Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

“ከማክበር ባለፈም እንድናምነው ይፈልጋል”

0 398

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አቶ ልደቱ አያሌው ትውልድና ዕድገታቸው ወሎ ላሊበላ አካባበቢ ነው፤ እስከ 12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ያጠናቀቁትም በዚያው በላሊበላ ነው:: የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በታሪክ፣ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን በፖለቲካል ሳይንስና ዓለማቀፍ ግንኙነት ሁለቱንም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በደቨሎፕመንት ስተዲስ ደግሞ ሌላ የሁለተኛ ዲግሪ ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ለንደን ተከታትለዋል::

አብዛኛውን የሥራ ዘመናቸውን ያሳለፉት በተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ በንቃት በመሳተፍ ነው:: ጎን ለጎንም በአስመጭ የንግድ ዘርፍና በማማከር አገልግሎትም በግላቸው ሠርተዋል:: በዚህ ወቅትም ከፖለቲካ ተሳትፏቸው ጎን ለጎን በሪልስቴት ዘርፍ ተሠማርተዋል:: አቶ ልደቱ በፖለቲካው ዘርፍ ጎልተው የወጡት በ1997 ዓ.ም የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት በሚሰነዝሯቸው ጠንካራ ትችቶች ነበር፤ ከዚያ በኋላም ፖለቲካዊ አመለካከቶቻቸውንና የ97ን ምርጫ ሂደትና ውጤት ከሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ጋር በማያያዝ በመጽሐፍ መልክ አሳትመው ለአድናቂዎቻቸው አበርክተዋል:: ዛሬ ደግሞ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የበኩር እንግዳችን አድርገናቸዋል፤ መልካም ንባብ!

በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች ብሔርን መሠረት ያደረጉ የሚመስሉ ግጭቶች ታይተዋል፤ ምክንያታቸው በእርስዎ ዕይታ ምንድን ነው?
በገዥው ፓርቲ በኩል የሚጠቀሰው የመልካም አስተዳደር ዕጦትም በተቃዋሚዎች የሚነሳው የዴሞክራሲ ዕርዛትና የብሔር ተኮር ፖለቲካ ጉዳይም ምክንያቶች ናቸው:: ከእነዚህም በላይ ተጨማሪ ምክንያት አለው:: ችግሩ የሚጀምረው ከሕግ ነው፤ ሀገሪቱ የምትመራበት ሕገ-መንግሥት በውስጡ የያዛቸው ጉዳዮች የሀገሪቱን አንድነት የሚያጠናክሩ አይደሉም:: በሒደት ወደ መዳከም፣ መለያየት፣ መከፋፈል የሚያመሩ ናቸው:: ከሕገ-መንግሥቱ ቀጥለው የመጡ አዋጆች፣ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችም ከሕገ-መንግሥቱ ስለሚቀዱ የተሻሉ ሊሆኑ አይችሉም:: ስለዚህ አንደኛው የብጥብጡ መነሻ የሕግ ጉዳይ ነው እላለሁ::

ሁለተኛው ምክንያት አደረጃጀት ነው፤ አደረጃጀት ስንል በፓርቲዎች ውስጥ ያለውንና ፌዴራሊዝሙን ነው:: በፓርቲዎች መካከል ያለውን አደረጃጀት ብንመለከተው ገዥው ፓርቲ እራሱን ያደራጀው በብሔር ማንነት ነው:: በብሔራዊ ማንነት የተደራጀ ፓርቲ ምንጊዜም ወደ ተሻለ አንድነትና መቀራረብ ሊመጣ አይችልም:: በሂደት ተገቢ ወዳልሆነ ፉክክር ነው የሚሄደው፤ ለዚህም ነው በኢሕአዴግ ውስጥ ያሉ ድርጅቶች ጊዜ ባገኙ ቁጥር እየተራራቁ የሄዱት:: ለምሳሌ በኢሕአዴግ አራት ድርጅቶች (ሕወኃት፣ ብአዴን፣ ኦሕዴድና ደኢሕዴን) መካከል ምንም ዓይነት ልዩነት እንዳለ ሰምተን አናውቅም ነበር:: በሂደት ግን ግንኙነታቸው እየተለወጠ፣ በመካከላቸው ጤናማ ያልሆነ ፉክክር እየተፈጠረ ነው የመጣው:: በመጨረሻም የችግሩ አካል ነው የሆኑት:: ስለዚህ በፓርቲዎች ውስጥ ያለው አደረጃጀት በገዥውም በተቃዋሚዎችም ያለው በብሔራዊ ማንነት የተመሠረተ መሆኑ አንዱ የችግሩ ምንጭ ነው:: ብሔራዊ ማንነትን መሠረት አድርጎ የሚፈጠር የፓርቲ አደረጃጀት መጨረሻው ግጭት እንደሚሆን አስቀድሞ የሚታወቅና በብዙ ሀገራት ያጋጠመ ጉዳይ ነው::

የፌዴራሊዝሙ አደረጃጀትም ሌላኛው የችግሩ ምንጭ ነው:: ፌዴራሊዝም ብዝኃነት ላለው ሀገር በጣም አስፈላጊ መሆኑ ሀቅ ነው:: ብዝኃነት ሲባል ግን ኢሕአዴግ እንደሚለው የቋንቋና የሃይማኖት ብዝኃነት ብቻ አይደለም:: የሐሳብ ብዝኃነትም ግምት ውስጥ መግባት አለበት:: ኢትዮጵያ ውስጥ እጅግ ብዙ የሆነ የአስተሳሰብ ልዩነት (ብዙኃነት) አለ፤ ፌዴራሊዝሙ ለዚህም ቦታ ሊሰጠው ይገባል:: ነገር ግን ፌዴራሊዝሙ የተደራጀው እንደ ሕገ-መንግሥቱና እንደ ኢሕአዴግ በብሔር ላይ አተኩሮ ቋንቋን መሠረት አድርጎ ነው:: ስለዚህ እንደ ፓርቲዎቹ ሀገርም በብሔር ተከፋፍሎ ሲደራጅ በሂደት ወደ አላስፈላጊ ፉክክርና ግጭት እንደሚሄድ ይታወቃል:: በዚህም ሀገር ሕልውናዋ አደጋ ላይ ይወድቃል፤ እያየን ያለውም ይህንኑ ነው:: በታሪካችን ሰምተናቸውና ዓይተናቸው የማናውቃቸው የእርስ በእርስ ግጭቶች እየተፈጠሩ ነው:: በቅርቡ በሶማሌና ኦሮሚያ ክልሎች መካከል የተፈጠረው ግጭት የዚህ ውጤት ነው::

ኢሕአዴግ እንደሚለው የመልካም አስተዳደር ጉዳይም አንዱ የችግሩ ምንጭ ነው:: በሕገ-መንግሥቱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት የሚያስችሉ መርሆዎች ቢኖሩም መሬት ላይ የሉም:: በወረቀት ላይ ባሉት ልክ ሕዝቡን ተጠቃሚ አላደረጉም:: በአፈጻጸምም ክፍተት አለ፤ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ የሙስና ጉዳዮች፣ በተለይ የፖለቲካ ሙስና መኖር የግጭቶቹ ዋነኛ መነሻ ነው:: የፖለቲካ ሙስና መኖር ገዥው ፓርቲ ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ያሉ የሕዝብ ምክር ቤቶችን መቶ በመቶ እንዲይዝ አድርጎታል:: ስለዚህ የሕግ፣ የአደረጃጀትና የአፈጻጸም ጉድለቶች የወለዱት ግጭት ነው እየተመለከትን ያለነው::

ኢሕአዴግ ከምርጫ 97 በኋላ የተከተለው አካሄድም አንዱ የችግሩ ምንጭ ነው:: እንደሚታወቀው በወቅቱ ሕዝቡ የመረጣቸው ተቃዋሚዎች ያሸነፉባቸውን ቦታዎች ያለመረከብ ጭቅጭቅ ውስጥ ገቡ፤ ኢሕአዴግም ወዳልሆነ እርምጃ ውስጥ ገባ:: ያንን ተከትሎ ሕዝቡ በተቃዋሚዎች ተስፋ ቆረጠ:: ከዚያ በኋላ ወጣቱ በተለይም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሥራ ለመያዝ የኢሕአዴግ አባል መሆን እንዳለባቸው ስላመኑ አምነውበትም ሳያምኑበትም አባል ሆኑ:: በርካታ የተቃዋሚ አባላት ሁሉ ወደ ኢሕአዴግ አባልነት ተሰገሰጉ:: ወደ ኢሕአዴግ ገብተው በአባልነት ድርሻቸውን ወደ መዝረፍ ገቡ፤ በየጊዜው የመዋቅር ማሻሻያ ቢያደርግም ችግሩን መፍታት አቃተው፤ በሂደትም ከዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ደረሰ::

ከብሔር ጋር የተያያዙ እንቅስቃሴዎች አሁን ለተከሰቱት ችግሮች አስተዋፅዖ አላደረጉም?
በሚገባ እንጅ! ላለፉት 26 ዓመታት ሲሰበክ የነበረው ፕሮፖጋንዳ እኮ ልዩነት ተኮር፣ ብሔርን እንደ ትልቅ አጀንዳ የያዘ ነበር:: የተሰበከው ፕሮፖጋንዳ ለአብሮነት እሴቶች ጀርባውን የሰጠ፣ በአንጻሩ ልዩነትን ጣሪያ ድረስ ሰቅሎ የሚሰብክ ነበር:: እንዲህ ዓይነት ፕሮፖጋንዳዎች በሂደት እንዲህ ዓይነት የሕብረተሰብ ግጭቶችን እንደሚወልዱ ይታወቃል:: አሁን እያየን ያለነው ብሔር ተኮር ግጭት ተኮትኩቶ ያደገው በተሳሳተ የፕሮፖጋንዳ ስልት ነው::
እኔ የብሔር ብሔረሰቦች መብት መከበሩ ተገቢ መሆኑን በሚገባ አምናለሁ፤ ነገር ግን የብሔር ብሔረሰቦች መብት ከሀገር ሕልውና በላይ መሆን አልነበረበትም:: በአፈጻጸምም ጉድለቶች አጋጥመውታል:: ለምሳሌ ክልሎች በሕገ-መንግሥቱ ጠንካራ ነፃነቶች አሏቸው፤ በተግባር ግን በፓርቲ አደረጃጀት ተጠልፎ የክልሎች ስልጣን በመጣሱ አሐዳዊ ሥርዓት እንዲሆን ሆኗል:: አራት ኪሎ ያለው ፓርቲ (ከቤተ መንግሥት ያለው ኢሕአዴግ) የሚያወጣው መመሪያ ነው እስከታች ድረስ የሚሠራው:: ክልሎች የራሳቸውን አንጻራዊ ሁኔታ ገምግመው ከክልላቸው ጋር የሚጣጣም ፖሊሲ ሲተገብሩ አላየንም:: የብዙኃን ፓርቲ፣ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ፣ የዴሞክራሲ ጉዳይ፣ … በሕገ-መንግሥቱ ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል፤ መሬት ላይ ግን አይገኙም፤ ይህም የተሳሳተ የፕሮፖጋንዳ ስልት መነሻም ውጤትም ነው::

ሥርዓቱ የኢትዮጵያንና የሕዝብን አንድነት ትኩረት በመንፈጉ የድሮ ማዕከላዊ ኃይል የምንለው የአሁኑ አማራ ክልልና አብዛኞቹ ከተሞች አካባቢ የሚኖረው እራሱንና ኢትዮጵያዊ ማንነትን ለያይቶ የማያየው ሕብረተሰብ ሥርዓቱን ከልቡ አልተቀበለውም፤ አኩራፊ ሆነና “ይህ ሥርዓት የኔ አይደለም” ብሎ አሰበ:: በዚያ ወቅት እንኳ “ይህ ሥርዓት የኛ ነው፤ ጥያቄያችንን መልሷል” ብለው የሚያምኑት፣ የብሔር ጥያቄ ዋነኛ ጥያቄ እንደሆነ የሚያምኑትና መብታቸው ዕውቅና ያገኘላቸው እንኳ በሂደት በአፈጻጸም ተግባራዊ ሳይሆን ሲቀር የሥርዓቱ ተቀናቃኝ ሆኑ:: በዚህ የተነሳ ሥርዓቱ ከሁለት ያጣ ጎመን ሆነ:: ይህ በመሆኑ ፕሮፓጋንዳው ከሸፈ፤ በአንጻሩ ፕሮፓጋንዳው ግጭቶችን የሕዝብና የመንግሥት አደረጋቸው::

ባለፉት ሁለት ዓመታት በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ያየናቸው ሁኔታዎች ያሳዩን ይህንን ነው:: በፓርቲ የማይመሩ በሕዝብና በመንግሥት መካከል ግጭቶች ተስተውለዋልና:: ኢሕአዴግ አሁንም “የአፈጻጸም ችግር ነው” እያለ ለ25 ዓመታት ሲለው የነበረውን ደጋግሞ እያቀነቀነ ነው፤ የአፈጻጸም ችግር እኮ የሚመጣው የማይፈጸም ፖሊሲ ሲኖርህ ነው፤ መቃኘት ያለበት ከዚያ ጀምሮ ነው:: ለዚህን ያህል ዓመት የአፈጻጸም ችግር አጋጠመው ማለት ደግሞ ፖሊሲው ችግር አለበት የሚለውን የተቃዋሚዎችን ሐሳብ የሚደግፍ ነው:: ችግሩ የሕግና የፖሊሲ ከሆነ ደግሞ በየጊዜው ብትታደስ፣ የመዋቅርና የአመራር ለውጥ ብታመጣ አይስስተካከልም:: መፍትሔው ሕጉን ራሱን ማስተካከል ነው:: ለማስተካከል ጥልቅ የሕዝብ ውይይት ማካሄድ ያስፈልጋል፤ የሕዝብ ውይይቱ በትክክለኛው ሕዝብ መካከል መሆን አለበት:: ችግሩ ኢሕአዴግ የራሱን ሰዎች ሰብስቦ በመመካከር ነው “ከሕዝብ ጋር ተወያየሁ” የሚለው:: ለዚህም ነው በየዓመቱ “እየታደስኩ ነው” የሚለውና ለውጥ የማይመጣው:: መመካከር ያለበት ከትክክለኛው ሕዝብ፣ ከሲቪክ ማኅበራት፣ ከተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ … ጋር ጭምር ነው::

ኢሕአዴግ መቶ በመቶ አሸናፊ እንዲሆን የተቃዋሚ ፓርቲዎች መብዛትና ድምፅ መበተን አስተዋፅዖ አላደረገም?
አንድ ችግር ነው፤ ግን አጠቃላይ የምርጫ ውጤቱን የሚገልፅ አይመስለኝም:: ተቃዋሚዎች እንዲህ የተበታተኑ እንዲሆኑ ትልቁን ሥራ የሚሠራውም እራሱ ኢሕአዴግ ነው:: አንድ ጠንካራ ስብስብ እንዲፈጠር አይፈልግም፤ የተፈጠረ እንኳ ሲመስለው ሌት ተቀን ሠርቶ ያዳክመዋል፤ ይበትነዋል:: በዚህ ዙሪያ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ዓይተናል፤ ከበቂ በላይም ልምድ አለን:: እርግጥ ነው ተቃዋሚዎች ተበታትነው ወደ ምርጫ በገቡ ቁጥር ድምፅ ስለሚበታተን ገዥው ፓርቲ የማሸነፍ ዕድሉ ይጨምራል:: ያም ሆኖ ግን መቶ በመቶ ለማሸነፍ አያስችልም:: በየትኛውም ሀገር ያለ ማንኛውም ፓርቲ መቶ በመቶ አሸንፌያለሁ ካለ ምርምር አያሻውም፤ አጭበርብሯል ማለት ነው::

እንኳንስ እንደኛ ባለ የአስተሳሰብ ብዝኃነት ባለበት ሀገር በጣም በበለፀጉትና የአስተሳሰብ ቅርርብ ባለባቸው ዴሞክራሲያዊ ሀገሮች እንኳ የምርጫ ውጤቶች ከ40 እስከ 60 በመቶ ባሉት ቁጥሮች መካከል ነው:: ከ65 እስከ 70 ከመቶ እንኳ አሸናፊ መሆን የምርጫውን ጤነኛነት አያሳይም:: ስለዚህ የተቃዋሚዎች መብዛት ጥሩ ባይሆንም አሁን ላለው የምርጫ ውጤት ግን ብቸኛው ችግር አይደለም::

የሚደራጁ ፓርቲዎች በሕገ-መንግሥቱ ላይ ተቃውሞ ማሰማት የሚያበዙት ለምንድን ነው?
አንድ ሕግ ስታወጣ ከይዘቱ በፊት በአወጣጥ ሂደቱ ላይ አሳታፊ መሆን አለበት:: የሀገራችን ሕገ-መንግሥት አንዱ መሠረታዊ ችግር አሳታፊ አለመሆኑ ነው:: ኢሕአዴግ የራሱ የሆነ የፖለቲካ ቅርጽና ማኒፌስቶ ነበረው፤ ያንን ማኒፌስቶ ነው ወደ ሕገ-መንግሥትነት የመቀየር አቅጣጫ የተከተለው:: ይህ አካሄድ አንድ አቅጣጫን የሚከተል እንጅ የተለያዩ ሐሳቦች ቀርበው የሚስተናገዱበት ሂደት አልነበረም:: አንድ ሕግ የቱንም ያህል ጥሩ ቢሆን በተገቢው መንገድ አሳታፊ ካልሆነ የተቀባይነት ዕድሉ ዝቅተኛ ነው:: የኛን ሕገ-መንግሥት የገጠመው ጉዳይ ይኼው ነው፤ በረቂቅ ዝግጅቱ ወቅት አሳታፊነት አልነበረውም:: ይህም ተቀባይነት አሳጥቶታል::

ወደ ይዘቱ ስንመጣ ደግሞ መሠረታዊ የሆኑና ለኢትዮጵያ አንድነትና ለኢኮኖሚ ዕድገቷ እንቅፋት የሚሆኑ ብዙ አንቀፆች አሉበት:: ለምሳሌ የእኛን ፓርቲ ኢዴፓን አቋም ብነግርህ ከ106 የሕገ-መንግሥት አንቀፆች መካከል በ25 አንቀፆች ይዘት አንስማማም፤ በአብዛኞቹ አንቀፆች ግን ከሞላ ጎደል እንስማማለን:: ነገር ግን በሕገ-መንግሥት በአንድ መሠረታዊ ጉዳይ ላይም ልዩነት ካለ በጣም አስቸጋሪ ነው:: ዛሬ የምንገኝበት ችግር ዕድለ-ቢስ ስለሆንን ድንገት የገጠመን ሆኖ አይደለም:: ይህ ሊሆን እንደሚችል ደግሞ አብዛኞቻችን ለዓመታት ስንጮህ ኖረናል፤ ያኔ ስንናገር ሁኔታው በተግባር ስላልተፈተነ ተቀባይነት አላገኘንም ነበር:: አሁን ግን ውጤቱ ታይቷል፤ በ26 ዓመታ ጉዞው ያመጣው ውጤት ስንል የኖርነው ነው:: በኢትዮጵያ ታሪክ ተማሪዎች ተቀናጅተው ከሥርዓቱ ጋር ሲጋጩ እንጅ እርስ በእርስ በጎሳ ለይተው ሲጋጩ ሰምተን አናውቅም ነበር:: ዘርን መሠረት ያደረገ ዘረፋ፣ ግድያ፣ ድብደባ ያየነው በሥርዓቱ የአካሄድ ችግር ነው:: ስለዚህ ሥርዓቱ የመጣበት መንገድ ችግር ፈች ሳይሆን አዳዲስ ችግሮችን ወላጅ መሆኑና የሕገ-መንግሥት ማርቀቅ ሂደቱ ችግር፣ ከዚያም አልፎ በርካታ የአፈጻጸም ችግሮች ለፓርቲዎች መብዛት አስተዋፅዖ ያበረከቱ ይመስለኛል::

ከዚህ ችግር ለመውጣት ኢሕአዴግ እንደ ሚካኤል ጎርቫቾቭ ዓይነት መሪ ያስፈልገዋል:: የቀድሞዋ ሶቪዬት ሕብረት ከ70 በላይ ዓመታትን የሶሻሊስት ሥርዓት ያዋጣት መስሏት ወደ ድህነት አረንረቋ ወረደች፤ ከድህነትም አልፎ የሕልውና አደጋ ውስጥ ገባች:: ጎርቫቾቭ መጥቶ በተሀድሶ ዘመቻ ሁሉን ነገር ፈነቃቀለው:: ከዚህ በኋላ “የኮሙኒስት ርዕዮተ ዓለም አያዋጣም፤ አዲስ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ፍልስፍና ያስፈልገናል” ብሎ የአስተሳሰብ ለውጥ አመጣ:: እንደገና ወደ ልዕለ ኃያልነቷም መለሳት:: ኢሕአዴግም እንዲህ ዓይነት መሪ የሚያስፈልገው ወቅት ላይ ነው፤ እንጅ እስከዛሬ ሲያወራው የነበረውን ቀኖና በመደጋገም የተለየ ውጤት መጠበቅ የለበትም፤ አይመጣምም::
ተፎካካሪ ፓርቲዎች በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበን ሕገ-መንግሥቱ እንዲሻሻል ጥረት እያደረግን ነው፤ ሕገ-መንግሥቱን ተቀብለንና አክብረን:: ነገር ግን ኢሕአዴግ ሕገ-መንግሥቱን ከመቀበልና ከማክበር ባለፈም እንድናምነው ይፈልጋል፤ አለማመን ሕገ-መንግሥታዊ መብት ሆኖ ተቀምጦ እያለ::

“ኢሕአዴግ ለብሔር ብሔረሰቦች መብት ዕውቅና ሰጠ፤ ተቃዋሚዎች ደግሞ ኢሕአዴግን ለማስጠላት የተሳሳተ ብሔርተኝነትን ሰበኩ፤ ውጤቱም የምናየው መከፋፈል ሆነ” የሚለውን ሐሳብ እንዴት ያዩታል?
ይኼ በእኔ ዕይታ ሕዝቡን መናቅ ነው፤ ተቃዋሚዎች እኮ በዚህ ወቅት ተጽዕኗቸው ከዚህ ግባ የሚባል አይደለም፤ ከጥቅም ውጭ ተደርገዋል:: ተቃዋሚው የሚመራው ምንም እንቅስቃሴ የለም፤ ይህንን ኢሕአዴግም ያምናል:: ለዚህ እኮ “የራሴ ችግር ነው” ብሎ ለመጀመሪያ ጊዜ እኮ ተቃዋሚዎችን መውቀስ ያቆመበት ደረጃ ላይ ደርሷል:: ኢሕአዴግ በራሱ መንገድ ሄዶ ተቃዋሚዎችን አዳክሞ ሚና የለሽ አድርጓቸዋል:: በእርግጥ ከተቃዋሚዎች ውስጥም ኢሕአዴግ የሚያራምደውን የዘር ፖለቲካ የሚያራምዱ አሉ፤ እነሱ የችግሩ አካል ናቸው ብዬ አምናለሁ:: በተለይ ሕብረ-ብሔራዊ ፓርቲ ሆነን እየታገልን ያለን ፓርቲዎች ግን ከመጀመሪያው አንስተን ስጋታችንን ስንናገር የኖርን ነን:: የተጀመረው የፌዴራል ሥርዓት ሄዶ ሄዶ ከባድ ችግር ውስጥ ይከተናል ስንል ኖረናል:: ስለዚህ ችግሩ እንዲፈታ እንጅ እንዲፈጠር ተቃዋሚዎች ሚና ያለን አይመስለኝም:: ባለፉት 26 ዓመታት ኢሕአዴግ የሠራው ሥራ ሊያመጣ የሚችለው ውጤት ነው የተገኘው::

የሕገ-መንግሥቱ አንድ የጋራ የኢኮኖሚና ፖለቲካ ማኀበረሰብ የመገንባት ራዕይ ሊሳካ ይችላል?
በሕገ-መንግሥቱ መግቢያ ላይ አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መገንባት እንደ ግብ ተቀምጧል፤ በተግባር ግን በሕገ-መንግሥቱ ውስጥ የተካተቱት ጉዳዮች ሐሳቡን ለማሳካት የሚያግዙ አይደሉም:: የፌዴራሊዝም አወቃቀሩ፣ የሚነዛው ልዩነት ላይ ያተኮረ ስብከት፣ … ወደ አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማኅበረሰብነት የሚመራን አይደለም:: ዜግነት እና የሀገር አንድነት በሌለበት አንድ የጋራ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ያለው ማኅበረሰብ መገንባት አዳጋች ነው:: ቡድን ምን ጊዜም በመበላለጥ ላይ ያተኩራል፤ በቁጥር፣ በተፈጥሮ ሀብት፣ ባለው የስልጣን ደረጃ፣ … ይበላለጣል:: በመበላለጥ ተመሥርተህ አንድ የጋራ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መገንባት አትችልም:: በዜጎች መካከል ግን መበላለጥ የለም፤ አንድ ሰው አንድ ድምፅ ብቻ ነው ያለው:: ይህ ሲሆን ነው አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መገንባት የሚቻለው::

አንቀጽ 39 እያለ እንዴት አንድ የጋራ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መገንባት ይቻላል? ገዥው ፓርቲ እኮ ራሱን ያደራጀው በብሔራዊ ማንነት ነው:: በብሔር የተደራጁት የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች እያደሩ ልዩነት እየፈጠሩ እንዴት ሀገራዊ አንድነትን እንጠብቃለን? ባለፉት ዓመታት የተሠራው ሥራም በተግባር የሚያሳያው ልዩነትን በማጉላት አንድ የጋራ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መገንባት እንደማይቻል ነው:: ለምሳሌ ሀገሪቱን የሚመራው ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመረጠው ከአራቱ ብሔራዊ ድርጅቶች ሊቀ-መናብርት አንዱ ነው::

የአንድ ብሔር መሪ እንዲሆን ተኮትኩቶ ያደገ ሰው በምን ሒሳብ ሀገሪቱን በእኩልነት ሊያስተዳድርስ ይችላል? ሌሎችስ “ይህ ሰው በእኩልነት ያስተዳድረናል” ብለው ያምናሉ? አይመስለኝም! በድርጅቶቹ መካከልም እኩልነት ሊኖር አይችለም፤ “እንወክለዋለን” የሚሉት ሕዝብ በቁጥር፣ በክልሉ ባለው ተፈጥሮ ሀብት ስለሚለያይ:: ይህ ደግሞ ሁል ጊዜ “እኔ ነኝ ትልቁ ድርሻ የሚገባኝ!” የሚል ክልል እንዲኖር ያደርጋል:: ኢሕአዴግ ውስጥ በዚህ ወቅት የሚታየው ችግርም ይህ ነው:: በአንድ በኩል ሕወኃት “የዚህ ሥርዓት ዋነኛ ባለቤት እኔ ነኝ፤ ትልቅ መሰዋዕትነት ከፍያለሁና ትልቁ ድርሻ ይገባኛል”ይላል:: በሌላ በኩል ብአዴን “በሀገር አስተዳደር ታሪካዊ ሚና ያለኝ እኔ ነኝ፤ ይህንን ሚና አሁንም እኔ መጫወት አለብኝ” ይላል፤ ኦሕዴድ ደግሞ “ትልቁ ሀብትና ከፍተኛው የሕዝብ ቁጥር ያለው ከእኔ ነውና ትልቁ ድርሻ ይገባኛል” ይላል፤ ታዲያ በዚህ አግባብ እንዴት ሆኖ አንድ የጋራ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ሊገነባ ይችላል? በአስተሳሰብና ሀገራዊ አንድነት ተደራጅተው የብሔር ብሔረሰቦችን መብት የሚያከብሩ ፓርቲዎች ሲኖሩ ብቻ ነው ግቡ ሊሳካ የሚችለው::

“ሕገ-መንግሥቱ ማንነትን በአግባቡ አልመለሰም” ብለው በመጽሐፍዎ ጠቅሰዋል፤ እስኪ ያብራሩት?
በኛ ሕገ-መንግሥት ግለሰባዊ ማንነት በአግባቡ አልተመለሰም፤ ለምሳሌ ከተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ቅልቅል የተወለዱ ሰዎች ማንነት በሕገ-መንግስቱ አልተገለፀም:: አባቱ ከኦሮሞና ትግሬ፣ እናቱ ከአፋርና አማራ የሚወለድ ልጅ ብሔሩ ምንድን ነው? ማንነትን መወሰን ያለበትስ ማን ነው? እኔነት መገለፅ ያለበት በግለሰቡ ነው:: ብሔራዊ ማንነት ሰዎችን አይገልፅም፤ አብረውኝ የሚኖሩና የምቀርባቸው ሰዎችም በዘር ማንነታቸው የምመርጣቸው አይደሉም:: ቋንቋም ማንነትን አይገልፅም፤ የሁለት አማራ ልጆች ነቀምት ተወልዶ አፉን በኦሮሚኛ ሊፈታ ይችላል:: ግን ማንነታችን በሌላ አካል ተወስኖ በመታወቂያችን ላይ ሳይቀር ሰፈረ:: ይህ ስህተት ነው፤ እኔን የምገልፀው እኔ ነኝ:: በተለይ ከተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ወላጆች የተገኙ ሚሊዮኖች የተሰፋላቸው ማንነት ልካቸው አይደለም:: ለዚህ ነው ፓስፖርት ሲያወጣ የግድ አንድ ብሔራዊ ማንነት ለመቀበል የሚገደድ ሰው የበዛው::

ከዚህ ችግር እንዴት ልንወጣ እንችላለን?
ከችግሩ ለመውጣት በጣም ቀላል ነው፤ መቼም በአንድ ሀገር ሕዝብ ላይ የሐሳብ አንድነት የምንጠብቅ አይመስለኝም:: የሐሳብ አንድነት ፈጽሞ ሊኖር አይችልም፤ እንደ መልካችን ሐሳባችንም የተለያየ ነው:: በመልካችን መለያየት እንደማንጋጨው ሁሉ በሐሳባችን መለያየትም ሳንጋጭ የምንኖርበት ሀገር ግን መፍጠር እንችላለን:: ይህንን ማድረግ የምንችለው ሕዝቡ በነፃነትና በፍትሐዊነት መሪዎቹን መምረጥ የሚችልበት ሥርዓት ስንፈጥር ነው::

ኢሕአዴግ የጀመረውን ግምገማ የበለጠ ጥልቀት መስጠት አለበት:: የተፈጠረው ችግር አስተማማኝ መፍትሔ እንዲያገኝ የጠቀስናቸውን ችግሮች ሁሉ በዝርዝር ማየት ከመንግሥት ይጠበቃል፤ ከገመገመም በኋላ ለሕዝብ ውይይት ማቅረብ አለበት:: ሐቀኝነት የተሞላበት ግልፅ ውይይት፤ የካድሬ ውይይትም አይደለም የሚያስፈልገው:: ሕዝቡ በካድሬ ውይይት ተሰላችቷል:: የመገናኛ ብዙኃን በነፃነት ተከታትለው የሚዘግቡት፣ ሕዝቡም በነፃነት የሚናገርበት ውይይት ያስፈልጋል:: ከውይይት በኋላም ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎች እኩል የሚያስተናግዱ ነፃና ገለልተኛ ተቋማት መፈጠር አለባቸው::

ከዚያ በኋላ አሁን በተለያየ ጎራ ያሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ቢፈልጉ ሊዋሐዱ፣ ባሉበት ሊቀጥሉ ወይም የበለጠ ሊበታተኑ ይችላሉ:: ችግር ግን ሊሆኑ አይችሉም፤ የሐሳብ ብዝኃነት የሚያስተናግዱ የዴሞክራሲ ተቋማት እስከተገነቡ ድረስ አሳሳቢ አይሆንም:: ሕዝቡ በነፃና ፍትሐዊ ምርጫ መሪውን ይመርጣል፤ ያልተመረጠው ታማኝ ተቃዋሚ ሆኖ ይቀጥላል:: መፍትሔው ይህ ነው:: የሕዝብ ውይይት ሲደረግ የሚመጣው ውጤት ስልጣን እንኳ የሚያሳጣው ቢሆን በፀጋ መቀበል አለበት:: ይህ ሳይሆን የፈለገው ቢሆን ለውጥ አይመጣም፤ ያለዚህ ደግሞ ለውይይት መቅረብ የለበትም:: ስለዚህ ሕዝቡ በነፃነት የሚመርጥበት፣ በምርጫ ጣቢያው ምንም ዓይነት ተፅዕኖ የማይደርስበት፣ ድምፁ የማይጭበረበርበት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሲደግፍም ሆነ ሲነቅፍ ጥቃት የማይደርስበት መሆኑን ሲያምን ነው ከችግሩ በትክክል መውጣት የምንችለው::

“ኢሕአዴግ ጥልቅና የተለየ ግምግማ አድርጌ መጥቻለሁ” ብሎ መግለጫ ሰጥቷል፤ እንዴት አዩት?
በአሁኑ የኢሕአዴግ ግምገማ አንዳንድ አዳዲስ ነገሮችን ከመግለጫው ተረድቻለሁ:: ከዚህ ቀደም የሚደረደሩ የኢሕአዴግ ሰበቦች ማለትም የመልካም አስተዳደር ችግሮች፣ የሙስናና ብልሹ አሠራር ጉዳዮች፣ የውጭ ኃይሎች የሚልኳቸው ሰዎች የሚፈጥሯቸው ተግባራት እንደነበሩ ነበር የሚገለፀው:: አሁን ግን ችግሩን በጥልቀት አይቶ ሀገራዊ ሕልውናን የሚፈታተን መሆኑን ተረድቶ መምጣቱ የተለየ ያደርገዋል:: ሌላው አዲስ ነገር ደግሞ ሥርዓቱ ራሱን “ኢ-ዴሞክራሲያዊ ነኝ” ብሎ በይፋ ገምግሞ መምጣቱ ነው:: ከዚህ ቀደም እንደ ድርጅት ፀረ-ዴሞክራትነቱን አያምንም ነበር፤ እንዲያውም “የዴሞክራሲ ስነ-ምኅዳሩ እየሰፋ ነው” ብሎ ነበር የሚከራከር:: አሁን ግን ለችግሩ ዕውቅና ሰጥቶ መቀረፍ እንዳለባቸውም አምኗል::
በብሔራዊና በኢትዮጵያዊ ማንነት ግንባታ ዙሪያ ሚዛናዊ ሥራ አለመሠራቱን ማመኑም እንደኔ አዲስ ነገር ነው::፡ እስከዛሬ ሥርዓቱ “አንድነታችን እየተጠናከረ ነው” ሲል ነበር የምናውቀው:: እኛ ለዘመናት ችግሩ እንዳለ ስንለፈልፍ በፍጹም አይቀበለንም ነበር፤ አሁን አካሄዱ ስህተት እንደሆነና ጩኸታችን ተገቢ እንደነበር በመግለጫው ማመኑን ነግሮናል:: እኛ ብሔራዊ መግባባትና ብሔራዊ ዕርቅ የሚሉ ጉዳዮችን ስናነሳ “የተጣላ የለም” ሲለን ነበር የኖረው:: ሥርዓቱ እንደ ሥርዓት በይፋ “ለዚህ ሁሉ ጥፋት ተጠያቂው እኔ ነኝ፤ ለዚህም ሕዝቡን ይቅርታ እጠይቃለሁ” ማለቱ አዲስ የኢሕአዴግ ተግባር ነው:: ትልቅ ድፍረት የሚጠይቅና ተገቢ ነገር ነው:: ስለዚህ በጥያቄህ መሠረት ከመግለጫው ያገኘኋቸው አዳዲስ ነገሮች እነዚህ ናቸው::

ከችግሩ ለመውጣትስ እነዚህ ነገሮች በቂ ናቸው?
አይደሉም! አንዱ መሠረታዊ ጉድለት ከሕገ-መንግሥቱ ጀምሮ ያሉ ሀገራዊ ሕጎች አሉታዊ አስተዋፅዖ ማበርከታቸው አልተዳሰሰም:: ሕግ የሚባለው ጉዳይ ችግር እንዳለበት ሲነሳ የአፈጻጸም ጉድለት ብቻ የወለደው ችግር እንደሆነ ተደርጎ መገምገሙ ስህተት ነው:: ከሀገር አንድነት በላይ ብሔራዊ ማንነትንና መገንጠልን ሕገ-መንግሥታዊ ዕውቅና ሰጥቶ ብሔራዊ አንድነትን የዘነጋ ሕገ-መንግሥታዊ ድንጋጌ እንደ ችግር አለመነሳቱ ስህተት ነው:: አሁን ላለንበት ችግር ያበቃን ሕጋችን ጭምር ነው:: በሕጎቹ ዙሪያ ያሉ ችግሮችን ሳንፈታ ከዚህ የቀውስ አዙሪት የምንወጣ አይመስለኝም:: የኢትዮጵያ ሀገራዊ አንድነት ሕገ-መንግሥታዊ ዋስትና ሊሰጠው ይገባልና::
የአደረጃጀት ክፍተቶችም እንደ ችግር አልተነሱም:: መጀመሪያ አካባቢ ላይ እንደገለፅኩት የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ ብሔርን መሠረት አድርጎ መደራጀቱና ይህም ሕገ-መንግሥታዊ መሆኑ ስህተት ነው:: ብሔርተኝነት ተቋማዊ መደረጉ አልተገመገመም::

ይህም የጥልቅ ተሀድሶው ጉድለት ይመስለኛል:: የፕሮፖጋንዳ ስልቱ ላይም ያሉ ችግሮች አልተገመገሙም:: ባለፉት 25 ዓመታት የኢሕአዴግ ካድሬዎችና የመገናኛ ብዙኃን ሲከተሉት የነበረው ፕሮፖጋንዳ ልዩነት ተኮር ነበር፤ ይህ እንደ ችግር መገምገሙን ከመግለጫው አልተረዳሁም:: ለዛሬው ብጥብጥና መተራመስ ያበቃን ይህ የተዛባ የፕሮፖጋንዳ ስልት ነው:: የሰማሁት ግምገማ “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሕዝብን በሕዝብ ላይ የሚያነሳሱ፣ ክልልን ከክልል የሚያጋጩ …ሚዲያዎች” ተብሎ ነው:: ይህ ግምገማ ያለፉትን የኢሕአዴግ የአገዛዝ ዘመናት የሚዲያ ሁኔታ የሚያሳይ አገላለፅ አይደለም:: የሚዲያ ቅኝቱ ከኢሕአዴግ አፈጣጠር ጋር የተገመደ፣ የብሔርና የሃይማኖት ልዩነት እንጅ የአስተሳሰብ ልዩነት እንደሌለ በጭፍን የሚሰብክ፣ የአስተሳሰብ ልዩነት ካለም እንዲደፈቅ የሚያደርግ ፕሮፖጋንዳ ነበር ሲከተል የኖረው:: ይህ ግን እንደ ችግር አልተገመገመም::

ከመግለጫው እንደተረዳሁትም በመድረኩ አብዛኛው ሰዓት የጠፋው በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል የተፈጠረውን አለመተማመን ለመፍታት ነው:: ይህ ግን የሁለት ዓመታት ዕድሜ ያለው ችግር ነው፤ በሕዝቦች መካከል ግጭትና አለመተማመን ከተፈጠረ ግን ቆይቷል:: የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች እኮ እርስ በእርስ አልተገዳደሉም፤ አልተፈናቀሉም:: የሀገሪቱ ችግር ኢሕአዴግ ውስጥ ካለው ችግር በላይ ነው:: የችግሩን መፍትሔ ሁልጊዜ በኢሕአዴግ ዙሪያ መፈለጉ ተገቢ አይደለም:: ኢሕአዴግ ግንባር ቀደም መሆን ቢኖርበትም ሌሎችም አካላትም መካተት አለባቸው::

የፖለቲካ እስረኞችን ለመፍታት መወሰኑን እንዴት አዩት?
የፖለቲካ እስረኞች መፈታት ለሀገሪቱ ከችግር መውጣት አስተዋፅዖ እንደሚኖረው ተረድቶ ይህንን መግለጫ ማውጣቱ ለእኔ ትልቅ እርምጃ ነው:: በዙሪያው ግን ብዙ ችግሮች አሉት:: የመጀመሪያው ጉድለት ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ እስረኞች ስለመኖራቸው ኢሕአዴግ ዕውቅና አልሰጠም፤ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በጥንቃቄ ሲገልፁ “በራሳቸው ጥፋት የታሠሩ የፖለቲካ ሰዎችና ሌሎችም በምሕረት አዋጁ መሠረት ይፈታሉ” ብለዋል:: የምሕረት አዋጁን መሠረት አድርጎ ጥናት ተደርጎ እንደሚፈቱ ነው የተገለጸው፤ ይህ ተገቢነት ይጎድለዋል:: ሥርዓቱ “በሀገሪቱ የፖለቲካ ችግር ነበር” ብሎ አምኗል፤ “ለዚህ ችግር ዋናው ተጠያቂ እኔ ነኝ” ብሎም አመነ፤ አምኖም ይቅርታ ጠይቋል:: በዚህም መግለጫው በይፋ ባይናገረውም ሥርዓቱን ይቃወሙ የነበሩ አካላትን ትክክለኛነት ነው ያረጋገጠው:: ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ እነዚህን ሰዎች ወንጀለኞች አድርጎ በምሕረት አዋጅ ለመፍታት ማሰብ ተገቢ አይደለም:: እውነት ከችግር ለመውጣት ታስቦ ከሆነ ማናቸውም ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ የታሠሩ ሁሉ ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ መፈታት አለባቸው::

በምሕረት አዋጁ መሠረት ከተባለ ቅድመ ሁኔታ አለ፤ የምሕረት አዋጁ ጥፋትን ማመንና ይቅርታ መጠየቅን እንደ መነሻ ይጠይቃልና:: ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ጥፋተኛነታቸውን አምነው ይቅርታ እንዲጠይቁ ከተደረገ ለሚጠበቀው ፖለቲካዊ መግባባት አስተዋፅዖ የሚያበረክት አይመስለኝም:: ምክንያቱም በምሕረት አዋጁ መሠረት ለመፍታት ከተሞከረ የሚፈቱና የማይፈቱ የፖለቲካ እስረኞች ይኖራሉና:: ከዚህ የፖለቲካ ችግር ለመውጣት፣ የተሻለ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠርና የመደበለ ፓርቲ ስርዓት እንዲጎለብት፣ የሐሳብ ብዝኃነት እንዲኖር ከተፈለገ እስካሁን ድረስ ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ ጉዳይ የታሠሩ ሁሉ መፈታት፤ የፖለቲካ እስረኞች እንደነበሩም መታመን አለበት:: “ለዚህ ሁሉ ችግር ተጠያቂው እኔ ነኝ፤ አጥፍቻለሁና ይቅርታ አድርጉልን!” ያለው ሥርዓት እኮ አልታሠረም፤ በስልጣንም ሊቀጥል ነው:: እንዲያውም ከእርሱ መፍትሔ እየጠበቅን ነው:: ታዲያ ይህንን ሥርዓት የተቃወሙ ሰዎች ስለምን ይታሠራሉ?
መፈታት ያለባቸውም አሁን ባለው ብጥብጥ ምክንያት የታሠሩት ብቻ አይደሉም:: በኦብነግ ምክንያት በሶማሌ ክልል ብዙዎች ታሥረዋል፤ በኦነግ ምክንያት ኦሮሚያ ክልል ብዙ ሺዎች ታስረዋል፣ በግንቦት7፣ አርበኞች ግንባርና በወልቃይት ጉዳይ ብዙዎች በአማራ ክልል ለዓመታት ታሥረዋል:: በራሱ በሠራዊቱ ውስጥ የነበሩ እነጀነራል አሳምነው ሳይቀር በመፈንቅለ መንግሥት ተጠርጥረው ታሥረዋል:: በመገናኛ ብዙኃን የማናውቀዋቸው በየወረዳውና በየዞኑ ብጥብጥና ሁከት እንደፈጠሩ እየተሳበበ የታሠሩ ብዙ ናቸው:: እነዚህ ሁሉ መፈታት አለባቸው:: ከዚያ በኋላ በምርጫ ወደ ስልጣን መውጣትና መውረድ ሲኖር ነው ብሔራዊ መግባባት የሚፈጠረው:: ካልሆነ እራስህ ዴሞክራሲን እያፈንክ ያንን የተቃወሙትን ወንጀለኛ እያልክ ማሠር ተገቢ አይደለም::

ስለመግለጫው ምን ይላሉ?
መግለጫው አሁንም ኢሕአዴግ ከልቡ እንዳልታደሰ የሚያሳይም ጭምር ነበር፤ ከመግለጫ አሰጣጡ የነበረው ሁኔታ ይህን ይመሰክራል:: አራቱ የኢሕአዴግ ድርጅቶች ሊቀመናብርት መግለጫ ሲሰጡ የነበሩት ጋዜጠኞች እኮ ሦስት ብቻ ነበሩ፤ ሁሉም ከመንግሥት መገናኛ ብዙኃንና ማንን ምን መጠየቅ እንዳለባቸው ጭምር ተጽፎ የተሰጣቸው:: የድርጅቶቹ መሪዎችም ማን ምን መናገር እንዳለበት ተወስኖላቸው የመጡ መሆናቸውን ያሳያል:: ሕዝቡ ይህንን አይጠብቅም ነበር::

ጋዜጣዊ መግለጫ ከሆነ አይቀር የመንግሥት፣ የግልና የውጭ ሀገር መገናኛ ብዙኃን ሁሉ መጋበዝ ነበረባቸው:: ተጋብዘውም በነፃነት ጥያቄዎችን ማንሳት ነበረባቸው:: ግን አልሆነም:: የተሀድሶው አንድ አካል መገናኛ ብዙኃንን ነፃ ማድረግንም ማካተት ነበረበት:: ሌላውና መታረም ያለበት ችግር ደግሞ ሰሞኑን በመንግሥት ዙሪያ ያሉ መገናኛ ብዙኃን በየክፍለ ሀገሩ የኢሕአዴግ ደጋፊ የሆኑ ሰዎችን እየጠየቁ “የችግሩ ምንጭ በደንብ ተዳስሷል፤ ዘላቂ መፍትሔ የሚያመጣ ነው፤ ኢሕአዴግ ትክክለኛ አቅጣጫ ይዟል፤ …” የሚሉ ዘገባዎችን እየሠሩ ነው:: ይህ ዓይነቱ የተሰላቸ የዘመቻ ፕሮፖጋንዳ መቅረት አለበት:: ከፕሮፖጋንዳ ሥራ መቅደም አለበት:: ይኸው የፖለቲካ እሥረኞች ይፈታሉ ከተባለ እኮ ሳምንት ሊሆን ነው፤ ግን እስካሁን የተፈታ የለም:: ይህ ነው ፕሮፖጋንዳውን የሚያስጠላው::

ሰፊ ጊዜ ወስደው ለሰጡኝ ማብራሪያ አመሠግናለሁ!
እኔም አመሠግናለሁ!
በአብርሃም በእውቀት ከበኩር ጋዜጣ

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy