Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ከዜሮ ዝንጣፊ…

0 416

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከዜሮ ዝንጣፊ…

                                                   ደስታ ኃይሉ

ሰሞኑን “ብሉንበርግ” (Bloomberg) የተሰኘው የዜና አውታር “ኢትዮጵያ በላቲን አሜሪካ የአበባ አምራቾች የተያዘውን የአሜሪካ የአበባ ገበያ የበላይነት ለመንጠቅ በአበባ ኢንዱስትሪውን እያሳደገች ነው” በማለት ዘግቧል።

ዘገባው ከአስር ወይም ከአስራ አምስት ዓመታት በፊት አንድ ዝንጣፊ አበባ እንኳን ወደ ውጭ የማትልከው ኢትዮጵያ፣ መንግስት በተከተለው ትክክለኛ የልማት መስመር ከዓለም አራተኛ እንዲሁም ከአፍሪካ ከኬንያ ቀጥሎ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ልትቀመጥ እንደቻለችም ያስረዳል። ይህም አገራችን በመንግስት መሪነት ትናንት ከነበረችበት ከዜሮ ዝንጣፊ አበባ ላኪነት ወደ ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት ዘልቃ ከቀዳሚዎቹ አራት አገራት አንዷ እንድትሆን አስችሏታል።  

የኢፌዴሪ መንግስት ከዚህም በላይ መስራት የሚያስችለው እቅድ ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ነው። የለሙ ተራሮችን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች መሬት የማቅረብ፣ የማሽነሪ ሊዝ የማመቻቸት፣ የማስፈፀምና የመፈፀም አቅም ሥልጠና በመስጠትና የግብኣትና የገበያ አውታሮችን በማመቻቸት በተለይ ለኤክስፖርት ገበያና ለአግሮ ፕሮስሲንግ ኢንዱስትሪዎች ግብዓት በማምረት የወደፊቱ የአገራችን ልማታዊ ባለሃብቶችን ለመፍጠር እየሰራ ነው።

በዚህም የግል ባለሃብቶችን የግብርና ልማት ተሳትፎን እያጎለበተ ነው። በአባባ ልማት ዘርፍ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች ከሚያደርጉት ተሳትፎ ውጭ ውስን ባለሃብቶች በጥጥ ልማት እንዲሁም በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሳተፉ እየተደረገ ነው።

ሆኖም አገራችን ካላት ዕምቅ ለግብርና ምቹ የሆነ መሬትና የተፈጥሮ ሃብት ሁኔታ ጋር የሚመጣጠን የግልባለሃብቱ የግብርና ኢንቨስትመንትና ልማት እስከ አሁን ኛረጋገጥ አልቻልንም። ይህን ችግር ለመፍታት መንግስት ከ3 ሚሊዮን ሄክታር ያላነሰ ምቹ መሬት ውስጥ ከ100 ሄክታር እስከ 5000 ሄክታር ድረስ መሬት የያዙ የአገር ውስጥ ባለሃብቶች ወይም አነስተኛና መካከለኛ ባለሃብቶች የያዙትን መሬት በአግባቡ እንዲያለሙት የተቀናጀ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።

በአነስተኛና መካከለኛ ደረጃ ልማት ውስጥ በአዲስ መልክ ለሚገቡትም ክልሎች መሬት አዘጋጅተው ከተቀናጀ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ጋር እንዲያቀርቡ እየተደረገ ነው። አነስተኛና መካከለኛ ባለሃብቶች ለኤክስፖርትና ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት በሚቀርቡ የሰብል፣ የአበባ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም እንስሳት ሃብት ልማት ዘርፍ እንዲሳተፉ በማድረግ ላይ ይገኛል። አነስተኛና መካከለኛ ባለሃብቶች ከተማሩ ወጣት የግብርና ኢንቨሰተሮችና ከከፍተኛ ባለሃብቶች ጋር የሚቀናጁበት ሁኔታንም በመፍጠር ላይ ነው።

ከፍተኛ የግብርና ባለሃብቶች የሚባሉት ከ5000 ሄክታር በላይ በአንድ ኩታ ገጠም አካባቢ የሚያለሙና በፌዴራል ደረጃ ክትትል የሚደረግላቸው ናቸው። እስከ አሁን ድረስ በጥጥ ልማት የተሳተፉ ውስን ባለሃብቶች ካልሆኑ በስተቀር ውጤታማ የሆኑ አሉ ለማለት አያስደፍርም።

የሰፋፊ እርሻዎች ልማት የሚካሄድባቸው አካባቢዎች ያለውን የመሠረተ ልማት አቅርቦት ጉድለት፣ የአገልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር ችግርና በአንዳንዶቹ ባለሃብቶች አካባቢ የሚታየውን የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር በማስተካከል ለሀገራችን የኢኮኖሚ ዕድገት ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዲያበረክት በመደረግ ላይም ነው።

እነዚህ የግብርና ልማት መስኮች ሰፊ ጉልበትን ማንቀሳቀስ የሚያስፈልጉ ናቸው፡፡ በገጠር የሥራ ዕድል በመፍጠርም የራሳቸው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ፡፡ ስለሆነም ግብርና በተለይም ለሴቶችና ወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር ተኪ የለሽ ሚናውን እንዲጫወት ይደረጋል፡፡

በዚህ መሠረት ግብርና በመሰረታዊ አማራጭ ቢያንስ በየዓመቱ የ8 በመቶ ዕድገት እንዲሁም እስከተቻለ በከፍተኛው አማራጭ በእጥፍ እንዲያድግ በማድረግ ዕድገቱ ዋነኛ ምንጭ ሆኖ በማገልገል የምግብ ዋስትናችንን በአስተማማኝ ሁኔታ ለማረጋገጥ፣ የዋጋ ግፊትን ለመቋቋም፣ የአግሮ-ፕሮስሲንግ ኢንዱስትሪዎች የጥሬ ዕቃ ፍላጐት ለማሟላትና የወጪ ንግድ (ኤክስፖርት) ገበያ በማሳደግ የክፍያ ሚዛኑን እንዲያጠብ ከፍተኛ ማድረግ በሚችልበት ሁኔታ እየተሰራ ነው።

በአሁኑ ወቅት በግብርና ሥራው በዓመት ሁለቴና ከዚያም በላይ ለማምረት አየተቻለ ነው። እንዲሁም በከርሰ ምድርና በገጸ -ምድር ያለውን የውኃ ሃብት የመጠቀም ሰፊ ተግባር አከናውኗል። በውኃ ማሰባሰብና ማቆር፣ የጉድጓድ ውኃን በመጠቀም የወንዝ ውኃን ጠልፎ ጥቅም ላይ በማዋል ብዙ ርቀት ተጉዟል። በመሆኑም አርሶ አደሩ ከራሱ ፍጆታ አልፎ ለከተማው ነዋሪዎች ከፍተኛ ፍላጎት የሆኑትን ምርቶች ማቅረብ ችሏል። ከነዚህ ውስጥ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች በግንባር ቀደምነት ተጠቃሽ ናቸው።

ከዝናብ ጥገኝነት በተላቀቁ አመራረት የተገኙትን ምርቶች መጠቀምም እየተቻለ ነው። የመስኖ ልማት ሥራው በበጋ የበቆሎ እሸት ተመጋቢዎች እንዲሆን አስችሎናል። ባለፉት ሁለት ዓመታት ደግሞ ሥራው ከሁለት እጥፍ በላይ አድጓል። ለገበሬው በዚያው ልክ ገበያው ተመቻችቷል። አርሶ አደሩ በራሱ ባቋቋማቸው የአርሶ አደሮች የህብረት ሥራ አማካይነት ምርቱን ለገበያ በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ ተጠቃሚ መሆን ጀምሯል።

ይህ ሁኔታ የውጭ ምንዛሬን ከሚያስገኘው የአበባ ምርት ጋር ሲደመር ለአገሪቱ ተስፋ ነው። የአበባ ምርት በአነስተኛ መሬት ላይ ከፍተኛ ምርት ሊያስገኝ የሚችል ስራ ነው። ይህም በተለይ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በቁርኝት የሚከናወን በመሆኑ ምርታማነቱን ከፍ ያደርገዋል።

በኢትዮጵያ የሚገኙ አበባ አምራቾች ከምስራው አፍሪካ ሀገሮች ሀገራችንን ይመርጧታል። ምርቱን ለአለም ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪን ማሳደግ ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያም ዘርፉን የምትደግፍበት ቀደሚ ፍላጎትም ይህ ነው፡፡ ለአበባ አምራቾች የሚደረገው የታክስ ቅናሽ እና የባንክ ብድር አቅርቦት ከማበረታቻዎቹ መካከል ይጠቀሳሉ።

በኢትዮጵያ ባንኮች የውጭ ምንዛሪ ማስቀመጥ እንዳለባቸው የወጣው ደንብ አበባ አምራቾች ገንዘቡን በአንድ ወር ውስጥ ወደ አገር ውስጥ ገንዘብ እንዲቀይሩ ያስገድዳል፡፡ የኢንቨስትመንት ደንቡ ትርፋቸውን በአገራቸው እንዲያስቀምጡ መፍቀዱ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዲኖር አድርጓል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ከእጅ ወደ አፍ የሆነውን ግብርና ለመቀየር እና ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት የቀየሰውን መንገድ  የሚደነቅ ነው። ይህም አገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በማግኘት የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንድትችል የሚያደርጋት ነው።

በዝዋይየሚገኘውን የኤ.ኪው አበባ አምራች ኩባንያን በምሳሌነት ብንወስድ በሆላንድ ለሚገኙት የረጅም ጊዜ ደንበኞቹ ከማሳው በአመት ከሚያመርታቸው 100 ሚሊዮን ዘንግ አበቦች መካከል ደረጃቸውንና ጥራታቸውን የጠበቁ 80 በመቶ ምርቶቹን የሚያቀርብ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ጠንካራ ውድድር የኢትዮጵያ አበባ አምራቾች በሆላንድ አልስሚር ከተማ የሚገኘውን በአለም ግዙፍ የሆነውን የአበባ ጨረታ እንዲቀላቀሉና ተገቢውን የውጭ ምንዛሬ አገሪቱ እንድታገኝ እያደረጉ ነው።

ኢትዮጵያ በ2015 ያመረተችው የአበባ ዘንግ 50 ሺ ሜትሪክ ቶን መሆኑን የኢትዮጵያ አበባ ላኪዎች ማህበር መረጃ ያሳያል። ጎረቤቷ ኬንያ በበኩሏ 122 ሺህ 800 ቶን አብቅላለች፡፡ ይህ ደግሞ ገና ብዙ ስራ እንደሚጠብቃት ማሳያ ነው። ከዜሮ የአበባ ዝንጣፊ ተነስተን አሁን የምንገኝበት ደረጃ የሚያስመሰግን ቢሆንም አሁንም ለአበባ ላኪዎች የበለጠ ትኩረት በመስጠት አሁን ከምንገኝበት ከአፍሪካ ሁለተኛነትና ከዓለም አራተኛነት ደረጃችንን ማሻሻል ይጠበቅብናል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy