Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የዕድላችን መንገዶች

0 345

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የዕድላችን መንገዶች

ዳዊት ምትኩ

አገራችን እያከናወነች ያለችው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ የመጪው ጊዜ ዕድላችን በር ከፋቾች ሊሆኑ መቻላቸው ግልፅ እየሆነ ነው። በአሁኑ ወቅት ፓርኮቹ የውጭ ምንዛሬን ከማስገኘት፣ ለዜጎች የስራ እድል ከመፍጠር፣ የአርሶ አደሮችን ምርት በግብዓትነት ከመጠቀም፣ አካባቢን ካለመበከልና የአገራችንን አረግጓዴ ልማት ፖሊሲ እውን ከማድረግ አኳያ እየተጫወቱት ያለው ሚና አርኪ ነው።

ይህ አርኪ ተግባርም ኢትዮጵያን የምስራቅ አፍሪካ ብሎም የአፍሪካ የኢንዱስትሪ ማማ በማድረግ ረገድ የመንግስት የመሪነት ሚና ከፍተኛ ነው። በየአካባቢዎቹ የሚገነባቸው ፓርኮች የመጪው ዘመን ዕድላችንን መንገዶች ጥርጊያ መንገድ እያበጀና በጠንካራ መሰረት ላይ እያኖረ መሆኑን ለመገንዘብ አያዳግትም። ኢኮኖሚው ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ እንዲሸጋገር እንዲሸጋገር ዕቅዶቹን ከቢራዊ እያደረገ ያለውም ከዚህ እውነታ በመነሳት ይመስለኛል።

በመልማት ላይ የሚገኙት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ዓለም የደረሰበትን የግንባታ ሂደት ተከትለው የሚገነቡ በመሆናቸው ከአካባቢ ብክለት ነፃ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ  በምርት ወቅት ተረፈ ምርታቸውን እንደገና መጠቀም በሚያስችል ሁኔታ የተገነቡ በመሆናቸው የሃብት ብክነትን ማስወገድ ይችላሉ። ይህም ፓርኮቹ በምርትም ይሁን በተረፈ ምርት ውጤታማ መሆን የሚያስችሉ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።

የኢንዱስትሪ ፓርክ ልማቱን በበላይነት ከሚመራው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የተገኙ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ የኢንዱስትሪ ፓርክ ማለት በአንድ በተከለለ አካባቢ ወይም ቦታ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች የሚቋቁሙበት ሆኖ ልማቱን ለማፋጠን ልዩ ልዩ ማበረታቻዎች በሕግ አግባብ የሚሰጡበት ማዕከል ነው። በዚህ አግባብ የሚገነባ ማንኛውም የኢንዱስትሪ ፓርክ የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን ማሟላት የግድ ይለዋል።

በፓርኩ ውስጥ የሚገነቡት ኢንዱስትሪዎች የሚጠቀሙባቸው የጋራ መገልገያዎች፣ መጋዘን፣ የብክለት ማጣሪያና ማስወገጃ፣ የጥናትና ምርምር ማዕከል፣ መኖሪያ ቤቶች፣ የቢሮ መገልገያ ህንፃዎች፣ የሕክምና ማዕከል፣ ትምህርት ቤት፣ ማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት፣ መዝናኛዎች፣ አረንጓዴ ቦታዎችና ለኢንዱስትሪዎቹ የሚያገለግሉ መሰል ተቋማትን የሚያካትቱ አገልግሎት መስጫዎች ይኖራቸዋል። ይህ በመሆኑም ፓርኩ በውስጡ የተገነቡት ኢንዱስትሪዎች ደህንነታቸው ተጠብቆ በጤናማ ሁኔታ የእርስ በእርስ ውድድር የሚያደርጉበት አካባቢ ነው ማለት ይቻላል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ማንኛውም ሀገር በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፖለቲካ መስኮች ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ተጠቃሚ ያደርጋል። ልማቱ እንደ ጨርቃጨርቅ በመሳሰሉ ቀላል የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በርካታ የስራ ዕድል የሚፈጠር እና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትንም በስፋት መሳብ የሚችል ነው። ይህም የህዝቦችን ተጠቃሚነት ከፍ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ፤ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ረገድም የራሱን ሚና ይጫወታል። ከዚህ ጎን ለጎንም የቀላል ማኑፋክቸሪንግ ልማቱን ያፋጥናል፤ ከተሞችን ወደ ላቀ የዕድገት ደረጃ የማሸጋገር ብሎም አዳዲስ ከተሞች እንዲፈጠሩና በዚያኑ ልክም የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲቀረፉ የራሱን አዎንታዊ ሚና ይጫወታል።

እነዚህን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን ለማግኘትም በመንግስት በተቀመጠው ዕቅድ መሰረት ከሃዋሳው የኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት በተጨማሪ የመቀሌና ኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ግንባታ ማስጀመር መቻሉን መረጃዎች ያስረዳሉ። የቦሌ ለሚ ሁለትና ቂሊንጦ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የዲዛይን ዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውም እንዲሁ። የድሬዳዋ፣ የአዳማ፣ የባህርዳርና የጅማ ኢንዱሰትሪ ፓርኮች አብዛኛው የቅድመ ዝግጅት ስራዎቻቸው የተጠናቀቁ ሲሆን፤ አንዳንዶቹም ወደ ተግባራዊ የግንባታ ስራ እንደገቡ ተገልጿል።

ይህ በሀገራችን የተተለመው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ፕሮግራም መሬትን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለልማት ስራ ብቻ እንዲውል የሚያደርግና የኪራይ ሰብሳቢነት በር የሚዘጋ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ይመስለኛል። ርግጥም ልማቱ ለመሰረተ ልማት ግንባታ የሚወጣውን ወጪ በተቀናጀ መልኩ መጠቀም የሚያስችልና ለአካባቢ ጥበቃ ሥራ ትኩረት የሚሰጥ በመሆኑ ኢንዱስትሪዎችን በእሴት ሰንሰለት እርስ በርስ ስለሚያስተሳስር ብክነትን የሚቀንስና የኪራይ ሰብሳቢነትን በመዋጋት ረገድ ሚናው የጎላ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ በውጭ ሀገር ባለሙያዎች የሚከናወኑ ስራዎችን በሂደት በሀገር ውስጥ የሙያው ባለቤቶችና በሀገር በቀል ተቋማት አማካኝነት እንዲከናወኑ መሰረት ይጥላል። ይህም የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲረጋገጥ ሰፊ ዕድልን ይፈጥራል። ለዚህም በምሳሌነት ተገንብቶ ወደ ስራ የገባው የሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክን ብንመለከት፤ ፓርኩ በተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች መያዙንና የሀገር ውስጥ ባለሙያዎችም በስራ ሂደት የቴክኖሎጂ ሽግግር ተግባርን እንደሚከውኑ ይጠበቃል።

እዚህ ላይ ከካሳ ክፍያ ጋር በተያያዘ አንድ ግንዛቤ መያዝ የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ይኸውም ከመጀመሪያው የአዲስ አበባ ቦሌ ለሚ አንድና ሁለት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማትን ብንመለከት እንኳን፤ ፓርኮቹን ለማልማት ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር 346 አባዎራዎች የተሟላ መሰረተ ልማት ያለው ምትክ ቦታ እንዲሰጣቸው የተደረገ መሆኑን ለመገንዘብ አይከብድም።

እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ራሳቸውን በማህበር አደራጅተው እንዲያቋቁሙ ለማድረግም በእንስሳትና በእንስሳት ተዋፅኦ ስራ ላይ እንዲሰማሩ ምቹ ሁኔታዎች የተፈጠረላቸው መሆኑን መረጃዎች ያስረዳሉ።

ከአገራችን የልማቱ ጀማሪነትና ስራው ከሚጠይቀው በጀት አኳያ ዘርፉ የተወሰኑ ተግዳሮቶች ሊኖሩት እንደሚችሉ አያጠራጥርም። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከዘርፉ ተግዳሮቶች ውስጥ፤ ልማቱን ለማረጋገጥ ዘላቂ የፋይናንስ ምንጭ በበቂ ሁኔታ አለመኖር፣ የመሰረተ ልማት አቅርቦት ችግርና ግንባር ቀደም ባለሃብቶች በስፋት መሳብ የሚያስችል አቅም አለመኖሩ በዋነኛነት የሚጠቀሱ ናቸው።

ይሁንና እነዚህን ችግሮች መፍታት ይቻላል‒ የተሻለ አቅም በመፍጠር፣ የገንዘብ ምንጮችን በማፈላለግና ሁሉም ዜጋ የበኩሉን እገዛ በማድረግ ችግሩን በሂደት ዘላቂነት ባለው ሁኔታ በመፍታት።

በዚህ ድምር ውጤትም የፓርኮቹ ልማት የሀገራችን ህዝቦች የስራ ዕድል አግኝተው የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ እንዲሁም ሀገራችን ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር የልማት ስትራቴጂ እንድታድግ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ።

ይህ ትስስር ሌላው ቀርቶ አርሶ አደሩ የምርቱ ተጠቃሚ ከመሆን ባሻገር በግንባታውም ይሁን ከግንባታው በኋላ ስራ እንዲያገኝ የሚያስችለው ነው። ይህ ተጨማሪ ስራም የቤተሰቡን ህይወት ለመለወጥና የተሻለ ህይወት ለመምራት ያስችለዋል። በመሆኑም በሁሉም መስኮች በዚህ ረገድ ያሉትን ጉዳዩች አኟጦ መጠቀም የዕድላችን መንገዶች የሆኑትን የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ልንጠብቃቸውና ልንከባከባቸው ይገባል።  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy