Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

እውን ግብፆችን አለመጠራጠር ይቻላልን?

0 305

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

እውን ግብፆችን አለመጠራጠር ይቻላልን?

ኢዛና ዘ መንፈስ

ሀገራችን ኢትዮጵያ በፈርጀ ብዙ የህዳሴ ጉዞ ላይ ሰለመሆኗ መላው የዓለም ማህበረሰብም ጭምር ምስክርነቱን ሲሰጥ የተደመጠበት ወቅት ቢኖር 2007ዓ.ም ነው ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህ ደግሞ በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዘዳንት የነበሩትን ባራክ ሁሴን ኦባማን ጨምሮ፤ የግብፁ ፕሬዘዳንት አብዱልፈታህ ዓልሲሲና እንዲሁም ሌሎች በርካታ የሀገራት መሪዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ይፋዊ ጉብኝት ያደረጉበት ዓመት መሆኑን ማስታወስ ብቻ በቂ ይመስለኛል፡፡ በተለይም የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማና የግብፁ አቻቸው የአብዱል ፈታህ ዓል ሲሲ ያኔ ኢትዮጵያን ከጎበኙበት የታሪክ አጋጣሚ ጋር በተያያዘ መልኩ፤ መላው ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የሀገራችንን የህዳሴው ዘመን በጎ ገፅታዎች አጉልቶ ያንፀባረቀ ሰፋፊ ዘገባ አየር ላይ ሲያውሉ መስተዋላቸውን ፈፅሞ የምንዘነጋው ጉዳይ አይደለም፡፡

እንግዲያውስ እኔ ሀገራችን ኢትዮጵያ ከመቸውም ጊዜ ይልቅ የህዳሴ ጉዞ ላይ ስለመሆኗ አጉልቶ ያንፀባረቀ ዲፕሎማሲያዊ ድል ያስመዘገበችበትን የ 2007 ዓ.ም ስኬታማ የበጀት ዓመት በማስታወስ መንደርደሬም ያለምክንያት እንዳይመስላችሁ፡፡ ይልቅስ የዓመቱ  እንግዶቻችን ከነበሩበት የበርካታ ሀገራት መሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት የግብፁ ፕሬዘዳንት አብዱል ፈታህ ዓል ሲሲ በፌደራላዊት፤ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፊት ቀርበው ስለሁለቱ የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት በመልክዓ ምድራዊ የጋራ ዕጣፈንታ የተቆራኘ ግንኙነት ጉዳይ ያደረጉትን “ታሪካዊ ነው” የተባለለትን ንግግር ዛሬ ላይ ማስታወስ ጠቃሚ መስሎ ቢሰማኝ እንጂ፡፡ ስለሆነም አሁን በቀጥታ ወደያኔው የፕሬዘዳንት አብዱልፈታህ ዓል ሲሲ ንግግር አልፍና ለዚህ ፅሁፌ ማጠንጠኛ አድርጌ የማነሳውን የኢትዮ.ግብፅ መንግስታት የውሃ ፓለቲካ ያስከተለው ዲፕሎማሲያዊ ትንቅንቅ የሚያስቃኝ መሰረተ ሃሳብ ፈር በማስያዝ ረገድ ይጠቅማሉ የምላቸውን አንዳንድ ነጥቦች ለማስታወስ እሞክራለሁ፡፡

እናም ከዚህ አኳያ የግብፅ ፕሬዘዳንት አብዱል ፈታህ ዓል ሲሲ ገና የከፍተኛ ጀነራል መኮንንነት ወታደራዊ የደንብ ልብሳቸውን አውልቀው በመጣል የሀገር መሪነቱን መንበረ ስልጣን የመቆናጠጣቸው ዜና መሰማቱን ተከትሎ፤ ኢትዮጵያን ለመጎብኘት የመጡበት አጠቃላይ ቅኝት ብዙዎቻችንን “ግብፃዊው የቀድሞ ጀነራል በእርግጥም ሌሎች የካይሮ መንግስታት ከዓባይ ተፋሰስ ጉዳይ ጋር በተያያዘ መልኩ ሲያራምዱ የኖሩትን የዘመነ ቅኝ አገዛዝ ኢ.ፍትሐዊ ፓሊሲ ለማስቀጠል መሞከር እንደማያዋጣ ሳይገነዘቡ አልቀሩም” የሚል ተስፋ እንድናሳድር ያደረገ ወዳጅነት የተንፀባረቀበት እንደነበር ነው እኔ በግሌ የማስታውሰው፡፡ ምክንያቱም ደግሞ ፕሬዘዳንቱ መላው የሀገራችን ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ለሚወከሉበት ምክር ቤት ባሰሙት ረጅም ሊባል የሚችል ንግግራቸው ላይ፤ ያንፀባረቁት መሰረተ ሃሳብ “የኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችን የህዳሴ ጉዞ ለኛ ለግብፃውያንም ጭምር የሚጠቅም አፍሪካ  አቀፍ ህዳሴ እንደሆነ እረዳለሁ” እስከማለት የደረሱበት እንደነበር አይዘነጋምና ነው፡፡ ይሁን እንጂ ግን፤ የግብፅ ፕሬዘዳንት በያኔው ለፌደራል ፓርላማችን አባላት የቀረበ ንግግራቸው ላይ ለኢትዮጵያውያን ህዝቦች የካይሮ መንግስታት ፓለቲከኞች ለወትሮው ከሚታወቁበት ግትር አቋም አኳያ የማይጠበቅ ዓይነት የወዳጅነት ስሜት የማሳየታቸውን ያህል፤ እግረ መንገዳቸውን አንዳንድ ለጊዜው ልብ ያላልናቸው ብርቱ ማስጠንቀቂያዎችን ሰንዝረው እንደነበረም ጭምር ነው ዘግይቶ ይገለፅልን የጀመረው፡፡

ለአብነት ያህልም ፕሬዘዳንቱ “በእርግጥ ነው የዓባይ ወንዝ ውሃ ለኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሃይል ለማመንጨት ያስፈልጋት ይሆናል፡፡ ለኛ ለግብፃውያን ግን የዓባይ ወንዝ ማለት ህልውናችን ነው” ሲሉ ያኔ ለኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ይፋዊ ንግግር ጣልቃ አጠንክረው ያስገነዘቡበትን ዲፕሎማሲያዊ ቋንቋ ታላቁን የህዳሴ ግድብ ለመገንባት የጀመራችሁት ጥረት በኛ ሀገራዊ ህልውና ላይ አሳሳቢ ስጋትን ስላስከተለ ይሄን ጉዳይ አውቃችሁ ግቡበት የሚል ውስጠ ወይራ ትርጉም ያዘለ እንደነበር፤ አሁን አሁን ሀገራችንን ክፉኛ ሲፈታተናት ከሚስተዋለው የሰላምና መረጋጋት መጓደል ችግር ጋር አያይዘው የሚያስታውሱ ወገኖች መኖራቸውን ማንሳት የሚቻል ይመስለኛል፡፡ በእርግጥም ደግሞ የግብፁ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ ዓል ሲሲ እንደኛ የዘመን ቀመር 2007ዓ/ም መገባደጃ ላይ ለኢፌዴሪ ፓርላማ ያን መሰል ንግግር አሰምተው ከሔዱ ከጥቂት ወራት በሁዋላ ነው በአንዳንድ የሀገራችን ክፍሎች ያልተለመደ ዓይነት የሁከትና ብጥብጥ ተግባር የተቀሰቀሰው፡፡

ይሄው አሁንም ድረስ ኢትዮጵያና መላው የብሔር ብሔረሰብ ህዝቦቿ ከመሰል አካባቢያዊ ግጭት ጋር ተያይዞ በሚከሰት የነውጠኝነት እንቅስቃሴ ሳቢያ ለፈርጀ ብዙ ኪሳራ እየተዳረጉ ይገኛሉ፡፡ በዚህ ምክንያትም እቺ ሀገር የበርካታ ንፁህን ዜጎቿን ህይወት የቀጠፈና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩትን ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ያፈናቀለ ተደጋጋሚ የፀጥታ መደፍረስ ችግር እያስተናገደች መቆየቷ የማይስተባበል ጥሬ ሀቅ ነው፡፡ በፅሁፌ መግቢያ ላይ ለመንደርደሪያነት ያህል በተወሳው የ2007ዓ/ም ዲፕሎማሲያዊ ስኬት አማካኝነት ዓለም አቀፋዊ ምስክርነት የተሰጠው የህዳሴው ዘመን ኢትዮጵያ ፈርጀ ብዙ በጎ ገፅታ እየደበዘዘ የመጣበት ሀገር አቀፍ እውነታ ስለመፈጠሩም ነው ደፍሮ መናገር የሚቻለው፡፡

ምንም እንኳን ከታህሳስ ወር 2008ዓ/ም ጀምሮ በተለይም የኦሮሚያንና የአማራን ብሔራዊ ክልሎች ያማከለ ሀገር አውዳሚ ነውጠኝነት የተቀላቀለበት የተቃውሞ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ተደጋግሞ ሲከሰት ከሚስተዋልበት አጠቃላይ ትርምስ የመፍጠር አዝማሚያ በስተጀርባ፤ እጃቸው ስላለበት የውጭ ሃይሎች ትክክለኛ ማንነት፤ ጉዳዩ ከሚመለከተው የኢፌዴሪ መንግስት ባለድርሻ አካል የሰማነው ነገር ባይኖርም፤ግን ደግሞ ግብፅን አለመጠርጠር እንደሚያዳግት የሚያመለክቱት ተጨባጭ ማሳያዎች መኖራቸው የሚካድ አይሆንም፡፡ ይህን ስልም ደግሞ የካይሮ መንግስት አንዳንድ ፖለቲከኞች አሁንም ድረስ በየአጋጣሚው የሚሰነዝሩትን ሀገራችን በዓባይ ወንዝ ላይ የምትገነባውን የህዳሴ ኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ እንድታቆም የሚጠይቅ የተቃውሞ ሃሳብ ጨምሮ ሌሎች በርካታ ግብፆች ኢትዮጵያን በህዝቦቿ የብሔር ብሔረሰብ ማንነትን መሠረት ባደረገ የዕርስ በርስ ቅራኔና ግጭት ምክንያት አተራምሰው ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ ዓል ሲሲ ከሶስት ዓመት በፊት እዚህ አዲስ አበባ መጥተው፤ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባሰሙት ንግግር ላይ አስጠንቅቀዋል የተባለለትን ዲፕሎማሲያዊ ዛቻ ተግባራዊ ለማድረግ ያለመ ስራ እየሰሩ ናቸው ብለን እንድንጠረጥር የሚያስገድዱ አንድምታዎች ተበራክተዋል ማለቴ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የፕሬዚዳንት ዓል ሲሲ መንግስት ጉዳዩን የያዘበት ዲፕሎማሲያዊ አግባብ አንዳንዴ መረርና ከረር ወዳለ አዝማሚያ ያመሩ መስለው የሚታዩበት፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ እንብዛም የሚያሰጋ ነገር የለም ብለን እንድናምን የሚያደርግ ወላዋይና አዘናጊ አቋምን የተከተለ ገፅታ እንዳለው ሆኖ ይሰማኛል፡፡

እስቲ ለዚህ አስተያየቴ መነሻ የሆኑኝን የግብፅ መንግስት ከኢትዮጵያ አቻው ጋር ያለውን በውሃ ፖለቲካ ላይ የተመሰረተ ዲፕሎማሲያዊ የግንኙነት መስመር ለፍርድ እንዳያመች አርጎ እያምታታ ስለያዘበት አግባብ፤ የታዘብኩባቸውን ሁለት ነጥቦች ብቻ እንደ አብነት ላቀርብ፡፡ የመጀመሪያው ነጥብ፤ ባሳለፍነው 2009ዓ/ም መጨረሻ ላይ ለተካሔደው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ወደ ኒዮርክ አሜሪካ በተጓዙበት አጋጣሚ ተገናኝተው እንደተወያዩ የተነገረላቸው የኢትዮጵያና የግብፅ መሪዎች ስለተለዋወጡት የሁለትዮሽ ሃሳብ የተዘገበው ዜና፤ የካይሮን ፖለቲከኞች ከመጠርጠር እንድንቆጠብ ሲባል ብቻ የቀረበ ዲፕሎማሲያዊ ስብከት እንደነበር መረዳቴ ነው፡፡ ሁለተኛውና ከዚያን ጊዜ ወዲህ ራሳቸው ሆነ ብለው  ወደ ከረረ ጡዘት እንዲያመራ አድርገውት የነበረውን የኢትዮ-ግብፅ መንግስታት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት፤ እንደገና ለማለዘብ ያለመ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችለው ነጥብ ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ሳሚህ ሹክሪ ሰሞኑን ወደ አዲስ አበባ መጥተው፤ ከኢትዮጵያው አቻቸው ከዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ጋር የተወያዩበት አግባብ ነው ማለት ይቻላል፡፡ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ የካይሮ መንግስት ለኢትዮጵያ የልማት አጋር ስለመሆኑ ሊያሳምነን ሲሞክር የሚስተዋልባቸው መሰል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ሁሉ፤ ሀገራችንን ለማተራመስ ያለመ የሁከትና ብጥብጥ ተግባር እያቀነባበሩ እኛን እርስ በርስ ሊያናቁሩን ሲሞክሩ ከሚስተዋሉት ፅንፈኛ ተቃዋሚ ቡድኖች በስተጀርባ የግብፅ ፖለቲከኞች ስውር እጅ እንዳለበት የሚሰማንን ጥርጣሬ አያስቀረውም ባይ ነኝ እኔ፡፡ እንዴት ማለት? የሚል አንባቢ ቢኖር ደግሞ አሁንም የሚከተሉትን ሁለት የመከራከሪያ ነጥቦች በምክንያትነት አነሳለሁና እነሆ አብረን እንመልከት…

ስለዚህ ኢትዮጵያውያን ህዝቦች የግብፅ ፖለቲከኞችን ሀገራችን ውስጥ እየተስተዋለ ካለው ተደጋጋሚ የሁከትና ብጥብጥ ተግባር ጋር በተያያዘ ጣልቃ ገብነት አለመጠርጠር እንዳንችል ከምንገደድባቸው አሳማኝ ምክንያቶች የመጀመሪያው ነጥብ፤ የካይሮው መንግስት አሁንም ድረስ በጎርጎሪሳውያኑ የዘመን ቀመር 1929 እና እንዲሁም 1959ዓ/ም ‹‹ተፈራርመናል›› እያለ የሚሞግትበትን የዘመነ ቅኝ አገዛዝ ‹‹ውል›› ለማስቀጠል እንደሚፈልግ እየገለፀ የሚገኝ መሆኑ ነው፡፡ እናም ግብፆች ይህን ያረጀ ያፈጀ አስተሳሰባቸውን የሙጥኝ እንዳሉ ባሉበት ሁኔታ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የምትገነባውን የህዳሴ ኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ ለማስቆም ያለመ ማንኛውንም ዓይነት አሉታዊ ተፅእኖ ለመፍጠር ከመስራት ይቆጠባሉ ብሎ ማሰብ ተራ የዋህነት ይመስለኛል፡፡ ጉዳዩ ከዚህ አኳያ ሲታይ፤ ለካይሮ ፖለቲከኞች የተሻለው የተፅእኖ ማሳደሪያ መንገድ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችለው ፀረ ኢትዮጵያ እንቅስቃሴ ደግሞ፤ እንደ ኦ.ነ.ግና እንደ ግንቦት ሰባት ዓይነቶቹን የሽብር ቡድኖች በገንዘብ እየደገፉ እኛን ሰላም የሚነሳ የሀገራዊ ትርምስ አጀንዳቸውን እንዲያስፈፅሙላቸው ማሰማራት ነው፡፡ ከዛም ተጠቃሾቹ ቡድኖች ‹‹የውስጥ አርበኞቻችን›› ለሚሏቸው የአገር ቤት ጉዳይ አስፈፃሚዎቻችን እየቆነጠሩ በሚልኩት ገንዘብ ወጣቶቻችንን እያታለሉ ኢትዮጵያን ለማተራመስ ያለመ የሁከትና ብጥብጥ ተግባር እንዲቀሰቀስ ያደርጋሉ፡፡ ስለዚህም ይሄኛውን ጉዳይ እንደ ሁለተኛ ስጋት ፈጣሪ ነጥብ ትወስዱልኝ ዘንድ እጠይቃለሁ፡፡ ለነገሩ ሌላም ግብፆችን አለመጠርጠር እንደሚያዳግት የሚያሳይ ምክንያታዊ የመከራከሪያ ነጥብ መጨመር ከባድ አይሆንም፡፡ ወጣም ወረደ ጉዳዩ ተገቢ ጥንቃቄን ይጠይቃልና ልብ ያለው ልብ ይበል እያልኩኝ ለዛሬ ሐተታየን እዚህ ላይ አበቃለሁ፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy