Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የልማታችን ፈርጥ

0 292

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የልማታችን ፈርጥ

                                                           ታዬ ከበደ

የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ በትምህርት መሰረት ልማት ዝርጋት እና አገልግሎት ማስፋፋት ረገድ ወደፊት ከተራመዱ የአፍሪካ አገራት መካከል አንዷ መሆኗን ሰሞኑን ዘግበዋል። መንግስት ትምህርትን በማዘመን፣ ተደራሽነቱን በማስፋፋትና ጥራቱን በመጠበቅ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ዘገባው ያትታል።

ከበጀት አኳያም አገራችን ለትምሀርት ዘርፍ ባለፉት ተከታታይ አስር ዓመታት ውስጥ ካላት በጀት በየዓመቱ በአማካይ 18 በመቶውን ለትምህርት ከመደቡ በጣት የሚቆጠሩ ጥቂት የአፍሪካ አገራት ተርታ እንድትሰለፍ ያደረጋት መሆኑንም አብራርቷል። ይህም መንግስት ለዘርፉ ምን ያህል ትኩረት እንደሰጠና ‘ያለ ትምህርት ዕድገት የለም!’ ብሎ በቁርጠኝነት መነሳቱን የሚያሳይ ይመስለኛል።

እርግጥ ዘገባው ትክክል ነው። መንግሥት የአገራችንን የትምህር ዘርፍ ተደራሽ፣ ጥራቱን የጠበቀና የልማት መሰረት እንዲሆን እየሰራ ነው። ቀደም ባሉት ጊዜያት በአገራችን በተለያዩ ደረጃዎች ይካሄዱ የነበሩ የልማት ስራዎችን ጎብኝተን አሊያም በመገናኛ ብዙሃን ተከታትለናቸው ይሆናል። ከእነዚህም መካከል በግዙፍነታቸው አልያም በዘመናዊነታቸው እንግዳ የሆኑብን የሚታጡ አይመስለኝም።

ያኔ በአገሪቱ አንድም የግል ዩኒቨርስቲ ሆነ ኮሌጅ አልነበረም፡፡ በአሁኑ ሰዓት ግን ትምህርት በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ዘልቆ ገብቷል፡፡ በከተሞችም እንዲሁ ተስፋፍቷል፡፡ እድሜው ለትምህርት  የደረሰ ህጻን ሁሉ የማዕዱ ተቋዳሽ የሆነበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በአገሪቱ ያለው የትምህርት ሽፋንም ሰፍቷል፡፡ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህጻናት በሙሉ የሚታደሙበት ማዕድ ሆኗል፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በገጠር ቀበሌዎች ሳይቀር ተስፋፍተዋል፡፡

ዛሬ ከሶስቱ ኢትዮጵያዊ አንዱ በትምህርት ገበታ ላይ እንዲገኝ አድርጓል፡፡ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩ የትምህርትን አስፈላጊነት ከማስተማር ጎን ለጎን ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር  በትምህርት ቤቶች ለሚገኙ ህፃናት የምግብ አገልግሎት እየተሰጠ ነው፡፡

በአገራችን ባለፉት 26 ዓመታት ከተሰሩት ተግባራት አንዱ በአገሪቱ ፍትሃዊ የትምህርት ስርጭት እንዲኖር መደረጉ ነው፡፡ በእያንዳንዱ ክልል በርካታ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ ኮሌጆች እና ዩኒቨርስቲዎች ተቋቁመው የትምህርት አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡ በአገሪቱ የነበሩት የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ታድሰዋል፣ የማስፋፊያ ግንባታም ተደርጎላቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በርካታ አዳዲስ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል፡፡

የቴክኒክና ሙያ ተቋማት በልዩ ትኩረት እንዲስፋፉ በመደረጉ የተቋማቱ ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መጥቷል፡፡ ይህ የአገሪቱ የምጣኔ ሀብት እድገት የሚጠይቀውን የሰው ኃይል ከማፍራት ረገድ የማይተካ ሚና እንዳለው ባለፉት 26 ዓመታት በተግባር ታይቷል፡፡ ተማሪዎች ስራ ፈጣሪ እንጂ ክፍት ስራ ፈላጊ እንዳይሆኑ በማድረግ ረገድም ውጤታማ ተግባር እየፈፀሙ ነው፤ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፡፡ ባለፉት 26 ዓመታት ወጣቶች ስራ ፈጣሪና ባለሙያ ሆነው የሚሰለጥኑበት ሁኔታ ተመቻችቷል፡፡ በአገሪቱ ሥራ ፈጣሪና በራሱ የሚተማመን ወጣት ማፍራት የሚችሉ ከአምስት መቶ በላይ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ተቋቁመው የሥልጠና አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም እንዲሁ ተስፋፍተዋል። ተቋማቱ በአንድ በኩል አገሪቱ የምትፈልገውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ያፈራሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የኅብረተሰቡን ችግር የሚፈቱ ጥናቶችንና ምርምሮችን ያደርጋሉ፡፡ ከዚህ አንፃር ባለፉት 26 ዓመታት በአገሪቱ የነበሩት ሁለት ዩኒቨርስቲዎች እንዲስፋፉና ቁጥራቸውም ከፍ እንዲል ብሎም ለትምህርት አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶች እንዲሟሉላቸው በመደረጉ የቅበላ አቅማቸው አድጓል፡፡ የሚሰጡት የሥልጠና ዓይነትና ደረጃም በዚያው ልክ እየሰፋ ሄዷል፡፡

እነዚህ ተቋማት ቀደም ሲል የነበረው የቅበላ አቅም ከ10 በመቶ አይበልጥም ነበር፡፡ ከ26 ዓመታት በኋላ ስናይ ግን በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ተማሪዎች መቀበል የሚያስችል አቅም ተገንብቷል፡፡ በአገሪቱ ያሉት ዩኒቨርስቲዎች በየዓመቱ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎችን ይቀበላሉ፤ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩትን ደግሞ ያስመርቃሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የኅብረተሰቡን ችግር መፍታት የሚያስችሉ የምርምርና የጥናት ተግባራት ላይ ማተኮር መጀመራቸው ነው፡፡

እንደሚታወቀው ሁሉ ባለፉት ስርዓቶች ጥናትና ምርምር ትኩረት የተሰጠው ዘርፍ አልነበረም፡፡ በዩኒቨርስቲዎች የሚደረጉ ጥናቶችም የአገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘቡና  የህዝቡን ተጨባጭ ችግሮች ለመፍታት ያለሙ አልነበሩም፡፡ የነበረው ሥርዓትም ይህንን የሚያበረታታ አልነበረም፡፡

ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ዩኒቨርስቲዎች የአርሶና አርብቶ አደሩን ኑሮ ለማሻሻል የሚያግዙ በርካታ ጥናቶችና ምርምሮች አካሂደዋል፡፡ በጓሮ አትክልት፣ በእንስሳት እርባታ፣ በመስኖ ስራ፣ በአፈር ለምነት እና በምርጥ ዘር አቅርቦት የተለያዩ የምርምር ተግባራት ተከናውነው ወደ ተግባር ተለውጠዋል፡፡

ዩኒቨርስቲዎች ሙሉ በሙሉ የምርምር ማዕከላት ሆነው የኅብረተሰቡን ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር ማድረግ እንዲችሉ መንግሥት አስፈላጊውን በጀት ከመመደብ ጀምሮ ሌሎች እገዛዎችን በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

የአገር ውስጥና የውጭ ሥልጠናዎችን በማመቻቸት፣ ለጥናትና ምርምር አስፈላጊውን ድጋፍ በማዘጋጀት፣ ዩኒቨርስቲዎች ከያሉበት ክልል የልማት ፍላጎት ጋር የተጣጣመ ሥራ ማከናወን የሚያስችላቸውን ቁርኝት በመፍጠር  ረገድ የተሰሩ ሥራዎች በዘርፉ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ በትምህርት ዘርፍ ያሳየችው ውጤትም አገሪቱ እያስመዘገበች ላለው የምጣኔ ሃብት እድገት መሠረት ነው። በዚህም አገራችን የሚሊየሙን የልማት ግብ ከማሳካት ባሻገር፤ ለጥራት ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው።  

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በውጭ ባለሙያዎች የሚከናወን ስራ በእጅጉ እየቀነሰ ነው። በልማቱ ስራ ላይ በወሳኝ ጉዳዮች ዙሪያ  የውጭ ሙያተኞች ዕውቀት ጥገኛ ለመሆን የተገደድነውም በዚሁ ሳቢያ እንጂ፤ ሀገሪቱ ከዓለም ገበያ ዕውቀት ለመግዛት የምታፈሰው የገንዘብ አቅም ስለነበራት አልነበረም።

ይሁን እንጂ ይህ ለረጅም ጊዜያት ከእህልና ገንዘብ ባልተናነሰ መልኩ የእውቀት ጥገኛ ሆነን የተጓዝንበት ምዕራፍ መፍትሄ ሳይበጅለት አልቀጠለም። ሀገራችን ውስጥ ዕውን በሆነው ልማታዊና ዴሞክራሲ መንግስት አማካኝነት ይህ ምዕራፍ ተዘግቶ ወደ አዲስ አስተሳሰብና የዕውቀት ሽግግር ለመጓዛችን በርካታ ማሳያዎችን ማቅረብ ይቻላል።

መንግስት የትምህርት ጥራትን ለማሳደግም በትምህርት አመራር፣ በመምህራን ልማት፣ በሥርዓተ ትምህርት ማሻሻል፣ በት/ቤቶች ማሻሻል እና በአይሲቲ ዙሪያ ሰፋፊ ተግባራት መከናወን ቢችሉም፤ እነዚህን ማሻሻያዎች አጠናክሮ በመተግበር እየታየ ያለውን የትምህርት ጥራት መሻሻል ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ትኩረት ሰጥቶ ይበልጥ መስራትን ይጠይቃል። ያም ሆኖ አሁንም በትምህርት ጥራት ረገድ የሚታዮ ችግሮችን መቅረፍ ይገባል።

እርግጥ ከትምህርት ጥራት አኳያ እየታየ ያለውን ጅምር መሻሻል ይበልጥ ማጎልበት ይገባል። ለዚህም ትምህርት ሚኒስቴርና በየደረጃው የሚገኙ የመስኩ ተቋማት የወጣውን የከፍተኛ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ ኘሮግራም በተገቢው ሁኔታና በዕናት መተግበር የሚጠበቅባቸው ይመስለኛል። እነዚህ ሃቆች ሀገራችን በትምህርቱ ዘርፍ ምን ያህል ርቀት እንደተየጓዘች የሚያሳዩ ናቸው።

ከትምህርት ዘርፍ አፈፃፀም የምንገነዘበው ነገር ቢኖር፤ በየትኛውም መስክ ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ። ግና ችግሮቹን በፅናት፣ በዓላማና በአገራዊ ፍላጎት መፈፀም ከተቻለ ከላይ በማሳያነት ያቀረብኩት የመገናኛ ብዙሃን ዘገባ በአፍሪካ ተጠቃሽ ለመሆን መብቃት እንችላለን። በዘገባው ላይ የተጠቀሰው የትምህርት ዘርፉ እመርታ የመንግሥት ተጨባጭ ስራ ውጤታማ መሆኑን ብቻ ሳይሆን ዘርፉ የልማታችን ፈርጥ መሆኑን የሚያመላክት ነው።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy