Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የጉዲፈቻ ምንነት

0 1,739

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የጉዲፈቻ ምንነት

                                                         ታዬ ከበደ

ጉዲፈቻ ይዘቱ ከሌላ ሰው አብራክ የተገኘን ልጅ ከሌላ ሰው የተወለደ መሆኑን አምኖና ተቀብሎ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መብቱን ጠብቆ እንደ ልጅ ማሳደግ ነው የሚል ትርጓሜ ሊሰጠው ይችላል፡፡ በአገራችን ጉዲፈቻ በባህል መሠረት ለረጅም ጊዜ ሲፈጸም የነበረ ሥርዓት ሲሆን፤ ወላጅና አሳዳጊ ያጡ ሕፃናትን የሚያሳድጉ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ መሃኖች የሆኑና ጧሪ ቀባሪና ወራሽ የሌላቸው ሰዎች እንደሆኑ የጉዲፈቻን ታሪካዊ ዳራ የጻፉ ሰዎች ያስረዳሉ፡፡

ይህ የዳበረ ልምድ በዋናነት ዓላማ የሚያደርገው የጉዲፈቻ አድራጊውን ጥቅም እንጂ የጉዲፈቻ ልጁን ጥቅም ባለመሆኑ፣ ዘመናዊ ሕግጋት የሕፃኑን መሠረታዊ ጥቅም ማዕከል ባደረገ መልኩ እንዲቀረፅ ምክንያት ሆኗል፡፡ በአገራችን በሕገ መንግሥቱም ሆነ በቤተሰብ ሕግጋት ሕፃናትን የሚመለከቱ ዕርምጃዎች በሚወሰዱበት ጊዜ የሕፃናት ደኅንነት በቀደምትነት መታሰብ እንዳለበት የሚያሳስቡ ድንጋጌዎች ተቀርፀዋል፡፡

በፌዴራል ደረጃ የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ በምዕራፍ አሥር ስለ ጉዲፈቻ በዝርዝር የሚደነግግ ሲሆን፣ በአንድ ሰውና በአንድ ልጅ መካከል በሚደረግ ስምምነት የጉዲፈቻ ዝምድና ሊፈጠር እንደሚችል ይደነግጋል፡፡ ሕጉ የጉዲፈቻ ሥርዓት አፈጻጸም መሠረታውያንን ማለትም የዕድሜ ገደብ፣ የስምምነት አሰጣጥ፣ የባለድርሻ አካላትን (የእጓለማውታ ድርጅቶች የሕፃናትን ጉዳይ የሚመለከተውን የመንግሥት አካልን የፍርድ ቤቶችን) ሚና በዝርዝር ደንግጓል፡፡

ሕጉ ሕፃናት ኢትዮጵያዊም ሆነ የውጭ ዜግነት ባላቸው የጉዲፈቻ አድራጊዎች በስምምነት ሊሰጡ እንደሚችሉ የሚገልጽ ሲሆን፣ በተግባር የተለመደውና በብዙ ችግሮች የሚስተዋሉበት ለውጭ ዜጎች የሚፈጸም ጉዲፈቻ ነው፡፡ የውጭ አገር ጉዲፈቻ (Inter country adoption) የመጨረሻ አማራጭ ሲሆን፣ አንድን ሕፃን የውጭ አገር ዜጋ በጉዲፈቻ እንዳያሳድገው የሚፈቀደው በጉዲፈቻ አድራጊ ቤተሰብ ወይም በሌላ ተስማሚ ዘዴ በአገር ውስጥ ሊረዳ ካልቻለ ብቻ ነው፡፡

ጉዲፈቻ አድራጊው የውጭ ዜጋ ሲሆን የሕፃናትን ደኅንነት ለመከታተል ሥልጣን የተሰጠው አካል ስለጉዲፈቻ አድራጊው ግላዊ፣ ማኅበራዊና፣ ኢኮኖሚያዊ አቋም አግባብ ያላቸውን መረጃዎች በማጠናቀርና በመመርመር ስምምነቱ ቢደረግ ለልጁ ጠቃሚነት ይኖረዋል ሲል አስተያየቱን ካልሰጠ በስተቀር የጉዲፈቻውን ስምምነት ፍርድ ቤት ሊያፀድቀው አይችልም፡፡

የቤተሰብ ሕጉ ከወጣ በኋላ ብዙ የውጭ ጉዲፈቻዎች በፍርድ ቤት እየፀደቁ ኢትዮጵያውያን ሕፃናት ወደ ውጭ አገር የተላኩ ሲሆን፣ ይህንንም ለማሳለጥ ብዙ የእጓለማውታ ድርጅቶች ተቋቁመዋል፡፡ ሆኖም በተግባር እንደሚስተዋለው የውጭ ጉዲፈቻ ሥርዓት አፈጻጸም በብዙ ችግሮች የተሞላ ከመሆኑ በተጨማሪ ሕፃናቱ በውጭ አገር ከሄዱ በኋላ የተለያዩ ጥቃቶችና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደሚደርስባቸው መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

አልፎ አልፎም እንደሚደመጠው የውጭ አገር ዜጎች ኢትዮጵያውያን ሕፃናትን በጉዲፈቻ ከወሰዱ በኋላ አስነዋሪ ለሆነ ግብረ ሰዶማዊና ወሲባዊ በደል ያጋልጡዋቸዋል፡፡ ከዚህ አልፎ ጠቃሚ የሆኑ የሰውነታቸውን አካል ለምሳሌ እንደ ኩላሊት፣ ዓይን ወዘተ. በቀዶ ጥገና ካወጡ በኋላ በጎዳና ላይ እንደሚጥሉዋቸው በርዕሱ ላይ የተሠሩ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡

ይህን አጠቃላይ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ ሰሞኑን አገራችን ጉዲፈቻን አስመልክቶ ኢትዮጵያ አዋጅ አውጥታለች። በአዋጁ ላይም አገራችን የውጭ ጉዲፈቻ ስርዓትን አስቀርታለች። የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት የውጭ ጉዲፈቻ ስርዓትን የከለከለበት አግባብ አዋጁ ሲፀድቅ ተገልጿል። በተለይ በተሻሻለው የቤተሰብ ህግ 213/1992 አንቀፅ 193 እና 194 ላይ የውጭ ጉዲፈቻ እንደ አማራጭ መቀመጡ በህፃናት ላይ ለሚፈፀሙ የተለያዩ ወንጀሎች በር መክፈቱ ተገልጿል።

ከምክር ቤቱ አባላት ለህፃናት ምቹ እና በቂ ማሳደጊያዎች ሳይዘጋጁ የውጭ ጉዲፈቻን መዝጋቱ ተገቢ አለመሆኑ በምክር ቤቱ እንደ መወያያ የተነሳ ሲሆን፤ በአንፃሩ በውጭ ጉዲፈቻ ስም በህፃናቱ ላይ ከሚፈፀም ህገ ወጥ ዝውውር እና የመብት ጥሰት ጋር ሲወዳደር የውጭ ጉዲፈቻን ማቆሙ የተሻለ ነው የሚል ሃሳብም ተንሸራሽሯል።

በኢትዮጵያ የሚሰሩ በርካታ በጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ህብረተሰቡ ህፃናቱን በአገር ውስጥ ጉዲፈቻ ተቀብሎ የማሳደግ ተነሳሽነት እያሳዩ ናቸው። በመሆኑም የውጭ ጉዲፈቻን ማስቀረቱ በህፃናት ላይ የሚደርሰውን የማንነትና የስነ ልቦና ቀውስ ለማስቀረት የሚያግዝ ነው። አዋጁ የህፃናት ጉዳይ ፖሊሲውን በተሟላ ሁኔታ ለማስፈፀምና ህፃናት በሀገራቸው ባህል፣ ወግና ልማድ ታንፀው እንዲያድጉ ለማድረግም ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል።

ይህ አዋጅ ላለፉት አራት ዓመታት ያህል ሲያከራክር የነበረ ነው። ምክር ቤቱ ያፀደቀው አዋጅ መነሻውና አስፈላጊነቱ ከላይ የጠቀስኩት ቢሆንም፤ አንዳንድ የውጭ መገናኛ ብዙሃን አዋጁ በምክር ቤቱ በፀደቀበት ወቅት ቅሬታቸውን ሲገልፁ ተስተውሏል። የትኛውም ወገን ቅሬታ የመግለፅ መብት ቢኖረውም ለዜጎቿ የሚበጀውን ከአገራችን ውጭ ሌላ አካል ሊወን አይችልም። በእኔ እምነት አዋጁ መውጣቱ ተገቢ ብቻ ሳይሆን እስካሁን መዘግየት አይገባውም ነበር።

መረጃዎች እንደሚያስረዱት የማደጎ ልጆችን ከሚያሳድጉ አሜሪካውያን መካከል 20 በመቶ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ልጆች አሏቸው። እ.ኤ.አ. ከ1999 እስከ 2017 ባሉት 18 ዓመታት ውስጥ ከ15 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ህጻናት በማደጎነት ወደ አሜሪካ ተወስደዋል፡፡ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ህጻናት ደግሞ በዋናነት ወደ ስፔን፣ ፈረንሳይና ጣሊያን በማደጎነት ሲወሰዱ ነበር፡፡

ኢትዮጵያ ህፃናትን ለውጭ አገራት ዜጎች በማደጎነት በመስጠት ከሚታወቁ  አስር የዓለም አገሮች አንዷ እንደነበረችም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡  ህፃናቱ የሚያድጉት በማያውቁት ማህበረሰብ ባህልና ወግ ከመሆኑም በላይ በቸሁኑ ሰዓት አገራችን ዜጎቿን ማኖር የምትችልበትን አቅም እየፈጠረች በመሆኑ የአዋጁ አስፈላጊነት የሚያጠያይቅ አይሆንም።  

እዚህ ላይ ጉዲፈቻ በልጆች ላይ የሚያመጣው ችግር ምንድነው? ብሎ መጠየቅ ይገባል። ልጆች በጉዲፈቻ ሲሰጡ ከባህላቸውና ከህዝባቸው ርቀው ማደጋቸው የሚፈጥረው ችግር አንዱ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ብዙዎቹ በነጭ አሳዳጊዎች በማደጋቸው ልዩ መሆናቸውን ገና በልጅነታቸው እየተረዱት ማደጋቸው ይህን ችግር መፍጠሩ አይቀርም፡፡

በጉዲፈቻ የተወሰደው ልጅ ያለ እነርሱ ዕርዳታ መኖር እንደማይችል፣ የመጣልና የመተው ስሜት እንዲሰማው አድርገው በማሳደግ በአንዳንድ አሳዳጊዎች የሚፈጸም ሥነ ልቦናዊም ጉዳትም ሌላኛው ችግር ነው፡፡ እጅግ አልፎ አልፎ የሚከሰት አካላዊ ቅጣት አንዳዴም እስከ ሞት የሚያደርስ ጉዳት በውጭ አሳዳጊዎች መፈፀሙም ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳ ችግር ነው፡፡

ሌላውና የውጭ ጉዲፈቻን ተከትሎ የመጣው እጅግ አሳፋሪ ወንጀል ደግሞ የጉዲፈቻ ልጆችን ከአሳዳጊዎች ጋር የሚያገናኙ ድርጅቶች ሠራተኞች ሥራውን እንደ ንግድ ማየታቸውና ላልተገባ ጥቅም ዜጎችን አሳልፈው መስጠታቸው ነው፡፡

እነዚህ ሰዎች ስለ ውጭ ኑሮ የተጋነኑ እውነታዎችን በመንገርና የልጁን ወላጆች ወይም ዘመዶች በማሳመን አገር ውስጥ ማደግ የሚችለውን ልጅ ያላግባብ ወደ ውጭ እንዲወሰድ እየደረጉ ነው፡፡ በዚህ መልኩ በመቶዎች ሳይሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ሕፃናት በየዋህ ወይም በራስ ወዳድ ወላጆቻቸው ውሳኔ ምክንያት በፈረንጆች አሳዳጊዎች ለማደግ ይገደዳሉ፡፡

በሌላ ምልከታም የኢትዮጵያዊ ሕፃናት ወደ ውጭ በብዛት መጉረፍ፣ አገሪቱ ልጆቿን ማሳደግ እንዳቃታት ተደርጎ የሚገመት ሲሆን ይህ ዓይነቱ አተያይ የአገራችንን ገፅታ የሚያበላሽ መሆኑ አይቀርም። እነዚህ እውነታዎች የህፃናትን መብቶች የሚጋፉና የከፋ አደጋን የሚያስከትሉ በመሆናቸው ለአዋጁ መውጣት ምክንያት መሆናቸው አልቀረም።

ያም ሆኖ ሕጋዊ የአገር ውስጥ ጉዲፈቻ በአገራችን ማበረታታት ይገባል፡፡ በዚህ ተግባር ላይ የተሰማሩ ምግባረ ሰናይ ድርጅቶችን በመደገፍና በማወዳደር አገልግሎቱን ማስፋፋት ይቻላል። እናም የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት ያወጣውን አዋጅ ለመተግበር እንዲህ ዓይነት ስራዎች መጠናከር ይኖርባቸዋል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy