Artcles

    የማናችን ይብስ? የአንተ ወይስ የእኔ?

By Admin

January 30, 2018

    የማናችን ይብስ? የአንተ ወይስ የእኔ?

ወንድይራድ ኃብተየስ

የርዕሱን ጽንሰ ሃሳብ የወሰድኩት ግብር ስወራንና ተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲሁም ከዚህ ጋር ተያያዥ የሆኑ ነገሮችን በአግባብ ያለመሰብሰብንና ለመንግስት ገቢ አለማድረግ ወዘተ በተመለከተ የፌዴራል ስነምግባርና ጸረሙስና ኮሚሽን በቴሌቭዥን ሲያስነግር ከነበረው ማስታወቂያ ነው።  እንደእኔ አረዳድ የማስታወቂያው መልዕክት በአጭሩ  እንዲህ ነው። አንድ አሰሪ ወይም የድርጅት ባለንብረት ግብር ይሰውራል፤ ተጨማሪ እሴት ታክስ ይሰበስባል ግን ለመንግስት በአግባቡ ገቢ አያደርግም፤ እዚሁ ድርጅት  ውስጥ የሚሰራ አንድ ሰራተኛ ደግሞ ይህን የአሰሪውን መጥፎ  ተግባር ያውቃልና  ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ አሰሪውን በተደጋጋሚ ይሰርቀዋል።  አንድ ቀን ታዲያ ቀጣሪው ለተቀጣሪው እንዲህ ይለዋል፤ በተለያየ ጊዜ ይህን፣ ይህን ሰርቀኸኛል ይለዋል። ተቃጣሪም ፈጠን ብሎ ያደረጋቸውን ነገሮች ሁሉ ያለምንም ማመንታት አንዱንም ሳይደብቅ  ያምንለታል፤  እንዲህም  ይለዋል “ታዲያ ይህ ምን ያስደንቃል፣ አንተ ህዝብና መንግስትን ትሰርቃለህ፤ እኔ ደግሞ አንተን እሰርቃለሁ” ሁኔታው ይለያይ እንደሆን እንጂ ሁለታችንም ሌቦች ነን፤   የማናችን ይብስ ይሆን? የአንተ ወይስ የእኔ? የሚል መልዕክት ያለው ይመስላል። ሁለቱም ሌቦች ቢሆኑም እውነት  የማናቸው ይብስ ይሆን?

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን  ከሃምሌ 2009  እስከ  ህዳር 2010 ዓ ም  ባለው አራት ወራት  የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ለመሰብሰብ ያቀደው ገቢ 72 ቢሊዮን ብር ቢሆንም፣ የተሰበሰበው ገቢ ግን 63 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ግብር የመንግስት ትልቁ የገቢ ምንጩ ነው።  ይህ አፈጻጸም ዝቅተኛ የሚባል አስር ቢሊዮን ብር እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ  ነው። ጀግንነት በተለያየ አንደበት በተለያየ መልኩ ሊገለጽ ይቻላል፤ ጀግንነት እንደጊዜውና እንደቦታው ይለያያል። አባቶቻችን አድዋ ላይ የቀኝ ገዢ ሃይሎችን ድል ነስተው ጀግንነታቸውን በተግባር አስመስክረዋል። የዛሬው ትውልድ አገር ወዳድነቱን የሚያሳየው እንደአባቶቹና አያቶቹ አድዋ በመዝመት አይደለም። ጀግንነታችንን ለማሳየት ፋሽስት ዳግም እንዲመጣም  አያስፈልግ። አዎ የእኛ ትውልድ ትግል የአገራችንን ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥና ድህነትን መቀነስ  መቻል ነው። አሁን ባለው ሁኔታ የአገራችን ደመኛ ጠላት ድህነት ነው።

ይህ ትውልድ ጀግንነቱን የሚያሳየው በተሰማራበት መስክ በታማኝነት አገሩንና ህዝቡን ሲያገለግልና የሚጠበቅበትን በአግባብ ሲፈጽም ነው። ይህን የሚፈጽም  ዜጋ እርሱ ለእኔ ጀግና ነው። በግብርናው ዘርፍ ተሰማርቶ አገርንና ህዝብ በምርት እንዲትረፈረፍ ያደረገ፣ በመንግስት ስራ ተሰማርቶ ህብረተሰቡን በቅንነትና በታማኝነት ያገለገለ እሱ ጀግና ነው፤ በንግድ ተሰማርቶ የተጣለበትን ግብርና ታክስ በአግባብ የሚከፍል እሱ ጀግና ነው፤ በሲቪል ሰርቪስ ውስጥ ተሰማርቶ ህዝብን በቅንነት የሚያገለግል እሱ ጀግና ነው፤  ወዘተ ብቻ ሁሉም በተሰማራበት አገርንና ህዝብና አገርን  በቅንነት በታማኝነት የሚያገለግሉ ሁሉ ለእኔ ጀግኖች ናቸው!

ግብር መክፈል ምጣኔ ሀብታዊ  ዕድገትን ለማጋገጥ፣ የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ትርጉም ባለው ሁኔታ ለማሻሻል፣ የአገርን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ፣ ከድህነት ለመውጣት፣ ፍተሃዊ የሃብት ክፍፍል ለማስፈን ወዘተ ትልቅ ሚና አለው።  በአሁኑ ወቅት በበርካታ ሀገሮች ዘንድ ግብርን መክፈል እንደ ዋነኛ የዜግነት መብት ማረጋገጫና ክብር መገለጫ ሆኗል፡፡ በአገራችንም በርካቶች የሚጠበቅባቸውን ግብር በአግገባቡና በወቅቱ በመክፈል አገራዊ ግዴታቸውን በመወጣት ላይ ይገኛሉ። ይሁንና አሁንም ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ነጋዴዎች ግብር መሰወርን እንደወንጀል የማይቆጥሩ  እንዳሉ መመልከት ይቻላል። እንዲህ ያለ አስነዋሪ ተግባራት ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችን ወደ ትክክልኛ መስመር እንዲመለሱ መምከር ማስተካከል የሁላችንም ቀጣይ ስራ መሆን መቻል አለበት።

በጥናት ተረጋግጧል ብዬ ባልነሳም  ነባራዊ ሁኔታዎች እንደሚያሳዩት በሀገራችን ያሉ አንዳንድ ነጋዴዎች ከሚያገኙት ጥቅም ጋር ሲነፃፀር ተገቢውን ግብር አይከፍሉም የሚል ትችት ሲቀርብ እናያለን እናደምጣለን፡፡ እንዲያውም አንድ መካከለኛ ደመወዝ የሚከፈለው የመንግሥት ሠራተኛ በዓመት የሚከፍለውን ግብር ያህል እንኳ የማይከፍሉ ባለመደብሮች፤ ካፌዎች፤ ሆቴሎች፣ ወዘተ እንዳሉ አንዳንዶች በአደባባይ ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ኢትዮጵያ ካላት የህዝብ ብዛትና ሃብት  አኳያ ከሰሃራ በታች ካሉ አገሮች ሲነጻጸር እንኳን  አገራችን የምትሰበስበው የግብር  ገቢ ዝቅተኛ የሚባል ደረጃ ላይ ነው።

ከላይ እንዳነሳሁት የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የአራት ወራት አፈጻጸም ለተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበበበት ወቅት ባለስልጣኑ ከግብር አኳያ የያዘውን ዕቅድ ማሳካት አልቻለም። ለዕቅዱ አለመሳካት ተጨማሪ ምክንያቶችን ማንሳት ቢቻልም  በዋንኝነት የሚጠቀሰው ግን ግብር ከፋዩ ማህበረሰብ  የሚጠበቅበትን ግብር ሳይደብቅና በወቅቱ መክፈል ባለመቻሉ  ነው። በቅርቡ የተደረገው የግብር አከፋፈል ክለሳ በአንዳንድ  ነጋዴዎች ላይ ጫና አልፈጠረም የሚል እሳቤ ባይኖረኝም  አሁንም በርካታ የንግዱ  ማህበረሰብ  የሚጠበቅባቸውን  ያህል ግብር  እንዲከፍሉ ተመድቦባቸዋል  የሚል እምነት የለኝም። እስካሁንም  የተመደበባቸውን ግብር ያልከፈሉ አንዳንድ  የንግዱ ማህበረሰብ አባላት እንዳሉ እየተመለከተን ነው።     

አንድ ዜጋ አገር ሰላም ሆኗ ሰርቶ ከሚያገኘው ጥቅምና ገቢ ለሀገሩ ተገቢውን ግብር ካልከፈለ አገር ወዳድነት እምኑ ላይ ነው? ህዝባዊነት የቱ ጋ ነው? ሀገር ሰላም ልትሆን የምትችለው የጸጥታ አስከባሪዎች  ሲኖሩ ነው። እነዚህ አካላት ሊኖሩ የሚችሉት ደግሞ ሁላችንም የሚገባንን ማድረግ ስንችል ብቻ ነው። በአገራችን የተጀመረውን ልማት ለማስቀጠል ከእያንዳንዳችን ምን ይጠበቃል? የእኔ ድርሻ ምንድነው? ምን ላበረክት እችላለሁ? የሚለው አተያይ የእያንዳዳችን  እሳቤ  መሆን መቻል አለበት፡፡ ዜጋው ተገቢውን ግብር መክፈል ካልቻለ መንግስት ሊያቀርባቸው የሚገቡ መሃበራዊ አገልግሎቶች ሊሟሉ አይችሉም። የመንግስት እያንዳንዷ ወጪ ከእያንዳንዳችን ኪስ የሚሰበሰብ ገንዘብ እንጂ ከሰማይ የሚወርድ መና አይደለም። ግብርን በታማኝነት በወቅቱ  መክፈል መቻል ግዴታ ብቻ ሳይሆን   ኩራትም ጭምር  ነው። እኔ ግብር መክፈል የቻልኩት ሰርቼ መጠቀም በመቻሌ ነው የሚል አስትሳሰብ በሁሉም የግብር ከፋይ ዘንድ መጎልበት መቻል አለበት። አንዳንዶች  ግብር መሰወርን አገርና ህዝብን መስረቅ መሆኑን አይገነዘቡትም።

የንግዱ ኅብረተሰብ በአገሪቱ በሚካሄዱ የልማት ሥራዎች ላይ ዋነኛ ተሳታፊ ለመሆን ያለውን ተነሳሽነት ከሚያሳይበት መንገድ አንዱ  ትክክለኛ ግብርን በወቅቱ በመክፈል ብሄራዊ የዜግነት ግዴታን መወጣት ሲችል ነው። አገራችን ከድህነት ልትወጣ የምትችለው ሁሉም ዜጎች ከአገሪቱ ሃብት እኩል ተጠቃሚ የሚሆኑት አሰራር የሚዘረጋው መንግስት የማህበራዊ መገልገያዎችን ማስፋፋት ሲችል ነው። ይህ ደግሞ እውን የሚሆነው እያንዳንዱ ግብር ከፋይ ዜጋ የተጣለበትን ግብር በአግባብና በታማኝነት መክፈል ሲቻል ብቻ ነው።በአገራችን ግብር የመክፈል ስሜት ከፍተኛ መሻሻል እንዳሳየ አሌ የሚባል አይደለም። የአገራችን የኢኮኖሚ ዕድገት መፋጠን እንዲሁም  የመንግስት በጀት ከዓመት ወደ ዓመት እያደገና እየተመነደገ  የመጣው የአገራችን የግብር አሰባሰብ ስርዓትም ለውጥ እያሳየ መምጣቱን ይመሰክራል።

ይሁንና አሁንም አገራችን ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ገቢ ለማሰባሰብ ረጅም መንገድ መጓዝ ይኖርባታል።  ይህ ሥራም በዘመቻ መልክ የሚሰራ የአንድ ጊዜ ተግባር ሳይሆን ቀጣይነት እንዲኖረው ተደርጎ በቋሚነት ሊሰራበት ይገባል፡፡ በግብር አወሳሰንም ሆነ አከፋፈል ላይ ችግር ሊፈጠር ይችላል። በግብር አሰባሰብ ሂደት የሚፈጠሩ የአፈጻጸም ስህተቶችና ክፍተቶች የሚመለከተው የመንግሥት አካል በቀየሰው የቅሬታ አቀራረብና ማስተናገጃ ሥርዓት እልባት እንዲያገኙ  ተደርጓል፡፡ ይህ ደግሞ ሕጋዊና የሰለጠነ አካሄድ ነው፡፡ ነጋዴው ማህበረሰብም የተሰጠውን ውሳኔ በማክበር የሚጠበቅበትን ግብር በመክፈል አገራዊ ግዴታውን ሊወጣ ይገባል።

መንግስት የሚሰበስበው ግብር እንዲሁም የአገልግሎትና የመጠቀሚያ ክፍያዎች ተመልሰው ለሀገርና ለህዝብ ጥቅም የሚውሉ መሆናቸውን መገንዘብና አምኖ መቀበል ሁሉም ግዴታውን ለመወጣት ጥረት ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ በመሆኑም ግብርን በትክክልና በወቅቱ መክፈል ማለት “ማንኛውም ዜጋ የራሱን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥበት ነው፤ ግብር ከፋዩ ማህበረሰብ የምከፍለውም ግብር ዞሮ ዞሮ ለራሴ፤ ለልጆቼና ለወገኔ ነው” የሚል አመለካከት ማጎልበት እንዲችል ተከታታይ ስራ መስራት ተገቢ ነው።  እያንዳንዱ ግብር ከፋይ  ዜጋ  አገር ወዳድነቱንና ወገንተኝነቱን  ግብር በመክፈል መግለፅ ይኖርበታል፡፡ ግብር የሚያጭበረብር ህዝብንና መንግስትን እንደማጭበርበር ይቆጠራል። ምክንያቱም መንግስት አገርን ሊቀይሩ የሚችሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን የሚገነባው፣ የህዝብና አገር ደህንነትን የሚጠብቀውና የህግ የበላይነትን የሚያረጋግጠው  በሚሰበስበው ግብር እንደሆነ መታወቅ ይኖርበታል። ግብር መክፈል ያኮራል፣ ግብር መክፈል የአገርን የህዝብን ደህንነት ያስጠብቃል፣ ግብር መክፈል መሰረተ ልማትን ያስፋፋል፣ በአጠቃላይ ግብር መክፈል ልማትን ያፋጥናል። ግብር መክፈል ኩራት ነው። ግብር መክፈል በዚህ አግባብ ቢታይ መልካም ይመስለኛል።