Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የተሳሳተን በር ላለማንኳኳት…

0 289

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የተሳሳተን በር ላለማንኳኳት…

                                                         ታዬ ከበደ

ህገ ወጥ ስደት ዓለማችን የገጠማት ችግር ነው። ይህ ችግር በኢትዮጵያ ብቻ ተለይቶ የመጣ አይደለም። ችግሩ ዓለም አቀፋዊ እንደመሆኑ መጠን መፍትሔውም የሁሉንም አገራት ርብርብ የሚሻ ነው። ያም ሆኖ የኢፌዴሪ መንግስት ይህን የህገ ወጥ ስደት ችግር ለመከላከል ብርቱ ጥረት እያደገ ነው።

ይሁንና ጉዳዩ ለመንግስት ብቻ የሚተው አይደለም። ከቤተሰብ እስከ ማህበረሰብ ድረስ ያለው የህብረተሰቡ አካል ርብርብ ማድረግ ይኖርበታል። ይህን ማድረግ ካልተቻለ የችግሩን መንስኤና መፍትሔ ማግኘት ስለማይቻል ጉዳዩ የተሳሳተን በር እንደማንኳኳት ይቆጠራል። እናም የተሳሳተውን በር ላላማንኳኳት ሁሉም አካል ተግባሩን በብቃት መወጣት ይኖርበታል።

እንደሚታወቀው ሁሉ ህገ ወጥ ስደት በርካታ ሺህ ብሮች ወጪን ይጠይቃል። ወጪው አንድን ግለሰብ እዚህ ሀገር ውስጥ ሊያቋቁም የሚችል ነው። እናም ገንዘቡ እጅ ላይ እስካለ ድረስ እዚህ ሀገር ውስጥ ሰርቶ መቀየር የማይቻልበት ምክንያት አይታየኝም።

ይህን ገንዘብ ሊሳካ አሊያም ላይሳካ ለሚችል ነገር እንዲያው አውጥቶ ከመስጠትና በህይወት ላይ በራስ ገንዘብ ሞትን ለመጋበዝ ከማሰብ ይልቅ እዚሁ ሀገር ውስጥ አዋጪ ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮች እንዳሉ ማጤን ይገባል።

እርግጥ ድህነትና ስራ አጥነትን ለመቅረፍ የጥቃቱ ሰለባ የሚሆኑ ዜጎቻችን ቁጥር በቀላሉ እንደማይገመት ይገባኛል። ይሁንና የችግሩ መንስዔ ሁሉንም ይወክላል ብሎ መፈረጅ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም በህጋዊ መንገድ መውጣት እየተቻሉና እዚሁ ሀገር ውስጥ ሰርተው መበልጸግ የሚያስችል ገንዘብ እያላቸው ለህገ-ወጥ ደላሎች ከፍለው ለችግሩ የሚጋለጡ ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ ባለፉት 26 ዓመታት የኢትዮጵያ መንግስት በሀገራችን የተንሰራፋውን ድህነትንና ኋላቀርነትን ለማስወገድ የተለያዩ ስልቶችን ቀይሶ መንቀሳቀስ ሲጀምር፤ ስራ አጥነት መቅረፍ አንደኛው ተግባሩ በማድረግ ነበር፡፡ በዚህም በከተሞች የሚታየውን የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ ጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራትን በማደራጀት እንዲሁም የብድር አገልግሎት በመስጠት ለዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር ችሏል። ዜጎችም በየሙያቸው በመሰማራት ለሀገራዊ ልማት ከፍተኛ ጉልበትና አቅም መሆን መቻላቸውን አረጋግጠዋል።

በአሁኑ ወቅት በጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት ተደራጅተው ከመንግስት እንዲሁም ከቁጠባና ብድር ተቋማት ባገኙት ገንዘብ ተጠቅመው ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ ባለቤትነት የተሸጋገሩ ዜጎች በርካታ ናቸው፡፡ እነዚህ ዜጎች ከራሳቸው አልፈው ለሌሎችም የሥራ ዕድል በመፍጠር የመንግስትን ጥረት በመደገፍና የሀገሪቱን ልማት በማፋጠን ላይ እንደሚገኙ እማኝ የሚያስፈልገው ጉዳይ አይመስለኝም። በዚህ የኢኮኖሚ ስራ ውስጥ ገብቶ እንደሌሎቹ ወገኖች ራስን መቀየር እየታቻለ ስደትን እንደ አማራጭ መውሰድ ተገቢ አይደለም።

ይህ የህገ ወጥ ስደት ጉዳይ የእያንዳንዳችንን በር እስኪያንኳኳ ድረስ መጠበቅ የለብንም። እናም ለችግሩ መንስዔ የሆኑ ጉዳዩችን ማወቅ ይገባል። እነዚህ የችግሩ ተዋናዮች ግብ አንድና አንድ ነው። ሆኖም ገንዘብን አገኛለሁ ብሎ በወጡበት መቅረት መኖሩን ማስታወስ ይገባል። የህገ ወጥ ስደቱን መንገድ ለመቀነስ ብሎም ለመዝጋት መንግስት ፈርጀ ብዙ ጥረት እያደረገ ነው።

በአሁኑ ወትት መንግስት ለስራ አጥ ዜጎች የስራ ዕድልን በመፍጠር መንግስትነት ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚቻለውን ሁሉ አድርጓል፤ የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር አደጋን ለመከላከልም ከግንዛቤ ማስጨበጥ እስከ ተጨባጭ ርምጃዎችን መውሰድ ደረጃም ደርሷል።

እንደሚታወቀው ሁሉ በመላ ሀገሪቱ በተዋረድ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ተከላካይ ምክር ቤት ተቀቁሟል። በዚህም ህበረተሰቡ በጉዳዩ ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲያገኝ ሰፋፊ መድረኮች ተፈጥረው እንዲወያይበትና የመፍትሔው አካል እንዲሆን በየክልሉ በርካታ ተግባራት እውን ሆነዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የተደራጀው ግብረ ሃይልም በሀገራቸውም ሆነ ወደ ውጭ ሀገር በህጋዊ ተንቀሳቅሰው መስራት የሚፈልጉ ዜጎችን በቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በማስገባት በተለያዩ የስራ መስኮች የአጭር ጊዜ ስልጠና መስጠት እንዲሁም ከሥልጠናው በኋላ በሰለጠኑበት ሙያ በሀገር ውስጥ በመደራጀት ወደ ሥራ መሰማራት የሚፈልጉ ዜጎችን ከስራ ጋር ለማስተሳሰር ተችሏል።

ይህ ባለበት ሁኔታ አሁንም ዜጎች በህገ ወጥ መንገድ ወደ ውጭ ይሰደዳሉ። እርግጥ መንግስት ከላይ የጠቀስኳቸውን ተግባራት ቢፈጽምም አሁንም ችግሩ በበቂ ሁኔታ አልተቀረፈም። ይህን ችግር ለመፍታት ከህብረተሰብ እስከ ቤተሰብ ድረስ ያለው የህብረተሰብ ክፍል ወሳኝ ድርሻ ይኖረዋል። በተለይ ለችግሩ ተጋላጮች ቅርብ የሆነው ቤተሰብ የመንግስትን ጥረቶች መደገፍ ያለበት ይመስለኛል።

ቤተሰቦች ጥቂት የአካባቢያቸው ሰዎች ውጭ ሀገር ሄደው ሰርተው ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ኑሮ ማሻሻላቸውን ሲያይ ‘የእኔም ልጅ ምናለ በሄደ?’ የሚል ቁጭት ሲድርባቸው ይስተዋላል። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ቤተሰቦች የጎረቤቶቻቸው ልጆች በሚልኩት ገንዘብ በመማረክ ልጆቻቸው ወደ ውጭ ሄደው እንዲሰሩ ጫና ይፈጥራሉ። ይህ ጫናም ልጆች ወደ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር መረብ ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋቸዋል።

ይህ ግፊትም በህገ-ወጥ ደላላዎች በባዶ ሜዳ ላይ የተንጠለጠለ ተስፋ ጋር ታግዞ ልጆችም ‘እኔም ለምን እንደ ጓደኛዬ ውጭ ሰርቼ አልለወጥም’ የሚል ፍላጎት እንዲያድርባቸው ያደርጋል። ፍላጎት ገና ከጅምሩ በቤተሰብ የሚደገፍ በመሆኑ የተሻለ ኑሮ ለማግኘት ሲባል ህይወትን ማጣት እንዳለበት እንኳን ግምት ውስጥ አይገባም። እናም ከሰላማዊ ኑሮ ተነጥሎ የህገ-ወጥ ደላሎች ሲሳይ መሆንን ያስከትላል።

እዚህ ላይ ‘እናስ ምን ይደረግ?’ የሚል ጥያቄ ማንሳት ያስፈልጋል። ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የሀገራችን ዜጎች በህገ-ወጥ ደላላዎች ምክንያት በሚያጋጥማቸው ችግር በርካታ ውጣ ውረዶችን ከማለፍ ባሻገር በህገ-ወጥ መንገድ ተጉዘው ያሰቡበት ሀገር ሳይደርሱ መንገድ ላይ የሚቀሩበት ሁኔታ እየተከሰተ ነው።

ታዲያ ይህን ችግር ለመፍታት የኢፌዴሪ መንግስት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ሀገር አቀፍ የህገ-ወጥ ዝውውር አስወጋጅ ኮሚቴ አቋቁሟል። መዋቅሩም በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ተዘርግቶ ስራው ተጀምሯል። በየአካባቢው የሚገኘው የህብረተሰብ ክፍል በጉዳዩ ዙሪያ ግንዛቤ እንዲያገኝ ተደርጓል። የመንግስት ተቋማት እርስ በርስ በመናበብ ችግሩን ለመቅረፍ እየሰሩ ነው።

ይሁንና ይህ መንግሰታዊ ጥረት ለብቻው የሚያመጣው ለውጥ ያለ አይመስለኝም። በተለይም የችግሩ እምብርት የሆነው ቤተሰብ ዋነኛ ተዋናይ በመሆን አደጋውን ለማስቀረት የበኩሉን ድርሻ መወጣት ይኖርበታል። ይህ የተቀናጀ ጥረት ከተደረገ የችግሩ መፍትሔ ስለሚታወቅ ሌላ ተግባር በመከወን የተሳሳተን በር እንዳናንኳኳ ያደርገናል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy