ውይይት፤ ድርድር፤ እና ክርክር የሁል ጊዜ ምርጫ
ስሜነህ
መንግስት የአገራችን የዴሞክራሲ ስርዓት የበለጠ እንዲጎለብት ባለው የጸና አቋም የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር እንዲያደርጉ ሁኔታዎችን ያመቻቸ መሆኑ ይታወቃል፤ አስራ አምስት ፓርቲዎች በድርድር ሂደት ላይ መሆናቸውም እንዲሁ።
ለድርድር ተይዘው ከነበሩት አጀንዳዎች መካከል የፀረ ሽብር አዋጁ ለምን ለድርድር ሊቀርብ እንደሚገባ ገዥው ፓርቲ ላቀረበው የማብራሪያ ጥያቄ የውቅቱ የኢዴፓ ሊቀመንበር ዶ/ር ጫኔ ከበደ ‹‹አዋጁ ሙሉ ለሙሉ ይሰረዝ የሚል ጥያቄ የለኝም፤ ነገር ግን በአዋጁ የትርጉም ይዘት የተነሳ የሰብአዊ መብት ጥሰት እያጋጠመ በመሆኑ ድርድር ሊደረግበት ይገባል›› ማለታቸው ይታወሳል። የመኢአድ ተወካይ አቶ አዳነ ጥላሁን በበኩላቸው፤ “ህዝባችን በህጉ እየተሳበበ የሚንገላታበትና ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች በህጉ ምክንያት የሚታሰሩበት፣ ለስደት የሚዳረጉበት ሁኔታ እንዳለና ለሰብአዊ መብት ጥሰት መነሻ የሆኑ አንቀፆችን በማካተቱ ድርድር ሊደረግበት ይገባል” ብለው የነበረ መሆኑም በተመሳሳይ ይታወሳል። አሁን የሁሉም ድምጽ በድርድሩ ላይ ስለመወከሉ ያረጋገጠልን ይህና በጸረ ሽብር አዋጁ ላይ የተጀመረው ድርድር ነው።
የድርድሩ ይዘትም በዚሁ አዋጅ ላይ አንቀጾች እንዲሻሻሉ፣ እንዲሰረዙና አዲስ እንዲጨመሩ ነው። ተደራዳሪዎቹ ይህ ያስፈለገበትን ምክንያት ሲጠቅሱ አዋጁ ሕገ መንግሥቱንና የዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን የሚቃረን በመሆኑ ነው ብለዋል። በሕገ መንግሥቱ የተደነገጉትን ሰብዓዊ መብቶች በመፃረር ዜጎች በነፃነት የማሰብ፣ የመደራጀት፣ የመሰብሰብና በቡድን ሆኖ ቅሬታ የማቅረብ መብትን የሚገድብ መሆኑንም በተጨማሪነት ስለማቅረባቸው ተሰምቷል። ፖለቲከኞችን፣ ጋዜጠኞችንና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን እንቅስቃሴ በእጅጉ ስለሚቆጣጠር ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚደረገውን ተሳትፎ ያዳክማል በማለት ምክንያታቸውን የዘረዘሩት ተደራዳሪዎች፤ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሰላማዊና ሕጋዊ ትግል በማዳከም፣ በመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ ላይ ችግር የፈጠሩ በመሆናቸው ምክንያት መሻሻልና መሰረዝ አለባቸው ያሉዋቸውን አንቀጾች በተመለከተ ሃሳብ አቅርበዋል።
በአገሪቱ የምርጫ ማዕቀፍ ሕጎች፣ ተያያዥ ሕጎችና አዋጆች ላይ ከገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ጋር ድርድር በማድረግ ላይ የሚገኙት 15 አገር አቀፍ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 ላይ እያደርጉ ያሉትን ድርድር ዓርብ ታኅሳስ 13 ቀን 2010 ዓ.ም ነው የጀመሩት።
ከ15ቱ ተደራዳሪ ፓርቲዎች መካከል አንቀጽ 5(1)፣ 19(1) ከ3 እስከ 12፣ እንዲሁም አንቀጽ 22 እንዲሻሻሉ፤ አንቀጽ 3(6)፣ 5(1) (ሀ)፣ 14፣ 21፣ 23 እና አንቀጽ 25 ደግሞ እንዲሰረዙ የ11 የፖለቲካ ፓርቲዎች ኅብረት ጠይቋል፡፡ ይኸው ህብረት በሽብርተኝነት ተጠርጥሮ የተያዘ ግለሰብ የሚከተሉት ሰብዓዊ መብቶች ይኖሩታል፤ ሰብዓዊ ክብሩን በሚነካ ሁኔታ መያዝና ጭካኔ የተሞላበት ምርመራ መደረግ የለበትም፤ በቤተሰቡና በጓደኞቹ የመጎብኘት መብት አይከለከልም፤ የተያዘበትን ጉዳይ በጽሑፍም ሆነ በቃል ማወቅ አለበት፤ ተገዶ ቃል እንዲሰጥ መደረግ የለበትምና የተያዘበት/የታገደበት ጉዳይ በሚገባው ቋንቋ ተተርጉሞ ሊነገረው ይገባል፤ የሚሉ ድንጋጌዎች ደግሞ እንዲጨመሩ ስለመጠየቁም ተሰምቷል።
ይህ ሂደት የሚያጠይቀው ነገር ቢኖር በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል በድርድር ወቅት በያንዳንዱ ጉዳይ ተቀራርቦ መነጋገር እየተለመደ መምጣቱን ነው። አሁን ያለ ልዩነት ቢኖር በአካሄድ ጉዳዮች ላይ የሚኖር ልዩነት ነው። ይህም ቢሆን መሰረታዊ ችግር አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም። ችግር የሚሆነው ላይመለሱ በህግና ህገመንግስታዊ አግባብ የተቀበሩ አጀንዳዎችን አግበስብሶ እንወያይ ማለትና ለፓርቲዎች ከተሰጠ ስልጣን በላይ ርቆ የህዝብን መብትና ፍላጎት የሚጻረሩ ጉዳዮች ላይ ካልተደራደርን ብሎ አሻፈረኝ ማለት ነው።
ምንም በማያሻማ መልክ ሃገሪቷም ሆነች ህዝቦቿ በድርድር ወቅት ከፓርቲዎች የሚፈልጉት የህዝብንና የአገርን ጥቅም ቀዳሚ አጀንዳቸው በማድረግ የአገራችንን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለማጎልበት በሚያስችል አቅጣጫ እንዲቃኙ ብቻ ነው። የዴሞክራሲ ስርዓቱን በማጎልበት ልማትን ማፋጠን የሚያስችል የመደራደሪያ አጀንዳ እንዲያቀርቡ ነው። ሁሉም የፖሊቲካ ፓርቲዎች ሰጥቶ መቀበልን እንደመርህ ሲከተሉ እና እንዲህ የሁሉም ድምጽ ተወክሎ ሲታይ ደግሞ ማድነቅ ተገቢ ነው።
ለአገር ሰላም፣ መረጋጋት፣ ዕድገት፣ ብልፅግና፣ እንዲሁም ለሕዝብ የተሟላ እርካታ ሲባል ጤነኛ የሆነ ሥርዓት መገንባት መቼም ቢሆን የማይታለፍ መሠረታዊ ጉዳይ ነው። አገር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ያስፈልጋታል ሲባል በዴሞክራሲ መመዘኛ ብቁ የሆነ ቁመና መኖር አለበት ማለት ነው፡፡ ይህ ዕውን ይሆን ዘንድ ደግሞ እንዲህ የሁሉም ድምጽ የተወከለበትና በሕግ የበላይነት ላይ የተመሠረተ ጤናማ የውይይት ሥርዓት ሁሌም ቢሆን መለመድ አለበት።
ዜጎች ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በፈቃዳቸው እንዲመሠረት ዕውቀትን የተመረኮዘ ግንዛቤ ከነዚህ ፓርቲዎች ይጠብቃሉ። የሕግ የበላይነት ሲከበር ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ፣ የመሰብሰብ፣ የመደራጀትና በነፃነት ለመምረጥም ሆነ ለመመረጥ የሚያስችላቸው ዕድል በጣም የሰፋ ይሆናል፡፡ ይህ ዓይነቱ የተቀደሰ ሐሳብ ተግባራዊ ይሆን ዘንድ ደግሞ የፓርቲዎች ሚና ግንባር ቀደም ነው። ሚናቸው የሚለካው ደግሞ በአሉባልታ ላይ የተመሠረቱ ሳይሆን በመረጃና በማስረጃ የዳበሩ አስተሳሰቦችን ማንሸራሸር ሲችሉ ነው፡፡
ሰላማዊና ሕጋዊ የፖለቲካ ድርድሩ አሁን እንደሚታየው እና ከላይ በተመለከተው መልኩ ለአገራቸው ከሚታሰበው በላይ አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችሉ ወገኖች የሚሳተፉበት እና የሁሉም ድምጽ የተወከለበት ሆኗል። በዚሁ ላይ ደግሞ አገራቸውን በተለያዩ የሙያ መስኮች የሚያገለግሉ ወገኖች በነፃነት ያደራጁዋቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ብርታትና ጥንካሬ አግኝተው የሚፈለግባቸውን ሚና እንዲጫወቱ፣ ደጋፊ ወይም አባል መሆን የሚፈልጉ ዜጎች ያለምንም መሸማቀቅ እንዲሳተፉባቸው ቢደረግ የአገሪቱ የወደፊት ተስፋ ይለመልማል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው የሕዝቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎ በተግባር ሲረጋገጥና በሕግ የተደነገጉ መብቶች ሥራ ላይ ሲውሉ ብቻ ነው፡፡
ስናጠቃልለው፣ ህዝብ የሚሻው በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ለአገራቸው ክብር፣ ዕድገትና ብልፅግና አስተዋጽኦ ይኖረናል የሚሉ ሁሉ በቀና መንፈስ አማራጭ ሃሳባቸውን እንዲያቀርቡ ነው፡፡ በዚህም ለልማታችን መፋጠን ቅድመ ሁኔታ የሆነውን የዴሞክራሲያዊ ስርአት ማጎልበት ይቻላል። ይህንን ማድረግ ሲቻል መቀራረብ፣ መነጋገርና መደራደር ችግር አይሆንም።