Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የፖለቲካ ምሕዳሩን ማስፋት

0 209

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የፖለቲካ ምሕዳሩን ማስፋት

                                                               ይልቃል ፍርዱ

የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ካደረገው ሶስት ሳምንታትን የፈጀ ጥልቅ ግምገማ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ከሰማይ በታች አሉ ለሚባሉት ችግሮች ሁሉ መነሻ የሆኑ ምክንያቶች በገሀድ ወጥተው ታይተዋል፤ ተፈትሸዋል፡፡ በመጨረሻም ስራ አስፈጻሚው ለተፈጠረው ሀገራዊ  ችግር ሁሉ ኃላፊነቱን ወስዶ ሁሉንም ችግር ከሕዝቡ ጋር ሁኖ ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት ገልጾአል፤ ወደተግባርም በመግባት ላይ ነው፡፡

የሥራ አስፈጻሚውን ውሳኔና መግለጫ ተከትሎ ችግሮችን ለመፍታት ከሚወሰዱት እርምጃዎች ውስጥ ሀገራዊና ሕዝባዊ መግባባትን ለመፍጠር እንዲቻል የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞችን እንደሚፈታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በገለጹት መሰረት በርካታ እስረኞች እንዲፈቱ መደረጉን አቃቤ ሕጉ ጌታቸው አምባዬ በይፋ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡ ክሳቸው ተቋርጦ እንዲፈቱ ከተደረጉት መካከልም ዶ/ መረራ ጉዲና ይገኙበታል፡፡

የፖለቲካ ምሕዳሩን ማስፋት ማለት ሀገራዊ መግባባቱን መሰረት ባደረገ መልኩ ለዲሞክራሲው ማደግና መጎልበት ተገቢ ሚና መጫወት ለሚችሉት የሕብረሰተብ ክፍሎች ሁሉ የበለጠ ለሀገርና ለሕዝብ የሚጠቅሙ ስራዎችን እንዲሰሩ ሁኔታዎችን ማመቻቸት፤ ጠበበ የተባለውን መድረክ በማስፋት መጠቀም መቻል ነው፡፡ በሕገመንግስቱ በግልጽ ሰፍረው የሚገኙት ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች የፕሬስ፣ የመናገርና የመጻፍ፣ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብቶች ሳይሸራረፉ በሕጉ መሰረት ስራ ላይ እንዲውሉ በዚህም ሕዝብ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ መቻል ነው፡፡

የፖለቲካ ምሕዳሩን ማስፋት ማለት ጤነኛና ሰላማዊ በሆነ መንገድ በወይይት፣ በሰላማዊ ንግግርና ክርክር ልዩነቶችን በልዩነት ይዞ የጋራ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች በጋራ ቆሞ መስራት ማለት ነው፡፡ ለምሳሌም ሀገራዊ ሰላምና ደሕንነት ከሁሉም በፊት መጠበቅ መከበር ያለበት ጉዳይ መሆኑ ለክርክር አይቀርብም፡፡ ተቃዋሚውም ሆነ የገዢው ፓርቲ ፖለቲካዊ መስመር ለውይይትና ክርክር ቀርቦ የሕዝብ ይሁንታና ተቀባይነትን ወይንም አለመቀበልን ሊያገኝ የሚችለው ሰላማዊ የሆነ ጤነኛ የፖለቲካ ፉክክርና ውድድር ሲኖር ለዚህም ሀገር የተከበረና የተጠበቀ ሰላም ሲኖራት ብቻ ነው፡፡

የፖለቲካ ምሕዳሩን ማስፋት ማለት ማናቸውንም ጸረ ዲሞክራሲ እንቅስቃሴዎችን በመመከት የሀሳብ ልዩነቶችና ፍጭቶች በነጻነት ሀሳብን የመግለጽ መብት ያለማንም ተጽእኖና ጣልቃ ገብነት ነጻ የሀሳቦች መንሸራሸር እንዲደረግ ማስቻል ነው፡፡ ስድብ፣ ዘለፋ፣ ዛቻ፣ ክብረነክ መልእክቶች፣ ሕዝብን የማነሳሳትና ለሁከት የሚጋብዙ ንግግሮች፤ በዘር፣ በጎሳና ብሔር ላይ የተመረኮዙና ያነጣጠሩ፣ በሀይማኖት ጉዳይ ወገንተኛ የሆኑና አንዱን ደግፈው ሌላውን የሚያጥላሉ ሀሳቦች ሁሉ በሕግ የተከለከሉ ናቸው፡፡

በሀገራዊ ብሔራዊ የመከላከያና የደሕንነት ጉዳዮች በሕግ የተከለከሉና በመረጃ ነጻነት ማእቀፍ ሕጉ ውስጥ በግልጽ እገዳ በተጣለባቸው ጉዳዮች ላይ በአለም አቀፍ ሕግም የተጠበቁና የተከበሩ በመሆኑ በመናገር ነጻነት ስም መጠቀም አይቻልም፡፡ በዲሞክራሲ ምሕዳሩ መስፋት ስም ሌሎች በሀገር፣ በሕዝብ ላይ አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ እንቅስቃሴዎችንም ማድረግ ልክልክል ነው፡፡

ሰላማዊ የሌሎችን ዜጎች የግልና ማሕበራዊ ሕይወትና ተቀባይነትን የማይነካ ከስም ማጥፋት፣ ከባዶ ውንጀላ በራቀና ኃላፊነት በተመላበት መልኩ ነው የዲሞክራሲ ምሕዳሩ እንዲሰፋ ትግል መደረግ ያለበት። መብቶች ሁሉ በሕግ የተቀመጠ ነጻነትና በሕጉም መሰረት ተጠያቂነት የሚያስከትሉ የሕግ ግዴታዎች አሉባቸው፡፡ ግዴታ የሌለበት፣ ነጻና ልቅ የሆነ መብትና ነጻነት በየትም የለም፡፡ ሁሉም በሕጉ ስር ሁነው ሕጉን አክብረው ነው ነጻነታቸውን የሚጠቀሙት፡፡

በዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ውስጥ አንዱና ወሳኝ የሆነ ሂደት ተደርጎ የሚወሰደው የጋራ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተቃዋሚውም ሆነ ገዢው ፓርቲ የጋራ መግባባትን መፍጠር መቻላቸው ነው፡፡ በሀሳብ መለየት፣ የተለየ ሀሳብ መያዝና ማራመድ፣ ሰላም በማደፍረስ በሕብረተሰቡ ውስጥ ሁከትና ትርምስ የሚፈጠር አካሄድን እስካልተከተለ ድረስ ተገቢና ትክክለኛ የዲሞክራሲ ገጽታ በመሆኑ ሀሳቡን በሰላም በነጻነት በመግለጹ በሕግ ተጠያቂ የሆነም ሆነ የሚሆን የለም፡፡ ችግሩ የሚመጣው በሕግ በአሸባሪነት ከተፈረጁ አካላት ጋር በሚፈጠር ቁርኝትና ትስስር፤ ይሄም በተግባር በሚገለጽበት ሁኔታ ውስጥ ብቻ መሆኑን የሕግ ባለሙዎች ይናገራሉ፡፡

እዚህም ላይ የሚነሳ የሞቀ ክርክር አለ፡፡ አሸባሪነት በአለም አቀፍ ደረጃ ያለው ትርጉምና በእኛ ሀገር የተሰጠው የሕግ ትርጉም አንድ አይደለም (ወይም፣ የተዛባ ነው) የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ የሰሞኑ የተቃዋሚዎችና የገዢው ፓርቲ በጸረ ሽብር ሕጉ ላይ መሻሻል አለባቸው ባሉት ነጥቦች ላይ ይነሱ/ይለወጡ ያሉዋቸው አንቀጾች ለሀገሪቱ ሰላምና ደህንነት፣ የሕዝብን ሰላም ለመጠበቅ ሲባል አስፈላጊ ስለሆኑ እንደማይነሱ ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ በአለም አቀፍና በብሔራዊ ሕጎች ላይ ተመርኩዘው ማብራሪያዎችን ሰጥተዋል፡፡

ተቃዋሚዎች ካልተሻሻሉ ያሉዋቸው ነጥቦች እስካልተቀየሩ ድረስ ለመቀበል እንደሚቸገሩ ገልጸው ቀጣይ ዙር ውይይት ለማድረግ ቀጠሮ ተይዞአል፡፡ በመሰረቱ አክራሪነትና አሸባሪነት የመንግስታትና የአለምአቀፉ ሕብረተሰብ አደገኛ የስጋት መነሻ በመሆናቸው ተጨባጭ አደጋዎችን በበርካታ ሀገራት ውስጥ ስላደረሱ ለማድረስም ስለሚሰሩ የሚጠቀሙባቸው ስልቶች ተለዋዋጭና የዘመኑን ቴክኒዮሎጂ የተከተሉ በመሆኑ ሌላው አለም ተቀብሎ ያጸደቀውን የጸረ አሸባሪነት ሕግ ኢትዮጵያም በራስዋ ደረጃ ተቀብላ ሕግ አድርጋ ማውጣትዋ ተገቢ ብቻ ሳይሆን ትክክልም ነው፡፡ በመሆኑም የዚህ አዋጅ መኖር የዲሞክራሲ ምሕዳሩ ጠበበ ሊያስብል የሚችል አይደለም፡፡

የተቃዋሚው ስጋት በጸረ አሸባሪ ሕጉ መሰረት ተቀዋሚዎች ተወንጅለው በማንኛውም ሰአትና ግዜ በአሸባሪነት ተፈርጀው ይታሰራሉ፤ የሕግ ዋስትና የላቸውም፡፡ ቤት ንብረታቸው ይበረበራል፤ ናሙና ለመስጠት ይገደዳሉ፤ ስልካቸውና ኢሜላቸው ይጠለፋል፤ ኮምፒዩተራቸው ከነዶክመንቱ ለምርመራ ይወሰዳል፤ ተቃዋሚው በዜግነቱ ተቃውሞውን በሰላማዊ መንገድ የሚያሰማና መንግስት በሕግ በፈቀደው መሰረት የሚንቀሳቀስ በመሆኑ የፖለቲካ ተቃውሞ በአለም አቀፍ ደረጃ ያለው የአሸባሪነት ትርጉም ሊሰጠው አይገባም፡፡ በአጭሩ ሕጉ በተለየ ሁኔታ ተጋላጭና ሰለባ አድርጎናል ነው የሚሉት፡፡

መንግስት ሕጉ በስርአትና በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱትን ተቃዋሚዎች የማይነካ መሆኑን፣ የሕጉ መኖር ለሀገሪቱም ለሕዝቡም ሰላምና ደሕንነት ሲባል አስፈላጊ ዋስትና መሆኑን በመግለጽ ይከራከራል፡፡ መንግስትና ተቃዋሚው ከፖለቲካ አመለካከቶች ልዩነት ውጪ በጋራ የሚያግባቡዋቸውና የሚያቆሙዋቸው ጉዳዮች ሰፊ ናቸው፡፡

ድሕነትን ለማስወገድ መስራት፤ በሀገሪቱ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች፤ ሀገሪቱን ዳር እስከዳር የሚያገናኙ መንገዶች ዝርጋታ፤ የኃይል ማመንጫ ግድቦች ግንባታ የታላቁ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ፤ የጤና መሰረታዊ አገልግሎት በመላ ሀገሪቱ ለማስፋፋትና ለማዳረስ የሚደረገው ጥረት፤ የገጠሩ ልማት ማደግ፤ ቀላልና ከባድ ኢንዱስትሪዎች መስፋፋት፤ የባቡር መስመር ዝርጋታ፤ አዲስ አበባን ጨምሮ ሌሎች የክልል ከተሞችን ዘመናዊ ለማድረግ ሕብረተሰቡም ተጠቃሚ እንዲሆን የተሰሩት ስራዎች ሁሉ ለሀገርና ለሕዝብ የሚጠቅሙ በመሆኑ ልዩነት የለም፤ ይሄንን የሚቃወም ተቃዋሚ አይኖርም፡፡

የትምህር ተቋማት በመላ ሀገሪቱ መስፋፋት ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች ቀድሞ በቁጥር 5 ከነበሩበት ደረጃ ተነስተው በዚሁ ስርአት ውስት 40 መድረሳቸው፤ ግብርናውን  ለማዘመን፤ የተፈጥሮ አየር ንብረትን ለመጠበቅ፣ የተራቆቱ የሀገራችንን መሬቶች በደን ለማልበስ የተሰራው ስራና የተገኘው ተጨባጭ ውጤት፤ ባለፉት አመታት በአንዳንድ የሀገራችን አካባቢዎች የተከሰተውን ድርቅ የውጭ እርዳታ ከመድረሱ በፊት በራስ አቅም ለመመከት መቻሉ አለም አቀፍ ተቋማት የሰጡት ምስክርነት እንዳለ ሁኖ ይህንን ችግር መመከት የተቻለው ሀገራችን የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዘግብ በመቻልዋ ነው፡፡ በዚህም ልዩነት አይኖርም፡፡

በሌሎችም በርካታ መስኮች የሚጠቀሱ አለም አቀፍ እውቅና ያገኙ ሀገሪቱን ከድህነት ለማውጣት የተሻለች ሀገር እንድትሆን የማድረግ ስራዎች በኢሕአዴግና በሚመራው መንግስት ተሰርተዋል፡፡ እነዚህ ስራዎች በታሪክም በትውልድም ውስጥ ፈክተውና ገነው የሚጠቀሱና የሚታዩ ዘመን ተሻጋሪ ስራዎች ናቸው፡፡ በዚህ  ረገድ  የሀገሪቱ መልማት፣ ማደግና መለወጥ በብዙ መስኮች የተመዘገቡት ሀገራዊ ልማትና እድገቶች መንግስትን፣ ሕዝቡንና ተቃዋሚውን አንድ የሚያደርጉ፤ በጋራም የሚያቆሙና የሚያግባቡ ናቸው፡፡ በእነዚህም መሰረታዊ ጉዳዮች ልዩነት የለም፡

ኢሕአዴግ የተሰሩትን ሀገራዊ ታላላቅ ስራዎች የሰራው ለሀገርና ለሕዝብ እንጂ ለማንም ሲል አይደለም፡፡ ዛሬም፣ ነገም፣ ወደፊትም የሕዝብና የሀገር ሀብቶች ናቸው፡፡ በዚህ ደረጃ ሰፊ ሀገራዊ መግባባት እንደሚኖር ይታመናል፡፡ የዛኑም ያህል ራሱ ገዢው ፓርቲ አምኖ የተቀበላቸው መሰረታዊ የሆኑ፤ በአመራር ደረጃ የተፈጠሩና ሕዝብን ያስመረሩና ያስከፉ  ችግሮችን በተመለከተ ኃላፊነቱ የአመራሩ መሆኑን ሙሉ በሙሉ ተቀብሎ በፍጹም ቁርጠኝት ለማረም፤ ሕብረተሰቡንም ለመካስ እንደሚሰራ ገልጾአል፡፡ ይሄ ራሱ ትልቅ ክብር የሚሰጠው ጉዳይ ነውና መንግስት ያሳረፈውን ውሳኔ ወደተግባር በሚያሸጋግርበት ጊዜ የመላው ህዝብ ድጋፍና ትብብር ያስፈልገዋልና ሁላችንም የሚጠበቅብንን በማድረግ ሀላፊነታችንን እንወጣ፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy