ከመግለጫው በስተጀርባ
ዳዊት ምትኩ
የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዩች ጽሀፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ በቅርቡ አንድ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተው ነበር። መግለጫቸው የኢህአዴግ ስራ አሰፈፃሚ ኮሚቴ አመራሮች መግለጫ ላይ የሚነሱ የተሳሳቱ አስተሳሰቦችን የሚያርም ነው። አራቱ የፓርቲው አመራሮች እንደ መሪ ድርጅት በጋራ የሰጡት መግለጫ አንዱ የሌላውን የሚደግፍ እንጂ የተለያየ ሃሳብ የቀረበበት አለመሆኑን ሚኒስትሩ መግለፃቸውን አስታውሳለሁ።
የኢህአዴግ አመራሮች መግለጫው ትኩረት ህዝብን እንጂ ግለሰቦችን ለማጀገን የተዘጋጀ አይደለም። ይልቁንም ኢህአዴግ እንደ ድርጅት ችግሩን አምኖ በመቀበል ህዝቡን ለመካስ መዘጋጀቱን ያስታወቀበት ነው። ይህም የኢህአዴግ ሁሌም ሲሳሳት ተሳስቻለሁ የሚል አሰራር ያለውና ህዝቡንም ለመካስ ቁርጠኛ መሆኑን የሚያሳይ ይመስለኛል።
በአሁኑ ወቅትም በድርጅቶቹ የተሰጠው መግለጫ ተግባራዊ በመሆን ላይ ይገኛል። ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው መንግስት እስረኞችን መልቀቅ መጀመሩ ነው። ዳሩ ግን እስረኞቹ የሚለቀቁት ፖለቲከኛ ወይም ጋዜጠኛ ወይም የሌላ ሙያ ባለቤት ስለሆኑ አይደለም።
ኢትዮጵያ ውስጥ በፖለቲከኝነቱ ብቻ የታሰረ ግለሰብ ለመኖሩ ማስረጃ ማቅረብ የሚቻል አይመስለኝም። ግና ክርክሩ ‘አንድ ሰው ፖለቲከኛ ስለሆነ ወንጀል ቢፈፅምም መታሰር የለበትም’ የሚል ክርክር የትኛውንም ወገን የሚያስማማ አይመስለኝም። ምክንያቱም በየትኛውም ሀገር ውስጥ በዴሞክራሲያዊ አግባብ የተመረጠ መንግስት ከህዝብ በተሰጠው አደራ መሰረት የህግ የበላይነትን የማስከበር ኃላፊነትና ግዴታ ሰላለበት ነው።
እናም በተቃዋሚነት የተሰለፈም ይሁን ማንኛውም የመንግስት ባለስልጣን በወንጀል እስከ ተጠረጠረ ድረስ በህግ ጥላ ስር ውሎ ጉዳዩ መጣራቱ የሚቀር አይመስለኝም። በነፃው ፍርድ ቤት ተፈርዶበት በማረሚያ ቤት ሊቆይ ይችላል።
በዚህ ረገድ መንግስት ምን ያህል ቁርጠኛ እንደሆነ በቅርቡ በተለያዩ ክልሎችና ከተማዎች የህዝብን አደራ ወደ ጎን በማለት በሙስና እና በኪራይ ሰብሳቢነት በተዘፈቁ አመራሮችና በየደረጃው በሚገኙ አስፈፃሚዎች ላይ የወሰደውን አስተማሪ ርምጃ መጥቀሱ ተገቢ ይመስለኛል።
እዚህ ላይ የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ለዜጎች ካጎናፀፋቸው ዴሞክራሲያዊ መብቶች መካከል የቡድንና የግለሰብ መብቶችን መጥቀስ ማንም ሰው በሚከተለው ፖለቲካዊ እምነት ሳቢያ በህግ ጥላ ስር ሊውል እንደማይችል ማረጋገጫ ይመስለኛል። መብቶቹ በዋነኛነት የአመለካከትና ሃሳብን በነጻ የመያዝና የመግለጽ፣ የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነት እንዲሁም አቤቱታን ማቅረብን የሚያጠቃልሉ ናቸው።
እነዚህ መብቶች ሀገራችን ውስጥ ጥበቃ እየተካሄደላቸው ያሉ ብቻ ሳይሆኑ፣ በፖለቲካው ምህዳር ውስጥ በተጨባጭ ገቢራዊ እየሆኑ የመጡም ጭምር ናቸው። እንደሚታወቀው ሁሉ ሰብዓዊ መብቶች ከሰው ልጅ ስብዕና ጋር የተቆራኙና አንድ ሰው፣ ሰው ሆኖ በመፈጠሩ ብቻ የሚጎናጸፈው ተፈጥሯዊ መብቶች ናቸው፡፡
እነዚህ መብቶች የኢትዮጵያ መንግስት ስለፈለገ ለዜጎች የሚሰጡ፣ ሳይፈልግ ደግሞ የሚነፈጉ አይደሉም፡፡ ምክንያቱም በሀገሪቱ ውስጥ የተካሄደው ረጅም ጦርነት መነሻው የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አለመኖር በመሆኑና ይህ የሀገራችን ህዝቦች የዘመናት ጥያቄ በአሁኑ ወቅት በቂ ምላሽ በማግኘቱ ነው፡፡
ይሁንና አንዳንድ ወገኖች ላለፉት 25 ዓመታት እዚህ ሀገር ውስጥ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንደሌሉ ለመቁጠር ይዳዳቸዋል። አብዛኛዎቹ የሀገራችንን ሰላም ለማጎልበት፣ ልማታችንን ከኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባር ለመታደግ እንዲሁም ዴሞክራሲን ለማጠናከር የሚወጡ ህጎችን በማጣቀስ፤ ‘እነ እገሌ ጋዜጠኞች በመሆናቸውና ሃሳባቸውን በመግለፃቸው ብቻ ለእስር ተዳረጉ፣ የመደራጀት መብት ጠቧል፣ የፖለቲካ እስረኞች ተበራክተዋል፣ የሃይማኖት ነፃነት የለም…ወዘተ’ የሚሉ ክርክሮችን ሲያነሱ ይስተዋላሉ። ይህ አስተሳሰብ ትክክለኛ አይደለም።
እኔ እስከማውቀው ድረስ በፃፈው ፅሑፍ ወይም ሃሳቡን በነፃነት በመግለፁ ብቻ ለእስር የተዳረገ ሰው ያለ አይመስለኝም። በህግ ጥላ ስር የዋሉት ጋዜጠኝነትን በሽፋንነት በመጠቀም ከሀገሪቱ ህግ ውጪ ወንጀል የፈፀሙ ግለሰቦች ናቸው። ወንጀለኛ ደግሞ ጋዜጠኛም ሆነ ፖለቲከኛ፣ ቀዳሽም ሆነ ተኳሽ…በየትኛውም ሀገር በህግ አግባብ መጠየቁ አይቀርም።
እርግጥ የሀገሪቱን የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅንና ሌሎች ህጎችን አክብረው ሃሳባቸውን በነጻነት የሚያንጸባርቁ በርካታ የመገናኛ ብዙሃን የመፈጠራቸውን ያህል፤ ሀገሪቱን ለመበታተንና አንዱን ብሔር ከሌላው ጋር ለማጋጨት ይሰሩ የነበሩ መገናኛ ብዙሃን እንደነበሩ የሚካድ አይመስለኝም።
ይህም ሚዲያው ራሱ የሚከተለውን ሙያዊ ስነ-ምግባር ከመጣሱም በላይ፤ በተለያዩ ውስጣዊ ፍላጎቶቹ ሳቢያ የሀገሪቱን ህጎች አክብሮ ካለመስራት የመነጨ መሆኑ ከማንም የሚሰወር አይመስለኝም። እናም ሚዲያው ነጻና ጤናማ ሆኖ መስራት ሲገባው፤ በአንድ ሀገር ውስጥ የወጡ ህጎችን የሚፃረሩ ተግባራትን ከፈፀመ እንደማንኛውም ተቋም ከተጠያቂነት ሊያመልጥ የሚችል አይመስለኝም።
እንደ እውነቱ ከሆነ የኢፌዴሪ መንግስት በህገ-መንግስቱ ላይ በግልፅ የተደነገጉት ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብቶች እውን እንዲሆኑ ከመታገሉም በላይ፣ እንዳይሸራረፉም በፅናት ታግሎላቸዋል፤ እየታገለላቸውም ነው።
በተለይም ሚዲያ በሀገሪቱ የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ እመርታዎች ላይ የራሱን እሴት የሚጨምር መሳሪያ አድርጎ ነው የሚመለከተው፡፡ ይሁንና ሚዲያ ህግና ስርዓትን አክብሮ ካልተንቀሳቀሰ ከጠቀሜታው ባሻገር፤ በሁለንተናዊ የዕድገትና የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዓላማዎች ላይ ጉዳት ሊያደረስ እንደሚችልም እስካሁን ከታዩት ዝንባሌዎች የተረዳ ይመስለኛል።
እርግጥ በእኔ ዕይታ መንግስት የሚዲያን ጉዳት ለማስቀረት ሲል ጥቅሙን የመገደብ አካሄድ የሚከተል አይመስለኝም፡፡ እንደ ሌሎቹ የዴሞክራሲ ግንባታ ስራዎች ሁሉ፤ ሚዲያው ነፃና ጤነኛ ሆኖ እንዲያድግ ፈርጀ ብዙ ተግባራትን ማከናወኑንም ማጤን ያስፈልጋል፡፡
የቅርብ ጊዜውን ትውስታ ብናነሳ እንኳን ሚዲያ ለሀገራችን የዴሞክራሲ ግንባታ ጤነኛ በሆነ አኳኋን ሙያዊ ሃላፊነቱን እንዲወጣ የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ ማውጣቱን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በቅርቡ የመገናኛ ብዙሃን መማክርት ምክር ቤት በጋዜጠኞችና በአሳታሚዎች ሲቋቋም ድጋፉን የገለፀውም ከዚሁ ዕውነታ በመነሳት ይመስለኛል።
ታዲያ መንግስት ሚዲያው ነፃና ጤነኛ በሆነ አኳኋን እንዲያድግና እንዲመነደግ የሚያደርጉ ስራዎችን የሚፈፀመው ለማንም ብሎ አይመስለኝም። ምክንያቱም ተግባሩን የሚከውነው ከባህሪው በመነጨ፣ በሀገራችን ውስጥ በመገንባት ላይ የሚገኘው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲያብብና ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ካለው ፅኑ ፍላጎት ተነስቶ መሆኑን ሁሌም ሲገልፅ ስለምንሰማው ነው። ይህ ሃቅ የኢህአዴግ አመራሮችም በመግለጫቸው ላይ ያነሷቸው ዴሞክራሲያዊው ስርዓት እንዲያብብና እንዲጎለብት ብሎም አገራዊ መግባባቱ እንዲጨምር ከማሰብ በመነጨ እስረኞችን መልቀቅ መጀመራቸውን የሚያሳይ ነው።