Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የብርሃን አውዶች

0 305

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የብርሃን አውዶች

                                                    ታዬ ከበደ

አገራችን የገነባቻቸውና እየገነባቻቸው ያሉት ሜጋ ፕሮጀክቶችን በጭላጭል ውስጥ ከመኖር የሚያላቅቁን የብርሃን አውዶች ናቸው። እነዚህ የብርሃን አውዶቹ ከእኛ አልፈው ለምስራቅ አፍሪካ እንዲሁም ለተፋሰሱ አገራት የህይወት ሻማዎች ይሆናሉ። በቀጠናውና በተፋሰሱ አገራት መካከል የሚኖረውን የምጣኔ ሃብት ትስስርን ለማጠናከር የሚኖራቸውም ድርሻ ከፍተኛ ነው።

ሜጋ ፕሮጀክቶቻችን ብርሃንም ጉልበትም ናቸው። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በፈጣን ዕድገት ላይ የሚገኙ ታዳጊ ሀገሮች ዜጎች ኤሌክትሪክ ብርሃንም ጉልበትም መሆኑ ግልፅ ነው። በተለይም ከከተሞች ዳርቻ ፈቅ ሳይል ዘመናትን ያስቆጠረው የሀገራችን የኤሌክትሪክ አቅርቦት የተደራሽነት ወሰኑን ከቀን ወደ ቀን በማሳደግ ላይ ይገኛል።

መላ ህይወቱን ከኩራዝ ጋር አቆራኝቶ ‘መብራት አይንሳችሁ’ በሚል ብሂል የኤሌክትሪክ ብርሃንን ከሩቅ ይናፈቅ ለነበረው አብዛኛው የሀገራችን ህዝብ፤ ምኞቱን እውን ለማድረግ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት በመከናወን ላይ ይገኛሉ።

የኤሌክትሪክ ኃይል መሠረተ ልማት ለልማት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ ለአቅርቦቱ የተሰጠው ትኩረትም የዚያኑ ያህል የጎላ ነው። ኃይል ለማቅረብ የየወቅቱን የልማት ጥያቄዎች ከመመለስ ባለፈ፤ የዘርፉን ስራ በማስፋትና በማቀላጠፍ ከድህነት ነፃ የሚያወጣ የሀገሪቱን ፈጣን ዕድገት ቀጣይነት በሚያረጋግጥ መልኩ የተቃኘ ነው።

ይህን መሠረት በማድረግም የሀገሪቱ ኢነርጂ ፖሊሲ ከመጋቢት 1986 ዓ.ም ጀምሮ ሥራ ላይ እንዲውል ተደርጓል። ኢትዮጵያን ‘ከመብራት አይንሳችሁ’ ብሂል ‘የብርሃን ፀዳል ያጎናፅፋችሁ’ ወደሚል ልማታዊ ይትብሃልና ቀጣናውን የጋራ ተጠቃሚ ወደሚያደርግ ትሩፋት ለማሸጋገር። ርግጥ የፖሊሲው ዓላማ የሀገሪቱን የኢነርጂ ሃብት ከአጠቃላይ የመንግስት የልማት ስትራቴጂ አኳያ ማጎልበትና ሥራ ላይ ማዋል፣ ሌሎች በየአካዳሚው ዘርፎች የዘረጉትን የልማት አቅጣጫ የሚደግፍ ግልፅና ውጤታማ የሆነ የኢነርጂ ኃይል እንዲኖር ማድረግ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ ውስን የሆነውን የውጭ ምንዛሬ በቁጠባ ለመጠቀም የሚያስችል ውጤታማ የኢነርጂ አጠቃቀም እንዲኖር ማስቻል እንዲሁም ከውስጥና ከውጭ የሚያጋጥሙ የአቅርቦት እጥረትና የዋጋ መዋዠቅ ለመከላከል የሚያስችል አስተማማኝ የኢነርጂ አቅርቦት በመፍጠር ኢኮኖሚውን መታደግ የሚሉ ዓላማዎችንም ጭምር በማንገብ ስራውን ጀምሮ ዛሬ ላይ ሀገራችንን የታላላቅ ሜጋ ፕሮጀክቶች ባለቤት ያደረገ ፖሊሲ ነው።

ታዲያ ፖሊሲው ዓላማዎቹን ለማሳካት ቀጣይነትና አስተማማኝ የኢነርጂ አቅርቦት እንዲሁም ዘርፉን የሚያጋጥሙ ችግሮች ለመፍታት ፈጣን የኢነርጂ ልማት እንዲፈጠር መመሪያዎችን ዘርግቷል። ከፍ ሲልም ሀገር በቀል የሆኑና የአየር ንብረት ብክለትን የሚያስወግዱ የኢነርጂ ልማት እንዲፈጠር የሚያደርግ ነው። በዚህ መሰረት ፖሊሲው የውሃ ኃይል ልማትን እንዲሁም የኢነርጂ አጠቃቀም ስብጥርን በማበረታታት ለታዳሽ የኢነርጂ አጠቃቀም፣ ለፀሐይ ኃይል፣ ለንፋስና ለጂኦተርማል ልማት እንዲሁም ዋጋ ተወዳዳሪነት ትኩረት የሰጠ ነው።

ተስማሚ የፖሊሲ ርምጃዎችን ለመውሰድ ደረጃ በደረጃ የህዝቡን ተለምዷዊ የኢነርጂ አጠቃቀም ወደ ዘመናዊውና ለአየር ንብረት ጥበቃ አጋዥ የሆነ አጠቃቀም የመቀየር ዓላማንም ያነገበ ነው—ፖሊሲው።

ማንኛውም የዚህ ፅሑፍ አንባቢ ሊገነዘበው እንደሚችለው የኢፌዴሪ መንግስት በሀገራችን ለሚገኝ ሁሉም ነዋሪ ዓለም አቀፍ ጥራትና ብቃት ያለው የኤሌክትሪክ አገልግሎት መስጠትና ተወዳዳሪ የኤሌክትሪክ ኤክስፖርት ኢንዱስትሪ የመሆን ትልሙን ለማሳት በትጋት በመስራት ላይ ነው።

ከግልገል ጊቤ አንድ እስከ ሶስት እንዲሁም እስከ ኮይሻ ግድብ ድረስ፣ የጣና በለስ ፕሮጀክቶች እንዲሁም የህዝባችን አንድነትና ህብረት መገለጫ የሆነውና ስድስት ሺህ 450 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል የማመንጨት አቅም ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታዎች የዚህ አባባሌ ሁነኛ አስረጅዎች ሊሆኑ የሚችሉ ይመስሉኛል። በመሆኑም እነዚህ ለአብነት ያህል ያነሳኋቸው ሜጋ ፕሮጀክቶች በሀገራችን ውስጥ በመፋጠን ላይ ያለውን ‘የኢንዱስትሪ አብዮት’ በበቂ የሃይል አቅርቦት ለመመለስ ከማገዛቸውም በላይ፤ በሀገራችን ኢኮኖሚ ውስጥ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን በመፍጠርና የቀጣናውን ሀገራት በሃይል አቅርቦት ለማስተሳሰር የታለሙ ናቸው።

ርግጥ ልማታዊው መንግስት ለሜጋ ፕሮጀክቶች ትኩረት ሲሰጥ እያደገ የመጣውን የኃይል ፍላጎት ከአቅርቦት ጋር እንዲጣጣም ስራውን እንደገና አደራጅቷል፣ ኢትዮጵያ በኃይል አቅርቦት ዘርፍ ስር ነቀል ለውጥ በማድረግ ከራሷ ፍጆታ ተርፋ በምሥራቅ አፍሪካ የታዳሽ ኃይል ምንጭ ማዕከል እንድትሆን እያደረገችም ነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሀገር ውስጥ ኮንትራክተሮችና የስራ ተቋማትን አቅም በመጠቀም ግንባታዎችን እንዲከናወኑ እየተደረገ ነው።

ከዚህ በመነሳትም ቀደም ሲል ይሰራበት የነበረውን 80 በመቶ የውጭ ምንዛሬ ድርሻ እዚህ ሀገር ውስጥ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን በማምረት ወደ 20 በመቶ ዝቅ እንዲል እየተደረገ ነው። ይህን ለማድረግ ይቻል ዘንድም ሀገር በቀሉ የብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽንን በማቋቋም ስራው እንዲሳለጥ እየተደረገ ነው።

በዚህ መሰረትም ኮርፖሬሽኑ በተለይም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት የኤሌክትሮ መካኒካልና የሃይድሮ እስቲል ስትራክቸር ሥራዎች እያከናወነ ነው። በኃይል ማመንጫ፣ የኃይል ማስተላለፊያ እና የኃይል ማሰራጫ ስራዎች ላይ ለአዳዲስና ጥገና ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ ግብዓቶችን እያመረተ በማቅረብ ላይ ይገኛል።

ከዚህ በተጨማሪ ሀገር በቀል ኮንትራክተሮችን ለመፍጠርና ብቁ ከማድረግ አኳያ በየክልሎች ከሙያና ቴክኒክ ትምህርት ቤቶች ተመርቀው የሚወጡ ተማሪዎችን በማደራጀትና ስልጠና እንዲወስዱ በማድረግ ሰፊ ተግባራት እንዲከናወኑ ተደርጓል። በቀጣይም በተሻለ ሁኔታ አቅማቸውን በመገንባት አስተዋጽኦአቸውን ከፍ በማድረግም እድሎች እየተመቻቹላቸው ነው። ይህም የተማረ የሰው ኃይልን ወደ ስራ ከማስገባትና የስራ አጥነትን ቁጥር ከመቀነስ አኳያ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል።

የኢፌዴሪ መንግስት የኤሌክትሪክ ኃይል ለሁለንተናዊ አገልግሎት ያለውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ በመገንዘብ ባለፉት 26 ዓመታት በተለይም ደግሞ ካለፉት 15 የስኬት ዓመታት ወዲህ በርካታ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን ከውሃ፣ ከንፋስና ጂኦተርማል በመገንባት ላይ ሲሆን፤ የኃይል ማስተላለፊያ ማከፋፈያ ጣቢያዎችንም ጎን ለጎን ለመገንባት ከሚመረተው ኃይል ጋር በማጣጣም በመላ ሀገሪቱ የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል። አሁንም እየተደረገ ነው። የብርሃን አውዶቹ ግንባታ የአገርና የቀጠናው አገራት በሃይል መተሳሰሪያዎች ናቸው።

የብርሃን አውዶቹ አገራችን ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ ልማት መር የምታደርገውን ሽግግር በመደገፍ ሜጋ ፕሮጀክቶቻችን ቀዳሚውን ሚና ይጫወታሉ። በሀገራችው ውስጥ በመፋጠን ላይ የሚገኘውን የኢንዱስትሪ ልማት እንዲሁም አገራዊ ዕድገትን በማፋጠን ረገድ ጉልህ ሚናቸውም የላቀ ነው። ለተፋሰሱ አገራትም የብርሃን አውዶች ሆነው ኢነርጂም፣ ምግብም፣ አቅምም የሚሆኑበት ጊዜ ሩቅ የሚሆን አይመስለኝም።  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy