Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ወደነበርንበት ለመመለስ

0 246

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ወደነበርንበት ለመመለስ

 

ዮናስ

 

ያልተማከለው ፌዴራላዊ አስተዳደር ሁሉም ህዝቦች ያላቸውን ፀጋ በማልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑና በፌዴራላዊ ስርዓቱ ላይ በጎ አመለካከት እንዲያዳብሩ አስችሏል። መንግስት ሁሉም ክልሎች በየራሳቸው ፍጥነት እያደጉ፣ ነገር ግን ደግሞ በአቅም ልዩነት ምክንያት የሚፈጠረውን ያልተመጣጠነ እድገት ለማካካስ እገዛ አድርጓል እያደረገም ነው። በተለይ በዳር አካባቢ የሚገኙ ታዳጊ ማህበረሰቦችን ከመቼውም ጊዜ በላቀ ኢትዮጵያዊ ገመድ እርስ በርስ እንዲተሳሰሩ አድርጓል፤ እያደረገም ነው። ይህ በሆነበት አግባብ በተነሱ ግጭቶች በርካቶች ሞተዋል፤ ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል። ግን ደግሞ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም እየተደረገ ባለው ጥረት ህዝቡ እጅና ጓንት ሆኖ እየተሳተፈ መሆኑ የፌደራላዊ ስርአቱ አስተማማኝነት ማሳያ ነው። በተለይ የኦሮሚያ ክልል በግጭቱ የተፈናቀሉ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ለ86ሺሕ ዜጎች የመኖሪያ ቤት ለመሥራትና የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ላይ ተሳታፊ የሆኑት አካላት የብዙህነታችን ጥግጋት እና የስርአቱ ትክክለኝነት ማሳያዎች ናቸው፡፡

 

በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭት የተፈናቀሉ ዜጎችን ለማቋቋም የፌዴራል መንግሥት ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት  መድቦም እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ይፋ ከሆነ ሰነባብቷል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ ሌሎች ሦስት ክልሎችና ባለሀብቶች ባደረጉት ድጋፍም ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉም ጭምር በተመሳሳይ። ከሁለቱ ክልሎች ለተፈናቀሉ ዜጎች ከ900 ሚሊዮን ብር በላይ ምግብ ነክ ለሆኑና ምግብ ነክ ላልሆኑ የፌዴራሉ መንግሥት ወጪ ማድረጉንና ይህ ጥረት ወደነበርንበት እስክንመለስም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን መንግስት አስታውቋል፡፡

 

ዜጎችን በማቋቋም ሒደትም የሶማሌ ክልል በእንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ ያስታወቀው መንግስት፤ በተደረገው ጥናት መሠረት ከሁሉም ወገኖች የተፈናቀሉ አካላት ወደ ቀድሞ ቀዬአቸው ተመልሰው መሄድ የሚፈልጉና የማይፈልጉ እንዳሉ ማረጋገጡን ይፋ አድርጓል፡፡ ስለሆነም ወደነበርንበት እስክንመለስም ስራው ይቀጥላል። ከሁሉም በላይ ሰላማችን ወደነበረበት እስኪመለስ ድረስ የተጠናከረ ስራ ያስፈልጋል።  ለዚህም  በሁለቱም  ክልሎች ሰላም በማደፍረስ የተጠረጠሩ ዜጎችን ወደ ሕግ የማቅረቡ ስራ መቀላጠፍ አለበት፡፡ የሕግ የበላይነት ከማረጋገጥ አኳያ በሁለቱ ክልሎች እጃቸው አለበት ተብለው ከተጠረጠሩና የእስር ማዘዣ ከወጣባቸው 55 ሰዎች መካከል እስካሁን በቁጥጥር ሥር የዋሉት 15 ብቻ  መሆናቸው አሳሳቢ መሆኑን ማጤን ያስፈልጋል።

 

በአሁኑ ሰአት አገሪቱን ከጫፍ ጫፍ የሚያስተሳስር የማህበራዊና የኢኮኖሚያዊ መሰረተ ልማት ተስፋፍቷል። ይህንንም በተናጠል ሳይሆን በጋራ ለመጠቀም የሚቻልበት እድል ተፈጥሯል። በዴሞክራሲ ላይ የተመሰረተውን አገራዊ ገመድ በጠንካራ የኢኮኖሚና የመሰረተ ልማት አውታር ለማወፈር ተችሏል። ይህ በሆነበት አግባብ ለሚነሱ ግጭቶች ምክንያት ሊሆን የሚችለው ስርአቱ ሳይሆን ኪራይ ሰብሳቢነት ብቻ ነው ብሎ ከስሩ ማስመር ስህተት ሊሆን አይችልም።   

 

በአገራችን ህዝቦች ዘንድ በልዩ ልዩ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ከመቼውም ጊዜ የተሻለ ብሔራዊ መግባባት ተፈጥሯል። ህገ መንግስቱ የዴሞክራሲና የሰላም፣ የፍትህና የእኩልነት ዋስትና እንደሆነ መግባባት ላይ ተደርሷል። እየተገነባ የሚገኘው ሥርዓት የገበያ መሆን እንዳለበትና ሰዎች በሰሩት ልክ የመጠቀም ህጋዊ ዋስትና ያገኙ በመሆናቸውም ላይ ተመሳሳይ መግባባት ተፈጥሯል፡፡ ይህ ማለት ግን የዚህ ስርአት ቀበኛ የሆኑ ጸረ ዴሞክራሲ ሃይሎች በስርአቱ ውስጥ የሉም ማለት አይደለም። እንዲያውም ከነዚህ ሁከቶች በስተጀርባም ስለመኖራቸው አሁን ተረጋግጧል።  

 

በዚሁም ላይ ከፈጣኑ እድገት ጋር ተያይዘው የተከሰቱ ነባርም ሆኑ አዳዲስ የስርዓቱ ችግሮችም እንደዚሁ ከሞላ ጎደል የጋራ ስምምነት ተይዞባቸዋል። በእነዚህ መሰረታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከመቼውም ጊዜ የተሻለ ብሔራዊ መግባባት የተፈጠረ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን በፅኑ የፖለቲካ ኢኮኖሚ መሰረት ላይ የተገነባ ባለመሆኑ አሁንም የመዋለልና ወደፊትና ወደኋላ የመመለስ አዝማሚያዎች እየታዩ ነው። በዚህች ሃገር ኢህአዴግ የአገሪቱን ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት ብቻ ሳይሆን ዴሞክራሲያዊ አንድነቷን የማስጠበቅ ችሎታ ጭምር እንዳለው የሚጠራጠሩ ሰዎች ቁጥር እየተበራከተ ነው።  ስለምን ሲባል ከአፈጻጸም ችግሮች በላይ በስተጀርባ ኪራይ ሰብሳቢዎች ስለሚፈነጩ ነው።

 

ህገ መንግስታዊ ድንጋጌዎችን በቶሎ መሬት ላይ ያለማውረድ ችግሮች ደግሞ የሚያስከፍሉት ዋጋ ከባድ ነው።  

በጥቅሉ ቀደም ሲል በአገራችን ብሔር ብሔረሰቦች ካላግባብ የተያዙበት መንገድ ለግጭትና ለዘመናት የእርስ በርእስ ጦርነት መንስዔ እንደነበር በመገንዘብ አዲሱ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ብዝሃነትን በማወቅና በመቀበል እንዲሁም በአግባቡ በማስተዳደር ላይ እንዲመሰረት ተደርጓል፡፡ ፌዴራላዊ  ስርዓቱ  ኢትዮጵያ የብዙ ህዝቦች አገር የመሆኗን እውነታ ያለማቅማማት የሚቀበል ስርአት ነው፡፡ ግን ደግሞ ፍትሃዊ የሆኑ የህዝብ ጥያቄዎችን፤ ያለአንዳች ማቅማማት ስርአቱ የተቀበላቸውን ጥያቄዎች በወቅቱ ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኝ ባለመደረጉ በአንዳንድ አካባቢዎች ለግጭት መንስኤ ሆኖ ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል፡፡

እዚህ ጋር አሁንም ሊሰመርበት የሚገባው አንድ አቢይ ነጥብ አለ። አንዳንድ ወገኖች ግጭቱ የተቀሰቀሰው ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርአቱ በራሱ የግጭት መንስዔ ስለሆነ ነው የሚሉት ጉዳይ ነው። ያም ሆኖ ግን ፌዴራላዊ ስርአቱ በመሰረታዊ ባህሪው የማህበረሰቦችን ማንነት ማክበር በመሆኑ ችግር ፈች እንጅ ችግር ፈጣሪ ወይም አባባሽ ሊሆን ከቶም አይችልም፡፡ ይህም አዲሱ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ሃገራችን በዘመናዊ ታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ሩብ ምዕተ ዓመት የሞላው ረዥም የሰላም ዘመን እንድትኖር፣  ህዝቦቿ ለሃያ ስድስት ዓመታት በሰላም፣ በፍቅርና በመካባበር እንዲኖሩ ያስቻለን በመሆኑ የሚረጋገጥ ነው። ስለሆነም ወደነበርንበት ለመመለስ በሚደረግ ጥረት የሚገጥሙ ፈተናዎችን በድል መወጣት የምንችለው ይህንን የፌደራላዊ ስርአቱን ትሩፋት ጋሻና መከታ በማድረግ ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy