Artcles

የምርት ብክነትን ለመከላከል…

By Admin

January 10, 2018

የምርት ብክነትን ለመከላከል…

ዳዊት ምትኩ

ኢትዮጵያ ላለፉት 26 ዓመታት በስኬቶች ታንኳ ላይ እየቀዘፈች የመጣች አገር ናት። የስኬቶቿ ሁሉ መሰረት የግብርናው ዘርፍ ነው። አገራችን በግብርናው ዘርፍ እያከናወነች ያለችው ተግባሮች ከእጅ ወደ አፍ የነበረው የአርሶ አደር ምርት ተለውጦ በዓመት ሁለቴና ከዚያ በላይ ማምረትና ከፍተኛ ምርት እንዲያገኝ ያስቻለ ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ መንግሥት ለዘመናዊ ግብርና ያልተደፈረውን የአገሪቱን አርሶ አደር የአስተራረስ ዘይቤ የመለወጥን አስፈላጊነት ተገንዝቦ በቀየሰው መስመር እነሆ የሚታየ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ነው። አርሶ አደሩ በድርቅ በቀላሉ መጠቃት ምክንያቱም ደግሞ የዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴ አለመኖር እንደሆነ ተረጋግጧል።

በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ኑሮው እንዲሻሻል ተገቢ ትኩረት አግኝቷል። ለዚህም በቂ ማሳያዎችንም ማቅረብ ይቻላል። መንግሥት የዘመናት ቁጭቱን አገራዊ መሠረት ባላቸው አቅጣጫዎች የመፍታት ትግሉን እያካሄደ ነው። አርሶ አደሩ ከራሱ ተርፎ ለገበያ በማምረት ተጠቃሚ የሚሆንበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ፣ ሀገሪቱም ከግብርናው ዘርፍ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ ለማድረግ የሚያስችል የለውጥ ጎዳና ላይ መሆኗን አረጋግጧል።

በአርሶ አደሩ እጅ እንዳለ የሚታሰበው መሬት አነስተኛ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ካለችው መሬት የሚያገኘው ምርት ዝቅተኛ ነው። ይህን መንግሥት በሚገባ በመገንዘቡ ዘርፈ ብዙ የማሻሻል ጥረቶች አድርጓል። በውጤቱም አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮችን ይዞ ለውጥ  ማምጣት አይቻልም የሚለውን አስተሳሰብ መስበር ችሏል።

አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች ትኩረት ከመስጠት ይልቅ ለሰፋፊ እርሻዎች ትኩረት መስጠትና ለውጥ ማምጣትን የሚሰብኩ ወገኖች እንዳሉ ግልጽ ነው። እነዚህ ወገኖች የሚሰብኩት በግብርናው ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ትኩረት የመስጠትን አስፈላጊነት የሚሰብክ ነበር። ይህ ደግሞ ሀገራዊና ህዝባዊ ጥቅም የሚመጣበትን ምስጢር ካለመረዳት ወይም ለመረዳት ካለመፈለግ የመጣ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።

መንግሥት አነስተኛ ይዞታ ላላቸው አርሶ አደሮች ምን ያህል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ በተደጋጋሚ ገልጿል። ይህን የመንግሥትን ፖሊሲ ትክክለኛነት ለማረጋገጥም ተችሏል። የሚታይና አሳማኝ ውጤት ማምጣትም እንደተቻለም ከአርሶ አደሩ በላይ ምስክር የሚያሻው አይመስለኝም።

ምንም እንኳን ለውጡን የማይፈልጉ ኃይሎች ስህተት ፈላጊ ሆነው ቢቀጥሉም፤ በግብርናው ዘርፍ ባመጣነው ለውጥ ብዙዎች በመስማማት ላይ ይገኛሉ። ኢትዮጵያ የአርሶ አደሩን ምርታማነት በማሳደግ፣ ለምርቱ ገበያ በማመቻቸትና ከግሉ ዘርፍ ጋር ትስስር በመፍጠር ምርትና ምርታማነትን አሳድጋ ተጠቃሚ በመሆን ላይ ትገኛለች።

አርሶ አደሩ የለውጥ መስመሩን ተረድቶ በእምነት ወደ ሥራው በመግባቱ በዓመት ሁለቴና ከዚያም በላይ ለማምረት ችሏል። እንዲሁም በከርሰ ምድርና በገጸ -ምድር ያለውን የውኃ ሃብት የመጠቀም ሰፊ ተግባር አከናውኗል።

በውኃ ማሰባሰብና ማቆር፣ የጉድጓድ ውኃን በመጠቀም የወንዝ ውኃን ጠልፎ ጥቅም ላይ በማዋል ብዙ ርቀት ተጉዟል። በመሆኑም አርሶ አደሩ ከራሱ ፍጆታ አልፎ ለከተማው ነዋሪዎች ከፍተኛ ፍላጎት የሆኑትን ምርቶች ማቅረብ ችሏል። ከነዚህ ውስጥ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች በግንባር ቀደምነት ተጠቃሽ ናቸው።

ከዝናብ ጥገኝነት በተላቀቁ አመራረት የተገኙትን ምርቶች መጠቀምም እየተቻለ ነው። የመስኖ ልማት ሥራው በበጋ የበቆሎ እሸት ተመጋቢዎች እንዲሆን አስችሎናል። ባለፉት ሁለት ዓመታት ደግሞ ሥራው ከሁለት እጥፍ በላይ አድጓል።

ለአርሶ አደሩም በዚያው ልክ ገበያው ተመቻችቷል። አርሶ አደሩ በራሱ ባቋቋማቸው የአርሶ አደሮች የህብረት ሥራ አማካይነት ምርቱን ለገበያ በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ ተጠቃሚ መሆን ጀምሯል። በዚህም ተጠቃሚነቱን እያረጋገጠ ነው።

የግብርናው ዘርፍም በአስተማማኝ ሁኔታ ገበያው ሳያሳስበው ምርትና ምርታማነቱን በማሳደግ ላይ ብቻ አተኩሮ ለልማት ለውጥ ሽግግሩ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥርበት ደረጃ ላይ ደርሷል ማለት ይቻላል። እንደሚታወቀው ሁሉ በአሁኑ ወቅት የምርት መሰብሰቢያ ጊዜ ነው። ምርቱ እንዳይባክን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል። በተለይም የምርት ብክነትን ለመከላከል የሚመለከታቸው አካላት የድርሻቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል።

ሆኖም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ መንግስታዊ ጥረት ላይ የተወሰኑ ተግዳሮቶች መኖራቸውን ግልፅ ነው። እርግጥ የግብርና ምርት የጥራት ችግርና ብክነት አሁንም ያልተሻገርናቸው ተግዳሮቶች ናቸው።

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በድህረ- ምርት አያያዝና አጠባበቅ ጉድለት የተነሳ አርሶ አደሩ በዓመት አንድ ሶስተኛው የግብርና ምርታችን እንደሚባክን ተረጋግጧል። መባከን ብቻም ሳይሆን በአጨዳ፣ በመሰብሰብ፣ በመውቃት፣ በማበራየት፣ በመጓጓዝና በማከማቸት የማምረት ሂደት ወቅት የምርት ጥራት በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል። ምርት በወቅቱ ባለመታጨዱ ምክንያትም ጊዜውን ባልጠበቀ ዝናብ ተበላሽቶ ለብክነትና ለጥራት መጓደል የሚጋለጥበት ሁኔታም መኖሩ ይታወቃል።

ይህ ሁኔታም አርሶ አደሩ ዓመቱን ሙሉ ከለፋበት ምርት እንዳይጠቀም የሚያደረግ ነው። ምርት ለብክነት ከተጋለጠና ጥራቱም ካሽቆለቆለ ተገቢውን ዋጋ ሊያስገኝ አይችልም። አንድ የምርት ዓይነት ሲታጨድ፣ ሲወቃና ሲበራይ እንዲሁም ሲጓጓዝና ሲከማች የሚባክን ከሆነ ከብዛት ሊገኝ የሚችል ጥቅም አይኖርም።

በእነዚህ የምርት ሂደቶች ወቅትም አመራረቱ ተገቢ ላልሆነ የጥራት ችግር ከተጋለጠ ከምርቱ አግባብ የሆነ ገቢን ማግኘት አይቻልም። እንደሚታወቀው በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሩ ምርቱን የሚሰበስብብበት ነው። እናም ምርቱ ለብክነትና ለጥራት ማነስ እንዳይጋለጥ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል። ማሳ ላይ የሚገኝ ምርት የአርሶ አደሩ የላብ ውጤት ነው።

አርሶ አደሩ ዓመቱን ሙሉ የተለያዩ ግብዓቶችን ተጠቅሞ እዚህ ደረጃ ያደረሰው ሰብል በስተመጨረሻው ለብክነትና ለጥራት መጓደል ችግር መጋለጥ የለበትም። የላቡን ፍሬ በሚያገኝበት በአሁኑ ወቅት በተግዳሮቶች ሳቢያ ከምርቱ ተጠቃሚ ሳይሆን መቅረት የለበትም።

የምርት ብክነትና የጥራት መጓደል የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት በሚገባ የማያረጋግጡ ከመሆናቸው ባሻገር፤ መንግሰት የአርሶ አደሩን ህይወት ለማሻሻል በሚያደርጋቸው ተግባራት ላይ ጥላ የሚያጠሉም ጭምር ናቸው።

ይህ ሁኔታ የአርሶ አደሩን ህይወት ከድህነት አዙሪት በፍጥነት እንዳይወጣ የሚያደርግ መሰናክል ስለሆነ በቀላሉ የሚታይ ተግዳሮት አይደለም። እናም አርሶ አደሩ በማምረት ሂደት ላይ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመቋቋም ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል።

በተለይ በአጨዳ ወቅት ምርቱ ከአረም ጋር እንዳይደባለቅ፣ ታጭዶ ንፁህ በሆነ ቦታ እንዲቀመጥና ምርቱ ለአላስፈላጊ የዝናብ አደጋ እንዳይጋለጥ በማድረግ ጥራቱን መጠበቅ ከአርሶ አደሩ የሚጠበቅ ተግባር ነው።

ከዚህ በተጨማሪ ምርቱ እንዳይባክን በአሰባሰብ ሂደቱ ላይ በቂ ትኩረት ማድረግ ይኖርበታል። ምርቱ ሲበራይ በንፋስ ተጠልፎ እንዳይሄድ፣ በሚበራይበት ቦታ ካለ ባዕድ ነገር ጋር እንዳይደባለቅ፣ ንፅህናው አስተማማኝ እንዲሆንና በአግባቡ እንዲመረት ማድረግም ይጠበቅበታል። ታዲያ ይህን እንዲያደርግ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ በመስጠት በኩል የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ መረባረብ ይኖርባቸዋል።