Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የኢንቨስትመንት ማዕከሎች

0 304

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የኢንቨስትመንት ማዕከሎች

                                      ታዬ ከበደ

አገራችን በተከታታይ ባከናወነቻቸው ምቹ የኢንቨስትመንት ስራዎች የዘርፉ መዳረሻ መሆን ችላለች። ይህ ሁኔታም በአሁኑ ወቅት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት (FDI) ወደ አገራችን እንዲፈስ ማድረግ ችሏል። በተለይ የኢንዱስትሪ ፓርኮች አሁን ባሉበት ቁመና የኢንቨስትመንት ማዕከሎች እየሆኑ መጥተዋል።

እነዚህ የኢንቨስትመንት ማዕከሎች አገራችን ከማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ ለማስቻል የተቋቋሙና በመቋቋም ላይ የሚገኙ ናቸው። እንደሚታወቀው ሁሉ በአሁኑ ወቅት መንግስትና ህዝብ ባካሄዱት ከፍተኛ ጥረት ሀገራችን በአለም አቀፍ ደረጃ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ከሚገኙ ሀገሮች ተርታ ለመሰለፍ በቅታለች። በዚህም ከሰሃራ በታች ግዙፍ ኢኮኖሚ ካላቸው የአፍሪካ ሀገራት በአምስተኛ ደረጃ፣ የነዳጅ ምርት ከሌላቸው ሀገሮች ደግሞ ቀዳሚውን ስፍራ የያዘችው ኢትዮጵያ፤ የበርካታ ኢንቬስተሮችን ቀልብ በመሳብ ላይ ትገኛለች።

ከዚህ አኳያ ቀደም ያሉና የቅርብ ተጠቃሾችን ማንሳት ይቻላል። ባለፉት ጊዜያት የሀገራችንን ምቹ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ተጠቅመው መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ ላይ የሚገኙት የቻይና፣ የቱርክ፣ የህንድ፣ የአውሮፓ፣ የአረብ ሀገሮች ትልልቅ ኩባንያዎችና ባለ ሃብቶች መዋዕለ ነዋያቸውን በማፍሰስ ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ባለሃብቶች በጨርቃጨርቅ፣ በማዕድንና በሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማሩ ናቸው።

በቅርብ ጊዜ ውስጥም የኢንዱስትሪ ፓርኮች በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች በመስፋፋታቸው የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ማግኘት እየተቻለ ነው። እርግጥ ለዚህ የኢንቨስትመንት ፍሰት ዋነኛው ምክንያት የኢፌዴሪ መንግስት በሀገራችን የተፋጠነ ልማት ለማምጣት የሚያስችል ትክክለኛ ፖሊሲና ስትራቴጂ ከመንደፉም ባሻገር፤ በተግባር መተርጎም መቻሉ ነው።

በአገራችን እየተመዘገበ ለሚገኘው ለውጥ በዋናነት ሊጠቀስ የሚችለው ጉዳይ የጠራ መስመር የያዘ፣ አገራዊውን ወቅታዊና ተጨባጭ ሁኔታ በማገናዘብ በተግባር ላይ የሚያውል አመራርና በህዝባዊ ተሳትፎ የተደገፈ አቅጣጫን የሚከተል የልማታዊ መንግስት መኖሩ የሚያጠያይቅ ጉዳይ አይደለም።

እንደሚታወቀው ሁሉ የኢትዮጵያ መንግስት በሀገሪቱ መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ፣ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው የውጭ ባለሃብቶችን ለመሳብ የተለያዩ ማበረታቻዎችን በማመቻቸት በሩን ከፍት በማድረግና በተለያዩ አለም አቀፋዊ መድረኮች ተጨባጭ ሁኔታውን በማስረዳት በርካታ ባለሃብቶችን መሳብ ችሏል።

በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በተለይም በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግና ኢንዱስትሪ ዘርፎች የተሰማሩ የውጭ ባለሀብቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መምጣት ችሏል።

አገሪቱ ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆኗን የተገነዘቡ በርካታ የውጭ ኩባንያዎችና ባለሃብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ከፍተኛ ፍላጎት እያሳዩ ነው። የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታም የዚህ መንግስታዊ ጥረት አንዱ ማሳያ ነው።

ኢንዱስትሪው ለኢኮኖሚው መዋቅራዊ ለውጥ ጉልህ ሚና ይኖረዋል። የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥን ዕውን ለማድረግ የሚከናወነው ስራም አገራችን ለነደፈችው ራዕይ የሚጫወተው ሚና የማይተካ ነው። እንዲያውም የሞት ሽረት ጉዳይ ነው ማለት ይቻላል። ለዚህም መንግስት ተጀምሮ ሶስተኛ ዓመቱን የያዘው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶታል።

ይህም የአገር ውስጥና የውጭ ቀጥተኛ በአዳዲስ ኢንቨስትመንቶችም ሆነ በነባር ኢንዱስትሪዎች ውስጥ የምርታማነት የጥራትና የተወዳዳሪነት ደረጃ እመርታና መዋቅራዊ ለውጥ እንዲያመጣ በከፍተኛ ደረጃ መንቀሳቀስ እንዲቻል ያደርጋል። እናም በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን በኢኮኖሚው ላይ የሚታይ መዋቅራዊ ለውጥን ለማስጀመር የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ በየዓመቱ ቢያንስ የ24 በመቶ ዓመታዊ አማካይ ዕድገት ማስመዝገብ ይኖርበታል። ይህ ማለት በ2012 ዓ.ም የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ በአጠቃላይ ኢኮኖሚው ያለውን ድርሻ ወደ ስምንት በመቶ ከፍ እንዲል ያደርገዋል።

ይህ ለውጥም የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ድርሻ በአሁኑ ወቅት ከሚገኝበት በአራት እጥፍ እንዲያድግ በማድረግ ወደ መጀመሪያው የመካከለኛ ጉዞ መንገድ ለመድረስ ለታለመው ዕቅድ እስከ 18 በመቶ የማድረስ ግብን ዕውን ይጥላል። ሀገራችን ለያዘችው የመካከለኛ ገቢ ራዕይን ለማሳካትም መደላድል ይፈጥራል።

በዕቅዱ ላይ እንደተመለከተው መዋቅራዊ ለውጡን ገቢራዊ በማድረግ ረገድ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው የኤክስፖርት ሚናው ሁነኛ ማሳያ ነው። ዛሬን ከነገ ጋር ብናስተያየው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ አሁን ካለው ሁኔታ አኳያ ሲታይ ከጠቅላላው የኤክስፖርት ገቢ ከአስር በመቶ አይበልጥም።  

ሆኖም ይህን አሃዝ በ2012 ዓ.ም ላይ ወደ 25 በመቶ ከፍ ለማድረግ ታስቧል። የህም አምስት ቢልዮን ዶላር ገቢ ሊያስገኝ የሚችል ነው። ታዲያ ለዚህ ስኬት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ተስፋ የተጣለባቸው ማዕከሎች ናቸው።

የኢንዱስትሪ ፓርክ ልማቱን በበላይነት ከሚመራው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የተገኙ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ የኢንዱስትሪ ፓርክ ማለት በአንድ በተከለለ አካባቢ ወይም ቦታ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች የሚቋቁሙበት ሆኖ ልማቱን ለማፋጠን ልዩ ልዩ ማበረታቻዎች በሕግ አግባብ የሚሰጡበት ማዕከል ነው። በዚህ አግባብ የሚገነባ ማንኛውም የኢንዱስትሪ ፓርክ የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን ማሟላት የግድ ይለዋል።

በፓርኩ ውስጥ የሚገነቡት ኢንዱስትሪዎች የሚጠቀሙባቸው የጋራ መገልገያዎች፣ መጋዘን፣ የብክለት ማጣሪያና ማስወገጃ፣ የጥናትና ምርምር ማዕከል፣ መኖሪያ ቤቶች፣ የቢሮ መገልገያ ህንፃዎች፣ የሕክምና ማዕከል፣ ትምህርት ቤት፣ ማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት፣ መዝናኛዎች፣ አረንጓዴ ቦታዎችና ለኢንዱስትሪዎቹ የሚያገለግሉ መሰል ተቋማትን የሚያካትቱ አገልግሎት መስጫዎች ይኖራቸዋል። ይህ በመሆኑም ፓርኩ በውስጡ የተገነቡት ኢንዱስትሪዎች ደህንነታቸው ተጠብቆ በጤናማ ሁኔታ የእርስ በእርስ ውድድር የሚያደርጉበት አካባቢ ነው ማለት ይቻላል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ማንኛውም ሀገር በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፖለቲካ መስኮች ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ተጠቃሚ ያደርጋል። ልማቱ እንደ ጨርቃጨርቅ በመሳሰሉ ቀላል የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በርካታ የስራ ዕድል የሚፈጠር እና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትንም በስፋት መሳብ የሚችል ነው። ይህም የህዝቦችን ተጠቃሚነት ከፍ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ፤ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ረገድም የራሱን ሚና ይጫወታል። ከዚህ ጎን ለጎንም የቀላል ማኑፋክቸሪንግ ልማቱን ያፋጥናል፤ ከተሞችን ወደ ላቀ የዕድገት ደረጃ የማሸጋገር ብሎም አዳዲስ ከተሞች እንዲፈጠሩና በዚያኑ ልክም የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲቀረፉ የራሱን አዎንታዊ ሚና ይጫወታል። እነዚህ ፓርኮች በቀጣዩቹ ጊዜያትም የአገራችን የኢንቨስትመንት ማዕከሎች ሆነው እንዲቀጥሉ ሁሉም ተገቢውን ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋል።

 

   

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy