Artcles

የብሩህ ዘመን መዘውሮች

By Admin

January 11, 2018

የብሩህ ዘመን መዘውሮች

                                                         ታዬ ከበደ

ሰሞኑን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ባለፉት አስር ዓመታት የአገራችን የውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በአምስት እጥፍ መጨመሩን ገልጿል። ይህም የአገራችንን ኢንቨስትመንት እመርታ የሚያሳይ ነው። በዚህም እ.ኤ.አ በ2007/2008 ዓ.ም 814 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር የነበረው የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት፤ እ.ኤ.አ በ2016/17 ዓ.ም በአምስት እጥፍ አድጎ 4 ነጥብ 17 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል።

ይህም አገራችን ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን እያሳደገች ምጣኔ ሃብቷን እያሳደገች እንደሆነች ያስረዳል። በተለይ በግብርና፣ በማምረቻ፣ በኮንስትራክሽን፣ በአገልግሎት እና በአበባ ምርት ዘርፎች የውጪ ቀጥኛ ኢንቨስትመንት ፍሰት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ በእነዚህ መዘውሮች ኢትዮጵያ መጪው ዘመንዋ ብሩህ መሆኑን የሚያሳይ ነው።

አገራችን ውስጥ ባለፉት 26 ዓመታት ውስጥ ባለሃብቶቹ የሃብት ባለቤት እንዲሆኑና ለዜጎች የስራ ዕድል እንዲፈጥሩ ሁኔታዎች ተመቻችተውላቸው በኢኮኖሚው ላይ አሻራቸውን ማሳረፍ ችለዋል። ብዙዎቹ ሀሃት እንዲያፈሩ እና ለብዙ ዜጎች የስራ እድል እንዲፈጥሩ ከማስቻሉም በላይ በኢኮኖሚው ውስጥ የራሳቸውን አሻራ ማሳረፍ ችለዋል።

የአገር ውስጥን ባለሃብቶች ከውጭ ባለሃብቶች ጋር በማቀናጀት ለመፍጠር የተቻለው የገበያ ትስስርም ምቹ የኢንቨስትመንት መሰረትን ጥሏል ማለት ይቻላል። ከእነዚህ ውስጥ የወጪ ንግድ የብድር ዋስትና ሥርዓት መተግበር፣ የውጪ ምንዛሪ ተመን ማስተካከልና የምንዛሪ ዋጋው በገበያ እንዲወሰን ማድረግ በዋነኛነት የሚጠቀሱ ምቹ ሁኔታዎች ናቸው።

የኤክስፖርት ምርትን ከቀረጥ ነፃ ማድረግ፣ ለኢንቨስትመንት ከቀረጥ ነፃ የሚገቡ የካፒታል ዕቃዎችና ግብዓቶች ያለ ቅድመ- ሁኔታ የሚገቡበትን ዕድል የመፍጠር ብሎም ባለሃብቶቹ ለስራቸው የሚሆን መሬት በሊዝ እንዲያገኙ መደረጉ ተጨማሪ አመቺ መደላድሎች ነበሩ። እነዚህ በመንግስት በኩል አቨስትመንትን ለማበረታታት የተወሰዱ እርምጃዎች የቅጭ ባለሃብቶች ሀገራችን ላይ ዓይናቸውን እንዲጥሉ ያደረጉ ተግባራት ናቸው።

የኢትዮጵያ ሰላም አስተማማኝ መሆኑ ሌላኛው ወደ ኢንቨስትመንት ጉዟችን የምናደርገውን መንገድ ያሳካ ሌላኛው ምክንያት ነው። ኢትዮጵያ የሰላም ተምሌት ናት። በምስራቅ አፍሪካ ስለ ሰላም ጉዳይ ሲነሳ ቀድሞ የሚነሳው የሀገራችን ስም ነው። ይህ ሁኔታም የአገር ውስጥም ይሁን የውጭ ባለሃብቶች ስራቸውን ያለስጋት እንዲያከናውኑ ታደረጋቸው ነው።

ይህ የሰላማችን ሁኔታ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ እዚህ ላይ አንድ ዕውነታን ማንሳት አግባብነት ያለው ይመስለኛል። ይኸውም ሀገራችን የትምህርት፣ የጤና፣ የመንገድና የንፁህ መጠጥ ውሃ መሰረተ-ልማቶች ሙሉ ለሙሉ ያልተሟሉባት በመሆኗ ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ ከሀገራዊው ዕድገት ጋር የሚመጣጠን ግንባታዎች ለማካሄድ በመንግስት በኩል እንደሚካሄደው በተመሳሳይ ሁኔታ የግሉ ባለሃብት ሊከናወን አለመቻሉ ነው።

የግሉ ዘርፍ የኦኮኖሚ ዕድገቱ አንቀሳቃሽ ሞተር መሆኑ በመንግሥት ታምኖበት በፍትሃዊ ውድድር ላይ እንዲመሰረት በመደረጉ ባለፉት ዓመታት በርካታ ሃገራዊ ባለሃብቶች እንዲፈጠሩ ቢደረግም፤ ባለሃብቱ ሊሰማራባቸው በማይችላቸው ዘርፎች መንግስት በተመረጠ አኳኋን ጣልቃ ገብቶ ልማቱን በዋነኝነት በማንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።

እነዚህ ድምር ውጤቶች የሀገራችን መፃዒ ዕድል አመላካች ይመስሉኛል። መንግስት የሚከተለው የኢንቨስትመንት ፖሊሲ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችን ያሳደገና የስራ ዕድል የፈጠረ ብቻ አይደለም።

ይልቁንም የአገራችንን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመቅረፍ በሚደረገው ጥረት እንደ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ሁሉ ተመጣጣኝ የውጭ ምንዛሬ ግኝት ማምጣት የሚችሉ የውጭ ባለሃብቶችም ወደ ሀገራችን እንዲተሙ አድርጓቸዋል።

ታዲያ ይህ በጎ የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዳይደናቀፍ በመንግስት ፈፃሚዎች በኩል ብርቱ ጥረት መደረግ ይኖርበታል። አሁንም ቢሆን በተለያዩ ወቅቶች የውጭ ባለሃብቶች የሚያሰሙትና ሆን ተብሎ በአስፈፃሚዎች የሚፈፀም የሚመስሉ አላስፈላጊ ውጣ ውረዶችን ማስቀረት ይገባል። ከዚህ ጎን ለጎንም በኢንቨስትመንት ስም ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው ምንም ዓይነት እሴት መጨመር ያልቻሉ ባለሃብቶችን ሚዛኑን በጠበቀና ፍሰቱን በማያስተጓጉል መልኩ ቁጥጥር በማድረግ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ማስፋት ይገባል።

ያም ሆኖ አሁንም ቢሆን የአገር ውስጥ ቁጠባን ከፍ ማድረግ ይገባል። በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የመንግስት ወጪን በዋነኝነት የካፒታል ክምችት ለሚፈጥር የኢንቨስትመንት ወጪ በመመደብ በቁጠባ ለታለመለት ዓላማ ለማዋል የተደረገው ጥረት የአገር ውስጥ ቁጠባ ከፍ እንዲል አግዟል። እነዚህ የሀገር ውስጥ ቁጠባን ለማሳደግ የተወሰዱ እርምጃዎች ውጤት እያስገኙ ነው።

ይህ መልካም የሚባል የኢንቨስትመንት አፈፃፀም በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ወቅት ይበልጥ ጎልብቶ ውጤታማ መሆን ያለበት ይመስለኛል። እስካሁን በታየው የቁጠባና ኢንቨስትመንት አፈጻፀም ረገድ ትኩረት የሚሻው ጉዳይ ቢኖርም ቅሉ፤ አሁንም መጠኑ የማይናቅ ኢንቨስትመንት በአገር ውስጥ ቁጠባ ገንዘብ ሳይሆን በውጪ አገር ቁጠባ ገንዘብ መሸፈኑ ከጉዳዩ አኳያ ቀዳሚ ተግዳሮት ይመስለኛል። ታዲያ ይህ ተግዳሮት እየሰፋ የሚሄድ ከሆነ ለውጪ ተፅዕኖ የሚያጋልጠንና የፖሊሲ ነፃነት የሚያሳጣን ከመሆኑም ባሻገር፣ አስተማማኝና ዘላቂ የመሆን ዕድሉም የመነመነ ነው።

ስለሆነም የዜጎችን እና የንግድ ድርጅቶችን ቁጠባ ከፍ ለማድረግ እስካሁን የታየውን አበረታች እንቅስቃሴ አጠናክሮ ማስቀጠል ወሳኝ ጉዳይ ይመስለኛል። ከዚህም አኳያ የዋጋ ግሽበትን ማረጋጋትና ወደ ዝቅተኛ አሃዝ መለወጥ፣ ህዝቡን ማስተማርና ማነሳሳት፣ የቁጠባ መሳሪያዎችና አገልግሎቶችን ማስፋፋትና ማጠናከር እንዲሁም የምጣኔ ሃብት ዕድገቱን ማፋጠንና የሥራ ዕድልን ይበልጥ የማስፋፋት ጉዳዩች ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡

የመንግስት ቁጠባን በተመለከተም የሚገኘው የመንግሥት ገቢም ሆነ የቁጠባ ገንዘብ ውጤታማ፣ ከብክነት የፀዳ እና በግልፅ ቅደም ተከተል ጥቅም ላይ የሚውል መሆኑም ትኩረት የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው።

የመንግስት ፕሮጀክቶችን የማስፈፀም አቅም በማሳደግ የሚካሄዱትን ግዙፍ ኢንቨስትመንቶች ውጤታማነትና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ ዕውን ማድረግ አገራዊው የቁጠባና የኢንቨስትመንት ሁኔታን ማጠናከር ስለሆነም ከዚህ አኳያ ትኩረት ሰጥቶ መስራት የሚገባው ይመስለኛል።

እንደሚታወቀው ሁሉ ለዘላቂና ፈጣን ዕድገቱ ምቹ የሆነ የማክሮ ምጣኔ ሃብት ሁኔታ ከመፍጠር አኳያ በኢንቨስትመንትና በቁጠባ መካከል ያለው ሚዛን ትልቅ ትርጉም አለው። በሁለተኛው የዕቅድ ዘመን የፈጣን ዕድገቱ አንዱ ምንጭ ኢንቨስትመንት እንዲሆን ተተልሟል።

በተለይም በማኑፋክቸሪንግና በግብርና፣ በመሠረተ-ልማት፣ በማህበራዊ ልማት ዘርፎችና በሌሎች መስኮች የሚከናወኑ የግልና የመንግስት ኢንቨስትመንቶች ፈጣን ዕድገትን በማረጋገጥ ትልቅ ሚና እንዲጫወቱ ታቅዶ እየተሰራባቸው ናቸው።በዚህም ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንትን መሳብ ተችሏል። ይህ የኢንቨስትመንት ዓይነት የውጭ ምንዛሬ እጥረትን በመቅረፍ በአገራችን ኢኮኖሚ ላይ ዓይነተኛ ሚና ይኖረዋል። በአገራችን ውስጥ የሚከናወኑት የተለያዩ ኢንቨስትመንቶች የብሩህ ዘመን መዘውር ናቸው። እነዚህ መዘውሮችን በአግባቡ መያዝና ማጠናከር ያስፈልጋል።