Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የተግዳሮቶቹ መፍትሔዎች ይፍጠኑ

0 348

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የተግዳሮቶቹ መፍትሔዎች ይፍጠኑ

ዳዊት ምትኩ

የኢፌዴሪ መንግስት በአገራችን ውስጥ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን በርካታ ጥረቶችን አድርጓል። ምንም እንኳን መልካም አስተዳደር በማንኛውም አገር ውስጥ በሂደት የሚከናወን ቢሆንም፤ መንግስት ላለፉት 26 ዓመታት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ የተጓዘባቸውን መንገዶች ረጅም ናቸው። ያልተፈቱ ተግዳሮቶችም ጊዜያቸውን ጠበቀው በሂደት ሊፈቱ የሚችሉ ናቸው። ሆኖም መንግስት የተግዳሮቶቹን ምክንያቶች አስቀድሞ በሚገባ ያወቃቸው ስለሆነ መፍትሔዎቹንም ፈጠን ብሎ በመስጠት በተቻለ መጠን የህዝቡን እርካታ ማረጋገጥ ይኖርበታል።

እንደሚታወቀው ሁሉ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ላይ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ ቃል ገብቷል። ይህንን ቃሉን ከህዝብ ጋር በመሆን መፈፀም አለበት።

እንደሚታወቀው በ“ዕትዕ አንድ” ወቅት የተረጋገጠው ዕድገት ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት በአገር ውስጥም ከአገር ውጭ ሰፊ ዕውቅና እና ተቀባይነት ያገኘ ነው፡፡ በመጀመሪያው ዕቅድ የተመዘገበው ፈጣን ዕድገት በሀገራችን ሕዝቦች ዘንድ ከፍተኛ መነሳሳት ከመፍጠር ባለፈ ምርትና መርታማነት እንዲያድጉ ያደረገ ነው፡፡ በዕድገቱም አርሶ አደሮች፣ የግሉ ዘርፍ እና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች በፍጥነት ማደግ እንደሚቻል አረጋግጠዋል፤ ለላቀ ዕድገት እንዲተጉም ከፍተኛ መነቃቃትን እየፈጠረም ነው፡፡  

በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ጠንካራ የማስፈፀም አቅም ያላቸው መንግስታዊ መዋቅር የመፍጠር፣ ግልፅነትን የማስፈንና ሙስናን ከምንጩ የማድረቅ፣ የህዝብ ተሳትፎን የማረጋገጥ እና የባለብዙ ዘርፍ ጉዳዮችን በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ የማካተትና የመተግበር አቅጣጫዎች ተይዘው በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ የግልፅነትና የተጠያቂነት አሠራርን በማስፈን የኪራይ ሰብሳብሳቢነት አመለካከትና ተግባራትን ለመቀነስ በየደረጃው የሚደረጉ የሚደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ የህብረተሰብ ተሳትፎ የሚጠናከርበትና ከመንግስት ተቋማት ጋር ቋሚ ግንኙነት የሚፈጥርበት አሰራርም ተዘርግቷል፡፡

በተለይም የሀገራችን ህዳሴ እንቅፋት ይሆናል ተብሎ የሚታሰበውን ሙስናንና ኪራይ ሰብሳቢነትን አስተሳሰብና ድርጊት ከምንጩ ለማድረቅ ሲባል መንግስት የራሱን ከፍተኛ ባለስልጣናት ሳይቀር በህግ ፊት በማቅረብ ቁርጠኝነቱን አሳይቷል። በዚህም አስተማሪ በሆነ መንገድ ትምህርት ለመስጠት ሞክሯል።

ምንም እንኳን የሙስና እና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር በአጭር ጊዜ በቁጥጥር ስር ሊውል የሚችል ባይሆንም፣ ድርጊቱን በሂደት የመቅረፍ ስራዎች ተከናውነዋል። “በሁለተኛው ዕትዕ” ወቅት በዘርፉ ዙሪያ የሚከናወነው ተግባርም በቀዳሚው የዕቅድ ዘመን የተካሄደውን ሁሉን አቀፍ ክንዋኔዎች የሚያጠናክርና አዳዲስ አሰራሮችን የሚከተል ነው።

እስቲ በቅድሚያ “ዕትዕ ሁለትን” ጥቅል እሳቤዎችን በአጭሩ እንመልከትና የልማት ዕቅዱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከመፍታት አኳያ ሊጫወት የሚችለውን ለመመልከት እንሞክር።

ሁለተኛው የአምስት ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በሀገራችን የተጀመረውን የትራንስፎርሜሽንና የህዳሴ ጉዞ በማፋጠን በ2017 ዓ.ም ኢትዮጵያን የመጀመሪያ ደረጃ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለማሳለፍ በሚደረገው ጥረት ወሣኙን ምዕራፍ የያዘ ነው። የዜጐችን እኩል የልማት ተሳታፊነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና ልማታዊ የፖለቲካ ኢኮኖሚ እና አንድ የጋራ ማህበረሰብ ለመገንባት የላቀ አስተዋፅኦ ያለው ዕቅድ ነው፡፡

ስለሆነም የዕቅዱ ዋና መነሻ በ2017 ዓ.ም ኢትዮጵያን የመጀመሪያ ረድፍ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ የማሰለፍ ሀገራዊ ራዕይን የነገበ ነው ማለት ይቻላል፡፡ እናም በቀጣዩ የአምስት ዓመት ዕቅድ እስከ 2012 ዓ.ም ድረስ የሚከናወኑ የልማት ተግባራት በጥቅሉ ሲታዩ፣ ወደዚሁ ሀገራዊ ራዕይ እንዲያደርሱን ሆነው የተቀረፁ መሆናቸውን መገንዘብ ያሻል፡፡ ሁለተኛው ዕቅድ ሀገራዊ የሴክተር ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችንም በመነሻነት የያዘ ነው። ሁላችንም እንደምንገነዘበው በሀገራችን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትንና ትራንስፎርሜሽንን ለማረጋገጥ እንዲሁም በየደረጃው የሕዝቡን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ዕውን ለማድረግ ብሎም የዴሞክራሲ ሥርዓታችንን ለመገንባት በሚገባ የተዘረዘሩ አገራዊ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ተዘጋጅተው በመተግበር ላይ ናቸው፡፡

እርግጥ እነዚህ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ከአንድ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ተሻጋሪ ከመሆናቸውም በላይ፣ እስካሁን ባለው አተገባበር መልካም ውጤቶች እያስገኙና ለህዳሴ ጉዟችን ፅኑ መሠረት እየጣሉ ናቸው። በመሆኑም ቀደም ሲል የጠቀስኩት የመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን አፈፃፀሞች የዕቅዱ መነሻ ተደርገው ተወስደዋል።

አንድ ዕቅድ ሲዘጋጅ የዕቅዱ ባለቤት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተስማማባቸው ጉዳዩች ታሳቢ ይሆናሉ። በመሆኑም ሀገራችን እ.ኤ.አ ከ2016 እስከ 2030 ገቢራዊ የምታደርገው ዘላቂ የልማት ግቦች በዕቅዱ ላይ በመነሻነት እንዲያዝ ምክንያት ሆኗል። ሁላችንም እንደምናስታውሰው በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ሲዘጋጅ የሚሊንየም የልማት ግቦችን ማሳካት እንደ አንድ መነሻ ተወሰዶ እጅግ ሰፋፊ ስራዎች ተከናውነዋል። ሀገራችን አብዛኛዎቹን የልማት ውጥኑን ግቦች በማሳካትም አመርቂ ውጤቶችን አግኝታባቸዋለች።

በሁለተኛው የዕቅድ ዘመን አምስት ዓመታት የሚከናወኑት “ዘላቂ የልማት ግቦችን” (SDG) ለማሳካት ሀገራችን ተነሳሽነቱን በመውሰድ ከዓለም አቀፉ ራዕይ ውስጥ የተወሰኑትን ለማሳካት ትችል ዘንድ በዕቅዱ ውስጥ እንዲካተቱ አድርጋለች። እነዚህን ግቦች ለማሳካት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከስር ከስር እየፈቱ መሄድ ያስፈልጋል።

እንደሚታወቀው ሁሉ ልማታዊ ፖለቲካ ኢኮኖሚ መገንባትና ኪራይ ሰብሳቢነትን ለማዳከም የዛሬ 16 ዓመት ገደማ በተካሄደው የተሀድሶ መስመር ተግባራዊ መሆን ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ መልካም ውጤቶችን ማስመዝገብ ተችሏል፡፡ ታዲያ አሁንም በገጠር ልማታዊ የፖለቲካ ኢኮኖሚ የበላይነት ያለው እንዲሆንና የግብርናና የገጠር ትራንስፎርሜሽንን ለማምጣት የበለጠ መትጋት ያስፈልጋል።

በአንፃሩም በከተሞች የበላይነት ያለው የኪራይ ሰብሳቢነት የፖለቲካ ኢኮኖሚ የሚያሳየን ነገር ቢኖር ኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰቡ ዛሬም ስር የሰደደ መሆኑን ነው። እናም ልማታዊነትን ይበልጥ በማጐልበትና ኪራይ ሰብሳቢነትን ከምንጩ በማድረቅ ፖለቲካ ኢኮኖሚው ልማታዊ እንዲሆን ማድረግ ይገባል፡፡

ይህን የዕቅዱን ትልም ዕውን ለማድረግ የፖለቲካ አመራሩና የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኛው ከህዝቡ ጋር በተደራጀ መንገድ በመቀናጀት መስራት ይገባቸዋል። ለዚህ ደግሞ ‘ይህ ስራ የእገሌ ነው’ ሳይባል ሁሉም የበኩሉን ገንቢ ሚና ሊጫወት ይገባል። እርግጥ ሀገራችን አረጋግጠዋለሁ ብላ ለተነሳችው የህዳሴ ጉዞ ትልልቆቹ አደጋዎች ሙስና እና ኪራይ ሰብሳቢነት መሆናቸው ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው። እናም አደጋዎቹን ለመዋጋትና ትግሉን በልማታዊና ዴሞክራሲያዊ  እሳቤ የበላይነት ለመደምደም በርካታ ስራዎችን ማከናወን የግድ ይላል። ለህዝቡ ጥያቄዎች አቅም በፈቀደ መጠን ምላሽ መስጠትም ጊዜ ሊሰጠው የሚገባ አይመስለኝም።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy