Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

እንነጋገር፤ እንወያይ፤ ችግሮቻችንንም እንፍታ

0 323

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

እንነጋገር፤ እንወያይ፤ ችግሮቻችንንም እንፍታ

ዮናስ

ኢትዮጵያውያን በመረጡበት ሥፍራ የመኖር፣ የመሥራት፣ የመዘዋወርና ሀብት የማፍራት መብታቸው በሕግ የተረጋገጠ ቢሆንም ተግባራዊ ባለመሆኑ ብቻ፣ በበርካታ ዜጎቻችን ላይ ከፍተኛ በደል ተፈጽሟል፡፡ ዜጎች በገዛ አገራቸው ‹‹መጤ›› እየተባሉ ጥቃት ሲፈጸምባቸው፣ ሲፈናቀሉና ሲገደሉ በተደጋጋሚ ጊዜያት ታይቷል፡፡ አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ ለመገንባት በሕገ መንግሥት አማካይነት ቃል ኪዳን በተገባበት አገር ውስጥ፣ ዜጎች በታጠቁ ኃይሎች ሳይቀር የግፍ ፅዋ ቀምሰዋል፡፡ በተደራጁ ኃይሎች አማካይነት ተቀስቅሰው በተነሱ አፍለኞች ሳይቀር  ለዘመናት አብሮ በሰላም ከኖረ ሕዝብ ፍላጎት ውጪ በርካቶች ህይወታቸውን አጥተዋል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ከቀዬአቸው ተሰደዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን በገዛ አገራቸው የባይተዋርነት ስሜት የሚሰማቸው ብሔርተኝነት እየተለጠጠ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ሲፈታተነው ነው፡፡ ዜጎች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደራቸው፣ በራሳቸው መዳኘታቸው፣ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማራቸው፣ ቋንቋቸውንና ባህላቸውን ማሳደጋቸው፣ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ማጎልበታቸውና በማንነታቸው መኩራታቸው መከበር አለበት፡፡ ነገር ግን በተለይ ወጣቶች ራሳቸው ላይ አጥር ሠርተው ሌሎች ወገኖቻቸውን አትድረስብኝ አልደርስብህም የሚል ችግር ውስጥ እንዲገቡ የሚደረጉት፣ በተለያዩ ገፊ ምክንያቶች መሆኑንም ማመን ተገቢ ነው፡፡ ዋናው ቁም ነገር ግን ለዘመናት አብሮ የኖረው ይህ ታላቅ ሕዝብ ጠባብነትና የጋራ እሴቱን የሚንዱ ድርጊቶችን እንደማይቀበል በታሪኩ በተደጋጋሚ አሳይቷል፡፡ ይህ ኩሩና አስተዋይ ሕዝብ የሚፈልገው በክፉና በደግ ጊዜያት አብሮ ተደጋግፎ እንደኖረው በዚሁ መሠረት መቀጠል ነው፡፡ ይህንን አስደሳችና የሚያኮራ የጋራ እሴት ለአንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ግንባታ መሠረት ማድረግ ሲገባ፣ ለግለሰቦችና ለቡድኖች ጥቅም ብቻ ሲባል ግጭት እየፈጠሩ አገር ማመሰቃቀል ሊቆም ይገባል፡፡ያለው አማራጭ አንድ ብቻ ነው።መነጋገር እና መደማመጥ።ለዚህ ደግሞ ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል ብቻ ሳይሆን ህገ መንግስታዊ እውቅናም አግኝተዋል።

ዴሞክራሲ የተለያዩ ሃሳቦች በነፃነት የሚንሸራሸሩበት የሃሳብ ገበያ ነው። ስለሆነም ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ሂደት ውስጥ ቅድመ ሁኔታ ይሆናል ማለት ነው። በዚህ ጊዜ ደግሞ ውይይት የሚደፋፈርና የሚበረታታ ይሆናል ማለትም ነው። ለየትኛውም አይነት ስርአት ግንባታና ልማት ሃሳብ ቀዳሚ አጀንዳ ነው። የሃሳብ ልውውጥ ሲኖር በእርጋታ መደማመጥ ይከተላል። ስለሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብት ስናወራ ወይም ስለሃሳብ ነጻነት እጨነቃለሁ የሚል አካል፤ ማንም ሰው የራሱ የፖለቲካ አቋም፣ የሕይወት ፍልስፍና ወይም የኑሮ ዘይቤ ሊኖረው እንደሚችል ታሳቢ ሊያደርግ የሚገባ መሆኑ አያከራክርም። ይህን ማድረግ ማለት ከሌሎች ጋር በሚደረግ ውይይት የተለያዩ ሃሳቦችን መጋራት እንደሚቻል ከማመን ይልቅ ይህን ማድረግ ከሚፈልገው አመለካከት የግድ እንዲላቀቅ የሚያደርግ ነው ብለው የሚያስቡ ሃይሎች ቀድሞ ነገር ስለ ሃሳብ ነጻነት ሊናገሩ መሞከር ምክንያታዊነት አይኖረውም።

ስለሃሳብ ነጻነት እንጨነቃለን ብለው የሚናገሩ ሃይሎች በተግባር ከላይ የተመለከተውን እየሆኑ በዚህች ሃገር የመነጋገርና የመደማመጥን አፈር ድሜ እያበሉት ነው። ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብትን ጨምሮ ተያያዥ የሆኑ ህገ መንግስታዊ መብቶች የተረጋገጡት በነዚሁ መብቶች ተጠቅመን በጋራ ጉዳዮች ላይ፤በሚኖሩን ልዩነቶች ላይ እንድንነጋገር እና ተደማምጠን ለሃገርም ሆነ ለራስ የሚበጀውን መውሰድ የሚያስችል መደማመጥ እንዲኖር ለማስቻል እንጂ እንድንደነቋቆር አልነበረም። የራስን ጠቃሚ የሚባል ሃሳብ ይዞ የሌሎችን ምልከታ መረዳት ይጠቅማል እንጂ፣ በነውጠኝነትና በእንቢ ባይነት ማጣጣል አምባገነንነት ካልሆነ ሊሆን የሚችለው አንዳች ነገር የለም።

ስለሃሳብ ነጻነት 30 እና 40 አመታትን መጨነቃቸውን ሲያወሱ የምናውቃቸው ግለሰቦች፤ ይልቁንም ፖለቲከኞች ነን ባዮች ዛሬም የተዘረጋውን፣ መነጋገርና መደማመጥን የሚያስችል ስርአት ክደው በማጣጣል ለዘመናት መናቆርን የጤነኝነታቸው ማረጋገጫ አድርገዋል። መንግስትን ዘወትር አድምጠን ሲሉ የሚወተውቱ ሰዎች ከመደማመጥ አስቀድሞ ሰከን ብሎ መነጋገር አስፈላጊ ይልቁንም ግድ የሚል መሆኑን እንኳ በቅጡ የተገነዘቡ አይመስሉም። ክስተቶችን እየተከተሉ በማጯጯህ አድምጠን ከማለት አስቀድሞ በክስተቶቹ መነሻና ምክንያት ላይ መነጋገር አስፈላጊ መሆኑንም የሚያውቁ አይመስሉም። አንዳንዴ ይህን አመክንዮ እናውቃለን የሚሉቱ ደግሞ ለመነጋገር የሚያስችል ስርአት ከየት መጥቶ ሲሉ ለመሞገት ሲሞክሩም ይሰማል። ዳሩ ግን መነጋገር ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብት ውስጥ የሚገኝ ቁንጽል ነገር ነው። ሃሳብን በነጻ ለመግለጽ መብት ህገመንግስታዊ ዋስትና የሰጠ ስርአት መነጋገር ጭንቅ የሚሆንበት አመክንዮ ሊኖር አይችልም።

ስለሆነም ስርአቱን በሃሳብ ሞግተው የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ሂደቱ አካልና ግብአት እንዲሆኑ የሚጠበቅባቸው እነዚህ ሃይሎች ከመነጋገር አስቀድሞ የኛን ብቻ ስሙ በሚል ደዌ ተለክፈዋልና ከመጯጯህ የዘለለ ቁም ነገር ልናገኝባቸው አልቻልንም። ስለሆነም አስተሳሰቤ ተሸናፊ ይሆንብኛል ወይም በዓይኔ እንኳ ማየት የማልፈልገው ሰው ሊሞግተኝ ይችላል ተብሎ ከውይይት ይልቅ ጠብ አጫሪነት መገለጫቸው ሆኗል።ከውይይት መሸሽ ብቻ ሳይሆን ነገሮችን በማራገብ በመነጋገር መቋጫ ሊገኝላቸው የሚችሉ ነጠላ ነገሮችን በማሳበጥ ሃገርን ለፈተና እየዳረጉ ነው። ይልቁንም በዚሁ አመላቸው ሊነጋገሩ የሚፈቅዱ ሃይሎችን በጠላትነት እየፈራረጁ ማናከስን ቁልፍ ተግባራቸው አድርገዋልና ጥንቃቄ ያስፈልጋል። ጉዳያችን ሁሉ በተዘረጋልን የመነጋገርና የመደማመጥ ስርአት ማለቅ የሚችል መሆኑን ሁሌም ማጤን ያስፈልጋል።

በግለሰብ ደረጃም ሆነ በመንግሥት የዕለት ተዕለት ሥራ፣ በፓርቲ ፖለቲካም ሆነ በተለያዩ ጉዳዮች መነጋገር ሲጠቅም እንጂ ሲጎዳ ተስተውሎ አያውቅም።የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት በነበሩት መስታጋብሮቹ ቋንቋዎች ሳይገድቡት በዓይኖቹ ጭምር በመግባባት ክፉና ደግ ዘመናትን በጋራ አሳልፏል።እምነት፣ ባህልና የተለያዩ ፍላጎቶቹን በመከባበርና በመተሳሰብ አቻችሎ ኖሯል። እየኖረም ነው። ህገ መንግስታዊ ዋስትናም በሌለበት ዘመን ሰብዓዊ ፍጡር መሆን ምንም ዓይነት እንከን ሳይገጥመው የጋራ እሴቶችን አክብሮና አስከብሮ መኖር የኢትዮጵያዊያን ትልቁ የጋራ መገለጫ ነው።ህዝቡ አገሩን ከወራሪዎች በአንድነት ሲከላከል የነበረው እርስ በርሱ ባለው የጠነከረ ፍቅር እና በጋራ ጉዳዮቹ ተነጋግሮ ስለተደማመጠ ብቻ ነው።ሌላ ብዙ ሚስጥር የለውም።የዚህ እሴት ባለቤት በሆነችው ሃገር የዛሬ ፖለቲከኞች ነን ባዮች በእርግጥም በፖለቲካው ዙሪያ ተኮልኩለው እንደሆነ እንጂ ተነጋግረው ሊደማመጡልን ቀርቶ ተነቋቁረው ሊያናቁሩን እየከጀሉ ነውና ጥንቃቄ ያስፈልጋል።

ለሃሳብ ነፃነት እታገላለሁ ሲል ዘወትር በየአውደ ጥናቱ ላይ የምናየው ሳይቀር ይቀናቀነኛል የሚለውን ተገዳዳሪውንና በገዛ ፓርቲው ውስጥ ሙግት የሚያነሳውን የትግል አጋሩን የተለየ ሐሳብ ለማዳመጥ ሲተናነቀው እየተመለከትን እንዴታ ለዚህች ሃገር መፍትሄ ሊሆኑ ይችላሉ ብለን እንጠብቅ?።

ድጋፍና ተቃውሞ ጭልጥ ብለው ጠርዝ እየያዙ ገደል አፋፍ ላይ ሆኖ በነገር መቋሰል፣ በዘር መሰዳደብ፣ ሕዝብን ማንጓጠጥና መዝለፍ፣ መለስተኛ ቅራኔዎችን መሠረታዊ በማድረግ ሕዝብን ለግጭት መቀስቀስ፣ የአገር ህልውናን በመናድ ለሶሪያ ዓይነት ውድመት ማመቻቸት፣ ለታሪካዊ ጠላቶች ሚስጥር መሸጥና ተላላኪ መሆን፣ አምባገነንትን የሚያበረታቱ ቅስቀሳዎች ማድረግ፣ የግለሰብንም ሆነ የቡድን መብት መጨፍለቅ፣ የሃሳብ ነፃነትን መጋፋት የነዚህ ሃይሎች መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑ አሁን በግልጽ ጎልቶ ወጥቷል።

መንግስት በበኩሉ እነዚህን ሁሉ መፍታት የሚያስችል ስርአት ቢዘረጋም በውስጡ የተሰገሰጉ ሰላማዊ ተቃውሞን የሚያፍኑ፤ መብታቸውን የሚጠይቁትን የሚያሰቃዩ፤ አገርን ለነውጥ የሚያጋልጡ፣ የሕዝብን መሠረታዊ ጥያቄዎችን በአግባቡ መመለስ የማይችሉ እና ለመመለስ የማይፈቅዱ፤የዜጎችን ሕገ መንግሥታዊ መብቶች የማያከብሩ፤ ሃይሎችን ነቅሶ አለማስወገዱ ከላይ ለተመለከቱት ሃይሎች ምቹ መደላድል የፈጠረላቸው መሆኑን ሊገነዘብ ይገባል።ስለሆነም በሁለቱም ጎራ ያሉት ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ውስጥ መሽገው የሚረጩት መርዝ አዲሱን ትውልድ እየመረዘ ለመሆኑም ሰሞንኛዎቹን ለመነጋገርም ሆነ ተደማምጦ ችግሩን ለመፍታት ያላስቻሉ ክስተቶችን በማስታወስ መገንዘብ ይቻላል።  

ከተጋረጠብን አደጋ ለመዳን የተለያዩ ሃሳቦችን ይዞ የመነጋገርን ጸጋ የተገነዘቡ እና በተግባርም የሆኑ ሃይሎች ብቻ ናቸው የሚያስፈልጉን። መከተል የሚገባን ለመነጋገርና ለመደማመጥ ዋጋ የሚሰጡትን ብቻ ነው። አንደኛው ጎራ ሌላውን በጅምላ እየፈረጀ የተመጣበት መንገድ ለማንም ሲጠቅም አልተመለከትንምና ይህንኑ ዋጋ ቢስ አካሄድ አለመከተል ብቻ ሳይሆን ልናወግዘው ይገባል።

ተቀራርቦ መነጋገር ማለት ሥልጣኔ ነው።የግድ አሸናፊና ተሸናፊን እንመልከት ማለት ኋላ ቀርነት ነው። አንድ አገር ፅኑ የሆነ መሠረት የሚኖረው ሰላም፣ ዴሞክራሲና ፍትሕ ሲኖሩ ብቻ ነው። እነዚህ በተሟላ መንገድ ይኖሩ ዘንድ ደግሞ እየመረረንም ቢሆን ለመነጋገርና ለመደማመጥ ክፍት መሆንን ይጠይቃልና ፤ ለመነጋገር በተዘረጋው ስርአት ተጠቅመን ሃገሪቱን ከውድቀት ማዳን ወቅቱ የሚጠይቀው የዜጎች ግዴታ ነው።

ለመነጋገር በተዘረጋው ስርአት ተጠቅመን፤ በመወያየት ሃገራችንን ከገጠማት ቀውስ  ማዳን ወቅቱ የሚጠይቀው የሁላችንም ግዴታ ነው!!

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy