Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የኢንቨስትመንት ካስማ

0 515

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የኢንቨስትመንት ካስማ

ዳዊት ምትኩ

ኢትዮጵያ በቀውስ ውስጥ እያለች እንኳን በርካታ ኢንቨስትመንቶችን በመሳብ ላይ አገር መሆኗን አስመስክራለች። በተለይም በኢንዱስትሪው ዘርፍ የኢንዱስትሪ ልማቶችን በማስፋፋትና ለዚህ ምቹ የሆነ የባቡር መሰረተ ልማት ዝርጋታን በማሳለጥና በመጀመር ትገኛለች። ይህም ፓርኮቹ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ከማሳደግ አኳያ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲያበረክቱ የሚያደርጋቸው ነው።

የፓርኮቹ ግንባታ የዕድገት መሰረት የሆነውን ኢንቨስትመንት ከማስፋፋት በተጨማሪ፤ ኢትዮጵያ እንደ አገር ያለባትን የፋይናንስ እጥረት በመቅረፍ የበኩሉን ሚና እየተጫወተና የኢንቨስትመንት ካስማ ሊሆን የሚያስችል ነው። ይህም የኢንቨስትመንት ካስማዎቹ ከአገራችን አልፈው የአህጉራችን መመኪያ የሚሆኑበት ጊዜ ሩቅ አመላካች ይመስለኛል።

እንደሚታወቀው ሁሉ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ሀገራችን ውስጥ የስራ ዕድል ይፈጥራል። የውጭ ምንዛሬ ግኝታችንም ይጎለብታል። ይህ ግኝታችን የሀገር ኢኮኖሚን በማጎልበት ኢትዮጵያ ላለመችው መካከለኛ ደረጃ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ ያስችላታል። ታዲያ እዚህ ላይ ለኢንቨስትመንት መዳበር ከፍተኛ ድርሻ ያበረከተውን ፖሊሲ መመልከት ተገቢ ይመስለኛል።

እንደሚታወቀው የገበያ መር ኢኮኖሚ ሥርዓትን ተከትሎ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ተነድፎ በሥራ ላይ ውሏል፡፡ በዚህም በኢኮኖሚው ውስጥ የመንግሥት ሚና የተለያዩ የልማት ኃይሎችን በማቀናጀት መምራት የመሠረተ ልማት በማቅረብና የሰው ሀብት ልማትን በማካሄድ እንዲሁም ፈጣንና ውጤታማ የመንግሥት አገልግሎት በመስጠት ለልማታዊ የግሉ ዘርፍ ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠርና የመደገፍ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጮችን መዝጋት እና በግሉ ሴክተር የማይሰሩ የልማት ሥራዎችን መንግስት ገቢራዊ እንዲያደርጋቸው የሚያስችሉ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል።

የኢንቨስትመንት ካስማዎቹ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የዚህ እውነታ መገለጫዎች ይመስሉኛል። በሀገራችን የተተለመው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ፕሮግራም መሬትን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለልማት ስራ ብቻ እንዲውል የሚያደርግና የኪራይ ሰብሳቢነት በር የሚዘጋ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ይመስለኛል። እርግጥም ልማቱ ለመሰረተ ልማት ግንባታ የሚወጣውን ወጪ በተቀናጀ መልኩ መጠቀም የሚያስችልና ለአካባቢ ጥበቃ ሥራ ትኩረት የሚሰጥ በመሆኑ ኢንዱስትሪዎችን በእሴት ሰንሰለት እርስ በርስ ስለሚያስተሳስር ብክነትን የሚቀንስና የኪራይ ሰብሳቢነትን በመዋጋት ረገድ ሚናው የጎላ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ በውጭ ሀገር ባለሙያዎች የሚከናወኑ ስራዎችን በሂደት በሀገር ውስጥ የሙያው ባለቤቶችና በሀገር በቀል ተቋማት አማካኝነት እንዲከናወኑ መሰረት ይጥላል። ይህም የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲረጋገጥ ሰፊ ዕድልን ይፈጥራል።

በመላ ሀገሪቱ የሚገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን ማሟላት የግድ ይላቸዋል። በዘመናዊ አሰራር ውስጥ የሚታወቀውን የአንድ መስኮት አገልግሎት አሰጣጥ አሰራርንም ይከተላል።

በማንኛውም የኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የሚገነቡት ኢንዱስትሪዎች የሚጠቀሙባቸው የጋራ መገልገያዎች፣ መጋዘን፣ የብክለት ማጣሪያና ማስወገጃ፣ የጥናትና ምርምር ማዕከል፣ መኖሪያ ቤቶች፣ የቢሮ መገልገያ ህንፃዎች፣ የሕክምና ማዕከል፣ ትምህርት ቤት፣ ማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት፣ መዝናኛዎች፣ አረንጓዴ ቦታዎችና ለኢንዱስትሪዎቹ የሚያገለግሉ መሰል ተቋማትን የሚያካትቱ አገልግሎት መስጫዎች ይኖራቸዋል። ይህ በመሆኑም ፓርኩ በውስጡ የተገነቡት ኢንዱስትሪዎች ደህንነታቸው ተጠብቆ በጤናማ ሁኔታ የእርስ በእርስ ውድድር የሚያደርጉበት አካባቢ ነው ማለት ይቻላል።

በዚህ መሰረትም መንግስት በአሁኑ ወቅት በመላ ሀገሪቱ በራሱ ወጪ እየገነባቸው የሚገኙት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኢትዮጵያ በማምረቻ ኢንዱስትሪው ዘርፍ የአፍሪካ ማዕከል እንድትሆን የነደፈውን ዕቅድ ለመሳካት ጥረት እያደረገ ነው።

በዚህም የልማት ዕቅዱን ግብ ለማሳካት በግል ባለሃብቱ ከሚገነቡ የኢንዱስትሪዎች ባሻገር በመንግስት ሙሉ ወጪ አስፈላጊ መሰረተ ልማቶች የተሟሉላቸው 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮች እና 17 የግብርና ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች  በመላ አገሪቱ  በመገንባት ላይ  ይገኛሉ። አንዳንዶቹም ስራ ጀምረው ስራ ፈጣሪና የውጭ ምንዛሬ ግኝት መፍጠሪያዎች ሆነዋል። እንዲህ ዓይነቱ የኢንቨስትመንት ካስማዎች ለሀገርም ይሁን ለአፍሪካ ወሳኝ ናቸው።

እርግጥ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዕድገት ሊረጋገጥ የሚችለው ከኢንቨስትመንት መስፋፋት ጋር ተያይዞ እንጂ ለብቻው ተፈፃሚ እንዲሆን ብቻ አይደለም። የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ኢንቨስትመንትን ዕውን ከማድረግ አኳያ መቆራኘት ይኖርበታል። ይህን ዕውን ለማድረግም በአሁኑ ወቅት ያሉትም ይሁኑ በቀጣይ ወደ ስራ የሚገቡት ኢንዱስትሪዎች፤ የቴክኖሎጂ አቅማቸውን፣ ምርታማነታቸውን፣ የጥራት አመራር አቅማቸውን ብሎም ተወዳዳሪነታቸውን በቀጣይነት መገንባት ይችሉ ዘንድ አስፈላጊው ድጋፍ ይደረግላቸዋል።  

ከዚህ ጎን ለጎንም የሳይንስ፣ የቴክኖሎጅና የኢኖቬሽን አቅምን ለማሳደግ ከሀገሪቱ የዕድገት ፍላጐት ጋር የተጣጣመ የቴክኖሎጅ ሽግግር ለማድረግ በዕቅዱ ላይ ተቀምጧል። ይህን ለማከናወንም በተለይ ለሀገር ውስጥ ኩባንያዎችና ባለሃብቶች ቅድሚያ ይሰጣቸዋል።

ስለሆነም በዘርፉ እስካሁን ድረስ የተደራጁ የኢንዱስትሪ ልማት ደጋፊ ተቋማትና ዩኒቨርስቲዎች አቅማቸው ይበልጥ እንዲጎለብትና ጥራት ባለው የትምህርት ማሳለጫዎች እንዲደጉ ይደረጋል። ከውጭ መሰል ተቋማት ጋር የሚኖራቸው ቁርኝትና እንዲጠናከር አሰራራቸውም እንዲዘምን እየተደረገ ነው።

በመሆኑም ተስማሚና የተሻሻሉ ቴክኖሎጅዎችን የማፈላለግ፣ የመምረጥ፣ የማለማመድና የመጠቀም ብሎም የማሻሻል ስራዎችን በማከናወን የዘርፉን ምርታማነትን ለማሳደግ ጥረት ይደረጋል። እናም ጥራትን፣ ምርታማነትን እንዲሁም ተወዳዳሪነትን ለማጐልበት ሀገራችን የመረጠችው የካይዘን የአመራር ፍልስፍና በሁሉም ዓይነት ኢንዱስትሪዎችና የኤክስፖርት ዘርፎች ገቢራዊ እየሆኑ ነው።

ኢትዮጵያ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የምታደርገውን ሽግግር በማሳለጥ ረገድ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ሚና ከፍተኛ ነው። ይህን ዕውነታ በመገንዘብ የኢፌደሪ መንግስት በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች በራሱ ከፍተኛ ወጪ ፓርኮቹን በመገንባት ላይ ይገኛል። የፓርኮቹ ልማት ለዜጎች የስራ ዕድል የሚፈጥሩ ናቸው።

ታዲያ መንግስት ፓርኮቹን የሚገነባው የሀገር ውስጥም ይሁን የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ነው። ፓርኮቹ አስፈላጊው የመሰረተ ልማት ተሟልቶላቸው የሚገነቡ በመሆናቸው ባለሃብቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ስራ እንዲገቡ የሚያደርጓቸው ናቸው።

በመልማት ላይ የሚገኙት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ዓለም የደረሰበትን የግንባታ ሂደት ተከትለው የሚገነቡ በመሆናቸው ከአካባቢ ብክለት ነፃ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ  በምርት ወቅት ተረፈ ምርታቸውን እንደገና መጠቀም በሚያስችል ሁኔታ የተገነቡ በመሆናቸው የሃብት ብክነትን ማስወገድ ይችላሉ። ይህም ፓርኮቹ በምርትም ይሁን በተረፈ ምርት ውጤታማ መሆን የሚያስችሉ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች በአገራችን መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ከማምጣት፣ ኢንቨስትመንትን ከመሳብ፣ ለዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠርና ቁጠባን ከማበረታታት እንዲሁም የኤክስፖርት አቅማችንን ከማሳደግ ብሎም ከውጭ የሚገቡ ዕቃዎችን በአገር ውስጥ ምርት ከመተካት አኳያ የላቀ ጠቀሜታ አላቸው። ይህም የአንቨስትመንት ካስማ ስለመሆናቸው ሌላኛው አረጋጋጭ ጉዳይ ነው። ስለሆነም የኢንቨስትመንት ካስማዎቹ ይበልጥ እንዲስፋፉ የመንግስትን ጥረት መደገፍ ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ተግባር ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy