Artcles

የሰላም ማዕከሎች

By Admin

January 25, 2018

የሰላም ማዕከሎች

ዳዊት ምትኩ

በአገራችን ውስጥ እየተስፋፋ ያለውን የትምህርት ዘርፍ ለማጎልበት በመንግስት በኩል በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል። በመስፋፋት ላይ በሚገኘው ትምህርት ሁሉንም ዜጋ ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል።

ትምህርት ሲስፋፋ ተፎካካሪ ወይም ተወዳዳሪ ተማሪዎችን ማፍራት ይቻላል። ይህም በመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ ጤናማ ፉክክርን በመፍጠር የአገር እድገትን የሚያፋጥን ነው። በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከነበረባቸው የግጭት ችግር ተላቅቀው ዛሬ በሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ውስጥ ገብተዋል። የሰላም ማዕከሎችም ሆነዋል። ይህም ተቋማቱ አገርን ለመጥቀም በሚያስችላቸው መንገድ እየተጓዙ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው።

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አገሪቱ የምትፈልገውን የተማረ የሰው ሃይል በማፍራት ረገድ  ፋይዳቸው የላቀ ነው። እንደሚታወቀው ሁሉ ባለፉት ጊዜያት ህዝቡ ከውጭው ዓለም እንዲቸረው ይጠብቅ የነበረው የእህል አሊያም የገንዘብ ድጋፍና ዕርዳታን ብቻ አለመሆኑን ነው። በሀገራችን በተለያዩ ደረጃዎች በሚካሄዱ የልማት ስራዎች ውስጥ የእውቀት ድጋፎችንም የሚሻ ነበር። የዚህ ችግር ዋነኛው መንስኤ ደግሞ ቀደም ባሉት ጊዜያት ሀገራችን ውስጥ ልማታዊ አስተሳሰብ ያለው፣ በእውቀትና ክህሎት የታነፀ በቂ የሰው ሃይል ሊፈራ አለመቻሉ እንደሆነ አያከራክርም።

እዚህ ላይ በልማቱ መስክ ላይ ተሰማርቶ ተጨባጭ ውጤት ማምጣት የሚችል የሰለጠነ የሰው ሃይል በጥራትና በበቂ ሁኔታ ካለመኖሩ ጋር ተያይዞ ባለፉት ጊዜያት በህብረተሰባችን ውስጥ ይንፀባረቅ ስለነበረው አንድ እውነታ በማሳያነት ላንሳ።

ባለፉት ጊዜያት በሃገራችን በተለያዩ ደረጃዎች ይካሄዱ የነበሩ የልማት ስራዎችን ጎብኝተን አሊያም በመገናኛ ብዙሃን ተከታትለናቸው ይሆናል። ከእነዚህም መካከል በግዙፍነታቸው አልያም በዘመናዊነታቸው እንግዳ የሆኑብን የሚታጡ አይመስለኝም። እዚህ ላይ ለማንሳት የምፈልገው ጥያቄ ታዲያ “እነዚህ ስራዎች የኢትዮጵያዊያን ዕውቀት አርፎባቸው ለውጤት የበቁ ናቸው” ብለን የምናስብ ስንቶቻችን ነበርን? የሚለውን ነው። እርግጠኛ ነኝ በርካቶቻችን እንደነዚህ ዓይነቶቹን ስራዎች ስንመለከት ቀድመን የምናስበው የውጭ ሙያተኞች እውቀት የፈሰሰባቸው እንደሆኑ ስንገምት ኖረናል።

እርግጥ ዓይነቱ አመለካከት መኖሩ ተገቢ አልነበረም የሚል ግምት የለኝም— ለረጅም ጊዜያት በልማቱ መስክ ላይ ውጤት ማምጣት የሚችል በእውቀትና በክህሎት የዳበረ በቂ የሰው ሃይል ሳይገነባ ቆይቷልና።

በልማቱ ስራ ላይ በወሳኝ ጉዳዮች ዙሪያ  የውጭ ሙያተኞች ዕውቀት ጥገኛ ለመሆን የተገደድነውም በዚሁ ሳቢያ እንጂ፤ ሀገሪቱ ከዓለም ገበያ ዕውቀት ለመግዛት የምታፈሰው የገንዘብ አቅም ስለነበራት አልነበረም።

ይሁን እንጂ ይህ ለረጅም ጊዜያት ከእህልና ገንዘብ ባልተናነሰ መልኩ የእውቀት ጥገኛ ሆነን የተጓዝንበት ምዕራፍ መፍትሄ ሳይበጅለት አልቀጠለም። ሀገራችን ውስጥ ዕውን በሆነው ልማታዊና ዴሞክራሲ መንግስት አማካኝነት ይህ ምዕራፍ ተዘግቶ ወደ አዲስ አስተሳሰብና የዕውቀት ሽግግር ለመጓዛችን በርካታ ማሳያዎችን ማቅረብ ይቻላል።

ዛሬ በተለያዩ አካባቢዎች በሚደረጉ የልማት ተግባሮች ውስጥ የተማረ የሰው ሃይላችን ከውጭ ባለሙያዎች ስራን እየተረከበ ነው። ለምሳሌ በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ስር የሚገኙት ባለሙያዎችን እንዲሁም በባቡር ኮርፖሬሽን ስር ተሰማርተው ሙሉ ለሙሉ ስራውን ከቻይና ባለሃብቶች ለመረከብ በዝግጅት ያሉ የተማሩ ወጣቶችን መጥቀስ ይቻላል። ይህ የሆነውም የሀገራችን ከፍተኛ የትምህርት ዘርፍ በችግር ፈቺ ዘርፎች ተማሪዎችን እያበቃ በመሆኑ ነው።

ሆኖም በአሁኑ ወቅት የትምህርት ጥራት ችግር ሙሉ ለሙሉ ተፈትቷል ማለት አይቻልም። ተማሪዎቹ በዚህ ረገድ ተዋንያን መሆን አለባቸው። እርግጥ ከትምህርት ጥራት አኳያ እየታየ ያለውን ጅምር መሻሻል ይበልጥ ማጎልበት ይገባል። ለዚህም ትምህርት ሚኒስቴርና በየደረጃው የሚገኙ የመስኩ ተቋማት የወጣውን የከፍተኛ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ ኘሮግራም በተገቢው ሁኔታና በጽናት መተግበር የሚጠበቅባቸው ይመስለኛል። እነዚህ ሃቆች ሀገራችን በትምህርቱ ዘርፍ ምን ያህል ርቀት እንደተየጓዘች የሚያሳዩ ናቸው።

እርግጥ ከዚህ የትምህርት ዘርፍ አፈፃፀም የምንገነዘበው ነገር ቢኖር በየትኛውም መስክ ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ። በመንግስት ትኩረት የተሰጠው የትምህርት ጥራትን የማሻሻል ጉዳይ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ነው።

ታዲያ ተማሪዎች በዚህ መንግስታዊ ጥረት ላይ የበኩላቸውን ድርሻ በተጠናከረ ሁኔታ መወጣት ከቻሉ ችግሩን ለመቅረፍ በሚደረገው ጥረት አዎንታዊ ሚና በመጫወት የትምህርት ዘርፉን ሊደግፉት ይገባል።

በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ትምህርት ዙሪያ በተከናወነው የማስፋፋት ሥራ በቅድመ ምረቃ የቅበላ አቅምን ወደ 400 ሺህ እንዲጠጋ አድርጎታል። በድህረ ምረቃም በኩል የቅበላ አቅም ከ28 ሺህ በላይ ሆኗል። የሴት ተማሪዎች ድርሻ በቅድመ ምረቃ 32 በመቶ፣ በድህረ ምረቃ ደግሞ 19 በመቶ ደርሷል።

እርግጥ ከትምህርት ጥራት አኳያ እየታየ ያለውን ጅምር መሻሻል ይበልጥ ማጎልበት ይገባል። ለዚህም ትምህርት ሚኒስቴርና በየደረጃው የሚገኙ የመስኩ ተቋማት የወጣውን የከፍተኛ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ ኘሮግራም በተገቢው ሁኔታና በዕናት መተግበር የሚጠበቅባቸው ይመስለኛል። እነዚህ ሃቆች ሀገራችን በትምህርቱ ዘርፍ ምን ያህል ርቀት እንደተየጓዘች የሚያሳዩ ናቸው።

እርግጥ ከዚህ የትምህርት ዘርፍ አፈፃፀም የምንገነዘበው ነገር ቢኖር በየትኛውም መስክ ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮች እንደሚኖሩና በችግሮቹ ሳቢያ የሚፈጠሩ የትምህርት ሥርዓቱ አጠቃላይ መገለጫ ሊሆኑ እንደማይችሉ ነው።

በመሆኑም ሀገራችን “ዕውቀት ሁሉ ከውጭ የሚገባ ነው” ከሚባልበት ዘመን ወጥታ፣ ዛሬ ላይ በራሷ አቅም የትምህርትን በማስፋፋት ላይ ትገኛለች። በዚህም በየደረጃው በሚገኙ የዘርፉ መስች የቅበላ አቅሟን አሳድጋለች። የትምህርት ጥራትን ይበልጥ ለማረጋገጥም በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመኗ እየተረባረበች ነው።

ይህ የአገራችን ጥረት በከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎቿ ሊታገዝ ይገባል። ከፍተኛ የትምህርት ተቋማቷ ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎች አካባቢያቸውን ይበልጥ የሰላም ማዕከሎች ማድረግ ይኖርባቸዋል። ተምረው አገራቸውን ‘አለንልሽ’ ሊሏት ይገባል። የምታስተምራቸውን አገራቸውን መካስ የሚችሉትም ይህን በማድረግ ነው። እናም በአሁኑ ወቅት የሚገኙበትን ሰላማዊ የመመማር ማስተማር ሂደት በማጠናከር አገራቸው ከእነርሱ የምትጠብቀውን ግዴታ መወጣት ያለባቸው ይመስለኛል።