Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ዕመኑ፣ ዕውነታው ይህ ነው!

0 349

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

 

ዕመኑ፣ ዕውነታው ይህ ነው!

አባ መላኩ

ሰሞኑን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን  በግብጽ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት  ሲያካሂዱ ሰንብተዋል። አባይን በተመለከተም ለግብጽ ህዝብና መንግስት የመንግስታቸውን የማይለወጥ አቋም አስረግጠው ገጸዋል።  ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት የግብጻዊያንን ህይወት ለማመሳቃቀል እና ልማታቸውን ለማደነቃቀፍ ምንም ዓይነት ፍላጎት  የላቸውም። የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት አቋም ለዘመናት በባህልና በሃይማኖት ከተሳሰረውና ከሚደጋገፈው ከግብጽ ህዝብ ጋር ይቅርና ከማንኛውም የዓለም አገራት ህዝቦች ጋር  አብሮ የመኖርና አብሮ የመልማት ጠንካራ  ፍላጎት ያለው ነው። ግብጻዊያን ተረዱን ዕውነታው ጠቅላያችን የገለጹላችሁ ነው። ለሁላችንም የሚበጀው መተማመን፣ መደጋገፍና አብሮ ማደግ እንጂ በትንሹም በትልቁም  አካባቢውን  የውጥረት  ቀጠና ማድረጉ ለሁላችንም የሚበጅ አይሆንም።   

 

አባይን በተመለከተ ዛሬ ላይ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ለግብጻዊያን  ያረጋገጡላቸው  የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት አሁንም  ወደፊትም  የሚያራምዱት አቋም ቀድሞ ያራምዱት የነበረው “የፍትሃዊ  ተጠቃሚነት” መርህ ነው።  የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት  እየጠየቁ ያሉት  በተፋሰሱ ላይ “የእኩል ተጠቃሚነት” መርህ ሳይሆን  “የፍትሃዊ  ተጠቃሚነት” መርህን  ነው።  ይህም ማለት  ግብጻዊያን ወንድሞቻችን ሳተጎዱ በድህነት እየኖረ ያለው ኢትጵያዊ  ወንድማችሁ ሃይል ያግኝና አካባቢውን ያልማ ነው። ግብጻዊያን  ሳትጎዱ  እኛ እንጠቀም የሚል የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት አቋም በየትኛውም መስፈርት እጅግ ቅን አስተሳሰብና  ተቀባይነት ያለው አቋም ነው። ኢትዮጵያ  የዓባይን ውሃ በተመለከተ  በዓለም ዓቀፉ መርህ ልዳኝ ብትል  የጋራ ሃብትን “እኩል የመጠቀም” መብቷ እንደሚረጋገጥ ብታውቅም  ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ካላት ፍላጎት “ፍትሃዊ” የሚለውን መርህ  ተግብራለች። ይህ ነው መልካም ጉርብትናን፤ መልካም ወንድማማችነትን  የሚያጠናክር ተግባር።  

 

የኢትዮጵያ መንግስት ወሰን ተሻጋሪ ወንዞች በዓለም ዓቀፍ ስምምነት መሰረት የሚተዳደሩ መሆናቸውን ከግንዛቤ በማስገባት የህዳሴው ግድብ ፕሮጀክትን ይፋ ሲያደርግ  ጀምሮ ሳይንሳዊ መንገድን መሰረት አድርጎ ነው።  በመሰረቱ ኢትዮጵያ እንደ ሱዳን ሰፊ የመስኖ መሬት የሌላት ከመሆኑም በላይ የግድቡ ስፍራ ወደ ሱዳን ጠረፍ የተጠጋ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ  የህዳሴው ግድብ ከኃይል ማመንጫነት ባሻገር ለመስኖ ስራ የሚያገለግል ፕሮጀክት  አይደለም። ይህን ጉዳይም  የኢትዮጵያ መንግስት  ለሚመለከታቸው አካላት  በተደጋጋሚ አሳውቋል። የግብጽ ፖለቲከኞችና ምሁራን አውቆ የተኛ  እንደሚባለው ሆኖ እንጂ  ዕውነታውን  አጥተውት አይመስለኝም። ለማንኛውም ጠቅላያችን አሁንም  በድጋሜ  እውነታውን በሚገባ መንገድ  አስረግጠው ያብራሩት ይመስለኛል። የኢትዮጵያ መንግስት እየገነባ ያለው ፕሮጀክት የግብጽ ህዝብ እዚህ ግባ የሚባል ጉዳት ሳያደርስ የኢትዮጵያ ህዝቦች ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ፕሮጅክት ነው። እንደእኔ እንደኔ መልካም ጉርብትና ማለት ይህ ነው። ግብጻዊያን  ታላቁ የኢትዮጵያን  የህዳሴ ግድብ  ፕሮጀክት የሚያመሰግኑበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፤

 

የኢትዮጵያ ህዝብና  መንግስት ለግብፃዊያን ወንድሞቻችን እንዳሰብንላቸው፣ በባለፉት የግብጽ መንግስታት ዘመን  የነበሩት ፖለቲከኞችና ምሁራኖች የተቸረው ምላሽ እጅግ ኋላ ቀርና በየትኛውም መስፈርት በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ተቀባይነት ሊኖረው የሚችል አስተሳሰብ ሆኖ አልተገኘም። ለአብነት  በሙሃመድ ሙርሲ ዘመን “ጠብታ ውሃ በጠብታ ደማችን ይተካል’’ የሚሉ መፈክሮችን በአደባባይ ሲያሰሙ እንደነበር  የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። ይሁንና የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ሂሳብን ማወራረድ  ውስጥ  መግባት ሳይፈልጉ፤  ከወረደ ጋር አብረው ሳይወርዱ  ነገሮችን በሰከነ ሁኔታ  መያዝ  በመቻላቸው  ግጭትን ማስወገድ ችለዋል።    ዛሬ ግብጻዊያን የቀድሞው የፉከራና የማስፈራራት ፖለቲካ  የሚበጅ  አካሄድ ሆኖ  እንዳላገኙት  ይሰማኛል። ለጠቅላያችን የነበራቸው አቀባበል የሚያመላክተው ነገር እንዳለ ያሳያል።

 

ግብጻዊያን ፖለቲከኞችና ምሁራን  አገራችንን በድሮው መነጽራቸው  መመልከቱ እንደማያዋጣ  የተገነዘቡት ይመስለኛል። በአንድ ወቅት አንድ የግብጽ ምሁር እንዲህ ሲል ጽፎ ነበር። ኢትዮጵያን የመሰለ ድሃና ኋላ ቀር አገር እንዲህ ያለ ግዙፍ ግድብ “ስድስት ሺህ ሜጋ ዋት’’ የሚያመነጭ ፕሮጀክት ምን ያደርግላታል? ሆን ብላ በግብፅ ላይ ጫና ለመፍጠር የምታደርገው ጥረት  ነው ሲል አስፍሯል። እውነታው ግን ይህ አይደለም።  ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ  በፈጣን  የለውጥ  ምህዋር ውስጥ ናት።  የኢንዱስትሪ አብዮት በኢትዮጵያ  ፈንድቷል። በኢትዮጵያ 12 የኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲሁም  ወደ 17 የሚሆኑ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ የጎጆ እንዱስትሪዎች በመገንባት ላይ ናቸው። በመሆኑም አሁን ላይ የኢሌክትሪክ አቅርቦትን ማሳደግ ለኢትዮጵያ መንግስት የሞት የሽረት ጉዳይ ነው።  በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል የተደረገ ጥናት እንደሚያመላክተው በየዓመቱ የአገራችን የኤሌክትሪክ  ፍጆታ   በአማካኝ  ከ25- 30 በመቶ  ዕድገት እያሳየ ነው። ይህን ፍጎት ለማሟላት ደግሞ  እንደቀድሞው በቁጥቁጥ የሃይል  ማመንጫዎች ግንባታ   ማሳካት አይቻልም። ይህን የተረዳው የኢትዮጵያ መንግስት እንደጊቤ ሶስትና ታላቁ የህዳሴ ግድብ ያሉ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን መገንባቱን ተያይዞታል። ዕውነታው ይህ ነው።  

 

ግብፃዊያን ፖለቲከኞች የውስጥ ችግሮቻቸውን በአባይ ለመሸፋፈን ካልሆነ በስተቀር የታላቁ የህዳሴ ግድብ ያለመግባባት ምንጭ ሊሆን የሚችልበት ምንም አይነት ክፍተት የለም። ምክንያቱም ይህን ፕሮጀክት በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግስት ዕውነታውን ለሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ሲገልጽ ቆይቷል።  ግብፃዊያኖች በበጎ አልተመለከቱትም እንጂ የላይኞቹ የተፋሰስ አገራት በግንቦት 24/2010 በኢንቴቢ ኡጋንዳ ያደረጉት ስምምነት  በተፋሰሱ አገራት መካከል  ፍትሃዊ  ተጠቃሚነትን  ማስፈንን  የተመለከተ ነው።  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ  ዓለማችን  በአየር ለውጥ ሳቢያ  ቀውስ ውስጥ እየገባች ነው። በተለይ ምስራቅ አፍሪካ  በከባድ ድርቅ  ሳቢያ  ፈተና  ውስጥ  እየገባ ነው። ይህ በተግባር እየተመለከትነው ነው። በድርቅ ሳቢያ  የአባይ ወንዝ ዓመታዊ የፍሰት መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ እንደመጣ  የተለያዩ ጥናቶች እያመላከቱ ናቸው። በመሆኑም  በላይኞቹ የተፋሰስ አገራት  በተለይ ዋንኛው የውሃ መገኛ በሆነችው ኢትዮጵያ ውጤታማ የሆነ የአካባቢ ጥበቃ  ስራ ካልተከናወነ በስተቀር  የአባይ ወንዝ ደህንነት ቀጣይነት እንደማይኖረው ግብፃዊያኖች ሊያውቁት ይገባል። በወንዙ ቀጣይ ህይወት ከማረጋገጥ አኳያ  በኢትዮጵያ የሚከናወን የተፋሰስ ልማት እጅግ ወሳኝ ነው። የተፋሰስ ልማት ደግሞ  ሊካሄድ የሚችለው የኢትዮጵያ ህዝብ  ወንዙ  የእኔ ነው  የሚል ስሜት  እንዲያድርበት ከወንዙ  ፍትሃዊ ተጠቃሚነቱ  ሲረጋገጥለት ብቻ ነው።  

 

ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ በተመለከተ ገና ከመጀመሪያ  ጊዜ ጀምሮ ባቀረበችው ሳይንሳዊ  ትንታኔዎች ሳቢያ  የሱዳንን ይሁንታ ማግኘት ችላለች። ሱዳን ለህዳሴው ግድብ ድጓፏን የለገሰችው የህዳሴውን ፕሮጀክት በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግስት ያቀረበውን ተጨባጭ ማስረጃዎች በመመርመርና እንዲሁም ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ከገነባቻቸው ፕሮጀክቶች ያገኘችውን ጥቅም ታሳቢ አድርጋ ነው። ግብጻዊያን ፖለቲከኞችና ሙሁራኖች ኢትዮጵያን በህደሴው ግድብ ጉዳይ በሳይንሳዊ መንገድ መሞገት ሲሳናቸው ጉዳዩን ፖለቲካዊ መልክ ለማላበስ ቢሯሯጡም አልተሳካላቸውም። የአባይ ጉዳይ መፍትሄ በጠረጰዛ ዙሪያ እንጂ ከየትኛውም መድረክ ማግኘት እንደማይቻል ግብጻዊያን ዘግይተውም ቢሆን የተረዱት ይመስለኛል።  ዛሬም ደግመን ደጋግመን  የምንናገረው ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ጀርባ ከአንድ መቶ ሚሊዮን በላይ  ኢትዮጵያዊያኖች እንዳሉ  ሊታወቅ ይገባል። ይህን በተመለከተ ታላቁ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ የታላቁን የኢትዮጵያ  የህዳሴ ግድባችንን  መሰረት በጣሉበት ጊዜ እንዳሉት “መሃንዲሶቹም እኛው፣ ግንበኞቹም  እኛው፣ የገንዘብ  ምንጮቹም  እኛው” በማለት የተናገሩት ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ ለእኛው በእኛው የሚሰራ ሰፊ ህዝባዊ መሰረት ያለው መሆኑን ለማመላከት  ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy