Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

“የሰላም ምንጭ እንጂ

0 498

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

“የሰላም ምንጭ እንጂ

የቦንብ መጠቅለያ ወረቀቶች” አይደሉም

ዮናስ

 

በሰላምና በመቻቻል በኩል አኩሪ እሴት ያለው ህብረተሰብ ቢኖረንም መቼም ድሬደዋን የሚተካከለው የለም። ከቅርብ ጊዜ በፊት ሃገራችን አጋጥሟት የነበረውን መቃወስ ተከትሎም ድሬደዋን በዩኒቨርሲቲዋና በወጣቶችዋ በኩል በሽታው ሊያጠቃት ዳድቶ ነበር። ግን ተደርሶበታል። ሲደረስበትም በቀላሉ እንዲፈወስ አልተፈለገም። በአስተማማኝ መልኩ ዳግም እንዳያገረሽ ተደርጎ ነው የታከመው። በድሬዳዋ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሥር የተደራጁ ወጣቶችን የተመለከተው ሰሞንኛ ዜናም ለዚህ ማሳያ ነው። ወጣቶቹ የአብሮነት እሴትን በማጎልበት የአካባቢያቸውን ሰላምና ልማት አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡ የቦንብ መጠቅለያ ወረቀት ሊያደርጓቸው የሚሹ የማህበራዊ ሚዲያ አርበኞችን ላለመስማት ቃል ኪዳናቸውንም አድሰዋል።

 

ይህ የተነገረው በድሬዳዋ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሥሩ ለተደራጁና በየቀበሌው ከሚገኙ ቤተ-እምነቶች ለተውጣጡ ወጣቶች እና ሴቶች በሰላም እሴት ግንባታ ላይ ለሁለት ቀናት ስልጠና በሰጠበት ወቅት ነው፡፡ በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ ከሰባት ቤተ-እምነቶች የተውጣጡ ሴቶችና ወጣቶች አደረጃጀታቸውን በማጠናከር ለሰላም መረጋገጥና ለአካባቢያቸው ልማት መጠናከር ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡“በሃገራዊና በሰላማችን ላይ ክርስቲያኑና ሙስሊሙ ያለልዩነት በመነጋገር ተቀናጅተን ለመስራት ተዘጋጅተናል” መባሉም ከስፍራው ተዘግቧል፡፡ በሀገራችን ከጥንት ጀምሮ የነበረውን እርስ በርስ የመረዳዳት፣ የመከባበርና የመቻቻል እሴት በጋራ በመጠበቅ ለቀጣዩ ትውልድ የማስረከብ ኃላፊነት የሁሉም በመሆኑ በየቤተ-እምነቱ ለመተግበር ወጣቶቹና ሴቶቹ መዘጋጀታቸውንም አረጋግጠዋል፡፡

 

እንዲህ በወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳይ ላይ መነጋገር የበለጠ ኃላፊነትን ለመወጣት ያነቃቃል። በሰላም እሴትና በሕብረት መኖር ላይ ሁሌም መወያየት ያስፈልጋል። ሁሉም ቤተ-እምነቶች ተቀራርበውና ተከባብረው የሀገሪቱን ሰላምና ልማት ለማስቀጠል ወጣቶችንና ሴቶችን የማብቃት ስራቸውን እንዲህ እንደድሬደዋ ሊያጠናክሩ ይገባል። ወጣቶች ሁልጊዜም የሃይማኖት አባቶች የሚሉትን መቀበልና ካላስፈላጊ ድርጊት በመራቅ ለሰላምና ልማት መጠናከር መቆም አለባቸው።  በሃገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦችና የተለያዩ እምነቶች በልዩነት ውስጥ ባዳበሩት አንድነትና ፍቅር ተቻችለው እየኖሩ ነው። የአሁኑ ትውልድ ይህን እሴት ተቀብሎ ለማጠናከር መትጋት ይጠበቅበታል። በመላው ሃገሪቱ ሰላም እንዲጠበቅ በየቤተ-እምነቱ ለወጣቶችና ሴቶች ተከታታይነት ያለው ትምህርት መስጠት ያስፈልጋል።

ሁለት ሶስተኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ወጣት ነው፡፡ የነገዋ ኢትዮጵያ እጣ ፋንታ በእነሱ እጅ ስለሆነ ይህ ለሀገሪቱ ትልቅ ሃብት ነው፡፡ ወጣቶቹ  ሀሳብ፤ ከፍተኛ የማደግ ፍላጎትና ህልም አላቸው፡፡ ይህ ህልማቸውና ፍላጎታቸው ኢትዮጵያን አይደለም ዓለምን መቀየር የሚችል ነው። እስከ አሁን ችግር ሆኖ የቆየው በዚህ ከፍተኛ ቁጥር ባለው ህብረተሰብ ከፍል የሚታየው ስራ አጥነት ነው፡፡

ወጣቶችና ሴቶች የማህበራዊ፤ የኢኮኖሚና የስራ አጥነት ችግሮች አሉባቸው፡፡ ስለሆነም መንግስት የችግሮቹን መንስኤ መርምሮ በማየት በተለይ ለወጣት የሥራ አጥነት ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ሌሎች ችግሮችን ለማቃለል በመትጋት ላይ ይገኛል። የወጣቶችን እና ሴቶችን ችግር መቅረፍ ሀገሪቱ እያስመዘገባች ያለችውን የሁለት አሃዝ ኢኮኖሚያዊ እድገት ማስቀጠል ማለት ነው።  

 

የወጣቶችና ሴቶች  ልማት ፓኬጅ ዋንኛ አላማ የወጣቶችና ሴቶችን አመለካከት ከማስተካከል በዘለለ የወጣቶችና ሴቶችን ፖለቲካዊ  ተሳትፎ  ማሳደግና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን  ማረጋገጥ ነው፡፡ ፓኬጁ ወጣቶችና ሴቶችን  በሁሉም የመንግስት እቅድ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡

ግን ደግሞ በሃገሪቱ እየተመዘገበ ባለው የኢኮኖሚ እድገት እኩል ተጋሪ እና ተጠቃሚ ያለመሆን ችግር በተከሰተው  ሁከትና  ብጥብጥ  ውስጥ ወጣቶችን ተሳታፊ አድርጓቸው የነበረ መሆኑም ሊዘነጋ አይገባም። ይልቁንም ሌላ አጀንዳ ያላቸው ሃይሎች የቦንብ መጠቅለያ ወረቀቶች እንዲሆኑም ተደርገው ነበር በሎ መናገር ይቻላል።  እዚህ ላይ ግን መንግስት በርካታ የስራ እድሎችን ለወጣቶች መፍጠሩ ሊዘነጋ የማይገባና የችግሩ መነሻ ካለው ፍላጎት አንጻር  የተመጣጠነ አለመሆኑ ነው።  

ይህን የመሰለው ችግር በየአካባቢው እንዲቀሰቀስ ምክንያት የሆኑ ወቅታዊ ችግሮች እንደነበሩ ባይካድም፣ ከተከሰተበት ሁኔታና ከደረሰው የህይወትና የንብረት ጉዳት በመነሳት ወጣቶቹ አካባቢ ያልተሰራ እና ይልቁንም ለምሬት ያበቋቸው መሰረታዊ ምክንያቶች ያሏቸው መሆኑን ለመገመት አይከብድም። ያም ሆነ ይህ ውጫዊ ምክንያቶች ለጥፋት ተልእኮ መሳሪያ ሆነው ሊያገለግሉ የሚችሉት በውስጥ ያሉ ችግሮች እስካልተፈቱ ድረስ ብቻ መሆኑ የማያከራክር እውነታ ነው። የሃገሪቱን ህዝብ ከከፊል በላይ የሆነውን ወጣት ታሳቢ ያደረገ የትምህርት ስርአት ቢዘረጋም ተመጣጣኝ የሆነ የስራ እድል አለመመቻቸቱ እና ከተማረው ህዝብ ጋር የሚመጥን የአስተዳደር ስርአት አለመዘርጋቱ ዋነኛው ምክንያት ነው።

ለአንድ አገር ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኀበራዊና ባህላዊ ልማት የሁሉም የኀብረተሰብ ክፍል ንቁ ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑ እሙን ነው። ግን ደግሞ ወጣቶች እና ሴቶች አዳዲስ ሀሳቦችን ለመቀበል እንዲሁም የፈጠራና የማምረት እምቅ አቅም ያላቸው በመሆኑ በሁሉም የልማት ዘርፎች ውስጥ የላቀ ሚና ሊጫወቱ የሚችሉ መሆኑ አያከራክርም። ይህ የሚሆነው ደግሞ እምቅ ሀይላቸውንና ችሎታቸውን በተግባር ለማዋል የሚያስችል ምቹ አካባቢያዊ ሁኔታዎች ሲፈጠሩላቸው ነው። ይህ ሳይሆን ቀርቶ ፍላጐቶቻቸውን እውን ለማድረግ የሚያስችሏቸው ሁኔታዎች ካልተፈጠሩላቸው ግን ፈጥነው ተስፋ በመቁረጥ እና ሁሉንም ነገር በመተው የህብረተሰቡን እንቅስቃሴ በገለልተኛነት ከርቀት ሊመለከቱ የሚችሉበት እድል የሰፋ ይሆናል። አልፈውም ለማኀበራዊ ጠንቆች ተጋላጭ ስለመሆናቸው በአለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ተሞክሮዎችም ያረጋግጣሉ።

 

    በአገራችን የወጣትና ሴቶች ጉዳዮችና አደረጃጀት ተገቢው ትኩረት ካለማግኘቱ የተነሳ  በወጣቶች፣ በሴቶች በቤተሰብ፣ በህብረተሰብ፣ በሌሎች ተባባሪ አካላት እና በመንግስት መካከል የጋራ ትብብርና ቅንጅት ተፈጥሮ በተፈለገው መጠን ሲሰራበት ያልነበረ መሆኑ በአንድ በኩል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ስርአቱ በፈጠረው እድል ተጠቅመው እራሳቸውን በእውቀት ባበቁ ወጣቶችና ሴቶች ልክ የስራ እድል አለመፈጠሩ ለተለያዩ አሉባልታዎች እና የግጭት አጀንዳዎች ተጋላጭ እንዳደረጋቸው ይልቁንም የቦንብ መጠቅለያ ወረቀቶች እስኪሆኑ ድረስ ያበቃቸው መሆኑም ይታወቃል።

 

በጥቅሉ ወጣቶች በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ ብቃት ባለው መልኩ ተሳትፈው፣ ኢኮኖሚያዊና ማኀበራዊ ልማትን በማፋጠን የራሳቸውንና የኀብረተሰባቸውን ጥቅም ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ፈርጀ-ብዙ ተግባራትን ለማከናወን ሁኔታዎች ያልተመቻቹላቸው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የወጣቶችና ሴቶችን ተጋላጭነት በመጠንም ሆነ በጥልቀት ጨምሮታል ማለት ይቻላል።

 

ስለሆነም ዛሬ በአገራችን የተፈጠሩትን ምቹ የፖለቲካ ሁኔታዎች፣ ለልማት የሚበጁ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ተነድፈው ተግባር ላይ እንዲውሉ መደረጋቸውና ፖሊሲዎቹንም በብቃት ለማስፈፀም የአቅም ግንባታ ስራዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ ትኩረትና ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ተግባራዊ እንዲሆኑ መንግስት ቁርጠኛ አቋም ወስዷል። በተለይም ወጣቶችና ሴቶች በሃገር ጉዳይ ላይ የጋራ ራዕይና አመለካከት ፈጥረው፣ በራሳቸውና በሀገራቸው ጉዳዮች ላይ የባለቤትነት ስሜት ኖሯቸው በሃገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኀበራዊና ባህላዊ ልማቶች የበኩላቸውን ተሳትፎ እንዲያደርጉና ከውጤቱም በተገቢው መንገድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችላቸው ፕሮግራሞች በመንደፍ እና ፓኬጆችን በመቅረጽ በየደረጃው ርብርብ እየተደረገ ነው። ይህንን መጠቀም የወጣቶቹና ሴቶቹ ድርሻ ነው።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy