Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ከሃይማኖት አባቶች ምን እንጠብቅ?

0 798

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከሃይማኖት አባቶች ምን እንጠብቅ?

                                                      ቶሎሳ ኡርጌሳ

በሀገራችን ሁሉም እምነቶች ውስጥ የሃይማኖት አባቶች ህብረተሰብን በመልካም ስብዕና የሚያንፁ ናቸው። እነዚህ አባቶች በተከታዩቻቸው ዘንድ ተሰሚነት ያላቸው እንደ መሆናቸው መጠን፤ ህብረተሰቡን ስለ ትክክለኛ የምግባር መንገድ የሚያስተምሩ ናቸው። የሃይማኖት አባቶቹ ተልዕኳቸው ሰማያዊውን ፅድቅ ለምዕመናቸው ማስተማር ቢሆንም፤ የሰው ልጅ በምድር ላይ እስካለ ድረስ በፈጣሪው ዘንድ ለሚያገኘው ሰማያዊ ፅድቅ የሚያከናውናቸውን ምድራዊ ተግባራትንም ሊገልፁ ይችላሉ።  

ይህ ማለት ግን የሃይማኖት አባቶች የመንግስትን ስራ ተክተው ሊሰሩ ይገባል እያልኩ አይደለም። በሀገራችን ህገ መንግስት ላይ ሃይማኖትና መንግስት መለያየታቸው በግልፅ ሰፍሯል። መንግስት በሃይማኖት ስራ ውስጥ ጣልቃ አይገባም። ሃይማኖትም በመንግስት ስራ ውስጥ ጣልቃ ሊገባ አይችልም።

ሆኖም ሁለቱም አካላት የሚያገናኛቸው ነጥብ አለ። ይኸውም መንግስትም ይሁን ሃይማኖት ስራቸውን የሚከውኑት ምድር ላይ በመሆኑ ነው። ከዚህ አኳያ ሁለቱ የሚገናኙበት ምድራዊ አሰራር መኖሩ አይቀርም። በአስተዳደርና በተለያዩ ምድራዊ አሰራሮች መገናኘታቸው አይቀርም። እናም ዋናው የሃይማኖትና የመንግስት መለያየት ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ ሳይታለፍ በሚያገናኛቸው ጉዳይ አብረው ሊጓዙ ይችላሉ።

ምናልባትም ስፋትና  ደረጃው ይለያይ እንደሆን እንጂ፤ ሁለቱም  ከሀገራቸው ዜጎች ጋር  አብረው እስከሰሩ ድረስ አንደኛው  ከሌላኛው ጋር መገናኘቱ  የሚቀር  ጉዳይ አይደለም። በሌላ አገላለፅ፣ የመንግስትና የሃይማኖት መለያየት ምስጢር እንደ ሰሜንና ደቡብ  ዋልታዎች ፈፅሞ የማይገናኙ ዓይነት ናቸው ማለት አይቻልም። ‘ለምን?’ ቢባል፤ መንግስት ህዝቦቹን በልማታዊና ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ዙሪያ ለማሰለፍ የመሪነት ሚናውን ሲወጣ፣ ሃይማኖቶች ደግሞ የእምነት ተግባራቸውን ሲያከናውኑ በቀጥታም ይሁን  በተዘዋዋሪ መገናኘታቸው አይቀሬ ስለሆነ ነው። ይህ ግንኙነታቸውም ለአንድ አገር በአንድ ላይ እንዲሰሩ የሚያደርጋቸው ሌላኛው ነጥብ ይመስለኛል።

 

በዚህ መሰረትም የሃይማኖት አባቶች ምዕመኖቻቸው የሚከተሉት ቅዱስ መፅሐፍ በሚፈቅደው መሰረት ስለ ሰላም፣ መቻቻልና አብሮ በጋራ ተካፍሎ ስለመብላት፣ ባለ ፀጋዎች ድሆችን ማገዝ ስላለባቸው ጉዳዩች ተከታዩቻቸውን ሊያስተምሩ ይችላሉ።

ምዕመናን ለሀገራቸው ሰላም መሆን የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ፣ በሀገራቸው ውስጥ ሰላም በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ እንዲስተጓጎል በር የሚከፍቱ ክስተቶችን እንዲቃወሙና የሰላም ዋጋን እንዲገነዘቡ ማድረግ ይችላሉ።

እንዲሁም እርስ በርስ ተከባበሮና ተሳስቦ የመኖርን ጠቀሜታ በማሳወቅ እንዲሁም ከጥላቻና ከቂም በቀል አስተሳሰብ ምንም ዓይነት ሰማያዊ ትርፍ እንደማይገኝ በየእምነታቸው ውስጥ በማስገንዘብ አባታዊ ሃላፊነታቸውን ሊወጡ የሚችሉ ይመስለኛል።

የሃይማኖት አባቶች በምዕመኖቻቸውና በመንግስት መካከል ድልድይ ሆነው የሰላም ሃዋርያነታቸውን መወጣት አለባቸው። ለዚህም ይመስለኛል በቅርቡ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ሱራፌል “ያለ ፍርሃት የጥፋት ኃይሎችን መገሰጽ ከእኛ ይጠበቃል” በማለት የሃይማኖት አባቶች ስለ ሀገራቸው ሰላም መትጋት እንዳለባቸው የገለፁት።

ብፁዕ ካርዲናሉ የሃይማኖት አባቶች የሰላምና የእርቅ መገለጫ በመሆን ኃላፊነታቸውን በሚፈለገው መልኩ መወጣት እንደሚኖርባቸው ማስገንዘባቸውም፤ ሁሉም ሃይማኖቶች ስለ ሰላም እንጂ ስለ ሁከት የማይሰብኩ፣ በምዕመናቸውና በሀገራቸው ሰላም ዙሪያ ፋና ወጊ ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉ ማሳያ ነው ብዬ አምናለሁ።

ርግጥ የሃይማኖት አባቶች በአካባቢያቸውና በሀገር አቀፍ ደረጃ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በማሰማት የህግ የበላይነት እንዲሰፍንና የሰው ልጆች መብት እንዲጠበቅ ያለ ፍርሃት የጥፋት ኃይሎችን መገሰፅ የሚጠበቅባቸው ይመስለኛል። ይህም የምዕመኖቻቸውን መብቶች በማስጠበቅ ከሁከት ርቀው ወደ ሰላም መስመር እንዲመለሱ የሚያደርጋቸው ነው።

የሃይማኖት አባቶች ይህን የሰላም መንገድ ሲያስተምሩ እግረ መንገዳቸውንም በውስጣቸው ሊፈጠር የሚችለውን የሃይማኖት አክራሪነትን አደጋ መዘንጋት የለባቸውም። ሁሉም እምነቶች የሰላምን መንገድ እንጂ የአክራሪነትንና የሁከትን መስመር እንደማይደግፉ እንዲሁም ምዕመናን እንዲህ ዓይነቱን የተሳሳተ መንገድ የሚከተሉ ሌሎች ምዕመናንን ማረቅ እንዳለባቸው ማስገንዘብ ይኖርባቸዋል።

ርግጥ በማንኛውም ዴሞክራሲያዊ ሀገር ውስጥ የእምነት ነፃነትና የሃይማኖት እኩልነት ሳይሸራረፉ ገቢራዊ መሆን ይኖርባቸዋል። ሀገራችን በምትከተለው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥም፤ እነዚህ መብቶች ህገ መንግስታዊ ከለላና ጥበቃ የተሰጣቸው ናቸው።

አንድ ግለሰብ የእምነት ነጻነቱ የሚከበርለት፣ የሁሉም ዜጎች አምልኮአዊ ነፃነት በሚከበርበት ማዕቀፍ  ውስጥ  መሆኑን  በሁሉም እምነቶች ውስጥ ማስተማር ይገባል። የብዙሃኑ መብት ሲከበር እግረ መንገዱን የግለሰቦች ተነፃፃሪ መብቶች እውን መሆናቸው አይቀሬ መሆኑንም ማስረዳት ተገቢ ነው።

የማንኛውም ሰው ሃይማኖታዊ የአምልኮ ነፃነት ሊረጋገጥ የሚችለው፤ የሌሎችን ነፃ አመለካከት የመያዝ ዴሞክራሲያዊ መብት አክብሮ ከመንቀሳቀስ ጋር የሚያያዝ እንደሆነም መግለፅ ያስፈልጋል። የእምነት ነፃነት ከዴሞክራሲያዊ ፋይዳው ባሻገር፣ ሃይማኖታዊ ተቀባይነትና ድጋፍም ያለው በመሆኑ፤ ማንኛውም ሃይማኖት ለምዕመናኑ ሲያስተምር ራሱ የሚከተለውን ቀኖና በማስረፅ  እንጂ፤ ‘የሌሎች እምነት የተሳሳተ ነው’ በሚል  አካሄድ  መሆን የለበትም።

አንድ ሃይማኖት ራሱ የሚከተለውን ስርዓተ እምነት ከመስበክ ባለፈ፤ ‘ከእኔ ውጪ ያሉት ሃይማኖተ መከተል ያለባቸው መመሪያ ይህ ነው’ የሚል አቅጣጫን ሊከተል የሚገባው አይመስለኝም። ለዚህም ይመስለኛል— ማንኛውም ዜጋ ‘ትክክል ነው’ ብሎ የሚያምንበትን አምልኮ የማመን ነፃነት እንዳለው በሃይማኖት አባቶች በስፋት ሲነገር የምናደምጠው።  ይህ እውነታም የአንዱ ሃይማኖታዊ ነፃነት መታፈን፤ የሌላኛውም በተመሳሳይ ሁኔታ  እክል እንደሚገጥመው አስረጅ የሚሆን ይመስለኛል።

የሃይማኖት አባቶች የሰላም እጦት አንዱ መነሻ የሆነውን አክራሪነትን ለመዋጋት የእምነት  እኩልነትን ፅንሰ ሃሳብን ማስረፅ የሚጠበቅባቸው ይመስለኛል። በሀገራችን ውስጥ ሁሉም ዜጎች እኩል ናቸው። የሚያከናውኑት ማናቸውም ተግባራት ተበላልጠው የሚታዩ አይደሉም።

አንድ ግለሰብ የሚከተለው እምነት ከሌላው  የሚበልጥም ሆነ የሚያንስ ሊሆን አይችልም። ይህም ሁሉም እምነቶች እኩል መሆናቸውን የሚያስገነዝበን ሃቅ ነው። እናም አንዱ ሃይማኖት ያለውን መብት ሌሎችም እንዳላቸው ማስረዳትና ማስገንዘብ ከሃይማኖት አባቶች የሚጠበቀው ሌላኛው ዘውግ ነው። ይህን ሲያደርጉ ለሰላም እጦት አንዱ መነሻ ሊሆን የሚችለውን የሃይማኖት የአክራሪነት አስተሳሰብን እነርሱ ታግለው ምዕመኖቻቸውም እንዲታገሉት ማድረግ የሚችሉ ይመስለኛል።  

እናም መንግስትና ሃይማኖት ቢለያዩም፤ የሃይማኖት አባቶች ምዕመኖቻቸው ያሉት በምድር ላይ እስከሆነ ድረስ በሚገናኙባቸውና የየእምነቱ ቀኖና በሚያዘው መሰረት አብረው መስራት ይኖርባቸዋል።

በእኔ እሳቤ ምዕመናን ሰላምና ደህንነታቸውን የሚያስጠብቁላቸው ሁለት መጠለያዎች አሏቸው። አንደኛው፤ ምድራዊውን ተግባር የሚመራው ምድራዊ መንግስት ሲሆን፤ ሁለተኛው ሰማያዊ ፅድቅን የሚያስገኝላቸው የእግዚሐብሔር መንግስት ነው። የሃይማኖት አባቶች እነዚህን ሁኔታዎች በማቻቻል ምዕመናንን ወደ ትክከለኛው የሰላም፣ የመተጋገዝና የመተሳሰብ እንዲሁም የእርቅ ማዕከል ሆነው የሸምጋይነት ሚናቸውን መወጣት የሚጠበቅባቸው ይመስለኛል።    

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy