Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ከግብፅ ሚዲያዎች አጀንዳ ባሻገር

0 441

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከግብፅ ሚዲያዎች አጀንዳ ባሻገር

                                                      ቶሎሳ ኡርጌሳ

ከመሰንበቻው የዓባይ ውሃ አጠቃቀምን አስመልክቶ በግብፅ ሚዲያዎች እየተናፈሰ ያለው መሰረተ ቢስ ጉዳይ የትናንቱን የግብፅ ገዥ መደቦች የሚያስታውሰኝ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ይኸውም ከአንዋር ሳዳት ጀምሮ እስከ መሐመድ ሙርሲ መንግስት ድረስ የነበረውና ካይሮ የውስጥ ሽኩቻዋን ለማብረድ ዓባይን እንደ እሳት ማጥፊያ ይጠቀሙበት እንደነበረው ሁሉ፤ ዛሬም የግብፅ ሚዲያዎች በተመሳሳይ መልኩ ይህንኑ ዘዴ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አስመልክቶ እንደ አዲስ አጀንዳ እያራመዱት ነው።

ርግጥ ዛሬ በግብፅ፣ በኢትዮጵያና በሱዳን መንግስታት መካከል ጥሩ ግንኙነት አለ። ግድቡን በተመለከተ በሶስቱ ሀገራት መካከል የጎላ ልዩነት የለም። ሰሞኑን የግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሽኩሪ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት በዓባይ ጉዳይ ላይ ብቻ ለመነጋገር አይደለም። በኢንቨስትመንት፣ በንግድና በፀረ ሽብርተኝነት የጋራ ትግል ዙሪያም ጭምር ነው። እንዲያውም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በያዝነው ወር ውስጥ በግብፅ ለሚያደርጉት ጉብኝት ሁኔታዎች እየተመቻቹ ነው። የሱዳኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በሩሲያ ባደረጉት ጉብኝት ላይ “የህዳሴው ግድብ ስጋት የሚዲያ አጀንዳ ነው” በማለት እውነታውን ማፍረጥረጣቸው የግብፅ ሚዲያዎችን ተልዕኮ በግልፅ ያሳያል።

ታዲያ ሃቁ ይህ ሆኖ ሳለ፤ የግብፅ ሚዲያዎች ይህን እውነታ ወደ ጎን በማለት ሆን ብለው ጉዳዩን ለማሟሟቅ (Sensational ለማድረግ) እየሰሩ ነው። አንድም፣ የተለመደውን “የዓባይ ጉዳይ ለግብፅ ህዝብ የሞትና የሽረት ጉዳይ ነው” በማለት፤ ሁለትም፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የግብፅ ጉብኝት እንዳይካሄድ “የግብፅ ፓርላማ አባላት ተፈራርመው አስገቡ” የሚል አጀንዳን በማራገብ ላይ ይገኛሉ። ግና ከአጀንዳቸው ባሻገር ያለውን እውነታ መመልከት ይገባል—ዛሬ ግብፅ ውስጥ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ለማስቀየስ የማሰብ የቆየ ዘዴን። ከዚያ በፊት ግን በግብፅና በእኛ መካከል ስለነበረው ሁኔታ በጥቂቱ ማውሳት ይገባል።

ርግጥ ነው—ኢትዮጵያና ግብፅ በዓባይ አጠቃቀም ዙሪያ ለዘመናት ሳንግባባ ኖረናል። አለመግባባት ደግሞ የጠላትነት መለኪያ አይደለም። ግብፅ ለዘመናት ብቸኛ ተጠቃሚ የሚያደርጋትን አሮጌውን የህግ ማዕቀፍ ደንግጋ በዓባይ ወንዝ የመጠቀም መብታችንን መንፈጓ የትናንት ሃቅ ነው። ኢትዮጵያ 86 በመቶ ያህሉን የናይል ወንዝ ድርሻ የምታበረክት ታላቅ ባለ ይዞታ ሀገር ብትሆንም ቅሉ፤ ከወንዙ ለዘመናት አንዳችም ጥቅም ጠብ ሳይልላት ትውልዶቿን ይዛ በበይ ተመልካችነት ተሻግራለች። ዓባይን እንዳሻቸው ሲበሉትም ሆነ ሲጠጡት የኖሩት ግብፆች ናቸው።

እናም ግብፆች በዓባይ ወንዝ የመጠቀም መብታችንን በተለያዩ መንገዶች ሲጋፉ መኖራቸው አይታበይም። ምንም እንኳን በታሪካችን ዓባይን ለመገደብ የተነሳ ትውልድ ኖሮ በግብፅ እምቢተኝነት ሳቢያ ከልማት ባይስተጓጎልም፤ በእጅ አዙር ለሙከራ ያህል የሚደረጉ ጥረቶችን ካይሮ ታመክን እንደነበር ግን የአደባባይ ምስጢር ነው።

በወቅቱ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ የተሰገሰጉ እንደ ቡጥሮስ ቡጥሮስ ጋሊ ያሉ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግብፃውያን፤ እንኳንስ ዓባይን መገደብ ቀርቶ ስለ አባይ ማሰብ እንዳንችል ጉዳዩን በእሾህ ማጠራቸው አይዘነጋም። በዚህም እ.ኤ.አ በ1929 እና በ1959 የተረቀቀን ያረጀ ያፈጀና ኢ ፍትሐዊ ብቻ ሳይሆን ኢ ሞራላዊ የቅኝ ዘመን ውሎችን አርቅቀው ከሱዳን ጋር በአንድነት በመሰለፍ እሾሁን በሌላ እሾህ አጥረውት ነበር—በቅርቡ ሱዳን “በውሎቹ ላይ የሰፈረውን የውሃ ድርሻዬን ግብፅ ልትመልስልኝ ይገባል፤ ያ የውሃ ድርሻዬ ደግሞ ለህዳሴው ግድብ ይዋል” በማለት አቋሟን እስከቀየረችበት ጊዜ ድረስ።

ያም ሆኖ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ኢትዮጵያ ለህዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት ካላት ቀናዒ ፍላጎት በመነሳት ግብፆች ከግድቡ ግንባታ ጋር በተያያዘ የሚያቀርቡትን ሃሳብ መተማመንን ለመፍጠር ስትል ብቻ በሆደ ሰፊነት ተቀብላዋለች። ግብፆች በተለያዩ ወቅቶች አንዴ “እንወያይ” ሲሉ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ “የቅኝ ግዛት ውሎች ገዥ ነጥቦች መሆን አለባቸው” በማለት ከውይይት ፍላጎታቸው ጋር የማይገጥም ጉዳዩችን ሲያነሱና ሲጥሉ ኢትዮጵያ አንዳንድ የካይሮ ባለስልጣናት ገዥ መደቦችን ሳይሆን የግብፅ ህዝብን በመመልከት ለጋራ ተጠቃሚነት ስትል ጉዳዩን በስልጡን መንገድ ይዛዋለች።  

ሆኖም የህዳሴው ግድብ ለግብፅ ሚዲያዎች ቋሚ አጀንዳቸው (አጀንዳ ማስቀየሻቸው) ከመሆን አላመለጠም። ግብፅ ውስጥ አንዳች ህዝባዊ ቁጣ የሚፈጥር ጉዳይ ሲፈጠር አሊያም ከምርጫ ጋር የተያያዙ ሁኔታዎች ሲኖሩ የህዳሴው ግድብ ጉዳይ እንደ ኮሶ መድሃኒት በማሻሪያነት ይቀርባል። የክፉ ቀን ቢጫ ካርድ ሆኖ ይመዘዛል። ዓባይ ለግብፅ የመጨረሻው የህይወቷ መድን መሆኑ በየሚዲያዎቻቸው ይነገራል። በቅብብሎሽ ይደሰኮራል። የአንድ ሰሞን ነጠላ ዜማ ሆኖ ይቀርባል። ዛሬም ከግድቡ ግንባታ ጋር ተያይዞ የግብፅ ሚዲያዎች ጩኸት አላባራም። ይህንኑ “የግብፅ ህዝብ ጉረሮ መታነቅ” ትርክት እያነበነቡት ነው።

ሃቁ ግን ይህ አይደለም። ኢትዮጵያ ዋነኛ አጀንዳዋን ድህነትን ማጥፋት አድርጋ እየሰራች ነው። የህዳሴው ግድብ የዚህ ጥረት አካል መሆኑን ደጋግማ ገልፃለች። ፕሮጀክቱ የግብፅ ህዝብን የሚጠቅም እንጂ የሚጎዳ አለመሆኑን በተለያየ መልክ ለግብጻውያን ወንድሞቻችን ለማስገንዘብ ያልተቆጠበ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት አድርጋለች። ይሁንና በግብፅ በኩል በየጊዜው የተለያዩ ግንባታውን ላለመቀበል ምክንያት ይሆኑኛል የተባሉ ሃሳቦች እየቀረቡ እስካሁን ድረስ ወደ ትክክለኛው መስመር መምጣት አልተቻለም።

ኢትዮጵያ የህዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ስትል የህዳሴው ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ከግብፅና ከሱዳን ጋር እስካሁን ድረስ በርካታ ስብሰባዎችን አካሂዳለች። ግድቡ ጉዳት እንደሌለው ከሱዳንና ግብፅ ጋር ለመተማመን የሚያስችሉ ተጨባጭ ሁኔታዎች ቀርበው “ጉዳት ያደርስብናል” የሚሉት ግብፃውያንም ሆኑ የግድቡን ጠቀሜታ የተረዳችው ሱዳን የተለያዩ ሃሳቦችን አንሸራሽረዋል። ግብፆች ግን አሁንም ከቅኝ ግዛት ውሎች አስተሳሰብ ሙሉ ለሙሉ ፈቀቅ ለማለት የፈለጉ አይመስሉም። እናም እንደ ትናንቱ ዛሬም ሀገራችን ግድቡን እንዳትገነባ የቻሉትን ሁሉ ከማድረግ የቦዘኑ አይመስልም።

ግብፆች በአንዳንድ ተቋሞቻቸውና በሚዲያዎቻቸው አማካኝነት እዚህ ሀገር ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዳይሰፍንና የህዝቡን የተነሳሽነት መንፈስ በመስለብ የግድቡን ግንባታ በትርምስ ውስጥ ሆኖ እንዳይገነባ ብዙ ጥረዋል፤ ግረዋል። ያም ሆኖ የኢትዮጵያ ህዝብ ጨዋ፣ ወደ ውስጥ መለስ ብሎ የሚያይ፣ በጋራ የአንድነት ስሜት የተጋመደና ከመናቆር ምንም ዓይነት ፋይዳ እንደማይገኝ የሚያውቅ በመሆኑ የግብፅ ተቋማት ፍላጎት በተፈለገው መጠን ተሳክቷል ማለት አይቻልም።

ርግጥ የቀደሙት የግብፅ መንግሥታትም ኢትዮጵያ የፋይናንስ ድጋፍ አግኝታ በዓባይ ወንዝ ላይ ልማት እንዳታካሂድ ተፅዕኖ ሲፈጥሩ ኖረዋል። በርካታ አለም አቀፍ  የልማት አጋሮች ፊታቸውን ከኢትዮጵያ እንዲያዞሩ አድርጋለች። ባለፉት ስርዓቶች በሀገራችን ልማትንና ሰላምን የሚያሰፍን አመራር ካለመኖሩ ጋር ተዳምሮ ኢትዮጵያ ከዓባይ ወንዝ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ሳታገኝ ዘመናት እንደ ዋዛ አልፈዋል። የህዳሴው ግድብ ይጀመራል በተባለ ማግስት በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ ዲፕሎማቶቿን በመጠቀም ኢትዮጵያ የገንዘብ ድጋፍ እንዳታገኝ ለማድረግ ተንቀሳቅሳለች።  

ታዲያ ይህ የግብፆች ፍላጎት አልተሳካላትም ማለት ባይቻልም፤ ግድቡ እንዳይገነባ ማድረግ ግን አልቻሉም። የህዳሴው ግድብ የግንባታ ማስኬጃ ገንዘብ የሚሸፍነው የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት በመሆናቸውና ይህ አዲስ አሰላለፍ ግብፆች ለዘመናት የተጠቀሙበትን “የፋይናንስ ምንጭን የማሳገድ” ስልት እንዳላዋጣቸው ተገንዝበው ፊታቸውን ወደ ድርድር መመለስ ግድ ብሏቸዋል። ሆኖም እስካሁን ድረስ ባለው ሂደት በድርድሩ ውጤታማነት ላይ አዎንታዊ ሚናቸውን ሊወጡ ግን የቻሉ አይመስልም።  

በእኔ እምነት በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በግብፅ በተያዩ ወቅቶች የተደረገው ውይይት ላይ መግባባት ሳይደረስባቸው ለሌላ ጊዜ የሚተላለፉበት ምስጢርም ይኸው ይመስለኛል። እንደሚታወቀው ቀደም ባሉት ጊዜያት ከሶስቱም ሀገራት የተውጣጣ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ታዋቂነት ያላቸው ባለሙያዎችን ያካተተ ቡድን ከህዳሴው ግድብ ግንባታ ማግስት በተካሄዱና ሀገራቱ በተስማሙበት መልኩ ጥናት አካሂዶ ውጤቱን አቅርቦ ነበር። ቡድኑ በዘርፉ በቂ ልምድና እውቀት ያለው ሲሆን፤ የህዳሴውን ግድብ ሙያዊ በሆነ መንገድ በማጥናት  ያገኘውን ውጤት ለየሀገራቱ አስረክቧል። “መፈፀም አለባቸው” ያላቸውን አስተያየቶችንም አቅርቧል።

ግና በወቅቱ ከሶስቱ ሀገራት የሚጠበቀው ነገር የቀረበውን ሪፖርት አይቶ መፈፀም ሆኖ ሳለ፤ ግብፅ ግን ወትሮም ‘የውሃ ድርሻዬ ሊነካ አይገባም’ በሚል አሮጌ አስተሳሰብ የምትመራ በመሆኗ ጉዳዩን እንደገና ወደ ኋላ መጎተት አስፈላጊ ሆኖ ታያት። እናም ግድቡ በታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ላይ የሚያስከትለው ተፅዕኖ በግልፅ በሶስቱ ሀገራት ኤክስፐርቶች ተጠንቶና ሪፖርቱም ጠረጴዛዋ ላይ ሆኖ ሳለ፤ “በገለልተኛ ዓለም አቀፍ አጥኚ ቡድን ይረጋገጥልኝ” ስትል ሃሳብ አቀረበች።

የኢትዮጵያ መንግስትም መተማመንን ለመፍጠር ሲል ብቻ አሁንም ይሁንታውን ሰጠ። ሁለት የፈረንሳይ አጥኚ ኩባንያዎችም በሶስቱም ሀገሮች ፍላጎት ተመረጡ። ግብፅ ግን አሁንም “የጥናቱ መመሪያ የቅኝ ግዛት ስምምነት ውሎች መሆን አለባቸው” የሚል ያንን “እኛ እንብላ፤ እናንተ ግን ጦማችሁን እደሩ” የሚል ሃሳብ አቅረበች። ኢትዮጵያና ሱዳንም ይህን ከፋፋይና የህዝቦችን የጋራ ጥቅም የማያስከብር የቅኝ ገዥዎችን ውል ወዲያውኑ ውድቅ አደረጉት። ይህን ተከትሎም ካልተገቡ የቃላት እሰጥ-አገባዎች በኋላ የግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሽኩሪ ለይፋዊ ጉብኝት አዲስ አበባ ተገኙ።

ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ጉብኝታቸው ከህዳሴው ግድብ ጋር ብቻ የተገናኘ አይደለም። ሁለቱ ሀገራት በኢንቨስትመንት፣ በንግድና በፀረ ሽብር ዘመቻ ተባብረው የሚሰሩ ናቸው። ሆኖም ግብፅ ግብቡን አስመልክቶ “ገለልተኛው የዓለም ባንክ ያደራድረን” እስከማለት መድረሷን አንዳንድ ሚዲያዎች አስደምጠውናል።

ኢትዮጵያም ድርድሩ የሶስትዮሽ እንጂ የግብፅና የኢትዮጵያ ብቻ አለመሆኑን በመግለፅ፤ ሃሳቡን እንደምታጤነው ገልፃለች። እንግዲህ ከሶስትዮሽ የኤክስፐርቶች ቡድን ወደ ዓለም አቀፍ አጥኙ ቡድን አረጋጋጭነት የተሻረገችው ግብፅ፤ አሁን ደግሞ “ገለልተኛው የዓለም ባንክ ያደራድረን” ማለቷ ግራ አጋቢ ይመስላል። ግና ማንም ቢሆን የሀገሪቱን ፍላጎት ለመረዳት የሚከብደው አይመስለኝም።

በእኔ እምነት ግብፆች ቀደም ባሉት ጊዜያት በዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ውስጥ የነበሩና ተሰሚነት ያላቸውን ዜጎቻቸውን እንዲሁም ዲፕሎማቶቻቸውን በማሰማራት ኢትዮጵያ ለግድቡ የሚሆን ምንም ዓይነት ድጋፍ እንዳታገኝ ሲያደርጉ ቆይተዋል። በእነርሱ እምነት በአሁኑ ወቅት ለግድቡ ግንባታ ማስኬጃ የሚሆን ገንዘብ ኢትዮጵያ የላትም። እንዲያውም ሚሲያዎቻቸው “ግድቡ ቆሟል” የሚል አጀንዳ ፈጥረው ሲያናፍሱ እንደሰነበቱ ይታወቃል። እናም የግድቡን ግንባታ ከዓለም አቀፍ ባንኮች ጋር በማገናኘት ግንባታውን እነርሱ በሚፈልጉት መንገድ ለማስኬድ ያሰቡ ይመስለኛል። ይህም ግድቡን እንዳሻቸው ሊዘውሩት እንደሚችሉ ‘ምቹ ሁኔታ ይፈጥርልናል’ ከሚል የተሳሳተ ድምዳሜ የመነጨ ይመስለኛል።

በእኔ እምነት ኢትዮጵያ ከዓለም ባንክ ጋር ግንኙነት ስላላት ባንኩ በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ ገብቶ የሀገራችንን ልማት ይመራል ማለት አይደለም። ባንኩ የልማት ደጋፊያችን እንጂ ልማቱን የሚፈፅም አካል አይደለም። ሊሆንም አይችልም። ርግጥ የባንኩ የልማት አጋርነት ጠቃሚያችን ቢሆንም፤ የህዳሴው ግድብ ግን በኢትዮጵያዊያን እንጂ በማንም የሚመራ አይደለም። ቀደም ሲል እንዳልኩት የግድቡ ፋይናንስ ባለቤቶች የኢትዮጵያ ህዝቦች ናቸው። ግድቡ የሀገሪቱ የባንዴራ ፕሮጀክት ነው። ይህ ፕሮጀክት ሊቆም የሚችለው በህዝቡ የተባበረ ሃይል ተገንብቶ ሲያልቅ ብቻ ነው። እናም በዚህ ጉዳይ ላይ ወሳኙ የኢትዮጵያ ህዝብና የኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ በመሆኑ የማንም እጅ ጣልቃ ሊገባበት አይችልም። የግብፅ ሚዲያዎችም ከተለመደው “ውሃችን አይነካም” መዝሙር ወጥተው ስለ ትብብርና ስለ ጋራ ተጠቃሚነት ጉዳይ ቢያወሱ ለሁላችንም የሚበጅ ይመስለኛል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy