Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

እየተገፈፈ ያለው የስጋት ደመና

0 220

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

እየተገፈፈ ያለው የስጋት ደመና

                                                        ዘአማን በላይ

በሀገራችን ተከስቶ የነበረውን ጊዜያዊው የሰላምና መረጋጋት እጦትን ለመፍታት መንግስት ችግሩን በአጣዳፊ ለማስቆም በገባው ቃል መሰረት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በቁጥጥር ስር ውሏል። በተለይ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ ቦታዎች ላይ ተከስቶ የነበረውን ግጭት ለማስቆም በኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የሚመራ ኮሚቴ ተቋቁሞ የተለያዩ ተግባራትን ፈፅሟል፤ በመፈፀም ላይም ይገኛል።

በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተከስቶ የነበረው የግጭት ሁኔታ በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ ሊቀየር ችሏል። ሁሉም ዩኒቨርስቲዎች ወደ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ውስጥ ገብተዋል። ይህም መንግስት ቃል በገባው መሰረት ባከናወናቸው አስተማማኝ የሰላምና መረጋጋት ስራዎች በሀገራችን ላይ አንዣቦ የነበረው የስጋት ደመና እንዲገፈፍ ያደረገ ነው ማለት ይቻላል።

የበርካታዎቻችንን ቀልብ በአሳዛኝ ሁኔታ ስቦ የነበረው በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ የድንበር አዋሳኝ አካባቢዎች ለተፈጠረው ችግር በመንግስት በኩል በተሰጠው ትኩረት በርካታ ስራዎች ገቢራዊ ሆነዋል። ለዚህ አባባሌ ዋቢ የማደርገው ፈረዴራል መንግስት ከችግሩ አኳያ ዘግይቶም ቢሆን ያደረጋቸውን ድጋፎች በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራው ቡድን ለፓርላማ ያቀረበውን መረጃ ዋቢ በማድረግ ነው።

በየትኛውም ቦታ ለህዝብ ቅድሚያ ደራሽ በአቅራቢያ የሚገኝ ህዝብ ነው። ለዚህም በእማኝነት የኦሮሚያ ክልል ተፈናቃዮችን መጥቀስ ይቻላል። ተፈናቃዩቹ እንዳሉት ቀድሞ የደረሰላቸውን የአካባቢያቸው ህዝብ መሆኑን ያስረዳሉ። “የበሰለ ምግብና የሚጠጣ ውኃ በማቅረብ፣ መንግስትና ሌላው አካል እስኪደርስልን ድረስ ህይወታችንን ታድጓል” በማለት ይገልፃሉ። አንዳንድ የአካባቢው አስተዳደር አካላትም የወረዳቸውን ህዝብና ከጎረቤት ወረዳም ጭምር በማስተባበር እህል አሰባስበው ለማሰራጨት ጥረት ማድረጋቸውንም አስረድተዋል።

ከየአካባቢው ህዝብ ቀጥሎ መንግስትና ረጂ ድርጅቶች በቆሎ፣ ስንዴ፣ ሩዝና ዱቄት በተፈናቃዮች የቤተሰብ ብዛት መጠን እያከፋፈሉ መሆኑ ተገልጿል። አልሚ ምግብ ለእናቶችና ሕፃናት፣ እንዲሁም የምግብ ማጣፈጫ ስርጭቱ ሁሉንም ያዳረሰ ባይሆንም ለማቅረብ ተሞክሯል።

በአሁኑ ወቅትም በበቂ ሁኔታ እየተከፋፈለ ነው። ከተለያዩ አካላት በእርዳታ የተለገሰ ገንዘብንም ለተፈናቃዮች ለማከፋፈል የተሞከረባቸውን ዞኖች መኖራቸውም ተገልጿል። በከተማ አካባቢ አንድ ላይ በሰፈሩባቸው መጠለያ ቦታዎች ጥሬ የምግብ እህል ከማከፋፈል ይልቅ፣ በተሻለ ሁኔታ ምግብ በጋራ አንድ ቦታ ላይ እንዲበስል በማድረግ ለማከፋፈል ጥረት ተደርጓል።

በሌላ በኩልም የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ተፈናቃዮች ያሉባቸው መጠለያ ጣቢያዎች ላይ ተፈናቃዮች በምግብ አቅርቦቱና አጠቃላይ አያያዛቸው ብዙ ችግር እንደሌለባቸው፣ ለሕፃናትና ለወለዱ እናቶች አልሚ ምግብ እንደሚቀርብላቸውና ምግብ አንድ ቦታ ተዘጋጅቶ እንደሚቀርብላቸው በምሥጋና ያስረዳሉ።

በጥቅሉ መንግስት በግጭት ለተፈናቀሉ ወገኖች በቂ ድጋፍ እያደረገ ነው። የፌዴራል መንግስት ቀደም ሲል 800 ሚሊዮን ብር በመመደብ ለአስቸኳይ ጊዜ ርዳታ አውሏል። ኋላ ላይም ለዘላቂ ማቋቋሚያ የሚሆን ተጨማሪ 900 ሚሊዮን ብር መድቧል። ወደፊትም ይህ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል። ይህ እውነታ የሚያሳየውም ነር ቢኖር፤ መንግስት ምን ያህል ለዜጎቹ የሚያስብ መሆኑን ነው። ህዝባዊነቱንም የሚያሳይ ነው።

የኢፌዴሪ መንግስት ህዝባዊ በመሆኑ ከሁሉም በላይ ለዜጎቹ ችግር ፈጥኖ ደራሽ ነው። ይህ ሁኔታም በዜጎች ላይ ችግር በተፈጠረ ቁጥር በሀገር ውሰጥም ይሁን በባህር ማዶ እየተገኘ ፈጣን ምላሽ በመስጠትና ተገቢውን ርምጃ መውሰዱ ለህዝቡ የሚሰጠው ከፍተኛ ክብር ምን ያህል እንደሆነ ያሳያል።

መንግስት ሁሌም እንዲህ ዓይነቱን ተግባር የሚያከናውነው መነሻውም ይሁን መድረሻው ከሚከተለው ህዝባዊ ወገንተኝነት የመነጨ ነው። በሀገር ውስጥ ዜጎቹ በድርቅ ሳቢያ ሲጠቁ፣ በባዕድ ሀገር ውስጥ በህገ ወጥነት ሲፈረጁ የከፋ ችግር ላይ ሳይወድቁ ቀድሞ የደረሰ የህዝብ አጋር ነው።

ይህ የኢትዮጵያ መንግስት ለዜጎቹ ፈጥኖ የመድረስ ማንነታዊ መገለጫ ዛሬ የተጀመረ አይደለም። ከአፈጣጠሩ ጀምሮ የነበረ ባህሪው ነው። የሚለወጥ አይደለም። የኢትዮጵያ መንግስት እንኳንስ ዛሬ የተሻለ አቅም እያለው ቀርቶ፤ ይህን ያህል ያልዳበረ አቅም ባልነበረው ጊዜም እንኳን ከሁሉም በፊት ለዜጎቹ ቅድሚያ ይሰጥ የነበረ መንግስት ነው።

ከዛሬ ዘጠኝና አስር ዓመት በፊት ወደ 14 ሚሊዩን ህዝብ በተፈጥሮ የድርቅ አደጋ ሲጎዳና ለጋሽ ሀገራት እጃቸውን አጣጥፈው በተመለከቱን ወቅት እንኳን መንግስት ባለው አቅም አንድም ለረሃብ አደጋ ሳይጋለጥ ለመታደግ መቻሉን እናስታውሳለን። ዜጎቻችን በሳዑዲ አረቢያ ውስጥ በህገ ወጥነት ሲፈረጁ የተኛውም መንግስት ባላደረገው መንገድ ፈጥኖ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴዎችን በመፈፀምና ችግር እንዳይደርስባቸው ከሀገሪቱ ባለስልጣናት ጋር በመነጋገር የጊዜ ገዶቦች በተደጋጋሚ ማስረዘሙም ሌላኛው መገለጫዎቹ ናቸው። እነዚህን ሁኔታዎች በእግረ መንገዱ ባነሳቸውም፤ ላለፉት ሁለት ዓመታት በሀገራችን ተከስቶ የነበረውን ችግር እንደሚቀርፈው በገባው ቃል መሰረት የስጋት ደመናዎችን ከትናንት እስከ ዛሬ እየገፈፈ መሆኑን ተደማሪ ማሳያዎች ናቸው ብዬ አስባለሁ።

ርግጥም መንግስት በገባው ቃል መሰረት የስጋት ገመናዎቹ እየተገፈፉ ናቸው። በአሁኑ ወቅት ብሔራዊ የደህንት ምክር ቤት አማካኝነት የሀገርን ሰላምና መረጋጋት የሚያረጋግጡ በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ ነው። የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች፣ የከተማ መስተዳድር ከንቲባዎች፣ የፌደራልና የክልል የፀጥታ ሃይሎች እንዲሁም የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት አዛዦች የሚገኙበትና በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የሚመራው ይህ ምክር ቤት ለሀገሪቱ ይበጃል ያለውን የጋራ ዕቅድ ነድፎ የስጋት ድባቦችን እያስወገደ ነው።

ዕቅዱ ሀገራችን ለአንድ ዓመት የምትመራበት ወጥ የሰላምና የፀጥታ ሰነድ ሲሆን፤ አሁን ያለውን የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ የወጣ ነው። ምንም እንኳን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተነሳ በኋላ እጅግ ጥቂት በሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች በስተቀር የሀገራችን ሰላምና መረጋጋቱ አስተማማኝ ሊባል የሚችል ቢሆንም፤ በምክር ቤቱ የተተለመውን ዕቅድ ገቢራዊ ለማድረግ ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ድረስ የሰላምና መረጋጋት ስራው እየተከናወነ ነው። ይህም የሀገሪቱን ብሔራዊ ደህንነት አመጣጣቸው ሊታይ ከሚችል አደጋዎችና ፈተናዎች በመጠበቅ ረገድ ዋስትና ሆኗል ማለት ይቻላል።

ርግጥ የሀገራችን የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ግንባታ ጉዞ እንዳይደናቀፍ የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤቱ ያዘጋጀው ዕቅድ ተገቢና ወቅታዊ መሆኑ አያጠያይቅም። ምክንያቱም እንደ እኛ ያለ በሁሉም መስኮች በአፍላ ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ የሚገኝ ሀገር በተለያዩ ሰንካላ አስተሳሰቦች ምክንያት ልማቱ መደናቀፍ ስለማይኖርበት ነው።

በሀገሪቱ ውስጥ በሚገኝ ትንሽ ቦታም ቢሆን የሚከሰቱ አላስፈላጊ ንትርኮችና የሰላም እጦቶች፤ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እውን ለማድረግ የሚሹትን የልማት ዕድገት በመጎተት አሉታዊ ሚና መጫወታቸው የሚቀር አይሆንም።

እነዚህን አሉታዊ ተግባሮች በመቀነስ ብሎም ከነጭራሹ በማጥፋት ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት እየሰሩ ያሉት የፀጥታ ሃይሎች ከየአካባቢው ህዝብ፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከአባገዳዎችና ከምሁራን ጋር በመሆን ጥሩ ውጤት እያመጡ ነው። ይህ የስጋት ደመናን የመግፈፍ ተግባራቸውን ከህዝቡ ጋር እጅና ጓንት ሆነው እየፈፀሙ ደመናዎቹን በሰላም ብራ አየር እንደሚቀይሯቸው ከወዲሁ መናገር የሚቻል ይመስለኛል። ምክንያቱም መንግስት ዛሬም እንደ ትናንቱ ለህዝቡ የገባውን ቃል የማያጥፍ ስለሆነ ነው።

  

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy