Artcles

የአካባቢ ጥበቃ ለዘላቂ ልማት

By Admin

January 25, 2018

የአካባቢ ጥበቃ ለዘላቂ ልማት

የኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ ከ80 በመቶ በላይ የሃገሪቱ ህዝብ የተሰማራበት ነው። በ2009 ዓ/ም የመንግስት አፈጻጻም ሪፖርት እንደሚያመለክተው ግብርና በአጠቃላይ ኢኮኖሚ ውስጥ ያለው ድርሻ 36 ነጥብ 3 በመቶ ነው። የሃገሪቱ የወጪ ንግድም በግብርና ላይ የተመሰረተ ነው። ቡና፣ ሰሊጥ፣ ጥራጥሬ፣ ቅመማ ቅመም፣ አበባና የቁም ከብት  ከሃገሪቱ የወጪ ንግድ ውስጥ 80 በመቶ ያህሉን ይሸፍናሉ።

እነዚህ እውነታዎች የሃገሪቱ ኢኮኖሚ ግብርና ላይ የተመሰረተ መሆኑን ያመለክታሉ። ሃገሪቱ የግብርናን ዘርፍ ችላ ብላ ለአምራችና ለአገልግሎት ኢንደስትሪ መፈጠርና እድገት የሚያስፈልጋትን ሃገራዊ የካፒታል ክምችት መፍጠር አትችልም። በኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ ተቶ የህዝቡን ኑሮ ደረጃ በደረጃ ማሻሻል የሚያስችል ልማት ማምጣት የማይታሰብ ነው። በመሆኑም እስካሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የሃገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ፖሊሲ ግብርና ላይ የተመሰረተ ከመሆን ውጭ አማራጭ የለውም፤ ግብርና ላይ የተመሰረተ የእድገትና ልማት ፖሊሲ።

በዚህ ፖሊሲ ትግበራ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የግብርናውን ዘርፍ ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የአርሶ አደሩን ህይወት ወደተሻለ ደረጃ ማሸጋጋር ተችሏል። የአርሶ አደሩ ገቢ ማደግ በሃገሪቱ ከፍተኛ የገበያ አቅም በመፍጠር ሃገራዊ የካፒታል ክምችት እንዲፈጠር አድርጓል። ይህም የአገልግሎት፣ የንግድና የአምራች የኢንደደስትሪ ዘርፉን አነቃቅቷልል። በአጠቃላይ ባለፉት አንድ ተኩል አስርት ዓመታት ከ2008 በጀት ዓመት በስተቀር የግብርናው ዘርፍ 8 በመቶ ያህል እድገት ማሳየቱን መረጃዎች ያመለክታሉ። በ2009 በጀት ዓመት የግብርናው ዘርፍ የ2 ነጥብ 3 በመቶ እድገት ነበር ያስመዘገበው። ይህ የሆነው ሃገሪቱ 10 ነጥብ 2 ሚሊየን ህዝብ ለምግብ እጥረት ባጋለጠው ኤል ኒኖ የተሰኘው የአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በተከሰተ ድርቅ በመመታቷ ነበር።

በ2008 በጀት ዓመት ወደ 2 ነጥብ 3 በመቶ አሽቆልቁሎ የነበረው የግብርናው ዘርፍ እድገት፣ በ2009 በጀት ዓመት የ6 ነጥብ 7 በመቶ እድገት አስመዝግቧል። በተያዘው በጀት ዓመት ማለትም በ2010 በጀት ዓመት የግብርና ዘርፍ በ8 በመቶ ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል። እስካሁን ባለው የምርት ስብሰባ ሂደት ያለው ሁኔታ የእድገት እቅዱ ሊሳካ እንደሚችል ያመለክታል። ከዘንድሮ የመኸር ምርት ብቻ በአጠቃላይ 345 ሚሊዮን ኩንታል የሰብል ምርት እንደሚጠበቅም የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር አስታውቋል። ባለፈው ዓመት ከመኸር እርሻ የተሰበሰበው አጠቃላይ ምርት 292 ሚሊየን ኩንታል ነበር።

ከላይ እንደተገለጸው የሃገሪቱ ኢኮኖሚና የህዝቡ የህልውና መሰረት የሆነው ግብርና በዝናብ ላይ ጥገኛ ነው። የግብርናውን ዘርፍ እድገት ቀጣይነት ለማረጋጋጥ፣ በየወቅቱ በሚከሰተው ድርቅ ምክንያት የሚደርሰውን ተጽእኖ በአስተማማኝ ሁኔታ ለመቋቋም፣ የወጪ ንግዱን ለማሳደግ፣ እንዲሁም ሰፊ እቅድ የተያዘለትን የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንደስትሪ ዘርፍ በቂ ግብአት ለመመገብ የግብርናው ዘርፉ ከዝናብ ጥገኝነት መላቀቅ ይኖርበታል። የሃገሪቱን የገጸና ከርሰ ምድር ውሃ በሚከናወን የመስኖ ልማት ግብርና ለአጠቃላይ የሃገሪቱ ኢኮኖሚ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ማጎልበት ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ ተስፋ ሰጪ ስራዎች እየተከናወኑ ነው። ባለፉት ጥቂት ዓመታት ተግባራዊ መደረግ የጀመረው የአነስተኛ የአርሶ አደር ማሳ የመስኖ ልማት ለዚህ ማሳያነት ሊጠቀስ ይችላል። ከዚህ ባሻገር ሰፋፊ የመስኖ እርሻዎችንም ለማስፋፋት ሰሞኑን ሃገር አቀፍ የመስኖ ልማት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ውይይት ተደርጎበታል።

የአርሶ አደር አነስተኛ ማሳ የመስኖ ልማትን በተመለከተ፣ የእርሻና የተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በ2009 በጀት ዓመት 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመስኖ ለምቷል። ከዚህ የመስኖ ልማት ከ370 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተገኝቷል። በዚህም 7 ሚሊዮን ያሀለ አርሶ አደሮች ተሳታፊ ሆነዋል።

ዘንድሮም በተመሳሳይ  ከ7 ሚሊየን በላይ አርሶ አደሮችን በመስኖ ልማት ፕሮግራም የማሳተፍ እቅድ ተይዟል። እነዚህ አርሶ አደሮች በተለይ የመኸር ምርት ከተሰበሰበ በኋላ ባሉ ደረቃማ ወራት በመስኖ ልማት ላይ የሚሰማሩ ናቸው። በመስኖ ፕሮግራሙ 3 ነጥብ 3 ሚሊየን ሄክታር መሬት ለማልማት ዕቅድ ተይዟል። አሁን የደረሱ ሰብሎች በተሰበሰቡባቸው አካባቢዎች የመጀመሪያው ዙር የመስኖ ልማት ፕሮግራም መካሄድ ጀምሯል። እስካሁን ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር መሬቱ በመስኖ ልማት መርሃ ግብር በሰብል መሸፈኑንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል። ከዘንድሮ የመስኖ ልማት 450 ሚሊየን ኩንታል ምርት ይሰበሰባል ተብሎ ይጠበቃል። የመስኖ ልማት ምርቶች በአመዛኙ አትክልትና ፍራፍሬ ላይ የሚያተኩሩ ናቸው። እርግጥ የአገዳ ሰብሎችም በመስኖ ይለማሉ።

በሌላ በኩል ሰፋፊ የመስኖ እርሻዎችንም የማስፋፋት እቅድ ተይዟል። በሰፋፊ የመስኖ እርሻን በተመለከተ እስካሁን ለስኳር ፋብሪካዎች ግብአት የሚውል የሸንኮራ አገዳ ከማልማት ያለፈ ይህ ነው የሚባል የሰፋፊ የመስኖ ልማት ስራ አልታየም። ይህን ለግብርናው እድገት ማነቆ የሆነ ሁኔታ ለማቃለል ሰሞኑን በኢትዮጵያ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከልና በአዲስ አበባ ቴክኖሎጂ ኢኒስቲቲዩት ሃገራዊ የመስኖ ልማት ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱ ተገልጿል። በዚህ ፍኖተ ካርታ  ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ውይይት ተካሂዷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያምን ጨምሮ ሚኒስትሮች በተሳተፉበት በዚህ መድረክ ላይ ሀገራዊ የመስኖ ልማት ሁኔታና በመስኖ ልማት ዘርፍ ያለውን ክፍተት እንደሁም ተግዳሮቶችና የአፈፃፀም አቅጣጫዎች የሚመለከት የባለ ሞያ ማብራሪያ ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል። ፍኖተ ካርታው ሀገሪቱ እስካሁን በመስኖ ልማት የምትገኝበትን ደረጃና ዘርፉን ለማሳደግ በቀጣይነት መከናወን ያለባቸውን ተግባራት የሚያመላክት መሆኑ ተነግሮለታል። ፍኖተ ካርታው ወንዞችን በተለይም ሀገር አቋራጭ ወንዞችን በአግባቡ መጠቀም የሚቻልበትን ሁኔታ የሚያመለክት እንዲሁም የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን የተዘጋጀ መሆኑ በውይይት መድረኩ ላይ ተገልጿል።

በመስኖ ልማት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱ ሃገራት ለመስኖ ልማት ከአጠቃላይ አገራዊ ምርታቸው ከፍተኛውን በጀት እንደሚመድቡ፣ አንዳንድ የአፍሪካ ሃገራት ከአጠቃላይ አገራዊ ምርታቸው ከ22 እስከ 30 በመቶ ለመስኖ ልማት እንደሚያውሉ በመድረኩ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ገልጸዋል። ኢትዮጵያ እስካሁን ከአጠቃላይ አገራዊ ምርቷ ለመስኖ ልማት የምትመድበው በጀት አነስተኛ መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ፍኖተ ካርታው ይህን ጥያቄ በአግባቡ ሊመልስ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ፍኖተ ካርታው ለሚቀጥሉት 10 ዓመታት ማገልገልና በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሸን ሁለት የትግበራ ዓመታትም ወደ ስራ መግባት እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።

ይህ ፍኖተ ካርታ በተያዘው በጀት ዓመት ወደስራ ይገባሉ ተብለው የሚጠበቁ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተገነቡ  ለመስኖ ልማት የሚውሉ የግድብ ፕሮጄክቶችን አጠቃቀም ለመምራት ሊያግዝ ይችላል ተብሎ ይገመታል። የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን  ዘንድሮ ወደስራ ይገባሉ ብሎ ያሳወቃቸው የተንዳሆ፣ ከሰም፣ ርብ፣ አልዌሮ፣ ቆጋ፣ መገጭና ጎዴ አካባቢዎች የሚገኙ ግድቦች ለአርሶ አደሩ አነስተኛ ማሳ ልማት የሚውሉም ቢሆኑ በዋናነት ግን ለሰፋፊ እርሻዎች የሚያገለግሉ ናቸው።

የመስኖ ልማት ከዝናብ ጥገኝነት የሚያላቅቅ ቢሆንም መስኖም ቢሆን ዞሮ ዞሮ በተፈጥሮ ላይ ጥገኛ ከመሆን እንደማያመልጥ ግን መታወቅ አለበት። ለመስኖ ልማት የሚውሉ በቂና አስተማማኝ የገጸና የከርሰ ምድር ውሃ ክምችት ለማግኘት የተስተካከለ የአየር ንብረት ሊኖር የግድ ነው። ይህ ደግሞ በዋናናት የተፈጥሮ አካባቢ እንክብካቤ ስራን ይጠይቃል።

ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ብዙ ርቀት ተጉዛለች ማለት ይቻላል። በተለይ ከ2003 ዓ/ም ጀምሮ በመላ ሃገሪቱ የተከናወኑትና አሁንም በመከናወን ላይ የሚገኙት የተፋሰስ ልማትና የተፈጥሮ ሃብት እንክብካቤ ስራዎች በዓለም አቀፍ ደረጃም በአርአያነት የሚጠቀስ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት አስችለዋል። ይህ የተፋሰስ ልማትና የተፈጥሮ እንክብካቤ ስራ የአየር ንበረት ተጽእኖን በመከላከል፣ ደርቀው የነበሩ ምንጮች ዳግም እንዲፈልቁ በማድረግና የወንዞችን ውሃ መጠን በመጨመር የአርሶ አደሩን ምርታማነት በማሳደግ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከት ጀምረዋል። ለሰፋፊ የመስኖ እርሻ የሚውሉ ግድቦችም ቢሆን በምንጮችና በወንዞች ውሃ ላይ ጥገኛ ስለሚሆኑ ሰሞኑን የተዘጋጀውን ሃገራዊ የመስኖ ልማት ፍኖተ ካርታ ተግባራዊ ማደረግ የአካባቢ እንክብካቤን የሚመለከት መሆን ይኖርበታል።