የማይዛነፈው አቋም
ዳዊት ምትኩ
ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ በተመለከተ ለጋራ ተጠቃሚነት ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው። የዓባይ ውሃ አጠቃቀምን በተመለከተ የአገራችን አቋም የማይዛነፍና ”ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል በተፋሰሱ አገራት መካከል መኖር ይኖርበታል” የሚል ነው። ይህ የፀና አቋም ትናንትም ይሁን ዛሬ የማይቀየር ነው። አገራችን ሁሌም ቢሆን ግጭትን እንደ መፍትሔ የማትወስድ ወደ ጦርነት ለመግባትም ፍላጎት የላትም።
ኢትዮጵያ ስለ ጦርነት አስከፊ ገፅታ ጠንቅቃ የምታውቅ ናት። ሆኖም ብሔራዊ ጥቅሟን አሳልፋ የምትሰጥ አገር አይደለችም። በአሁኑ ወቅት መንግሥት የውስጡን ችግሮች ለመፍታት እየሰራ እንዳለው ሁሉ፤ በዲፕሎማሲው መስክም ስኬታማ ሆኗል። ይህ ስኬታማ የዲፕሎማሲ መንገድም በህዳሴው ግድብ ላይ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን የመፍታት አቅም ያለው ነው።
እንደሚታወቀው ሁሉ መንግስት ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን እውን ለማድረግ ቆርጦ በሚነሳበት ወቅት ዕቅዱ በራሱ አቅም ብቻ ግቡን ይመታል የሚል ድምዳሜ ይዞ አልነበረም፡፡ እንዲሁም የውጭውን ዓለም ድጋፍና ዕርዳታ ጠብቆ ለማሳካት አስቦም አልተነሳም፡፡ ልማቱ የህዝብ እንደ መሆኑ መጠን፤ ስራውም በመላው ህዝብ ተሳትፎ እንደሚሳካ ጽኑ እምነትን አንግቦ ነበር ወደ ግድቡ ስራ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የገባው።
ታዲያ ይህም ቢሆን ህዝቡን በመዋጮ ለማጨናነቅ አንዳች ዕቅድ አልነበረውም፤ አይኖረውምም፡፡ ህዝቡ ለራሱ ልማት በፍላጎቱ ምንም ዓይነት ውሳኔ ላይ ሊደርስ የሚችልበት ነጻነት ያለው መሆኑን በጥብቅ ስለሚያምንም፤ እንደ መንግስት ፍትሃዊ ውሳኔ ላይ መድረስ እንደሚገባው በጥልቀት ከመረመረ በኋላ ነበር፤ ህዝባዊ ጥሪውን ያስተላለፈው፡፡ ለዚህም ነው መንግስትን፣ ሕዝብንና በአጠቃላይ አገርን የሚጠቅም አማራጭ በመያዝ “ራሳችንን በራሳችን እናልማ” በማለት ይፋ መግለጫ የሰጠው።
ይህ በመንግስት የያዘው አማራጭ ይፋ ሲሆን ሕዝቡ የሰጠው አፋጣኝ ምላሽ ለጉዳዩ ተገቢነት ብሎም በራሱ ለማደግ ያለው ቀናዒ ፍላጎት ምስክር ይሆናል፡፡ ሁኔታው እያንዳንዱ ዜጋ “ከኪሴም ጭምር ማዋጣት አለብኝ” የሚል ድምዳሜ ላይ እንዲደርስ ያደረገው መሆኑንም በገሃድ ያየነው ሃቅ ነው፡፡
የህዳሴው ግድብ ለአንዲት ሰኮንድም ሊቆም የማይችለው ፍትሐዊ በሆነ መንገድ በጋራ ተጠቃሚነት ማናቸውንም ልማታዊ ተግባሮች ማከናወን እንደምንችል ማሳያ መሆኑ አንዱ ምክንያት ነው። በሌላ በኩልም እዚህ ሀገር ውስጥ እየተፋጠነ ባለው የልማት ተግባር ዘርፈ ብዙ ኢንዱስትሪዎች “እየበቀሉ” ነው። ኢትዮጵያን የአፍሪካ የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ ነው።
ታዲያ ይህን የዕድገት ፍላጎት በአግባቡ ለማስኬድ የኤሌክትሪክ ሃይልን ከከባቢ ብክለት በነፃ መንገድ መጠቀም የግድ ይላል። ለዚህ ደግሞ ታዳሽ የተፈጥሮ ሃይላችንን መጠቀም ይኖርብናል። ይህን ካላደረግን አሁንም ከነበርንበት የከፍታ ቦታ ተንሸራትተን የኋሊት በድህነት አረንቋ ውስጥ ልንዘፈቅ እንችላለን። ይህን ደግሞ የሚፈቅድ ትውልድ የለም። እናም የህዳሴው ግድም ለአፍታም ቢሆን የማይቆምበት ሁለተኛው ምክንያት ይኸው ይመስለኛል።
እኛ ስናድግም የታችኛው የተፋሰሱ ሀገራትም የሁኑ ሌሎች የቀጣናው ሀገራት ተጠቃሚ ይሆናሉ። እኛ ከቀጣናው ሀገራት ተነጥለን ልንለማ አንችልም። የእኛ እድገት የቀጣናው ሀገራት ጭምር ነው። የግድቡ ግንባታ የቀጣናውን ሀገራት የኤሌክትሪክ ሃይል ችግርም የሚቀርፍ ነው። እናም ሶስተኛው ግድቡ ለአንድ ሴኮንድም ቢሆን ሊቆም እንዳይችል የሚያደርገው ምክንያት ይኸው ይመስለኛል።
መላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እነዚህን እውነታዎች በሚገባ ያውቃሉ። ምንም ዓይነት ብዥታ የለባቸውም። ለግድቡ ግንባታ የቦንድ ግዥ ዋንጫው በየክልሉ ሲዞር ከተጠበቀው በላይ ገንዘብ በማውጣት ቦንድ የሚገዙትም ለዚሁ ነው።
በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለዚሁ ግድብ ግንባታ እየፈፀሙት ካለው ቀላል የማይባል የቦንድ ግዥን ጨምሮ ካሉበት ቦታ ወደ ሀገር ቤት በመምጣት የግድቡን ግንባታ በመጎብኘትና ሌሎች ኢትዮጵያዊንም አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ በማነሳሳት ረገድ እየተጫወቱ ያሉት ሚናም በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
ይህ ቁርጠኛ የህብረት ስሜት ከሀገር ቤት እስከ ውጭ ድረስ የሚታይ ነው። ማንም በገሃድ የሚያየውም ጭምር። እናም ይህ የህዝቦች አንድነት የራስን የተፈጥሮ ሃብት በራስ አቅም የማልማትና በእርሱም ራስንና ከባቢውን የመጥቀም ተምሳሌት በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። ይህን የማስተባበር ስራ የሚያከናውኑት አካላትም ስራቸውን ሳያቆራርጡና ያዝ ለቀቅ ሳያደርጉ በቋሚነት ማከናወን ያለባቸው ይመስለኛል።
የኢትዮጵያ መንግስት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ እንጂ ሌሎች አገራትን የሚጎዳ ፕሮጀክት የመገንባት ፍላጎት የለውም። ሌሎችን የመጉዳት ታሪክም የለውም። የሚከተለው ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ፖሊሲም ይህን እንዲያደርግ አይፈቅድለትም።
ይልቁንም መንግስት እየሰራ ያለው ግድቡ ሀገራችን ኤሌክትሪክ በመሸጥ የቀጣናውን ሀገራት በኢኮኖሚ ለማስተሳሰር የምታደርገው ጥረት አንዱ ማሳያ እንዲሆን ነው የሚፈልገው። ከግድቡ ኬንያ፣ ጂቡቲ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ታንዛኒያና ሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ተጠቃሚ ይሆናሉ። ግብፅን ጨምሮ ሌሎች የተፋሰሱ ሀገራትም ተጠቃሚ መሆናቸው አይቀርም።
ከዚህ ቀጣናዊና የተፋሰሱ ሀገራት ተጠቃሚነትና በኢኮኖሚ የማስተሳሰር ፍላጎቷ በመነሳትም ሀገራችን ለዘመናት ተገድቦ የቆየውን ሀገሪቱ በተፈጥሯዊ ውኃ ሃብቷ የመጠቀም መብቷን አሳልፋ ልትሰጥ አትችልም። እናም የራሷን ፕሮጀክት በራሷ አቅም በመገንባት ላይ ያለች እንዲሁም ከድህነት ለመውጣት ስትል የምትገነባቸውን ማናቸውንም የልማት ግድቦችን ለአፍታም ቢሆን የማታቆም መሆኗን መገንዘብ ይገባል። ብሔራዊ ጥቅሟን ለማንም አሳልፋ የማትሰጥ መሆኑንም ጭምር መረዳት ያስፈልጋል።
እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ በየትኛውም የታሪክ አጋጣሚ ነፃነቷንና ሉዓላዊነቷን ለድርድር አቅርባ የማታውቅ የጥቁር ህዝቦች መኩሪያ ሀገር ናት። ከባርነት፣ ከጭቆና እና ከቅኝ ተገዢነት ለመላቀቅ ብርቱ ትግል ላደረጉ በርካታ የዓለማችን ህዝቦች አርአያና ምሳሌያቸው እስከ መሆንም ደርሳለች።
ዛሬ የሀገራችን ህዝቦች የራሳቸውና የቀጣናው ሀገራት ድህነት፣ ኋላቀርነት፣ ረሃብና ጦርነት ማብቃት አለበት ብለው ቆርጠዋል። ‘ዋነኛው ጠላታችን ማነው?’ ብለው ጠይቀው “ድህነት” የሚለውን ትክክለኛ ምላሽም አግኝተዋል። ጎረቤቶቻቸውን፣ በተለይም የተፋሰሱን ሀገራት ተጠቃሚ ለማድረግ በእኩልና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሰረተ የግንኙነት ፖሊሲን ቀርፀውም እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ። ‘ድህነትንም እንዴት እናስወግዳለን?’ ብለው መክረው መፍትሔ ካበጁም ቆይተዋል። በሁሉም መስክ ፈጣን ልማትን ሊያመጡላቸው የሚችሉ አቅጣጫዎችን መከተል ብቸኛ አማራጫቸውን ከማውጣትም ባሻገር፤ በትግበራ ሂደቱ ላይ የጋራ መግባባትን እየፈጠሩ ፈጥረዋል።
የጋራ መግባባታቸውም የሌላውን አገር ህዝብ ባለመጉዳት ላይ የተመሰረተ ከመሆኑም በላይ፤ ስራውም የሚከናወነው የሌሎችን ህዝቦች ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ያማከለ መርህን የተከተለ ነው።
ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ወደ ካይሮ አቅንተው ከግብፁ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር ያደረጉት ውይይትና የተፈራረሙት ስምምነት የዚህ አባባል ነፀብራቅ ነው። ይህ የአገራችን አቋም የግብፅን ህዝብ የማይጎዳ፣ ይልቁንም የህዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ነው። አቋሙም ዛሬም ይሁን ነገ የማይዛነፍ መሆኑን ሁሉም ወገኖች ሊያውቁት የሚገባ ይመስለኛል።