Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የፌዴራል ስርአቱ ባለቤት

0 485

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የፌዴራል ስርአቱ ባለቤት

ኢብሳ ነመራ

ኢትዮጵያ ቡራቡሬ ሃገር ናት፤ የሰማንያ የተለያዩ ብሄራዊ ማነነቶች የፈጠሩት ቡራቡሬ፤ አንድ አካል ላይ ያሉ የተለያዩ ማንነት ያላቸው ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች  የፈጠሩት ውብ ህብረ ብሄራዊነት። በልዩነት ውስጥ ያለ አንድነት የምንለው ይህን አንድ ሃገር የመሰረተ ህብረብሄራዊነት ነው። ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ገጽታዋ በልዩነት ውስጥ ያለ አንድነት ወይም ህብረብሄራዊነት/ ብዝሃነት ነው። ይህ ተጨባጭ እውነት ነው።

ኢትዮጵያ የተለያየ ማንነት ያላቸው ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሃገር ብትሆንም ብዝሃነት እውቅና የተሰጠው ግን ከ1983 በኋላ ነው። ከዚያ ቀደም የነበሩት ስርአቶች ልዩነቱን በሃይል አጥፍተው አንድ ብሄራዊ ማንነት ያላት ሃገር ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ የቆዩ ናቸው። ይህ ብዝሃነትን ወይም በልዩነት ውስጥ ያለን አንድነት በማጥፋት አንድ ማንነት ያላት ሃገር የመመስረት ስትራቴጂ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ማገባደጃ ጀምሮ ለአንድ ክፍለ ዘመን ያህል ስራ ላይ ውሏል።

የብሄር ብዝሃነትን በማጥፋት አንድ ማንነት ያላት ሃገር የመመስረት ስትራቴጂው በኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም። የትኛውም ብሄር ወይም ብሄረሰብ ማንነቱን ለሌላ የእርሱ ላልሆነ ማንነት መስዋዕት በማድረግ የማንነቱ መገለጫዎች እንዲጠፉ የመፍቀድ ፍላጎት አልነበረውም።

እንግዲህ አሁን ከጎልማሳነት እድሜ በላይ የሆንን ኢትዮጵያውያን ሁሉ እንደምናስታውሰው ቀደም ባሉትና የሃገሪቱን ብዝሃነት ያልተቀበሉ ስርአቶች በነበሩበት ዘመን ከራሳቸው ቋንቋ ውጭ መግባባት የማይችሉ በግርድፍ ግምት ከ85 በመቶ በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የመንግስት አገልግሎት የሚያገኙት በማያውቁት ቋንቋ ነበር። ፍርድ ቤት ቆመው ጉዳያቸው ላይ ምንም በማያውቁት ቋንቋ እንዲሟገቱ ይገደዱ ነበር። በማያውቁት ቋንቋ መሟገት ምን ያህል እንደሚከብድና እንደሚያሸማቅቅ አስተውሉ። አፍ ከፈቱበት ቋንቋ ውጭ ምንም ሰምተው የማያውቁ ህጻናት ፈጽሞ ባዕድ በሁነ ቋንቋ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ለመማር ይገደዱ ነበር።

የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የኑሮ ዘይቤ መገለጫ የሆኑ ባህሎች ይራከሱ ነበር። ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባህላቸውን የማሳደግ እድል አልነበራቸውም። በባህላቸው እንዲያፍሩና እንዲሸማቀቁ ይደረግ ነበር። ታሪካቸው በተዛባ መልክ ይቀርብ ነበር። እውነተኛ ታሪካቸውን የማጥናት፣ የመጻፍ፣ የመንከባከብ መብት አልነበራቸውም። በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በማነነታቸው እንዲሸማቀቁ ይደረግ ነበር። ይህ ሆን ተብሎ ነበር የሚደረገው። የተላየዩ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች ተወላጆች በቋንቋቸው የወጣላቸውን መጠሪያ ስም ይቀይሩ የነበረው ማንነታቸውን ይፋ ወጥቶ ለአሸማቃቃቂ ተረብ እንዳይጋለጡ በመስጋት መሆኑን ልብ በሉ። እርግጥ ቀደም ባሉት ጊዜያት የመንግስት የስራ እድልም ለማግኘት ማንነትን መሸሸግ ያስፈልግ ነበር።

የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ከብሄራዊ ጭቆና በተጨማሪ ለኢኮኖሚ ጭቆናም ተዳርገው ነበር። በዘውዳዊው ስርአት፣ ኑሯቸው በግብርና ላይ የተመሰረተ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች አርሶ አደሮች መሬት አልባ ነበሩ። ዘርማንዘራቸው አቅንቶ ሲጠቀምበት የኖረውን መሬታቸውን ተነጥቀው መሬቱ ለመሳፍንቱ፣ መኳንነቱ፣ በተለያየ ደረጃ ለሚያገለግሉ የመንግስት ተሿሚዎች እንዲሁም ለንጉሰ ነገስቱና መሳፍነቱ ወዳጆች ተሰጥቶ ቆይቷል። ታዲያ፣ መሬታቸውን የተነጠቁት ባለሃገር አርሶ አደሮች በገዛ መሬታቸው ላይ ለገባር ጭሰኝነት ተዳርገዋል። የራሳቸውን መሬት አርሰው ምርቱን መሬታቸውን ለነጠቃቸው ባለርስትና ባለጉልት ይገብራሉ፤ ጉልበታቸው ላይ የማዘዝ መብትም አልነበራቸውም።

እንግዲህ ይህ ከላይ በአጭሩ የተገለጸው በኢትዮጵያ የነበረ ታሪካዊ ነባራዊ ሁኔታ ነው። የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ይህን አስከፊና ክብረ ነክ የሰብአዊ መብት ጥሰት አሜን ብለው አልተቀበሉም። አቅምና ሁኔታዎች በፈቀዱት ልክ ለመታገል ሞክረዋል። የመጀመሪያዎቹ የትግል እንቅስቃሴዎች በአጥቢያ የተወሰኑ፣ ያልተደራጁና ድንገት የሚገነፍሉ አመጾች ነበሩ። በየአካባቢው የስርአቱ ሹመኞች ላይ ከተካሄዱና የአውራጃ ከተማ እንኳን ሳይሰሙ ከከሰሙ አመጾችና ተቃውሞዎች ባሻገር፣ በሃገር አቀፍ ደረጃ ለመሰማት የበቁ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችም ነበሩ። የትግራይ ቀዳማይ ወያኔ እና የባሌ አርሶ አደሮች አመጽ ከእነዚህ መሃከል ተጠቃሾች ናቸው።

በአጠቃላይ ቀደምቶቹ ብሄራዊና ኢኮኖሚያዊ ጭቆና የወለዳቸው ተቃውሞዎችና አመጾች በወጉ ያልተደራጁና መርህ ላይ የተመሰረቱ አልነበሩም። ከዚህ ይልቅ በአጋጣሚ የሚፈነዱና አካባቢያዊ ነበሩ። በመሆኑም አርሶ አደሩን ለእስር፣ ለመቀጣጫነት ገበያ መሃል በጅራፍ ለመገረፍ ከመዳረግ አልፈው ለውጥ ማምጣት አላስቻሉም። መርህ ላይ የተመሰረቱ ሳይሆኑ ግብታዊ ስለነበሩ ቦግ ብለው እልም የሚሉ የአፍታ ተቃውሞዎች ከመሆን ሳይዘሉ ቆይተዋል።

እየከራረመ አነሰም በዛም ከየብሄሩ የመማር እድል ያገኙ ልሂቃን ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ። እነዚህ ልሂቃን የብሄራዊና የኢኮኖሚ ጭቆናውን ስረ መሰረረት በመተንተን ምንጩን በማጋለጥ በመርህ ላይ የተመሰረተ የነጻነትና የእኩልነት ትግል ማካሄድ የሚቻልበትን ሁኔታ አመላከቱ። በኋላም በዚህ ላይ ተመስርተው የብሄራዊ ነጻነት እንቅስቃሴዎች ተጀመሩ። በወቅቱ የዜጎች የፈቀዱትን አመለካከት የመያዝ፣ አመለካከትን የመግለጽ፣  የመደራጀት፣ በግልም ይሁን ከመሰሎች ጋር በመደራጀት አመለካከትን የማራመድ ወዘተ ነጻነት በህግ የተገደበ ስለነበረ፣ የብሄራዊ ነጻነትና እኩልነት ጥያቄ አንግበው የተነሱት እንቅስቃሴዎች የነበራቸው አማራጭ ብረት አንስተው የትጥቅ ትግል ማካሄድ ብቻ ነበር። እናም በተለይ ከ1960ዎቹ አጋማሽ በኋላ እስከ ሃያ የሚደርሱ የብሄራዊ ነጻነት ቡድኖች ተደራጅተው የትጥቅ ትግል ማካሄድ ጀምረዋል። በኢትዮጵያ የብሄራዊ ነጻነት የትጥቅ ትግል እንዲጀመር ያደረገው ታሪካዊ ነባራዊ ሁኔታ ከላይ የተገለጸውን ይመስላል።

እነዚህ የትጥቅ ትግል በማካሄድ ላይ የነበሩ የብሄራዊ ነጻነት ቡድኖች ህዝቡ ውስጥ ሰርጸው በገቡበት መጠን፣ በተዋጊ ሃይል ብዛት፣ በወታደራዊ አቅም፣ በመርህና መስመር ጥራት የሚበላለጡ ቢሆንም ሁሉም ለብሄራዊ ነጻነት የሚታገሉ ነበሩ። ይህ ተመሳሳይነት የአንድ ታሪካዊ ነባራዊ ሁኔታ ውጤት መሆናቸውን ያመለክታል። ዓላማቸውን በህዝብ ውስጥ ያሰረጹበት ደረጃ፣ የመርህና የመስመር ጥራታቸው፣ የተዋጊ ሃይልና ወታደራዊ አቋም ጥንካሬ ላይ የነበራቸው ልዩነት ደግሞ አሃዳዊውን ስርአት በመጣል ረገድ ያላቸው ተሳትፎ እንዲለያይ አድርጓል። ይህ ተጨባጭ እውነታ ነው።

ያም ሆነ ይህ የመጨረሻው አሃዳዊ የወታደራዊ ደርግ የመንግስት ስርአት እነዚህ የብሄራዊ ነጻነት ግንባሮች በየአካባቢው ባካሄዱት ትግል ነበር የፈራረሰው። ቀደም ሲል እንደገለጽኩት የብሄራዊ ነጻነት ንቅናቄዎቹ በውጊያ አቅም የነበራቸው ድርሻ ቢለያይም ስርአቱን በማስወገዱ ሂደት ውስጥ ግን ሁሉም ድርሻ ነበራቸው ማለት ይቻላል። ወታደራዊው ደርግ ለመወገድ የበቃው በአጋጣሚ ሳይሆን የሃገሪቱ ታሪካዊ አስገዳጅ ሁኔታ በፈጠረው የብሄራዊ ነጻነት ትግል ነው።

በደርግ ውድቀት ማግስት ኢትዮጵያ የመበታተን አፋፍ ላይ ቆማ ነበር። በየአካባቢው ይንቀሳቀሱ የነበሩ የብሄራዊ ነጻነት ግንባሮች የሚወክሏቸው ብሄሮችና ብሄረሰቦች የሚኖሩባቸውን አካባቢዎች ወደመቆጣጣር ሄደው ነበር። ይሁን እንጂ ተበታትነው ትንንሽ ነጻ ሃገር ከመመስረት ይልቅ፣ ጨቋኝ ስርአት ስር በነበሩበትም ጊዜ ቢሆን ባካበቷቸው መልካም የጋራ እሴቶች ላይ በመመስረት ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ መብትና ነጻነቶቻቸው ተከብረው፣  በእኩልነትና በመከባበር ላይ በተመሰረተ አንድነት አብረው መኖር የሚችሉበት እድል ይኖር እንደሆነ ያለማንም የውጭ ጣልቃ ገብነት ለመምከር ሸንጎ ተቀመጡ፤ ደርግ በተወገደ በወሩ ሰኔ 1983 ዓ/ም ላይ።

የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ በእኩልነት መኖር የሚችሉበት ፌደራላዊ ስርአት መሰረት የተጣለው በዚህ ሸንጎ ነበር። በሸንጎው ላይ ሁሉም ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ በእኩልነት የሚኖሩበት የህዝቦች አንድነት ያለው ሃገር መመስረት የሚያስችላቸውን ህገመንግስት ለመቅረጽ ተስማሙ። ይህን ህገመንግስት የሚቀርጹበት የሽግግር መንግስትም መሰረቱ። በዚህ የሽግግር ወቅትም ቢሆን በአሃዳዊው ስርአት መዋቅር ለመኖር አልፈቀዱም። የሽግግር መንግስቱ እንደህገመንግስት በሚጠቀምበት ቻርተር ላይ ራሳቸውን በራሳቸው ለማስተዳደር በሚያስችላቸው ሁኔታ ነበር የተዋቀሩት። በዚህ የሽግግር መንግስት ሁሉም የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦች በተሳተፉበትና ስምምነታቸውን በገለጹበት ሁኔታ የኢፌዴሪ ህገመንግስት ተቀረጸ። ይህ ህገመንግስት አሁን ያለው ፌደራላዊ ስርአት የተመሰረተበት ህግመንግስት ነው።

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ፣ በእኩልነትና በመከባበር ላይ በተመሰረተ አንድነት የሚኖሩበት ፌደራላዊ ስርአት የተመሰረተው በአንድ ቡድን ፍላጎት ሳይሆን በኢትዮጵያ በነበረው ታሪካዊ ነባራዊ ሁኔታ ገፊነት ነው። ይህ ታሪካዊ ሁኔታ ሁሉም የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መብትና ነጻነታቸውን እንዲሹ ያደረገ በመሆኑ ፌደራላዊ ስርአቱ በኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎት የመጣ ነው። የስርአቱ ባለቤቶችም ኢትዮጵያውያን ብቻ ናቸው። ይህን ፌደራላዊ ስርአት መጋፋት የኢትዮጵያን ህዝብ መጋፋት ነው፤ ምናልባት ሃገሪቱን ወደመፍረስ ከመግፋት ያለፈም የሚያስገኘው ፋይዳ የለም።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy