Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የአገራችን መፃዒ ተስፋዎች

0 239

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የአገራችን መፃዒ ተስፋዎች

ዳዊት ምትኩ

የሀገራችንን ዩኒቨርስቲዎችንና በየዩኒቨርስቲዎች ውሰጥ የሚገኙት ወጣቶችን የአገራችን ተስፋዎች ናቸው። ወጣቶቹ የሚገኙባቸው ዩኒቨርቲዎች የሰላም ማዕከል መሆናቸውን፣ የአብሮነትና የተስፋ ማዕከሎችና የአዳዲስ ቴክኖሎጂ መፍለቂያ እንዲሁም የአገራችን መፃዒ ተስፋዎች መሆናቸው አይታበይም። በየዩኒቨርስቲዎቹ ውስጥ የሚገኙት ወጣቶች ልክ እንደሚማሩባቸው ዩኒቨርስዎች የአገራችን ተረካቢዎችና መፃዒ ተስፋዎች እንደሆኑ ግልፅ ነው።

መንግስት ዩኒቨርስቲዎችን በፍጥነት የሚገነባው ሀገራችን የጀመረችው የልማት ስልጠት በተማረ የሰው ሃይል መታገዝ ስላለበት ነው። በዕውቀት የተካነ ወጣት ሀገራችን ለጀመረችው የልማት እመርታ ቁልፍ ሚና ይጫወታል። በሌላ በኩልም ዩኒቨርስቲዎች ይህን ሀገራዊ የልማት ፍላጎት ለማሳካት ጠንካራ ወጣቶች የሚፈሩባቸው እንጂ የሁከት አምባዎች መሆን አይገባቸውም።

መንግስት ዩኒቨርስቲዎችና ተማሪዎቻቸው የሰላም ማዕከል፣ ‘የትንሿ ኢትዮጵያ’ ማንነት መገለጫ፣ የመከባበርና የአንድነት ማሳያ መድረኮች እንዲሆኑ በመስራት ላይ ይገኛል። ይህ የመንግስት ፍላጎት ሀገራችን የተያያዘችውን ሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን ከማሳካት የመነጨ ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ እርግጥ እቅዱ ከተጀመረ ሁለት ዓመትን እልፍ ያለ ቢሆንም መንግስት በየደረጃው የትምህርት ጥራትን የማሻሻል ፕሮግራም ዘርግቶ እየሰራ ነው። ለኢኮኖሚ እድገቱና ለማህበራዊ ልማቱ በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠነ ብቁ ዜጋ ማፍራት ቁልፍ ተግባር እንደመሆኑ መጠን፤ መንግሥት የከፍተኛ ትምህርት ጥራትን የማረጋገጥ ስራ በማጠናከር ተገቢውን ተግባር እየተወጣ ነው። ለዚህም የግል ባለሃብቶች በትምህርት ዘርፍ በሰፊው እንዲሳተፉ ማበረታታት፣ ድጋፍ መስጠትና ስታንዳርዱን የጠበቀ ለመሆኑ ተገቢው ክትትልን የማድረግ ስራዎችን እያከናወነ ነው። በመንግስት የትምህርት ተቋማትም እንዲሁ እየተከናወነ ነው።

ያም ሆኖ ግን በመንግስት ጥረት ብቻ የትምህርት ጥራት ሊጠበቅ አይችልም። በመሆኑም ህብረተሰቡ የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ በመደረገው ጥረት ግንባር ቀደም ተሳታፊ መሆን ይኖርበታል።

በእስካሁኑ ሂደት ህብረተሰቡ የመማር ማስተማሩ አካል እንዲሆን በማድረግ ከጥራት አኳያ የሚነሱትን ችግሮች ለመፍታት በሚደረገው ርብርብ የበኩሉን ድርሻ እንዲያበረክት እየተደረገ ነው። ይህ ሁኔታም በቀሪዎቹ የዕቅዱ ዓመታት ተጠናክሮ ከቀጠለ በትምህርት ጥራት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት የሚቻል ይመስለኛል።

የከፍተኛ ትምህርትን ለማስፋፋት በሚደረገው ጥረት ቀደም ሲል ከነበሩት በተጨማሪ አስራ አንድ የመንግስት ዩኒቨርስቲዎችን በመገንባት በቅድመ-ምረቃ መደበኛ ፕሮግራም 600 ሺህ ተማሪዎችን የመቀበል አቅም እንዲኖራቸው ይደረጋል። የድህረ ምረቃ ተማሪዎች ብዛትም ወደ 63ሺ ከፍ እንዲል ግብ ተጥሎ ስራው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እየተከናወነ ነው።

ይህም የሴት ተማሪዎች ተሳትፎን በቅድመ ምረቃ ፕሮግራም በ2007 ዓ.ም ከነበረበት 32 በመቶ በ2012 ዓ.ም ወደ 45 በመቶ ከፍ እንዲል፣ በሁለተኛ ዲግሪ ፕሮግራም በ2007 ዓ.ም ከነበረበት 22 በመቶ በ2012 ዓ.ም ወደ 35 በመቶ እንዲያድግ እንዲሁም በሶስተኛ ዲግሪ ፕሮግራም በ2007 ዓ.ም ከነበረበት 11 በመቶ በ2012 ዓ.ም ወደ 20 በመቶ እንዲያሳድግ ታስቦ መሰረታዊ ስራዎች ገቢራዊ እየተደረጉ ነው። ታዲያ ይህ የመንግድስት ግብ እንዲሳካ ዩኒቨርስቲዎቻችንና ተማሪዎቻቸው የሰላም ሃዋርያ መሆን ያለባቸው ይመስለኛል።

ለዚህ ደግሞ ተማሪዎች የበኩላቸውን ድርሻ መጫወት አለባቸው። የዛሬው ትውልድ ወጣት እድለኛ ነው። ትምህርት በሩ ድረስ ተዘርግቶለታል። ባለፉት ስርዓቶች የጥቂቶች መጠቀሚያ የሆነው ትምህርት ዛሬ የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል በር እያንኳኳ ነው። ወጣቱ በዚህ ዕድል ተጠቅሞ ራሱንና ሀገሩን ሊጠቅም ይችላል።

ቀደም ሲል የነበረውን የትምህርት ቤቶች ስርጭት ኢ- ፍትሃዊነትን ለማስወገድ በአገሪቱ እያደገ የመጣው የትምህርት ቤቶች ቁጥር ሥርጭት ፍትሃዊነቱን እንዲጠብቅ ተደርጓል፡፡  ከዚህ አንፃር ቀደም የአገሪቱ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እኩል ተጠቃሚ አልነበሩም፡፡

በትምህርት ሥርጭት ላይ የነበረው ኢ-ፍትሃዊነት በክልሎች መካከል ልዩነት ፈጥሮ እንደ ነበር አይዘነጋም፡፡ ይህ ኢ-ፍትሃዊ ስርጭት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በተመጣጣነ ሁኔታ ማደግ እንዳይችሉ እንዲሁም የልማት ተጠቃሚነታቸውም ላይ ልዩነት መፍጠሩ የሚታወቅ ነው፡፡

በአገራችን ባለፉት 26 ዓመታት ከተሰሩት ተግባራት አንዱ በአገሪቱ ፍትሃዊ የትምህርት ስርጭት እንዲኖር መደረጉ ነው፡፡ በእያንዳንዱ ክልል በርካታ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ ኮሌጆች እና ዩኒቨርስቲዎች ተቋቁመው የትምህርት አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡ በአገሪቱ የነበሩት የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ታድሰዋል፣ የማስፋፊያ ግንባታም ተደርጎላቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በርካታ አዳዲስ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል፡፡

የቴክኒክና ሙያ ተቋማት በልዩ ትኩረት እንዲስፋፉ በመደረጉ የተቋማቱ ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መጥቷል፡፡ ይህ የአገሪቱ የምጣኔ ሀብት እድገት የሚጠይቀውን የሰው ኃይል ከማፍራት ረገድ የማይተካ ሚና እንዳለው ባለፉት 26 ዓመታት በተግባር ታይቷል፡፡ ተማሪዎች ስራ ፈጣሪ እንጂ ክፍት ስራ ፈላጊ እንዳይሆኑ በማድረግ ረገድም ውጤታማ ተግባር እየፈፀሙ ነው፤ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም እንዲሁ ተስፋፍተዋል። ተቋማቱ በአንድ በኩል አገሪቱ የምትፈልገውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ያፈራሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የኅብረተሰቡን ችግር የሚፈቱ ጥናቶችንና ምርምሮችን ያደርጋሉ፡፡

እንደሚታወቀው በኢፌዴሪ መንግስት በኩል ለረጅም ጊዜያት ከእህልና ገንዘብ ባልተናነሰ መልኩ የእውቀት ጥገኛ ሆነን የተጓዝንበት ምዕራፍ መፍትሄ ሳይበጅለት አልቀጠለም። ሀገራችን ውስጥ ዕውን በሆነው ልማታዊና ዴሞክራሲ መንግስት አማካኝነት ይህ ምዕራፍ ተዘግቶ ወደ አዲስ አስተሳሰብና የዕውቀት ሽግግር ለመጓዛችን በርካታ ማሳያዎችን ማቅረብ ይቻላል።

ወጣቶች የሀገራችን መፃዒ ተስፋዎች ናቸው። የሚማሩባቸው ዩኒቨርስቲዎችም እንዲሁ። ዛሬ ዩኒቨርስቲዎቹ ሰላም መሆን ካልቻሉ የነገው የልማት ጉዞ ሊሳካ አይችልም። ወጣቶች በችግር ፈቺ የምርምር ተቋማት ላይ መሰለፍ ካልቻሉ ምንም ዓይነት ውጤት ለማግኘት አይቻልም።

በመሆኑም ወጣቶቹና ዩኒቨርስቲዎቻችን የነገው መፃዒ ተስፋዎቻችን በመሆናቸው ለአገራቸው ዕድገት መሰለፍ ይኖርባቸዋል። የአገራችን መፃዒ ተስፋ የሆነ ሃይል ደግሞ ቅድሚያ መስጠት የሚገባው ለአገሩና ለአገሩ ብቻ ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy