NEWS

የትግራይ ክልል ምክር ቤት በአስቸኳይ ጉባኤው አዲስ የስራ አስፈፃሚ አባላት ሹመትን ያፀድቃል

By Admin

January 05, 2018

የትግራይ ክልል ምክር ቤት ጥር 2 ቀን 2010 ዓመተ ምህረት 5ኛ ዘመን 3ኛ አስቸኳይ ጉባኤውን ያካሂዳል።

የምክር ቤቱ የህዝብ ግኑኝነት እና ኮንፍረንስ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ ታረቀኝ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለፁት፥ ምክር ቤቱ በአስቸኳይ ጉባኤው የክልሉን መንግስት የስራ አስፈፃሚ አባላት ሹመትን የሚያፀድቅ ይሆናል።

በምክር ቤቱ አብላጫ መቀመጫ በመያዝ ክልሉን እያስተዳደር የሚገኘው ፓርቲ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ /ህወሓት/ ስራ አስፃሚ ኮሚቴ በቅርቡ ያካሄደውን ስር ነቀል ግምገማ፣ ሂስና ግለ ሂስን ተከትሎ ዘጠኝ አባላት ያሉት የድርጅቱን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫን ማካሄዱ ይታወቃል።

ቀጥሎም በክልሉ እና በፌደራል ደረጃ የሚሰሩ የስራ አስፈፃሚ አባላት የስራ ምደባም አድርጎ ነበር።

በዚህ አዲስ ምደባ መሰረትም የህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤልን ጨምሮ ዶ/ር አዲስዓለም ባሌማ እና ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም በክልሉ እንዲሰሩ የተመደቡ ናቸው።

አቶ ዓለም ገብረዋህድ እና አቶ ጌታቸው ረዳ በህወሓት ፅህፈት ቤት እንዲሁም ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሄር፣ አቶ አስመላሽ ወልደስላሴ፣ ዶ/ር አብራሃም ተከስተ እና አቶ ጌታቸው አሰፋ በፌደራል ደረጃ እንዲሰሩ የተመደቡ ናቸው።

 

በሙሉጌታ አፅበሃ