምሳሌነት የሚጠቀስ የኢንቨስትመንት ፍሰት ግልፅ ይመስለኛል። ይኸውም መንግስት ለሀገር ውስጥና ለውጭ ባለሃብቶች እያደረገ ያለው ድጋፍ የኢንቨስትመንት ፍሰቱን እያጠናከረው መሆኑን ነው። መንግስት ሀገራችን ውስጥ መዋዕለ ነዋያቸውን በማፍሰስ ለሚሰሩ ልማታዊ የግል የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች ምቹ የአሰራርና የስራ ምህዳር በመፍጠሩ የባለሃብቶቹ ፍሰት ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲጨምር አድርጓል።

የዚህ ፅሑፍ አንባቢ እንደሚገነዘበው የሀገራችን ኢንቨስትመንትን የመሳብ ብቃት የመነጨው ከምንም ተነስቶ አይደለም—ካለን የኢንቨስትመንት አሰራር ተመራጭነት  የመነጨ እንጂ። የኢፌዴሪ መንግስት በሀገሪቱ መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ፣ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው የውጭ ባለሃብቶችን ለመሳብ የተለያዩ ማበረታቻዎችን በማመቻቸት በሩን ከፍት በማድረግና በተለያዩ አለም አቀፋዊ መድረኮች ተጨባጭ ሁኔታውን በማስረዳት በርካታ ባለሃብቶችን በመሳብ ላይ ነው። አንዱ ማሳያ ቀደም ሲል በመግቢያዬ ላይ የጠቀስኳቸው የቻይና የግል ባለሃብቶች በ11 ወራት ብቻ ያፈሰሱት መዋዕለ ነዋይ ነው።

መንግስት በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በተለይም በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግና ኢንዱስትሪ ዘርፎች የተሰማሩ የውጭ ባለሀብቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መምጣት ችሏል።

ሀገራችን እየተከተለችው ባለው ምቹ የኢንቨስትመንት ምህዳር ነፃ የመሬት አቅርቦት መዘጋጀቱ፣ የአበባ ማምረቻ ስፍራዎች በመንገድ እና በኤሌክትሪክ እንዲተሳሰሩ መደረጋቸው፣ የታክስ እፎይታ ጊዜ መኖሩ በርካታ የውጭ ባለሃብቶች ወደ ሀገራችን እንዲሳቡ ዋነኛው ምክንያት ሆኗል ማለት ይቻላል። ሀገራችን የምትከተለው የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር አሁን ለተገኘው የኢንቨስትመንት አመቺነት ምህዳር ወሳኙን ሚና መጫወቱ ግልፅ ነው።

መንግስት ሀገሪቱንና ህዝቦቿን ከድህነት ከኋላቀርነት ለማላቀቅ የነደፈው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመር ተግባራዊ በማድረግ ተስፋ ሰጪ ዕድገት በማስመዝገብ ላይ እንደሚገኝ የውጪው ዓለምና ባለሃብቶቻቸው ሳይቀሩ እየመሰከሩለት ይገኛሉ። ከመመስከር ባለፈም፤ የሀገራችንን መፃዒ ዕድል ከወዲሁ በአንክሮ አጢነው በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሳተፍ በልማት እግሮቻቸው ወደ ሀገራቸን እየተመሙ ነው።

እንደ እኔ እምነት በሀገራችን ውስጥ እየደገ የመጣ፣ ተጠቃሚ እንዲሁም መካከለኛ ገቢ ያለው የህዝብ ቁጥር መጨመሩ፣ ፈጣን የከተሞች ዕድገት መታየቱና ሳቢ የኢንቨስትመንት አሰራር መኖሩ ባለሃብቶችን እየሳበ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ሀገራችን በምስራቅ አፍሪካ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ ሀገራት ውስጥ አንዷ ስለሆነችና እያደገ የመጣውን ፍላጎት ለማሟላት አቅም ያላት መሆኗ ባለሃብቶቹ ለሚሳተፉበት የኢንቨስትመንት ዘርፍ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።

በኢትዮጵያ ፈጣን ምጣኔ ሃብት ውስጥ የፋይናንስ፣ የቴሌኮም እና የጅምላ ንግድን ጨምሮ ሌሎች ዋና ዋና የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለውጭ ባለሃብቶች የተከለከለ ነው። ይህም የሀገራችን የፋይናንስና ለሌሎች ተቋማት ራሳቸውን እስኪያጎለብቱና በአስተማማኝ ሁኔታ ተወዳዳሪ እስኪሆኑ ድረስ እንዲሁም መንግስት በተመረጠ አኳኋን በልማት ስራው ላይ ስለሚሳተፍ ነው።

ይሁንና የውጭ ባለሃብቶች በሲሚንቶ፣ በቡና፣ በወይን እና በብስኩት ማምረት እንዲሁም በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፎች ውስጥ በመሳተፍ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መገኘታቸው ሀገራችን የውጭ ባለሃብቶችን የሚያበረታታ አካሄድ እየተከተለች መሆኑን መገንዘብ የሚገባ ይመስለኛል።

ሀገራችን ያላት የተረጋጋ ሥርዓት እና ርካሽ የጉልበት ክፍያ እንዲሁም ለባለ ሃብቶች የተዘጋጀው የተሻለ የታክስ ድጎማና የእፎይታ ጊዜ ብሎም በታዋቂው አየር መንገዷ የዓለም ገበያን በቀላሉ ለመድረስ መቻሏ ለኢንቨስትመንት ምቹ እንድትሆን አድርጓታል።

እንደሚታወቀው ከውጭ የምናስገባው ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ሀገራችን ውስጥ የስራ ዕድል እየፈጠረ ነው። የውጭ ምንዛሬ ግኝታችንንም ያጎለብተዋል። ይህ ግኝታችን የሀገር ኢኮኖሚን በማጎልበት ኢትዮጵያ ላለመችው መካከለኛ ደረጃ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ ያስችላታል።

የኢንቨስትመንት ፖሊሲው የሚያሰራ ነው። በኢኮኖሚው ውስጥ የመንግሥት ሚና የተለያዩ የልማት ኃይሎችን በማቀናጀት መምራት የመሠረተ ልማት በማቅረብና የሰው ሀብት ልማትን በማካሄድ እንዲሁም ፈጣንና ውጤታማ የመንግሥት አገልግሎት በመስጠት ለልማታዊ የግሉ ዘርፍ ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠርና የመደገፍ ተግባራት እየተከናወኑ ነው። ከዚህ በተጨማሪ የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጮችን መዝጋት እና በግሉ ዘርፍ የማይሰሩ የልማት ተግባሮችን መንግስት ገቢራዊ እንዲያደርጋቸው የሚያስችሉ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል።

መንግሥት የግሉና የመንግሥት የዘርፎች ተዋንያን በፍትሃዊ የገበያ ውድድር የተመሩ ልማታዊ ኢንቨስትመንት የማስፋፋት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ገበያው የማይመልሳቸውን የልማት ጥያቄዎች በተጠናና በተመረጠ ሁኔታ መንግሥት በራሱ በቀጥታ የሚሳተፍባቸው አቅጣጫዎች በመከተል ላይ ይገኛል። መንግሥት የገበያ ጉድለቶችንና ተያያዥ የኪራይ ምንጮችን ለመዝጋት በመሰረተ ልማት እና በሰው ሃብት ልማት ሰፋፊ ኢንቨስትመንቶችን በማካሄድ ላይ ይገኛል።

የመሰረተ ልማትና የሰው ሃብት ልማት ኢንቨስትመንት የማስፋፋት ሥራ በእኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ እንደ ልማታዊ መንግሥት ማከናወን ያለበት ቁልፍ ተግባር እንደሆነ ታምኖበታል የሚካሄድ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። መንግስት በዚህ መልኩ የገበያ ጉድለቱን በማጥበብ የኪራይ ምንጮችን ለማድረቅ እንዲሁም የማኑፋክቸሪንግ፣ የግብርናና የመሳሳሉት ድጋፎች በማድረግ ልማታዊ ባለሃብቶች እንዲበረታቱ እያደረገ ይገኛል።

ይህ ሁኔታም እንደ መሬት፣ ብድርና የመሳሰሉትን ድጋፎችን የግሉ ባለሃብት በቅድሚያ እንዲያገኝ፣ ቀልጣፋና ግልጽ፣ ተገማችና ውጤታማ እንዲሆኑ ብሎም ለልማታዊ ኢንቨስትመንቶች ይበልጥ አዋጪ የሚሆኑበትና የሚስፋፉበት ሁኔታ በየጊዜው እየጎለበተ እንዲሄዱ በማድረግ ላይ ይገኛል።

ርግጥ ለሀገራችን ፈጣን ዕድገት አስፈላጊ የሆኑ አንዳንድ ኢንቨስትመንቶች ገበያው ላያስተናግዳቸው እንደሚችል ይታመናል። ስለሆነም ፈጣን ዕድገቱን ሳይቆራረጥ ለማስቀጠል የዚህ ዓይነት የኢንቨስትመንት መስኮች በጥንቃቄ እየተጠኑና እየተመረጡ በቀጥታ በመንግሥት በራሱ ብቻ ወይም ከግሉ ዘርፍ በጋራ እንዲካሄዱ እያደረገ ነው።

በመንግስት በኩል መካከለኛና ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች የቴክኖሎጂና የማምረት አቅማቸውን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል። ከእነዚህም መካከል የአቅም ግንባታ፣ የገበያ ትስስርን መፍጠር እንዲሁም የኢንቨስትመንት ክትትልና ድጋፍ መስጠትን ያጠቃልላል። ይህ ደግሞ የውጭ ምንዛሪ ግኝታቸውን እንዲያሳድጉ ይረዳቸዋል።

መንግሥት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪን በወጭ ንግዱ ለማጠናከር ባከናወነው ተግባር ከምንጊዜውም በላይ የተሻለ ውጤት መመዝገቡን ተመልክተናል። ለአብነት ያህል የጨርቃ ጨርቅና የአልባሳት ኢንዱስትሪ፣ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ተስፋ ሰጪ ለውጦች እየታየባቸው መሆኑን መጥቀስ ተገቢ ነው።

የመንግሥት ደጋፊ ተቋማት አቅም ለማሳደግ የፋብሪካዎች የቴክኖሎጂና የማኔጅመንት አቅም ካደገ ለኢንቨስትመንት ዘርፉ ማደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ከባለሃብቱ ጋር መግባባት ላይ መድረሳቸውና ለመፍትሔውም በጋራ መሰለፋቸው የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው ግልፅ ነው።

መንግስት በእርሱ ጣልቃ ገብነት ሳቢያ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ልማትን በማስፋፋት የተፋጠነ ልማትን ለማረጋገጥ የውጭ ምንዛሪ ገቢን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራት ላይ ይገኛል። በመሆኑም ቅድሚያ የተሰጣቸው ዘርፎች፣ በተለይም በግብርና ልማት እንዲሁም በኢንዱስትሪ መር አቅጣጫን በቀዳሚነት የገቢ ምርት መተካት ላይ አመርቂ ውጤት እየተመዘገበ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ በማዕድንና ፔትሮሊየም ኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ፕሮግራም ላይ የሚፈሰው ገንዘብ በመቶ ሚሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር እየሆነ ነው። ለዚህ ስራ አመቺነትም በመሰረተ ልማት ዘርፍ የሀገሪቱን የመንገድ አውታር ለማሳደግና ለማሻሻል እየተደረገ ያለው ጥረት ሳይጠቀስ የሚታለፍ አይደለም። እናም መንግስት በአሁኑ ወቅት ወደ ሀገራችን እንዲፈስ እያደረገ ያለውን ኢንቨስትመንት ማጠናከር ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ይመስለኛል።