Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የውይይት ትርፍ እንጂ ኪሳራ የለውም

0 277

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የውይይት ትርፍ እንጂ ኪሳራ የለውም

                                                          ደስታ ኃይሉ

የህዳሴውን ግድብ አስመልክቶ በግብጽ ሚዲያ በኩል በስሜታዊነት ለማነሳሳት የሚያደርጉትን ጥረት በርካታዎችን እያስደመመ ነው። የግብፅ ሚዲያዎች በአገራቸው ውስጥ ያለውን ችግር ለማዳፈን የህዳሴውን ግድብ እንደ አጀንዳ ማስቀየሻ አድርገው እየተጠቀሙበት ነው።

ያም ሆኖ የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ትናንትም ይሁን ዛሬ ያላቸው አቋም   የየትኛውንም የተፋሰሱን አገር ህዝብ በጉልህ ሁኔታ ሳይጎዱ ድህነትን መቅረፍ ብቻ ላይ የተመሰረተ ነው። ይህ ፍትሃዊ አስተሳሰብ አይቀየርም። ሊቀርም አይችልም። የኢትዮጵያ መንግስት ባለፉት ጊዜያት ከግብፅና ከሱዳን ጋር በመሆን መተማመንን ለመፍጠር ሲል የሶስትዮሽ ውይይቶችን እያካሄደ መጥተዋል።

ግብፆች ግን በአሁኑ ወቅት ‘የዓለም ባንክ ያደራድረን’ የሚል ምክረ ሃሳብ አቅርበዋል። ምንም እንኳን የዓለም ባንክ አደራዳሪነት በራሱ ችግር የሌለው ቢሆንም፣ የግብፆች ምክረ ሃሳብ ግን የሶስቱን አገራት የስምምነት መርህን የጣሰ ነው።

የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ፍላጎት አገራቱ ውይይታቸውን ቀጥለው በጋራ ለማደግ አንድ ላይ መስራት ያለባቸው መሆኑን የሚያምን ነው። ርግጥም የውይይት ትርፍ እንጂ ኪሳራ የሌለው ስለሆነ ግብፆች ወንድሞቻችንም  በዚህ መንገድ ቢጓዙ ተጠቃሚ የሚሆኑ ይመስለኛል።

እርግጥ የዓለም ባንክ በአደራዳሪነት እንዲሳተፍ በግብፅ መጠየቁ ችግር የለውም። ይሁንና ምክረ ሃሳቡ ሦስቱ አገሮች ስምምነት ካደረጉበት የውይይት ቅደም ተከተል የጣሰና በተናጠል የቀረበ ነው።

የሦስቱ አገሮች የቴክኒክ ኮሚቴ ሳይንሳዊ መርህን በመከተል በሚያደርጉት ውይይት ስምምነት ያልተደረሰበት ጉዳይ ለሦስቱ አገሮች የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች እንደሚመራ፣ በእነዚህ ሚኒስትሮችም ስምምነት ካልተደረሰበት እንዳስፈላጊነቱ ሦስተኛ ወገን እንዲመለከተው ወስነው በሚስማሙበት አቋም ሦስተኛ ወገን ሊሰይሙ ይችላሉ።

እናም ግብፅ የዓለም ባንክ እንደ ሦስተኛ ወገን አደራዳሪ እንዲሳተፍ ያቀረበችው ጥያቄ፣ ከሥነ ሥርዓቱ ያፈነገጠና በተናጠል የቀረበ በመሆኑ ስህተት ነው። ምንም እንኳን የዓለም ባንክ አደራዳሪ እንዲሆን መጠየቁ በኢትዮጵያ በኩል ችግር ባይኖረውም፤ ምክረ ሃሳቡ ሥነ ሥርዓትን ያልተከተለ ከአደራዳሪነትም በዘለለ ተቋሙ ዳኛ እንዲሆን የመፈለግ አዝማሚያ የታየበት ስለሆነ ቅቡል ሊሆን አይችልም።

እንዲሁም ስምምነት ባልተደረሰባቸው ጉዳዮች አደራዳሪ እንዲገባ መጠየቅ የሚቻለው፣ የተቀጠሩት ሁለት አጥኝ ኩባንያዎች ተግባራቸውን ፈጽመው ምክረ ሐሳብ ካቀረቡ በኋለ መሆኑን ግብፆች እያወቁ ለምን ወደ እንደዚህ ዓይነቱ የተናጠል ሃሳብ እንደገቡ ግልፅ አይደለም።

እንደሚታወቀው ግብፅ በተደጋጋሚ ከውይይት ሥነ ሥርዓቱ ታፈነግጣለች። ጉዳዩን በተመለከተ ግብፅ የምታደርገው ጥረት በሙሉ በኢትዮጵያና በሱዳን ጥቅም ላይ የራሷን ጥቅም ለማስከበር ከሚመነጭ ፍላጎት ነው። በአሁኑ ወቅት ውይይቱ የተስተጓጎለ ቢሆንም በነበረበት ሁኔታ በሦስቱ አገሮች የጋራ የቴክኒክ ኮሚቴ ተመልሶ መቀጠሉ ተገቢ ነው። የጋራ መፍትሔ የሚገኘውም በዚሁ መንገድ ብቻ መሆኑን ግብፆች ይስቱታል ብዬ አላስብም።

እርግጥ ከውይይትና ከመነጋገር የማያተርፍ አካል የለም። የአገራችን አቋም ደግሞ ድህነትን በመቅረፍ ተያይዞ ማደግ ነው። የሀገራችን ፍትሐዊ አስተሳሰብ አንዱን ለመጉዳትና ሌላውን ለመጥቀም ከማሰብ የመነጨ አይደለም። ይልቁንም ከዕድገታችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ተያይዞ የሚታይ ነው።

እንደሚታወቀው ባለፉት ዓመታት የሀገራችን የዕድገት ማነቆ ሆኖ የቆየው የኤሌትሪክ ሃይል አቅርቦት ችግርን የሚቀርፉ ጥቂት የማይባሉ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድቦችን በተሳካ ሁኔታ መገንባት ተችሏል። ጥረቱን አጠናክሮ በመቀጠልም በአባይ ወንዝ ላይ በአፍሪካ በግዙፍነቱ የመጀመሪያ የሆነውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እየተካሄደ ነው።

በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ መሰረቱ የተጣለውና የሀገራች ህዝቦች ችቦውን እየተቀባበበሉ ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ እንዲበቃ ያደረጉትና ለፍፃሜው እንደሚያበቁት እየገለፁት ያለው ይህ ግድብ፤ አሁን ያለውን የሀገራችንን የሃይል አቅርቦት ከሶስት እጥፍ በላይ የሚያሳድግ ነው። በቅርቡ የወጡ ጥናቶች እንደሚያመላክቱትም፤ ግድቡ በሙሉ አቅሙ ስድስት ሺህ 450 ሜጋ ዋት ማመንጨት ሲጀምር ለበርካታ ዓመታት ያህል በቀን ሁለት ሚሊዮን ዮሮ ለሀገራችን ማስገኘት ይችላል። ይህም ህዝቡ በታሪካዊነቱ ያስቀመጠው ሁለንተናዊ አሻራ ተመልሶ የታሪካዊ ዕድገት ተጠቃሚ እንዲሆን ያስችለዋል።

አዎ! ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመገንባት ላይ የሚገኘው በህዝቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎ ላይ ተመስርቶ ነው። በዚህም ሳቢያ ግድቡ ቀደምት የተመፅዋችነት አስተሳሰብን የቀረፈ፣ ለፀረ- ድህነት ትግሉ ስኬት ከፍተኛ ፋይዳ ያለው፣ የማንኛውንም ኢትዮጵያዊ ስሜት የኮረኮረ፣ የ“ይቻላል” መንፈስን መፍጠር የቻለና ከራሳችን አልፈን ለጎረቤቶቻችን እንድንተርፍ የሚያደርገን ነው። እናም ቢያንስ በእነዚህ ሁኔታዎች ብቻ የሀገራችንን ፍትሐዊና “ኑ አብረን እንጠቀም” የሚል ቀና አስተሳሰብን ለመገንዘብ የሚያዳግት አይመስለኝም፤ ለየትኛውም ወገን ቢሆን።

ምንም እንኳን ትናንት ሐብትን በጋራና በፍትሐዊ ሁኔታ የመጠቀም መርህን ተከትላ የህዳሴውን ግድብ በመገንባት ላይ የምትገኘው ሀገራችን፤ ዛሬም ከዚህ መርህዋ ዝንፍ የምትል አይሆንም። ግድቡም ወንድም የሆነውን የግብፅ ህዝብ እንደማይጎዳ፣ ይልቁንም ከግድቡ ግንባታ ተጠቃሚ እንደሚሆን በፅናት ታምናለች።

ይህ እምነቷ ከምንም ተነስቶ የሚባል አይደለም—መሬት ላይ ያለውን የግድቡን ግንባታ መሰረት ያደረገ እንጂ። ከዚህ በመነሳትም እምነቷንና የትኛውንም ወገን ያለመጉዳት መርህዋን በተለያዩ ወቅቶች ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብና ለታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት መንግስታትና ህዝቦች አስረድታለች።

ታዲያ ይህን የኢፌዴሪ መንግስት በጋራ የመልማት መርህን ቀደም ሲል ጎረቤት ሱዳን፣ አሁን ደግሞ ወንድሞቻችን ግብፆች እውነታውን እየተረዱ የመጡ ይመስላል—ብቅ ጥልም የሚለው አቋማቸው እንደተጠበቀ ሆኖ። በየትኛውም ሀገር ውስጥ የሚገነባ ፕሮጀክት በመርህ ላይ የተመሰረተ እንጂ በዘፈቀደ የሚመራ አይደለም። የኢትዮጵያ ህዝቦች የትኛውንም ሀገር የመጉዳት ዓላማ የላቸውም።

የህዳሴው ግድብ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ተመርኩዞ ሁሉም ሀገራት እንዲጠቀሙ ከማለም የመነጨ ነው። ይህን የትኛውም ሀገር ሊገነዘበው የሚገባ ይመስለኛል። ምክንያቱም የሀገራችን ህዝቦችም ይሁኑ መንግስት ለህዝብ የሚያስቡ እንጂ የሌሎች ሀገራትን ህዝቦች ተጠቃሚነትን የሚጋፉ አይደሉም። የትኛውም የተፋሰሱ ሀገር ከዚህ ቀደም አድርጎት በማያውቀው መልኩ ህዳሴው ግድብ በታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ተፅዕኖ ለማስጠናት በራቸውን ክፍት ያደረጉትም ለዚሁ ነው። እናም ግብፆች ወንድሞቻችን በህዳሴው ግድብ ዙሪያ መግባባት ያልተደረሰባቸው ጉዳዩች ላይ ትልቁ መፍትሔ በተጀመረው መንገድ ብቻ መወያየት መሆኑን መዘንጋት አይኖርባቸውም።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy