Artcles

ከኢንቨስትመንቱ ባሻገር

By Admin

January 31, 2018

ከኢንቨስትመንቱ ባሻገር

ዳዊት ምትኩ

በአገራችን በኢንቨስትመንት ዘርፍ እየመጣ ያለው እድገት የሚያስመካ ነው። ለኢንቨስትመንቱ ስራችን አገራችን ያላት እምቅ ሃብትና ለባለ ሃብቶች የምትሰጠው ማበረታቻ በዘርፉ ላይ ለውጥ እያስመዘገቡ ናቸው። በአገራችን እየተካሄደ ያለው ኢንቨስትመንት ለልማታችን ወሳኝ መሆኑ ግልፅ ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ በሀገራችን ውስጥ እሀየተካሄደ ያለው ልማት እንዳይስተጓጎል ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታችን የማይተካ ሚና አላቸው። እናም ከኢንቨስትመንቱ ባሻገር እያንዳንዱ ዜጋ ለሰላማችንና ለዴሞክራሲ ግንባታችን መትጋት ይኖርበታል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ከትናንት በስቲያ በፊውዳላዊው አገዛዝ ስር የማቀቀ፣ ትናንት ደግሞ በአምባገነኑ የደርግ ስርዓት የአፈና መዋቅር ውስጥ ሁለንተናዊ መብቶቹ ተረግጠው በስቃይ ውስጥ የኖረ ነው። ይህ ህዝብ የደርግን የጭቆና ቀንበርና ስቃይ አልቀበልም ብሎ ደርግን በሚገባው ቋንቋ ለማናገር ለ17 ዓመታት ያህል በጦርነት ውስጥ ያለፈ ነው። ጦርነት ምን ያህል አስከፊ፣ ምን ያህል የሰው ህይወት ቀጣፊ፣ ምን ያህል ንብረት አውዳሚና ትውልድን አሸማቃቂ መሆኑን ለዚህ ህዝብ መንገር ለቀባሪው የማርዳት ያህል ይሆንብኛል። እናም ዛሬ ላይ በሀገራችን ውስጥ አልፎ…አልፎ በሚፈጠሩ ችግሮች ሳቢያ  ሰላም ሲታወክ ህዝቡ በግንባር ቀደምትነት የሰላሙ ባለቤት ሆኖ ቢቆም እምብዛም የሚደንቅ አይሆንም። ይህ ህዝብ የሰላም ዋስና ጠበቃ ካልሆነ ከቶ ሌላ ማን ሊሆን ይችላል?

እርግጥ የሀገራችን ህዝብ ሰላም ወዳድ መሆኑ ተገቢና ትክክል ነው። እንደ አበራሽ ጠባሳ በሁከት ለመጫወት አለመፈለጉ፤ የትናንት ትውስታው ተመልሶ ዛሬ ላይ በሃሳቡም እንኳን ቢሆን ክሱት እንዲሆን ስለማይሻ ነው። ትናንት ያለፈበት አስከፊ መንገድ ዛሬ ያገኘውን አስተማማኝ ሰላም ገለል አድርጎ ቦታውን እንዲረከበው ቅንጣት ያህል ፍላጎት የለውም። በትውስታነት የኋሊት የሚሸሸውና ዳግም እንዳይመጣም ዶሴውን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የዘጋው የያኔው አባጣና ጎርባጣ መንገድ ተመልሶ እንዳይመጣ ለሰላሙ ፀር የሆኑ ሃይሎችን በማውገዝ፣ በማጋለጥና ተገቢውን ትምህርት እንዲወስዱ በማድረግ በባለቤትነት መንፈስ የመንቀሳቀስ ፍላጎቱ መሰረት ይኸው ይመስለኛል። አዎ! ይህ ህዝብ ከመቼውም ጊዜ በላይ ለሰላም ዘብ የሚቆምና ሰላም በምንም ሊተካ የማይችል እሴት መሆኑን ለማወቅ ነጋሪ የሚያሻው አይደለም—ባይሆን እርሱው ራሱ ለሌላው ያስተምራል እንጂ።

ለነገሩ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህዝብ ለሰላም ይህን ያህል ዋጋ የሰጠው የሞት ሽረት ጉዳይ የሆኑትን ልማትንና ዴሞክራሲን ለማምጣት ያደረገው እልህ አስጨራሽ ትግል የኋሊት እንዳይቀለበስበት ከመፈለግ ነው። ሰላም ከቁሳቁስ መጥፋትና መውደም ጋር ብቻ እንደማይያያዝ የሚገነዘበው፤ ነገ የሚገነባው ትልቅ ምጣኔ ሃብት ያለውና ለዘመናት ተነፍጎት የነበረው የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባት ስር እንዲሰድ ስለሚሻ ነው።

ይህ ህዝብ ላለፉት 26 ዓመታት ገደማ የተራመዳቸው የልማት አባጣና ጎርባጣ ውጣ ውረዶች በአሁኑ ወቅት የሚቀራቸው ተጨባጭ ለውጦች ቢኖሩም፤ ከትናንቱ በተሻለ ቁመና እንደሚገኙ ያውቃል። እርሱንም በተሻለ ማማ ላይ እንደሚያወጡት በልማቱ ውስጥ ተዋናይ የሆነው ማንኛውም ዜጋ በየደረጃው ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱን ራሱን ዋቢ አድርጎ መቅረብ የሚችል ህዝብ ነው።

ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ካሉ፣ ህዝቡን ከዳር እስከ ዳር የሚያንቀሳቅስ ልማታዊ መንግስት ካለና በዚሁ መሪ አካል አስተባባሪነት ብሎም በህዝቡ የባለቤትነት መንፈስ የሚዘወር ሰላም እስካለ ድረስ፤ ሰርቶ መለወጥና መደግ እንደሚቻል ሩብ ክፍለ ዘመንን እልፍ ባለ ዓመት ጊዜ ውስጥ ትምህርት ወስዷል።

አምባገነኑና የዕዝ ኢኮኖሚ መርህን የሚከተለው የደርግ ሥርዓት ከመውደቁ በፊት የሀገራችን ምጣኔ ሃብታዊ አሃዝ ከዜሮ በታች እንደነበር የማይዘነጋው ይህ ህዝብ ስለሰላም ቢናገር የሚበዛበት አይደለም። አምባገነኑ ስርዓት እንደወደቀም በአንድ በኩል ሰላምን የማረጋጋት፣ በሌላ በኩል ደግሞ የደቀቀውን ኢኮኖሚ ለማቃናት የከፈለውን ከባድ መስዕዋትነት በሚገባ ይገነዘባል።

ያኔ ተራራ የሚያክለውን የሀገሪቱን ድህነት ለመዋጋት የተለያዩ መርሆዎችን ቢሰንቅም የሚፈለገው ዓይነት ለውጥ እንዳልመጣና ለረጅም ጊዜ በሀገራችን ውስጥ ተንሰራፍቶ የነበረውን የድህነት አዙሪትን ለመቀልበስ እንዳልተቻለ በማወቁ ሌላ መንገድ እንዲቀየስ ማስፈለጉን የሚያስታውስ ህዝብ ነው። በመሆኑም በአንድ በኩል የሀገሪቱን ሰላም ማረጋጋትና የታጠቁ ሃይሎችን ወደ ልማት የማዞር ስራ፣ በሌላኛው ዘውጉ ደግሞ ፈጣንና ተከታታይ ልማትን የማምጣትና ሁሉንም ዜጋ በየደረጃው ተጠቃሚ የሚያደርግ ፖሊሲና ስትራቴጂን እውን ለማድረግ የወሰደው ጊዜና የጠየቀው ሁሉን አቀፍ መስዕዋትነት ከዚህ ህዝብ አዕምሮ ውስጥ የሚጠፉ አይመስለኝም።

ሰላሙም እውን ሆኖ የታሰበው ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት በማስመዝገብ ሂደት ውስጥ ሁሉም ዜጋ ድህነት በሚባለው አንገት አስደፊ በሽታ ላይ እንዴት  እንደዘመተና እስከ የመጀመሪያው ተሃድሶው ድረስ ሲጀመር ከዜሮ በታች የነበረውን ኢኮኖሚ ወደ አምስት ነጥብ አንድ በመቶ እንደምን ከፍ ሊያደርገው እንደቻለ ከዚህ ሰላም ወዳድ ህዝብ የሚሰወር አይደለም፤ ዋነኛው ተዋናይ እርሱው ነበርና።

ከቀዳሚው ተሃድሶ በኋላም የተገኘው እድገት የድህነትን አከርካሪ በሚፈለገው መጠን መስበር እንዳልተቻለ፣ በወቅቱ የተከሰቱት የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት፣ የኪራይ ሰብሳቢነት፣ የጥበትና የትምክህት አመለካከቶች ከልማታዊና ተራማጅ እሳቤዎች ጋር ግጭት መፍጠራቸው የህዝቡን የማደግ ህልም ሊያመክኑትና ወደ ጨለማው መንገድ ይዘውት ሊሄዱ እንደነበር ከዚህ ሰላም ወዳድ ህዝብ አዕምሮ ጓዳ ውስጥ ከቶም ቢሆን የሚጠፉ አይደሉም። እነዚያ አስተሳሰቦች በወቅቱ ባይቀጩ ኖሮ፣ ዛሬ የተገኘው ሁለንተናዊ ለውጥ ሊመጣ እንደማይችል ምስክሩ እርሱው ስለሆነ።

ከዛሬ 15 ዓመት በኋላም ቢሆን የነበሩት የተዛቡ አስተሳሰቦች ከሞላ ጎደል በመታረማቸውና መንግስትም ድህነትን ለመቀነስ በወሰዳቸው ሰፋፊ ርምጃዎች ባለ ሁለት አሃዝ ዕድገት ማስመዝገብ መቻሉ የሰላም መኖር ምን ያህል ፋይዳ እንደነበረው ያውቃል። የሀገራችን ህዝብ በአምባገነኑ የኤርትራ መንግስት የተቃጣበትን ወረራ ፈጥኖ በመመከት፣ ውሰጠ-ድርጅት ህፀፆችን በአስቸኳይ ፈትቶ ፊቱን ወደ ልማት ባይመልስ ኖሮ፤ ያለ ሰላም በጦርነትና በንትርክ ጊዜውን ያጠፋ እንደነበር ግልፅ ይመስለኛል። ይህን ደግሞ ከዚህ ህዝብ በላይ ሊገነዘብ የሚችል አይመስለኝም።

እንዲህ ዓይነቱ ሰላምን የሚያጎሉ፣ ልማትን የሚያፋጥኑና ንትርክን የሚያስቀሩ መንገዶችን መከተል ባይቻል ኖሮ፤ የመጀመሪያውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን እውን ማድረግና ህዝቡም የተጀመረውን የፀረ-ድህነት ዘመቻ አጠናክሮ ባልቀጠለ ነበር። ከልማት ዕቅዱም በየደረጃው ተጠቃሚ ሆኖ ተፈላጊውን የዕድገት ራዕይ ሰንቆ ባልተጓዘም ነበር። አሁን እያለመ ላለውና ከመጀመሪያው ዕቅድ ጋር ተመጋጋቢ የሆነውን ሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድንም ባላለመ ነበር።

በዚህ ደረጃ ላይ ሆኖ የተጀመረውን ዕድገት ለማስቀጠልና በዚያውም ልክ መሳ ለመሳ ዴሞክራሲው ሀገር በቀል ፍላጎትን መሰረት ባደረገ መልኩ እንዲጎለብት የተደረገው ጥረት፤ እንዳለ ሆኖ ይህ ህዝብ በአንዳንድ የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች ውስጥ ከመልካም አስተዳደር ጋር እንዲሁም ፅንፈኛ ኃይሎችና የሀገራችንን መለወጥ የማይሹ አንዳንድ ወገኖች አማካኝነት የተከሰተውን ሁከት ለመቋቋም ህዝቡ በባለቤትነት ስሜት የከፈለው መስዕዋትነት በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ይህ የህዝቡ ስሜት የመነጨው ከምንም ተነስቶ አይመስለኝም። ሰላምና ዴሞክራሲ ማበብ እንዳለባቸው ስለተገነዘበ ነው።

ከላይ እንዳልኩት ሰላምና ዴሞክራሲ ከሌለ ስለ ኢንቨስትመንት ማሰብ አይቻልም። የእነዚህ ሁለሩ ጉዳዩች ጥምረት አገራችን ኢንቨስትመንትን የበለጠ እንድትስብ ያደርጋታል። ኢንቨስትመንትን ስንስብ ደግሞ፤ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እናገኛለን፣ የስራ እድል እንፈጥራለን፣ በዚያው ልክም ዜጎቻችን ይጠቀማሉ፣ አገራዊ ህዳሴያችንም በተፋጠነ ጊዜ ውስጥ እውን ይሆናል።