Artcles

የቡድንና የግል መብቶች እንዴት ይስተናገዱ?

By Admin

January 05, 2018

የቡድንና የግል መብቶች እንዴት ይስተናገዱ?

                                                            ታዬ ከበደ

ኢትዮጵያ በምትከተለው ፌደራላዊ ስርዓት የቡንንና የግል መብቶች በተገቢው ሁኔታ እየተስተናገዱ ነው። የቡድንና የግል መብቶች ህገ መንግስቱን መሠረት አድርገው ገቢራዊ እየሆኑ ነው። በፌዴራላዊ ስርዓቱ ውስጥ እነዚህ መብቶች የሚታዩበትን አግባብም ህዝቦች በፈቃዳቸው ያመጧቸው ከመሆናቸው አኳያ ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ ሰብዓዊ መብቶች ከሰው ልጅ ስብዕና ጋር የተቆራኙና አንድ ሰው፣ ሰው ሆኖ በመፈጠሩ ብቻ የሚጎናጸፈው ተፈጥሯዊ መብቶች ናቸው፡፡ እነዚህ መብቶች የኢትዮጵያ መንግስት ስለፈለገ ለዜጎች የሚሰጡ፣ ሳይፈልግ ደግሞ የሚነፈጉ አይደሉም፡፡ ምክንያቱም በሀገሪቱ ውስጥ የተካሄደው ረጅም ጦርነት መነሻው የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አለመኖር በመሆኑና ይህ የሀገራችን ህዝቦች የዘመናት ጥያቄ በአሁኑ ወቅት በቂ ምላሽ አግኝቷል፡፡

የፌዴራላዊ ስርዓቱ ምሶሶ የሆነው የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን አጎናፅፏል። በተለይም መንግስት እነዚህን መብቶች ለማረጋገጥ የወሰዳቸው የተለያዩ ገንቢ ርምጃዎች ለፌዴራላዊ ስርዓቱ ወሳን ሚና እንዲጫወቱ አድርጓል።

በፌዴራላዊ ስርዓቱ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ከሀገራቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህይወት ተገልለውና ተረስተው በባይተዋርነት ለመኖር የተገደዱበት አድሎአዊና ፍትህ አልባ ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ ተቀይሮ፤ ዜጎች በማንኛውም ሀገራዊ ጉዳይ ውስጥ እኩል ተሳታፊ የመሆን ዕድል አግኝተዋል። ይህንንም በተጨባጭ ስራ ላይ በማዋል የሀገራችንና የህዝባችን የማደግና የመበልጸግ ተስፋን በእጅጉ ለማለምለም ችለዋል።

መላው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በመብቶቻቸው እየተገለገሉና ዘላቂ ጥቅሞቻቸውን እያስከበሩ በፈጣን ልማትና በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አቅጣጫ ላይ የተያያዙት ፈጣን የዕድገት ጉዞም የፌዴራላዊ ሥርዓቱ ተጨባጭ ፍሬ ነው።

በሀገራችን እውን የሆነው ፌዴራላዊ ሥርዓት ለሀገራችንና ለህዝባችን አንድነት፣ ሠላምና ዕድገት መጠናከር ወሳኝ አስተዋጽኦ ያበረከተ ነው፤ በማበርከት ላይም ይገኛል። የዚህ አዲስ ሥርዓት ግንባታ ሂደት በተጨባጭ ተፈትኖ ፍቱንነቱ የተረጋገጠ ነው።

በመገንባት ላይ የሚገኘው ፌዴራላዊ ሥርዓት በሀገራችን ላይ አንዣቦ የነበረውን የመበታተን አደጋ ያስወገደና በእኩልነትና በመፈቃቀድ ላይ ለተመሰረተ ከብረት የጠነከረ የህዝቦች አንድነት ዘላቂ ዋስትናን ያሰገኘ ነው።

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የአዲሲቷን ኢትዮጵያ የወደፊት ዕድል የመወሰን ሥልጣን ባለቤት መሆን እንዳለባቸው በወኪሎቻቸው አማካይነት ይፋ አድርገዋል። በምስረታው ወቅት የገቡትን ቃል በአፈፃፀም ሂደት እንዳይዛነፍ የመጠበቅ ኃላፊነት የሚሰጣቸውን ህገ መንግሥት የመተርጎም ሥልጣን ወስደዋል። የዚህ ድንጋጌ ቁልፍ ትርጉም በመከባበር፤ በመተማመንና በመተባበር በእኩልነት አብሮ የመኖር ስምምነት ነው።

የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት የግል መብቶችን ለማረጋገጥ ወሳኝ እንደሆነ የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚቴ ይገልፃል፡፡ ብዙ ፀሐፊዎች የቡድን መብቶች ከግል መብቶች ተለይተው መገደብ የሌለባቸው እንደሆኑ ይገልፃሉ፡፡ የግል መብቶችን በማረጋገጥ ብቻ የቡድን መብቶችን ማረጋገጥ እንደማይችል፣ የቡድን መብቶችን የሚከለክል ስርዓት የግለሰብ መብቶችን ብቻ በማስከበር የተሟላ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሊሆን እንደማይችል የሚገልፁም አሉ።

ከዚህ በተጨማሪ አንዳንድ ያደጉ የዴሞክራሲ አገሮች የቡድን መብቶችን በተሟላ መልኩ ባለመረጋገጣቸው ምክንያት የቡድን መብት ጥያቄዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከሩ የአገራቱን ውስጣዊ ስላም በማናጋት ላይ ይገኛሉ። የኢትዮጵያን ሁኔታ ስንመለከት ደግሞ የብሔሮችና ብሔረሰቦች እሥር ቤት ልትሆን የቻለችው የቡድን ማንነቶች ማፈን ዋነኛ የጭቆና መገለጫ ስለነበር ነው።

በፌዴራላዊ ስርዓቱ ከተደነገጉ የህዝብ መብቶች ውስጥ አንዱ የሃይማኖት እኩልነት ነው። መንግሥትና ኃይማኖት የተለያዩ መሆናቸውን፤ ሁሉም ሰዎች በመካከላቸው የዘር፣ የብሔር፣ የብሔረሰብ፣ የጾታ፣ የኃይማኖት ልዩነት ሳይደረግ እኩል የህግ ጥበቃ እንደሚደረግላቸው፣ ማንኛውም ሰው የማሰብ፣ የህሊናና የኃይማኖት ነፃነት፣ የመረጠውን ሃይማኖት ወይም እምነት ለብቻው ወይም ከሌሎች ጋር በመሆን የማምለክ፣ የማስተማርና የመግለፅ መብት አለው።

የስርዓቱ መሰረት የሆነው ህገ መንግስት ለእነዚህ ድንጋጌዎች ልዩ ትርጉም የሚሰጣቸው የኃይማኖቶች እኩልነትና የእምነት ነጻነት ሳይረጋገጥ ያለፈውን የተዛባ ግንኙነት ማስተካከል አይቻልም ከሚል መሠረታዊ አስተሳሰብ በመነሳት ነው።

አዲስ የኢትዮጵያዊነት ማንነት የመገንባት ጉዳይም ከእነዚህ መብቶች ጋር በቀጥታ የተቆራኘ ነው። ለህዝብ የሚገደብ መብት መኖር የለበትም የሚል መሠረታዊ እምነት ፌዴራላዊ ስርዓቱ ስለሚያምነበት ነው። የኢትዮጵያ ህዝቦች በግልም ይሁን በቡድን የመረጡትን እምነት የመከተል መብታቸውን ማረጋገጥ የህዝብ ልዕልና አንድ አካል ነው።

ፌዴራላዊ ስርዓቱ የህዝቦችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ይበልጥ አስተማማኝ ለማድረግ የተለያዩ መብት አስጠባቂ ተቋማትን በማቋቋም የተለያዩ ርምጃዎችን ወስዷል በመውሰድ ላይ ይገኛል። የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የእንባ ጠባቂ ተቋም፣ የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት…ወዘተ ተጠቃሽ ናቸው።

እነዚህ ተቋማት ህብረተሰቡ በተለያዩ መንግስታዊ ተቋማት አፈፃፀም ሳቢያ ሊፈጠሩ የሚችሉ ጉዳዩችን ጥያቄ ሲቀርብላቸውና በራሳቸው ተነሳሽነትም ይመረምራሉ፣ ችግሮችን በመለየት የመፍትሔ ሃሳቦችን በማቅረብም ተግባራዊነታቸውን ይከታተላሉ። በዚህ ተግራቸውም በስርዓቱ ውስጥ ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት ሚዛናዊ ጉዳዩች እውን እንዲሆን ያደርጋሉ።

ፌዴራላዊ ስርዓቱ በህገ መንግስቱ ላይ የተቀመጡ በርካታ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ተግባራዊ አድርጓል። እነርሱን የሚቆጣጠሩ ተቋማትን በገለልተኝነት በማቋቋም ጭምር አፈፃፀማቸውን በመከታተል መብቶቹ ሳይሸራረፉ እውን እንዲሆን ቢደረግም የሚፈለገውን ያህል ተሂዷል ማለት አይቻልም። በተለይም በመብቶቸቹ አስፈፃሚዎች በኩል ከአቅም ጋር በተያያዘ የሚታየውን የአፈፃፀም ችግር መፍታት ይገባል።

ይህ ከተደረገ በኋላም መብቶቹን የሚቆጣጠሩ አካላትን አቅም በማጎልበትና ህገ መንግስታዊ አግባቦችን በተከተለ መንገድ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ መስራት ያስፈልጋል። ሰብዓዊ መብቶች ህዝቦች በትግላቸው ያመጧቸው እንጂ ላያቸው ላይ የተጫኑ ባለመሆናቸው ጠባቂዎቻቸውም ራሳቸው የሀገራችን ህዝቦች ናቸው። እናም መብቶቹን በመጠበቅ ረገድ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል።