ከተሸናፊነት መንገድ እንውጣ
ብ. ነጋሽ
ባለፈው ሳምንት ከሃገሪቱ ሠላምና መረጋጋት ጋር ተያያዥነት ያላቸው ሁለት አበይት ጉዳዮች ተከናውነዋል። አንደኛው የፌዴራልና የክልል ፀጥታ ሃይል አመራሮች የብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት እቅድ አፈፃፀምን መገምገማቸው ነው። ሌላኛው ደግሞ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ሶማሌና በኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች የተቀሰቀሰውን ግጭት እንዲመረምር ያቋቋመው የሱፐርቪዥን ቡድን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሪፖርት አቅርቦ ውይይት መካሄዱ ነው።
የብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት የአንድ ወር አፈጻጸም ሪፖርቱን ከገመገመ በኋላ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር ሲራጅ ፈጌሳ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ባለፈው አንድ ወር የሃገሪቱን ዋና ዋና መንገዶች የመቆጣጠርና የዜጎችን በነጻነት የመንቀሳቀስ መብት የማረጋገጥ ስራ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰው፣ ከዚህ አንጻር የተሰሩ ስራዎችም በአብዛኛው ውጤታማ እንደነበሩም አሳውቀዋል። በተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተቀስቅሶ የነበረው አለመረጋጋትን ከማርገብ አኳያም የፌዴራልና የክልል የፀጥታ ኃይሎች አመርቂ ስራ መስራታቸውን ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማር ሂደቱ ወደ ነበረበት መመለሱን መስክረዋል።
በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልሎች መሃከል ተከስቶ የነበረው ችግርም የፀጥታ አካላት በሰሩት ስራ በአሁኑ ወቅት አንጻራዊ መረጋጋት እንዲኖር ማድረግ መቻሉንም አቶ ሲራጅ አስታውቀዋል። ይሁን እንጂ በግጭቱ ተሳታፊ የነበሩ አካላትን በተገቢው መልኩ ለህግ ከማቅረብ አንጻር ክፍተት መታየቱን ጠቁመዋል። በቀጣይ እነዚህን አካላት ለህግ የማቅረብ ስራ እንደሚሰራም አመልክተዋል።
በሌላ በኩል፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተቀሰቀሰውን ግጭትና ተያያዥ ጉዳዮችን እንዲመረምር ያዋቀረው የሱፐርቪዥን ቡድን ሲያካሄድ የቆየውን የመስክ ቅኝት ሪፖርት ለህዝብ ተወካዮች ምክር አቅርቦ ምክር ቤቱ ውይይት አካሂዶበታል። ሪፖርቱን ያቀረቡት የቡድኑ አስተባባሪ የመስክ ምልከታው የተደረገው በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች ወካይ በሆኑ ዘጠኝ ዞኖች ውስጥ በሚገኙ 16 ወረዳዎች፣ ተፈናቃዮች በተጠለሉባቸው 21 የከተማና የገጠር ቀበሌዎች መሆኑን ገልጸዋል
በተፈናቃዮች ላይ የደረሰው ኢሕገመንግሥታዊ ተግባር የተፈጸመው በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢ ነዋሪ በሆኑ ሕዝቦች ሳይሆን በልዩ የፀጥታ ኃይሎች፣ የየአካባቢው ፖሊሶችና ሚሊሻዎች፣ እንዲሁም የአስተዳደር አካላት መሆኑን የሚያመለክት መረጃ ከህዝቡ ማግኘታቸውን የቡድኑ አስተባባሪ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት አሳውቀዋል። በግጭቱ የተጎዱ ወገኖች በሠላም አብረን ለዘመናት በምንኖር ሕዝቦች መካከል ታይቶ የማይታወቅ ግፍ ሲፈጸም መንግሥት ፈጥኖ እርምጃ መውሰድ ሲገባው ዝም ብሎ ተመልክቶናል፤ ዘግይቶም ቢሆን ያለንበትን ሁኔታ የተመለከቱ አመራሮችም መፍትሔ አልሰጡንም የሚል ቅሬታ ማቅረባቸውም በሪፖርቱ ተመልክቷል።
የሱፐርቪዥን ቡድኑ አባላት ግጭቱ አፋጣኝ መፍትሔ ሳያገኝ መቆየቱ አደጋ እንዲከሰት ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል። ኢሰብአዊ ድርጊት የፈጸሙ አጥፊዎች በአፋጣኝ እርምጃ እንዲወሰድባቸውም ጠይቀዋል። ተፈናቃዮችን ወደ ሠላማዊ ኑሯቸው መመለስ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ ባለመሆኑ፣ የማቋቋም ሥራው ሊፋጠን እንደሚገባም አሳስበዋል። በሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች መካከል የነበረውን መልካም ግንኙነትና ትስስር ወደነበረበት ለመመለስ የሠላም ጉባዔዎች ሊካሄዱ እንደሚገባ የሱፐርቪዥን ቡድኑ አጽንኦት ሰጥቶ አሳስቧል።
ከላይ የሰፈሩ የሁለቱ አካላት ሪፖርቶች አንድ የሚያመለክቱት እውነት አለ። ይህም ባለፉት ጊዜያት በሃገሪቱ ባጋጠሙ ግጭቶና ግርግሮች፣ በተለይ በኢትዮጵያ ሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተቀሰቀሰው ግጭት የተጎዱት ኢትዮጵያውያን ዜጎች መሆናቸውን ነው። በተፈጠሩ አለመረጋጋቶችና ግጭቶቹ በተስተጓጎለ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አምራች፣ ሻጭና ሸማች ኢትዮጵያውያን ተጎድተዋል። በግጭቱ ሣቢያ በደረሰ የንብረት ውድመት ዜጎች ለፍተው ያፈሩትን ሃብት አጥተዋል።
በኢትዮጵያ ሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተቀሰቀሱ ግጭቶች፣ በሁለቱም ወገን ከተደላደለ ኑሯቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ለመኖር የተገደዱት ኢትዮጵያውያን ናቸው። ለእነዚህ ዜጎች የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ የማቅረብ፣ ወደነበሩበት ኑሮ የመመለስና የማቋቋም ሃላፊነት የወደቀውም በኢትዮጵያውያን ላይ ነው። በሁሉም አካባቢ በተፈጠሩ ግጭቶች ህይወታቸውን ያጡት፣ አካላቸው የጎደለው ኢትዮጵያውያን ናቸው። እነዚህ ግጭቶች በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ ኢንቨስትመንት ላይ ያሳደሩት ተጽእኖ መጠን እስካሁን በይፋ ባይገለጽም፣ መጠኑ ያንስና ይበዛ እንደሆን እንጂ ተጽእኖ ያሳደሩ መሆኑ እርግጥ ነው። በዚህ የኢንቨስትመንት መደነቃቀፍ ቀዳሚዎቹ ተጎጂዎች ኢትዮጵያውያን ናቸው።
ልብ በሉ፤ በግጭቱ መቀስቀስና መቀጣጠል ውስጥ የሃገሪቱ ጠላቶችና ተላላኪዎቻቸው እጅ ያለበት ቢሆንም፣ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ በግጭቶቹ ውስጥ የተሳተፉት ኢትዮጵያውያን ናቸው። በግጭቶቹ ሣቢያ ወዲያው የተጎዱት፣ በዘላቂነት የሚጎዱትም ኢትዮጵያውያን ናቸው። የግጭቱ ተሳታፊዎችም፣ ተሸናፊዎችም ኢትዮጵየውያን ናቸው ማለት ነው። ግጭቱን አስቀርተው ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ከተጎጂነት – ተሸናፊነት መታደግ የሚችሉትም ኢትዮጵያውያን ብቻ ናቸው።
በሃገራችን ያጋጠሙ ኢትዮጵያውያን የተሳተፉባቸውና የተጎዱባቸው ግጭቶች የሃገሪቱ ጠላቶች እንዲነቃቁ ማደረጋቸውም አይቀሬ ነው። እንደ ነጻ መንግስት ተመስርቶ ገና ሳይጸና ኢትዮጵያ ላይ ወረራ የፈጸመው የኤርትራ መንግሥት፣ እርስ በርስ በመጋጨትና በጠላትነት በመተያየት ተጠምደን ከትኩረታችን ውጭ ካደረግነው በቀጥታ ጥቃትም ይሁን በሰርጎ ገቦች የሽብር ጥቃት ሊጎዳንና እንደ ሃገር ህልውናችንን አደጋ ላይ ሊጥል እንደሚችል ማስተዋል አለብን። ለዘመናት ሸብቦን ከነበረ ድህነት መውጣት በመጀመራችን በአባይ ተፋሰስ ወንዞቻችን ውሃ ለመጠቀም ያገኘነው ጉልበት በተለይ ሁሉም ኢትዮጵያውያን አሻራቸውን ያሳረፉበትና የህዝብ ፕሮጀክት የሆነውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ተጀምሮ መጋመሱ የሚከነክናቸው የግብጽ መንግስት አካላትም አጋጣሚውን ለመጠቀም መነቃቃታቸው አይቀሬ ነው። በተፈጥሮ ሃብታችን መጠቀም የማንችል፣ በእርስ በርስ ግጭት ተጠምደን ለልማት ፋታ ያጣንና ደሃ አቅመቢስ እንድንሆን ለማደረግ አጋጣሚውን ሊጠቀሙ ይችላሉ። ይህ የግብጽ መንግሥት አካላት እርምጃ በተሳካበት ልክ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ተሸናፊ ይሆናሉ።
ሃገሪቱ በግጭት የምትተራመስ መሆኗ፣ ውስጥ ውስጡን ለሚንቀሳቀሱ ኃይማኖታዊ መንግስት እስከመመሰረት የሚዘልቅ ራዕይ ላላቸው አክራሪ ቡድኖችም መልካም አጋጣሚ ፈጥሮ ትርምሱን እንደሚያባብሰው ማሰብም ብልህነት ነው። ኃይማኖታዊ ጽንፈኝነት እንዲቀበር ያደረገው የኢትዮጵያ ህዝብ ኃይማኖታዊ አክራሪነትን አልቀበል ማለቱ፣ እንዲሁም የመንግስት ጠንካራ መሆን ነው። ኢትዮጵያውያን በእርስ በርስ ግጭት ከተጠመዱና የመንግስታቸውንም አቅም ካዳከሙት የተቀበረው ኃይማኖታዊ ጽንፈኝነት አፈሩን አራግፎ መነሳቱ አይቀሬ ነው። በዚህም ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ተሸናፊ ይሆናሉ።
በአጠቃላይ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈጠር ሁከት፣ ግርግርና የእርስ በርስ ግጭት የትኛውንም ኢትዮጵያዊ አይጠቅምም። ሁከት፣ ግርግርና የእርስ በርስ ግጭት ባየለበት ልክ ኢትዮጵያውያን ይሸነፋሉ። ይህ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ተሸናፊ የሚያደርግ ሁከት፣ ትርምስና ግጭት የሚካሄደው ተሸናፊዎች በሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ነው። በመሆኑም ኢትዮጵያውያን እጃቸውን በእጃቸው እየበሉ ራሳቸውን ለሽንፈት ከሚዳርግ ድርጊት መጠበቅ አለባቸው።