Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የአፍሪካዊያን ተምሳሌት

0 645

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የአፍሪካዊያን ተምሳሌት

                                                      ደስታ ኃይሉ

በያዝነው ወር የአፍሪካ ህብረት 30ኛ መደበኛ ስብሰባ በመዲናችን ይካሄዳል። ይህ ስብሰባ መደበኛ ቢሆንም አገራችን ለአፍሪካዊያን ያደረገችው ውለታ ሊዘከርበት የሚገባ ይመስለኛል። ኢትዮጵያ ለቀድሞው የአፍሪካ ህብረት (አ.አ.ድ) እና ኋላ ላይም ለአፍሪካ ህብረት (አህ) በርካታ አስተዋፅኦዎችን አበርክታለች።

ኢትዮጵያ ሁሌም ቢሆን ለአፍሪካዊያን ነፃነትና ተጠቃሚነት የታገለችና ዛሬም እየታገለች ያለች አገር ናት። ከዚህም አልፋ ለወንድሞቻችን አፍሪካዊያን የሰላምና የልማት እንዲሁም የዴሞክራሲ ተጠቃሽ መሆን እንደቻለችና በዚህም ሳቢያ ህብረቱ አገራችንን ከመቀመጫነቱ ባሻገር የአፍሪካ ተምሳሌት አድርጎ ይቆጥራታል። ታዲያ በያዝነው ጥር ወር የሚካሄደው የህብረቱ የመሪዎች ስብሰባ በመዲናችን ሲካሄድ በሁሉም መስኮች የአፍሪካዊያን ተምሳሌት መሆናችንን ማሳየት ይጠበቅብናል።  

ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ ለአፍሪካዊያን ወንድሞቿ የሰራችና ወደፊትም የምትሰራ አገር ናት። ሀገራችን በምትከተለው ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ መርህም ተቀባይነት ያላት ናት። በዚህ አስተሳሰቧም የአባይ ውኃ አጠቃቀም ፍትሃዊ በሆነ መልኩ መጠቀም አስፈላጊነቱን አምናም እየሰራች ነው።

የናይል የላይኛው ተፋሰስ ሀገሮች የጋራ ማዕቀፍ ፈርማ ወደ ማጽደቅ ሂደት በመግባት ላይ ነች። ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመገንባት 6 ሺህ 450 ሜጋ ዋት በማመንጨት ዓላማዋ ከሀገር ውስጥ ፍጆታ አልፎ ጎረቤት ሀገሮችንም መጥቀም ስለሆነ ነው።

ኢትዮጵያ ከደርግ ውድቀት በኋላ ሰላም መርሁ በሆነው የኢፌዴሪ መንግስት አማካኝነት አፍሪካዊ አስተዋፅኦውንና ኃላፊነቱን ከምንጊዜውም በላቀ ሁኔታ ተወጥቷል፤ እየተወጣም ይገኛል። በዚህ መሰረትም በሩዋንዳ እ.ኤ.አ በ1990ዎቹ በተከሰተውና የዓለምን ሕዝብ ባስደነገጠው የዘር ማጥፋት እንቅስቃሴ ሰላም እንዲያስከብሩ ከተደረጉት ሀገሮች አንዷ ሀገራችን ተደርጓል። ያኔ ቡሩንዲ ውስጥ ሁቱና ቱትሲ የተባሉ ጎሳዎቿ ግጭት ላይ ነበሩ። ዘር ለይቶ የተፈጠረውን ዘግናኝ ድርጊት ለማስቆም በአፋጣኝ ሰላም አስከባሪ ኃይላቸውን እንዲልኩ ከተደረጉት ሀገሮች መካከል ኢትዮጵያ ቀዳሚዋ ናት። በዚህም ታሪካዊ አስተዋጽኦዋን አበርክታለች። በላይቤሪያም እንዲሁ። ላይቤሪያ በከፍተኛ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ በነበረችበት ወቅት ሀገሪቱን ወደ ሠላምና መረጋጋት ጎዳና ለመመለስ በተደረገው ሂደት የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪነት ሚና የገዘፈ ነበር። በዚያች ሀገር ሰላምና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን በማድረግም ሀገራችን የተጫወተችው ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

በሱዳን ዳርፉር ግዛት ከሌሎች ሀገሮች ጋር በመሆን ባሰማራችው ሰላም አስከባሪ ሃይልም የእርስ በርስ ግጭት እንዳይከሰት በማድረግ ላይ መሆኗም ይታወቃል። ሱዳንና ደቡብ ሱዳን በይገባኛል በሚከራከሩበት የአብዬ ግዛት ከዓለም በብቸኝነት ተልዕኮውን የሚወጣ ሰላም አስከባሪ ኃይል በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥላ ሥር በመሆን አሰማርታለች። በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነቷን ያሳደገ ተግባርም እየከወነች ነው። ሀገራችን በምሥራቅ አፍሪካ ሀገሮች ሠላም፣ ጸጥታና መረጋጋት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተች ባለችው ሚና በሶማሊያ የነበረውን መንግሥት አልባነትና አክራሪነት በመታገልም ውጤታማ መሆን ችላለች።

እርግጥ ሰላማቸው የተረጋገጠ፣ በኢኮኖሚያቸው የበለጸገና ዴሞክራሲ ያበበባቸው ጎረቤቶች የጋራ ጥቅም መሠረት መሆናቸው የማይታበይ ቢሆንም፤ ሀገራችን ከዚህ ባለፈ ለጎረቤቶቿ ህዝቦች ሰላም ያለማሰለስ በመሥራት ላይ ትገኛለች። ለዚህም በአሁኑ ወቅት በአዲሲቷ ሀገር ደቡብ ሱዳን ውስጥ በተከሰተው የእርስ በርስ ግጭት የበኩሏን ጥረት በማድረግ የዚያች ሀገር ህዝብ የሰላም አየርን እንዲተነፍስ በማድረግ በገለልተኝነት የበኩሏን ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች።

ከዚህ በተጨማሪም ሀገራችን በኢኮኖሚው መስክ ያላት አህጉራዊ ትብብር ኮሜሳ በሚሰኘው በምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ የጋራ ገበያ የተጠናከረ ውህደት ለመፍጠር ያላት ሚናም ከፍተኛ ነው። በመሠረተ-ልማት ግንባታ መስክ ንግድና ኢንቨስትመንትን ለመሳብም ጥረት እያደረገች ነው። የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግም በመሥራት ላይ ነች። ከጅቡቲ፣ ከሱዳንና ከኬንያ፣ ከደቡብ ሱዳንና ከታንዛኒያ ጋር የኢኮኖሚ ትስስር በመፍጠር ለጋራ ተጠቃሚነት በመትጋት ላይ ትገኛለች። በዚህም ከጅቡቲ ጋር የሚያገናኝ የባቡር መስመር ግንባታው ተጠናቅቋል። ከኬንያ ጋር የሚያገናኘው መስመርም ወደ ስራ እንዲገባ ጥረት እየተደረገ ነው። ለጅቡቲ የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ተጠቃሚ እንድትሆን ከማድረጓም በላይ፤ ኬንያንን እንዲሁም ታንዛኒያን በተመሳሳይ ሁኔታ በኤሌክትሪክ ኃይል ለማስተሳሰር ጥረት እያደረገች ነው። ይህ ሁኔታም ወደፊት ለአፍሪካ ህብረት አንድ መሆን ለሚደረገው ጥረት የበኩሉን ዕገዛ ሊያደርግ እንደሚችል ህብረቱ የሚገነዘበው ይመስለኛል።

ሀገራችን ህብረቱ የሚቀበለውንና የአድሪካ ህዝቦች በፍትሃዊነት የተፈጥሮ ሃብቶቻቸውን እንዲቀበሉ በምታደርገው ጥረትም ትታወቃለች። በዚህም የአባይ ውኃ አጠቃቀምን ፍትሃዊና አግባብ ባለው መልኩ የመጠቀም አስፈላጊነትን አምና በፅናት እየሰራች ነው። የናይል የላይኛው ተፋሰስ ሀገሮች የጋራ ማዕቀፍ ፈርማን አብዛኛዎቹ ሀገራት እንዲፈርሙ ማድረጓን በምሳሌነት መጥቀስ የሚቻል ይመስለኛል።

በተለይም 6ሺህ ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለውን ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመገንባት ከሀገር ውስጥ ፍጆታ አልፎ ጎረቤት ሀገሮችንም ለመጥቀም እያደረገች ያለችው ጥረት በህብረቱ የሚታወቅ ነው። በአህጉሪቱ መልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲን ለማስፈን የተያዘውን ጥረትም በአፍሪካ እርስ በርስ መገማገሚያ ስልትንም “በኔፓድ” (NEPAD) አማካኝነት እንዲተገበር ፋና ወጊ ተግባራትን አከናውናለች።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ የተገነባበትን 2ሺህ ስኩዬር ሜትር መሬት በነፃ ከመስጠቷም በላይ፤ የአፍሪካ ህብረት ፅህፈት ቤት ግንባታ ዕውን እንዲሆን ከህብረቱ መሪዎች ጋር በመሆን የቻይናን መንግስት በማግባባት ያደረገችው አስተዋጽኦ በህብረቱ የታሪክ ድርሳን ላይ ሰፍሮ የሚገኝ ሃቅ ነው።

አዲስ አበባ የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ መናኸሪያ እንድትሆን በማድረግም የአፍሪካን ገፅታ እየገነባች ነው። በአፍሪካ መዲና አዲስ አበባ ውስጥ የሚካሄዱት ጉባዔዎች፣ ስብሰባዎችና ዐውደ ጥናቶች…ወዘተ. ከሚኖረው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባሻገር አንድ የአፍሪካ ከተማ በዚህ ረገድ ተመራጭ እንድትሆን ያደረገ ስለሆነ ለህብረቱ ሀገራትም በኩራት የሚመዘገብ ነው። አፍሪካዊ እሴትን በመጨመር ረገድም ዋጋው ከፍ ብሎ የሚታይ ይመስለኛል።

እነዚህ ጥቅል ዕውነታዎችም የአፍሪካ ህብረት ሀገራችንና ህዝቦቿ በሰላም ውስጥ ለአህጉሪቱ ያበረከቱትን አስተዋፅኦ ከግምት ውስጥ የሚገባና ህብረቱ ሁሌም ሀገራችን በምትሰጠው መረጃ ላይ እንዲመሰረት ያደረገው ነው ማለት ይቻላል። የአፍሪካ ህብረት የኢፌዴሪ መንግስትና ህዝቡ ለሰላም ያላቸውን ፍፁም የማያወላውል አቋም በሚገባ ይገነዘባል።

ላለፉት 26 ዓመታት ሀገራችን የራሷን ሰላም ዕውን ከማድረግ አልፋ የአፍሪካውያንን ሰላም ስትጠብቅ እንደነበረች የህብረቱ መሪዎች ያውቃሉ። የኢፌዴሪ መንግስት በሀገር ውስጥ የሚያከናውነው ሰላምን አስተማማኝ አድርገናል። በያዝነው ወር ለሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት መደበኛ ስበሰባ የአፍሪካ ተምሳሌት መሆናችንን ዛሬም ማሳየት ይኖርብናል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy