Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

እድገታችን ሳንካ እንዳይገጥመው…

0 305

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

እድገታችን ሳንካ እንዳይገጥመው…

                                                     ደስታ ኃይሉ

የአገራችን የግብርና ዘርፍ የዕድገታችን መሰረት ነው። ችግር ቀራፊም ጭምር። ዘንድሮ ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀው ከፍተኛ ምርት በድርቅና ባለመረጋጋት ሳቢያ ሊፈጠር የሚችለውን መስተጓጎል የሚያስቀር ነው። የመኸር ምርቱ ማደግ በአንድ በኩል እንደ ብክነትና ድርቅን የመሳሰሉ ተግዳሮቶችን መመከት የሚችል፣ በሌላ በኩልም የአገራችን ዕድገት ያለ አንዳች ሳንካ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያደርግ መሆኑ ግልፅ ነው። በመሆኑም ባለ ድርሻ አካላት ተግዳሮቶችን በመፍታት እድገታችን ሳንካ እንዳይገጥመው ይበልጥ መትጋት የሚጠበቅበባቸው ይመስለኛል።

በአሁኑ ወቅት የአገራችን ዕድገት ምሶሶ የሆነው ግብርና በምግብ ሰብል ራሳችንን እንድንችል ከማድረግ ባሻገር፤ የስራ ዕድልን በመፍጠር ረገድም ጉልህ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል። የአገራችንን ኢኮኖሚ ትርጉም ባለው ደረጃ ለማሳደግና ህዝባችንን ከድህነት ለማውጣት ለግብርናው ዘርፍ ትኩረት መስጠት የግድ ይላል።

መንግሥት ግብርናውን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር አማራጭ የሌለው መፍትሔ መሆኑን ተገንዝቦ ሲሰራ ቆይቷል። በያዝነው ሁለተኛው የልማት ዕቅድ ላይም ቀደም ባሉት የልማት ዓመታት የተገኘውን አመርቂ ውጤት ይበልጥ አጎልብቶ ለመቀጠል እየተሰራ መሆኑን መረጃዎች ያስረዳሉ።

እንደሚታወቀው ሁሉ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ለእርሻ ሊውል የሚችል ሰፊና ለም መሬት እንዲሁም የአርሶ አደሩ ጉልበት አለ። በአገሪቱ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ታዲያ ይህ ግብርናው ውጭ ከፍተኛ እምቅ ሃብት ነው። ይህ ሃብት ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል እየፈጠረ ሲሆን፤ ገና ምንም ያልተነካ እምቅ በመሆኑም ውጤት ሊያመጣ የሚችል ነው። ሀገሪቱን ለመለወጥ ወሳኙ ሃብት ተደርጎ መወሰዱም እንዲሁ።

በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ኑሮው እንዲሻሻል ተገቢ ትኩረት አግኝቷል። ለዚህም በቂ ማሳያዎችንም ማቅረብ ይቻላል። መንግሥት የዘመናት ቁጭቱን አገራዊ መሠረት ባላቸው አቅጣጫዎች የመፍታት ትግሉን እያካሄደ ነው። አርሶ አደሩ ከራሱ ተርፎ ለገበያ በማምረት ተጠቃሚ የሚሆንበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ፣ ሀገሪቱም ከግብርናው ዘርፍ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ ለማድረግ የሚያስችል የለውጥ ጎዳና ላይ መሆኗን አረጋግጧል።

በአርሶ አደሩ እጅ እንዳለ የሚታሰበው መሬት አነስተኛ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ካለችው መሬት የሚያገኘው ምርት ዝቅተኛ ነው። ይህን መንግሥት በሚገባ በመገንዘቡ ዘርፈ ብዙ የማሻሻል ጥረቶች አድርጓል። በውጤቱም አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮችን ይዞ ለውጥ  ማምጣት አይቻልም የሚለውን አስተሳሰብ መስበር ችሏል።

አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች ትኩረት ከመስጠት ይልቅ ለሰፋፊ እርሻዎች ትኩረት መስጠትና ለውጥ ማምጣትን የሚሰብኩ ወገኖች እንዳሉ ግልጽ ነው። እነዚህ ወገኖች የሚሰብኩት በግብርናው ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ትኩረት የመስጠትን አስፈላጊነት የሚሰብክ ነበር። ይህ ደግሞ ሀገራዊና ህዝባዊ ጥቅም የሚመጣበትን ምስጢር ካለመረዳት ወይም ለመረዳት ካለመፈለግ የመጣ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።

መንግሥት አነስተኛ ይዞታ ላላቸው አርሶ አደሮች ምን ያህል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ በተደጋጋሚ ገልጿል። ይህን የመንግሥትን ፖሊሲ ትክክለኛነት ለማረጋገጥም ተችሏል። የሚታይና አሳማኝ ውጤት ማምጣትም እንደተቻለም ከአርሶ አደሩ በላይ ምስክር የሚያሻው አይመስለኝም።

ምንም እንኳን ለውጡን የማይፈልጉ ኃይሎች ስህተት ፈላጊ ሆነው ቢቀጥሉም፤ በግብርናው ዘርፍ ባመጣነው ለውጥ ብዙዎች በመስማማት ላይ ይገኛሉ። ኢትዮጵያ የአርሶ አደሩን ምርታማነት በማሳደግ፣ ለምርቱ ገበያ በማመቻቸትና ከግሉ ዘርፍ ጋር ትስስር በመፍጠር ምርትና ምርታማነትን አሳድጋ ተጠቃሚ በመሆን ላይ ትገኛለች።

አርሶ አደሩ የለውጥ መስመሩን ተረድቶ በእምነት ወደ ሥራው በመግባቱ በዓመት ሁለቴና ከዚያም በላይ ለማምረት ችሏል። እንዲሁም በከርሰ ምድርና በገጸ -ምድር ያለውን የውኃ ሃብት የመጠቀም ሰፊ ተግባር አከናውኗል።

በውኃ ማሰባሰብና ማቆር፣ የጉድጓድ ውኃን በመጠቀም የወንዝ ውኃን ጠልፎ ጥቅም ላይ በማዋል ብዙ ርቀት ተጉዟል። በመሆኑም አርሶ አደሩ ከራሱ ፍጆታ አልፎ ለከተማው ነዋሪዎች ከፍተኛ ፍላጎት የሆኑትን ምርቶች ማቅረብ ችሏል። ከነዚህ ውስጥ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች በግንባር ቀደምነት ተጠቃሽ ናቸው።

ከዝናብ ጥገኝነት በተላቀቁ አመራረት የተገኙትን ምርቶች መጠቀምም እየተቻለ ነው። የመስኖ ልማት ሥራው በበጋ የበቆሎ እሸት ተመጋቢዎች እንዲሆን አስችሎናል። ባለፉት ሁለት ዓመታት ደግሞ ሥራው ከሁለት እጥፍ በላይ አድጓል።

ለአርሶ አደሩም በዚያው ልክ ገበያው ተመቻችቷል። አርሶ አደሩ በራሱ ባቋቋማቸው የአርሶ አደሮች የህብረት ሥራ አማካይነት ምርቱን ለገበያ በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ ተጠቃሚ መሆን ጀምሯል። በዚህም ተጠቃሚነቱን እያረጋገጠ ነው።

ያም ሆኖ በያዝነው ዓመት የሚሰበሰበው የመኸር ምርት በውጤታማ መንገድ ያለ ብክነት እንዲሰበሰብ ማድረግ ይገባል። ለዚህ ደግሞ አርሶ አደሩን ጨምሮ ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ርብርብ ማድረግ አለባቸው።

እንደሚታወቀው ሁሉ በድህረ- ምርት አያያዝና አጠባበቅ ጉድለት የተነሳ አርሶ አደሩ በዓመት አንድ ሶስተኛው የግብርና ምርታችን እንደሚባክን ተረጋግጧል። መባከን ብቻም ሳይሆን በአጨዳ፣ በመሰብሰብ፣ በመውቃት፣ በማበራየት፣ በመጓጓዝና በማከማቸት የማምረት ሂደት ወቅት የምርት ጥራት በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል። ምርት በወቅቱ ባለመታጨዱ ምክንያትም ጊዜውን ባልጠበቀ ዝናብ ተበላሽቶ ለብክነትና ለጥራት መጓደል የሚጋለጥበት ሁኔታም መኖሩ ይታወቃል።

ይህ ሁኔታም አርሶ አደሩ ዓመቱን ሙሉ ከለፋበት ምርት እንዳይጠቀም የሚያደረግ ነው። ምርት ለብክነት ከተጋለጠና ጥራቱም ካሽቆለቆለ ተገቢውን ዋጋ ሊያስገኝ አይችልም። አንድ የምርት ዓይነት ሲታጨድ፣ ሲወቃና ሲበራይ እንዲሁም ሲጓጓዝና ሲከማች የሚባክን ከሆነ ከብዛት ሊገኝ የሚችል ጥቅም አይኖርም።

በእነዚህ የምርት ሂደቶች ወቅትም አመራረቱ ተገቢ ላልሆነ የጥራት ችግር ከተጋለጠ ከምርቱ አግባብ የሆነ ገቢን ማግኘት አይቻልም። እንደሚታወቀው በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሩ ምርቱን የሚሰበስብብበት ነው። እናም ምርቱ ለብክነትና ለጥራት ማነስ እንዳይጋለጥ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል። ማሳ ላይ የሚገኝ ምርት የአርሶ አደሩ የላብ ውጤት ነው።

አርሶ አደሩ ዓመቱን ሙሉ የተለያዩ ግብዓቶችን ተጠቅሞ እዚህ ደረጃ ያደረሰው ሰብል በስተመጨረሻው ለብክነትና ለጥራት መጓደል ችግር መጋለጥ የለበትም። የላቡን ፍሬ በሚያገኝበት በአሁኑ ወቅት በተግዳሮቶች ሳቢያ ከምርቱ ተጠቃሚ ሳይሆን መቅረት የለበትም። በመሆኑም ግብርና የአገራችን የእድገታችን ምሶሶ እንደመሆኑ መጠን፤ የምርት ብክነትን ለመከላከል ሁሉም የበኩሉን አስተዋፅኦ ማበርከት አለበት።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy